ለእውቀትም ለመንደርደሪያም፤
ዩጋንዳዊያን አገራቸውን የሚጠሩት “የአፍሪካ ዕንቁ – Perl of Africa” እያሉ ነው። በዕንቁ የተመሰለችውን ይህቺን አገር ይህ ጸሐፊ ለመጎብኘት ዕድሉ ገጥሞት ነበር። የሌሎች የአፍሪካ አገራት የጋራ ችግሮች የዚህች አገርም ችግሮች መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በርግጥም “ዕንቁ” ሊያሰኟት የሚችሉ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች እንዳሏት ግን አፍ ሞልቶ መመስከር ይቻላል።
የአገሬ ስደተኞችም ሆኑ በሕጋዊ መንገድ ምድሯን የረገጡ ወገኖቻችን ተደላድለውና እፎይ ብለው የሚኖሩባት የቀጣናችን እህት አገር መሆኗን ያለመግለጽ ንፉግነት ነው። አንዳንድ በዚያች አገር የሚኖሩና ኑሮው የተሳካላቸው የአገሬ ልጆች “እምዬ” የሚለውን የባህላችንን የፍቅር መግለጫ ቃል ተውሰው ብቻ ሳይሆን ስለሚገባት ጭምር ዕንቁዬዋን ዩጋንዳ የሚጠሯት “እምዬ ዩጋንዳ” እያሉ መሆኑን በዚያች ለምለም አገር ከምትኖረው የቀድሞ ተማሪዬ አንደበት ሰምቼያለሁ። ተጨማሪውን አክለውበት፣ የጎደለውን ሞልተውበት በዚያች ለምለም ምድር እየኖሩ ሕይወትን በማጣጣም ላይ ያሉ ዜጎቻችን የልባቸውን ደስታ ቢመሰክሩ የተሻለ ብቻ ሳይሆን የጸሐፊውን የወፍ በረር ዕውቀት ለማጠናከር ስለሚበጅ ጭምር ድምጻቸውን ቢያሰሙ መልካም ይሆናል።
ዩጋንዳን ለጽሑፌ መንደርደሪያነት የጠቀስኩት በአገሪቱን ጉዳዮች ላይ አጠቃላይ ገለጻ ለመስጠት ሳይሆን ተፈጥሮ በምድሯ ውስጥ የምትፈጽመውን አንድ አስደናቂ ክስተት ለማስታወስ በመፈለግ ነው። ከካምፓላ ከተማ 72 ኪሎ ሜትሮች ያህል ርቃ በምትገኘውና ኬያብዌ (Kayabwe) በመባል በምትታወቀው አነስተኛ ከተማ ውስጥ Uganda Equator በመባል የሚታወቅና ምሥጢሩ በተመራማሪዎች ዘንድ በምልዓት ያልተፈታ አንድ ታላቅ የምድራችን የተፈጥሮ የሃሳብ መስመር ከተማዋን አቋርጦ ያልፋል። ይህ የኢኩዌተር መስመር ከዩጋንዳ ሌላ በርካታ የላቲን አገራትንና ሁለቱን ኮንጎዎች፣ ጋቦንን፣ ኬኒያንና ሱማሊያን የመሳሰሉ አገራትንም እያቆራረጠ እንደሚያልፍ ልብ ይሏል።
ኢኩዌተር እያልን የምንጠራው ይህ የሃሳብ መስመር የምድር ሰቅ (ቀበቶ) ተብሎ እንደሚጠራ የተማርነው ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ስለመሆኑ ማስታወሱም አግባብ ይሆናል። በአጭሩ ለመከለስ ያህል ኢኩዌተር (የምድር ሰቅ) የሚባለው የሃሳብ መስመር የዓለማችንን የሰሜኑንና የደቡቡን ንፍቀ ክበባት እኩል ለእኩል ለሁለት እየገመሰ በዜሮ ዲግሪ ላቲቲዩድ ላይ የሚያልፍ መስመር ነው። አንድን ብርቱካን እኩል ለእኩል ወገቡ ላይ ከመክፈል ጋር ማስተያየት ይቻላል።
