አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የተጀመረው ለውጥ በርካታ ስኬቶችን የተጎናፀፈ ቢሆንም፤ መራር ፈታናዎችን እያስተናገደ በመሆኑ ለውጡ አቃፊ፣ ሁሉን አካታችና ተቋማዊ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያስፈልገው ተገለፀ።
ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የመገናኛ ብዙኃን አመራሮችና የውጭ አገር ተሳታፊዎች የተገኙበትና የአገሪቱን አሁናዊና የቀድሞ የፖለቲካ ሥርዓቶችን የዳሰሰ ‹‹አዲስ ወግ›› የተሰኘ የውይይት መርሐ ግብር ትናንት በሸራተን ሆቴል ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ጉዞ፣ ታሪካዊ ዳራና ወቅታዊ ፈተናዎችን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ባቀረቡት ፅሁፍ፤ ኢትዮጵያ ላለፉት 160 ዓመታት በበርካታ የፖለቲካ ስንስሎች ውስጥ ያለፈች ሲሆን፤ በየጊዜያቱ የሚከሰቱ ስኬቶችና ውጥንቅጦች በልኩ የተሰፉና በህግ የበላይነት የሚዳኙ ባለመሆናቸው አገሪቱ የተሻለ የዴሞክራሲ ሥርዓት ማፅናት አልቻለችም። በተለይም አገሪቱ ስትተዳደርባቸው የነበሩት ሥርዓቶችና ተቋማት ጠንካራ መሰረት ኖሯቸው በየጊዜው እየዳበሩ አልመጡም። በመሆኑም የውጭ ዓለማት ርዕዮተ ዓለም መለማመጃ ሆነው ቆይተዋል።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለፃ፤ አሁናዊ የአገሪቱ ሁኔታም ብዙ ፈተና እንዳለበት አስገንዝበዋል። ይሁንና አንድ ዓመት ያስቆጠረው አገራዊ ለውጥ ከባለፉት ሥርዓቶችና የፖለቲካ ስሪቶች የተሻለ መሆኑንና ከውጫዊ ኃይሎች ይልቅ ውስጣዊ ኃይሎች በፈጠሩት ጫና የመጣ መሆኑ መልካም ጅምር መሆኑን አድንቀዋል። የአገሪቱ የአንድ ዓመት ጉዞም ከሞላ ጎደል የሚበረታታ ነው። ይሁንና በለውጡ ሁሉም የሚሳተፍበትና አግላይ ያልሆነ ብሎም ፖለቲካዊ መሰረቱ የፀና እንዲሆን ሁሉም አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው።
ሌላኛው ጥናት አቅራቢ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተመራማሪ ዶክተር ዲማ ነገዎ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለበርካታ ዓመታት በውጭው ርዕዮተ ዓለምና ጫና ስር የወደቀ እንደነበር ገልፀው፤ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የታየው ለውጥ ግን በዓይነትም ይሁን በይዘት የተሻለ ነው። ሆኖም ዛሬም ከ50 ዓመታት በፊት የሚጠየቁ ጥያቄዎች እየተሰሙ ሲሆን፤ ምላሾች እጅግ የዘገዩና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታዎች ተቋማዊ ከማድረግ አኳያ ደካማ መሆኑን አብራርተዋል።
ለውጡን እንደ ቀድሞ ሥርዓቶች የነበሩ ተቋማትን በማፈራረስ በአዲስ መጀመር ሳይሆን በውስጣዊ ፍትጊያ መፈጠሩ የዴሞክራሲ መሠረት ለመጣል ሰፊ ዕድል ይሰጣል ብለዋል። ይሁንና አሁንም ቢሆን በአገሪቱ ውስጥ ሁሉን አቀፍ እና አካታች ለውጥ ባለመዘርጋቱ መንግሥት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ህብረተሰቡ ወደ ተሻለ አገራዊ ግንባታ ለመግባት መታተር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ እንዳሉት፤ ለውጥ በረከት እየበዛ ክፋትን እየቀነሰ የሚሄድ መሆን አለበት። አገርን ለማፅናት ዴሞክራሲን ለማሳደግ በጉልበት ሳይሆን በስክነት፤ በመረጃና ማስረጃ፤ በአመክንዮ ላይ በተመሰረተ የሃሳብ ፍትጊያ መሆን ይገባዋል። የዘውግ፣ ቋንቋ እና ብሄር ስብስብ ሳይሆን የሐሳብ ልዕልና እንዲነግስ የውይይት ባህል እንዲዳብርም ዜጎችና ፖለቲከኞች ሊተጉ እንደሚገባም ፕሬዚዳንቷ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር