አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላት ግንኙነት የሌሎቹን የምስራቅ አፍሪካ አገራትን በማያስከፋና ከአገራቱ ጋር ያለውን የቀድመ ግንኙነት ሊያስቀጥል በሚችል መልኩ መሆን እንዳለበት ምሁራን ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት ‹‹አዲስ ወግ›› የተሰኘ የምሁራን መድረክ ትናንት ተካሂዷል። በወቅቱ የቀድሞ ዲፕሎማት እና የተባበሩት መንግሥታት አማካሪ ዶክተር ኅሩይ አማኑኤል እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሰላም መፍጠራቸው በቀጣናው ግንኙነት ላይ የበለጠ መጠናከርን መፍጠሩ አይቀርም። ይሁንና ግንኙነቱ ሱዳንንም ሆነ ጅቡቲን ማስቀየም አይኖርበትም። የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት በሌሎቹ አገራት ጥቅም እንደማይጎዳ እና ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የቆየውን ግንኙነታቸውን የማያናጋ ስለመሆኑ ማስረዳት ይገባል።
እንደ ዶክተር ኅሩይ ገለጻ፤ የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት በጅቡቲ የወደብ ገቢ ላይ ተጽዕኖ እንደማያሳድር ማሳወቅ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሲያድግ ከጅቡቲ አልፎ አሰብ እና ምጽዋን እንዲሁም ሌሎች አማራጮችን ሊጠቀም ይችላል። ይህንን በሚገባ በማስረዳት ከጅቡቲ ጋር ያለው ግንኙነት እንዲቀጥል ማድረግ ይገባል። በሱዳን በኩል ደግሞ ያለውን የፀጥታ ትብብር በማስቀጠል ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ግንኙነት ብትጀምርም ከሱዳን ጋር ያላት ግንኙነት እንደሚቀጥል ማሳመን ያስፈልጋል።
የአፍሪካ ህብረት የሰብዓዊና የህዝቦች መብቶች ኮሚሽነር ዶክተር ሰለሞን አየለ በበኩላቸው፤ በአፍሪካ ቀንድ ሁለት አገራት ግንኙነት ሲጀምሩ ለሌሎች አገራት ውድቀት እንደሆነ የሚታሰብበት አካባቢ ነው። በመሆኑም ሁለቱ አገራት ቀድሞ በነበራቸው የድንበር ውዝግብ ወቅት ከኢትዮጵያ ወገን እንደተሰለፉ የሚያምኑ የቀጣናው አገራት አሁን ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ወዳጅ ስትሆን ከኢትዮጵያ ጋር ባላቸው ግንኙነት ላይ ስጋት ይፈጠራል። በመሆኑ ከኤርትራ ጋር የሚደረገው ግንኙነት ከሌሎቹ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር የነበረውን መልካም ግንኙነት ማስቀጠል ላይ መሰረት ያደረገ መሆን አለበት።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞ ዋና ረዳት ፀሐፊ ወይዘሮ ሒሩት ገብረስላሴ ደግሞ፤ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት ለቀጣናው መረጋጋት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ሁሉ ግንኙነቱን ተቋማዊ ማድረግ ደግሞ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። እንደ እርሳቸው፤ በድንበር አካባቢ የሚገኙ ዜጎች የበለጠ ተቀራርበው እንዲሰሩ እና እንዲተዋወቁ ማድረግ ያስፈልጋል። በሌሎች የቀጣናው አገራት መካከልም ተመሳሳይ ግንኙነቶች በማህበረሰቡ መካከል ማጠናከር ይገባል።
ሌላው የመድረኩ አቅራቢ የአፍሪካ ህብረት አማካሪ አቶ አብዱል ሙሐመድ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ትልቅ ስፍራ ያላት በመሆኑ ሌሎቹ የቀጣናው አገራት አብረው መስራት ይፈልጋሉ። በመሆኑም በኢትዮጵያ በኩል ኤርትራን ብቻ ነጥሎ የሚያይ አካሄድ መፈጠር የለበትም። ይልቁንም ሁሉንም የቀጣናው አገራት ያማከለ ግንኙነት በመፍጠር ዘላቂ መስተጋብር በአገራቱ መካከል መፍጠር ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14/2011
ጌትነት ተስፋማርያም