በ40 ሺህ 075 ኪሎ ሜትሮች በምድር ወገብ ላይ የተጠመጠመው ይህ የሃሳብ መስመር በዐይን የማይታይ፣ በእጅ የማይዳሰስና የማይጨበጥ ሲሆን የሚገለጸው በልዩ ተዓምራዊና ትንግርታዊ ባህርይው ነው። አንዳንድ ክስተቶችን እናስታውስ፡- በዚያ መስመር አካባቢ ፀሐይ የምትወጣውና የምትጠልቀው በተለመደው ዝግመታዊ ጉዞዋ ሳይሆን ክስተቱ የሚፈጸመው ፈጠን ብሎ ነው።
ሃምሳ ሴንቲ ሜትር ያህል እግራችንን አንፈራጠን በዚህ የሃሳብ መስመር ላይ ብንቆም በተፈጥሯዊ የምድር ስበት ምክንያት ከክብደታችን ላይ የተወሰነ ኪሎ እንቀንሳለን። እዚያው እግራችንን አንፈራጠን በቆምንበት ቦታ የውሃ መያዢያ ገበቴ ወይንም የእጅ ማስታጠቢያ ውሃ ይዘን ብንቆምና አንድ ሌላ ሰው ውሃ በጆግ እያንቆረቆረ ወደ ሰሜኑ ንፍቀ ክበብ ብንዞር ውሃው የሚሽከረከረው ልክ በእጅ ሰዓታችን የዙረት አቅጣጫ መሰረት ከግራ ወደ ቀኝ Clockwise አካሄድን ተከትሎ ነው። ገበቴውን ወደ ደቡብ አዙረን ውሃ ብናንቆረቁር ደግሞ በተቃራኒው ውሃው ከቀኝ ወደ ግራ Anticlockwise ሊሽከረከር ይችላል።
ከዚህ እውነታ እንደምንረዳው የዩጋንዳው ኢኩዌተር ሃምሳ ሳንቲ ሜትር በማይሞላ የንፍቀ ክበባቱ አካፋይ ድንበር ላይ ተፈጥሮ እንደምን በተዓምራት አድራጊነቷ እንደምትራቀቅ ጥሩ ማሳያ ነው። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ የሃሳብ መስመሩ ለሰዎች የስሜት መለዋወጥ ምክንያት እንደሚሆንም ግምት አላቸው። የዩጋንዳው ኢኩዌተር ይህንን ያህል ካጨዋወተን ዘንዳ ወደ መነሻ ጉዳያችን እንመለስና በአገራችን ጉዳይ እንደተለመደው ቁዘማችንን እንቀጥል።
የጠብ ሱሰኛ የዶሮ ሻኛ አቅርቡልኝ ይላል፤
የግለሰቦችም ሆነ የቡድኖች አንዳንድ የጠብ መቆስቆሻ ምክንያቶች ከዩጋንዳ የሃሳብ መስመር ባህርይ ጋር በሱስም ቢሆን ይመሳሰላል። የሃሳባቸውና የዓላማቸው ስርና መሠረት በግልጥ አይታወቅም፣ ምክንያታቸውም በሚገባ አይጨበጥም። ተግባራ ቸው ሁልጊዜ ሰላምን በማናጋት የከፋፋይነት ተግባር መፈጸም ነው። አንዳንዴ የሚያነሱት ሃሳብ ልክ እንደ Clochwise አቅጣጫ የያዘ ቢመስልም ወዲያው አላዋጣ ሲላቸው ጊዜ ሳይሰጡ ዞር ብለው ተቃራኒ ሃሳብ በመምዘዝ የAnticlockwise አቅጣጫ ሲመርጡ ይስተዋላል። በኢኩዌተር የሃሳብ መስመር ላይ ስንቆም ተፈጥራዊ ክብደታችን እንደሚቀንሰው ሁሉ በጠብ ሱሰኞች ንፍቀ ክበብ ውስጥ መገኘትም እንዲሁ በራሱ የሰብእናን ክብደት ያሳንሳል። የባህርያቸው ተገለባባጭነትም ያስገምታል።
የኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች እንደ ሰሜኑና ደቡባዊ ንፍቀ ክበባት ፋታ ነስተውን ወዲህ ስንል Clockwise አቅጣጫ የተከተለ ሲመስለን፤ ወዲያው ፋታ ሳይሰጠን ነገሮች ሁሉ Anticlockwise እየተጠማዘዙ የሚያተረማምሱን ትንፋሽ እየነሱ በማጣደፍ ነው። ዋነኛው ምክንያት ደግሞ በጠብ ሱሰኞች የሚቀነባበር የረቀቀ ሴራ እንደሆነ እያረጋገጥን ነው። እነዚህን መሰል በጠብ አራራ የናወዙ የአገርና የሕዝብ ጠንቆች ሌትና ቀን ሲቃዡ ውለው የሚያድሩት ሰላም እንዲደፈርስና መከራችን እንዲያስገብረን ነው። ሲያሻቸው የሃይማኖት ካባ ደርበው በሕዝብ መካከል ሰይጣናዊ ተግባር ይፈጽማሉ። ይህን መሰሉ እቅዳቸው ሲከሽፍባቸው ደግሞ በፖለቲካ በርኖስ ተጀቡነው የጨለማ ትጋታቸውን በመቀጠል አገር እንዳትረጋጋ ይፍጨረጨራሉ።
ሱስ ያቅበዘብዛል፤ እረፍትም አይሰጥም። አራራው እስካልሰከነና ማፋሸኩ እስካልተገታ ድረስ የሱሰኞቹ ውሎ አዳር በመቅበዝበዝ የተሞላ እንደሚሆን የዘወትር ገጠመኛችን ነው። የሲጋራ፣ የቡና፣ የመጠጥ ወይንም የዕፅ ሱሰኞች እውነታውን እንዲያረጋግጡልን ለምስክርነት ብንጠራ “የሱስን አቅበዝባዥ” ውጤት ምን እንደሚመስል ሊያብራ ሩልን ይችላሉ።
“ጠብ ያለሽ በዳቦ” እያሉ በሕዝብ መካከል የሚቅበዘበዙ “የደም ሱሰኞች” ባህርይ ግን፤ ምንም እንኳን ማወዳደሩ ተገቢነት ባይኖረውም፤ ከላይኞቹ ሱሶች መቶ እጥፍ የከፋና የከረፋ እንደሆነ ውጤቱ ምስክር ነው። ቆሌያቸው የንጹሐንን ደም ካላሸተተ በስተቀር አይሰክኑም፤ አይረጋጉም። ግጭትና ማተረማመስ፣ ማፈናቀልና ማሳደድ፣ ውድመትና ፍጅት የጠብ ሱሰኞቹ የተገለጡ የሱስ ማርኪያ ተግባራት ናቸው።
እነዚህ የጠብ ሱሰኞች ፀረ ሰላም መሆናቸው ብቻም ሳይሆን የፀረ ሰብዓዊ ክብር ጌቶችም ጭምር ናቸው። የረከሰው ሰብእናቸው ሁሌም የሚናፍቀው የሕዝብ ዕልልታን ሳይሆን የአገር ልቅሶና ዋይታን ነው። “በቀኝ አውለኝ” የሚለው የሰርክ ተለምዷዊ የማለዳ ጸሎት በእነርሱ አፍ አይዞርም፤ የተለመደም አይደለም። የሚመቻቸውና የሚኖሩለት የሕይወት ፍልስፍናቸው ጤና ነስቶ ጤና የሚያሳጣ “ግራ አዋዋል” ነው።
ለጠበኛ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች ፀሐይ ደምቃ መውጣቷ ያበሳጫቸዋል። የጨረቃ ድምቀትም ያስከፋቸዋል። የአገር ስኬት እንደ ቅንቅን ይኮሰኩሳቸዋል። የሕዝብ እረፍት ጤና ይነሳቸዋል። ስለዚህም ኑሮ ብለው “የሚሞቱለት የነፍሳቸው ጥሪ” ማፍረስና መናድ፣ መቃወምና ማጥላላት ብቻ ነው። ሰሜን ንፍቀ ክበብ ሲሏቸው ደቡብ፣ ደቡብ ሲሏቸው ምሥራቅ፣ ምሥራቅ ሲሏቸው ምዕራብ እያሉ መቅበዝበዝ ልማዳቸው ነው።
ለጠብ ሱስ መገለጫነት ከሚጠቀሱት መካከል አሸባሪው ሕወሓትና መጋለቢያ ጌኛዎቹ ተቀዳሚዎች ናቸው። ለምን የሰሜን ዕዝን ተዳፈሩ? በምን ምክንያትስ በአገሪቱ ላይ ጦርነት ለማወጅ ተደፋፈሩ? ለምንስ የሰላማችንን ርግብ አቆሰሉ? እኮ ለምን የትግራይን ሕዝብ በጋሻነት መመከቻ አድርገው በርሃብና በችግር እንዲቀጣ ፈረዱበት? መንግሥት ስለ ሰላም ሲናገር ለምን ሽብርን የሙጥኝ አሉ? ሲያሻቸው እንደ Clockwise አቋማቸውን ከግራ ወደ ቀኝ ይቀይራሉ፣ ሲፈልጉ በAnticlockwise አቋማቸው እየተሽከረከሩ የዓለም ማኅበረሰብን ግራ ያጋባሉ።
በዚህ አቋማቸው ምን ያህል ኅሊናቸው “በጥቁር ትዕቢት” እንደተሸፈነ ማረጋገጥ አይከብድም። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በውስጣቸው ያረገዙት የጸብ ሽል “ግፋ በለው!” እያለ ስለሚያስገዝፋቸው ነው። አገር በማሸበር ላይ ያሉ መልከ ብዙ ቡድኖችም ቢሆኑ “ሰላምን ሸጠው” ጠብ ለመሸመት በጌቶቻቸው አማካይነት ስምሪት ስለሚሰጣቸው ከነፍሳቸው ጋር እየመከሩ በራሳቸው የሚወስኑት ምንም ዓይነት አቋም አይኖራቸውም።
የጠብ ሱሰኞችን በሌሊት ወፍ መመሰልም ይቻላል። የሌሊት ወፎች በበራሪዎች ዝርያ ውስጥ ይመደቡ እንጂ በሌላ ባህርያቸውም ከእንስሳት ወገን የሚመደቡ አጥቢዎችም ጭምር ናቸው። የሌሊት ወፎች ደምና ጥምብ ሥጋ እንደ ነፍሳቸው የሚወዱት ምግባቸው ነው። በሰዎች አእምሮ ውስጥ ከቫምፓየሮች ጋር የተቆራኙትም ስለዚሁ ነው። የሌሊት ወፎች አፈጣጠር እጅግ የተወሳሰበ ነው። አብዛኛው መኖሪያቸውም ምድረበዳና በዋሻ ውስጥ ነው። ብርሃን ለሌሊት ወፎች ፀር ስለሆነ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት በድቅድቅ ጨለማ ነው። ስለ እነዚህ ግራ አጋቢ እንስሳት ብዙ ማለት ይቻላል።
የጠብ ሱሰኞች ሁሌም ቆሌያቸው የሚያፋሽከው ለሕዝብ እልቂትና ለአገር ማፍረስ ሴራ ነው። ባህሪያቸው፣ አኗኗራቸውና ሕይወታቸው ልክ እንደ ሌሊት ወፍ ግራ የተጋባ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩትን ጽሑፎች፣ ምስሎችና ድምጾች ልብ ብሎ በማጤን ብቻ ባህርያቸውን በሚገባ ማየት ይቻላል። ገድለው ወይንም አስገድለው ራሳቸው ድራማ ሲሰሩ አያፍሩም፤ አይጸጸቱም።
ከዚህ በላይ ምን ማለት ይቻላል። ሕዝብ ለማባላት ሴራቸውን እየሸመኑ ያሉት በእኛው መካከል ተቀምጠው ነው። አገር ለማፈራረስ ወጥመድ የሚዘረጉትም እኛው መሃል ሆነው የክፋት እንከርዳድ በመዝራት ነው። አገሬ ሆይ! ያጥናሽ ብለን አንደመድምም። ምክራችን፡- “መንግሥታችን ሆይ! ጥያቄ አለን? በማሳ ላይ ከበቀለው አዝመራ ውስጥ ተመሳስሎ የሚበቅለውን አረም ለመለየትና ለማስወገድ እጅግም አይቸግርም። እንደነዚህ ዓይነቶቹን የጠብ ሱሰኞች የምትለይበትና ለፍትሕ የምታቀርብበት ሥርዓት የላላ አይመስልህም? ዛሬም የጽሑፋችን ማሳረጊያ “ልብ ያለው ልብ ይበል” የሚለው ይሆናል። ሰላም ይሁን!
በ(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2014