ደብረብርሃን፡- ከ20 ዓመታት በፊት በደብረብርሃን ከተማ የተቋቋመውና ምርቶችን ለውጭ ገበያ የሚያቀርበው ጥቁር አባይ ቆዳ ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ከፍተኛ የጤና መታወክ እንዳስከተለባቸው ነዋሪዎች አስታወቁ።
ፋብሪካው በበኩሉ ሥራ በማቆም ለመፍትሄ እየሠራ ቢሆንም ቀጣይ ዕጣ ፈንታውን ለመወሰን የከተማ አስተዳደሩን ቆራጥ ውሳኔ እፈልጋለሁ ብሏል።
ነዋሪዎቹ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደገለፁት፤ ፋብሪካው በቀበሌ 07 በተለምዶ ኢላላ በሚባለው አካባቢ ማንአግዶ ምንጭ ራስጌ ከፍታ ቦታ ላይ የተገነባ ሲሆን፤ በአካባቢው ትምህርት ቤት፣ ቤተ እምነቶችና ሌላ ማህበራዊ ግልጋሎት በሚሰጡ ተቋማት የተከበበ ነው። ከፋብሪካው በአጥር ብቻ ወሰን የተበጀላቸው የዱቄት ፋብሪካዎችና በርካታ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ከፋብሪካው በሚወጣው ቆሻሻና ሽታ በጤናቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል።
«ለአተነፋፈስ ችግር፣ ለቆዳ እና ተያያዥ በሽታዎች ተጋልጠናል» ያሉት ነዋሪዎቹ፣ ችግሩን በተደጋጋሚ ለማስረዳት ብንሞክርም የፋብሪካው ‹‹ባለቤት ነኝ፣ ሥራ አስኪያጅ ነኝ›› በማለት ግለሰቦች እየተቀያየሩ በመምጣት የተለያዩ ማደናገሪያዎችን ከመፍጠር በዘለለ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሄ ባለመስጠታቸው መንግሥት ቆራጥ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከፋብሪካው የሚለቀቀው ኬሚካል ከሳር እና ውሃ ጋር የሚቀላቀል ሲሆን፤ ፉሩሽካ የሚታሽበትና እንስሳት ከሚጠጡት ውሃ ላይ ውስጥ ለውስጥ በማስረግ ይገናኛል። በፋብሪካው በቅርበት የሚገኙ ነዋሪዎች ደግሞ ከእነዚህ እንስሳት የሚገኝ ወተት ለከተማው ህዝብ ያስረክባሉ። በተለይም በክረምት ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ኬሚካል የሚለቀቅ ሲሆን፤ ሽታው በጤና ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው። ይህን ችግር ለከተማው መስተዳድር፣ ለዞን እና ለክልል የሥራ ኃላፊዎች ተደጋጋሚ ቅሬታ እያቀረብን ዘላቂ መፍትሄ ማጣታችን አሳዝኖናል ብለዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ ከንቲባ ቢሮ የህዝቡን ቅሬታ መነሻ በማድረግ ሐምሌ 11 ቀን2010 ዓ.ም ደብዳቤ ቁጥር በደብከአ/879/1-1/2010 ለፋብሪካው በፃፈው ደብዳቤ ከፋብሪካው የሚወጣው ሽታ ነዋሪዎችን በከፍተኛ ደረጃ እየረበሸ በመሆኑ ሽታው እስካልቆመ ድረስ ፋብሪካው በአምስት ቀናት ውስጥ ሥራ እንዲያቆምና ደብዳቤው ግልባጭ የተደረገላቸው ተቋማት ክትትል እንዲያደርጉም አሳስቦ ነበር።
በሌላ ደብዳቤ ደግሞ የአማራ ክልል የአካባቢ፣ ደንና የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለሥልጣን ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም በፃፈው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ከፋብሪካው የሚወጣው ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ ወደ በሬሳ ወንዝ በመግባት የከፋ አደጋ እያደረሰ መሆኑን ጠቁሟል። ለዚህም ጉዳዩ የሚመለከተው የፌዴራል መንግሥት ባደረገው ክትትልና 10 ገፅ ሪፖርትን መነሻ በማድረግ ማስጠንቀቂያውን እንደፃፈ አትቷል። ችግሩ የማይስተካከል ከሆነም ባለሥልጣኑ የእርምት እርምጃ እንደሚወስድና ጉዳዩን ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ጭምር አሳውቃለሁ ብሎ ነበር።
የጉዳዩን አሳሳቢነትና የነዋሪዎችን ቅሬታ ከምን አደረሳችሁት ስንል ለደብረብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ደስታ አንዳርጌ ጥያቄ ያቀረብን ሲሆን፤ የነዋሪዎቹ ቅሬታ አግባብ መሆኑንና ለዓመታት ሲንከባለል የመጣ ችግር መሆኑን ተናግረዋል።
የቆዳ ፋብሪካው ከአንድ ፋብሪካ በስተቀር ማንም ባልነበረበት ወቅት ለልማት የመጣ ነው። ይሁንና የደረቅ ቆሻሻ ቦታ አልነበረውም፤ የቆሻሻ የማከም ሥራውም መልካም አልነበረም። ሆኖም ፋብሪካው አሽጋችሁ ውጡ ማለት አንችልም። ይሁንና አሁን ባለው ሁኔታ አካባቢው ላይ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ ፋብሪካው ሥራ አቁሟል። ለጊዜውም የቆሻሻ አወጋገዱን እንዲያዘምን ለደረቅ ቆሻሻ ማከሚያና ፍሳሽ አወጋገዱን ለማዘመን በ25 ሚሊዮን ብር ግንባታ እያከናወነ መሆኑን እናውቃለን ብለዋል።
በሌላ በኩል ፋብሪካው ቀድሞ የተመሰረተ በመሆኑ በአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሰፍሩ መደረጉ ተገቢ አልነበረም። ስህተቱ የፋብሪካው ብቻ ሳይሆን የመንግሥትም ችግር እንደነበር አስታውሰዋል። የሆነው ሆኖ የፋብሪካው ዕጣ ፈንታ በቅፅበት መወሰን ባይችልም፤ አሁን ባለበት ሥፍራ የመቀጠሉ ዕድል አነስተኛ መሆኑን አቶ ደስታ ገልፀዋል።
የጥቁር አባይ ቆዳ ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ ተክሉ በበኩላቸው፤ ፋብሪካውን ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ከልማት ባንክ 34 ሚሊዮን ብር በጨረታ የተገዛ ነው። በወቅቱ ቦታው የኢንዱስትሪ ቀጣና ተብሎ የተሰጠና ከከተማው በእጅጉ የራቀ ነበር። ይሁንና በሂደት በአካባቢው የዱቄት ፋብሪካ እንዲከፈትና ነዋሪዎች በአካባቢው ቤት እንዲገነቡ ተደርጓል። ፋብሪካው አገርን ለመጥቀምና ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተቋቋመ እንጂ ከነዋሪዎች ጋር ሆድና ጀርባ ሆኖ መቀጠሉ እንዳላስደሰተው ተናግረዋል። በነዋሪዎች ቅሬታና በተለያዩ አካላት ጫና የተነሳም ካለፈው ወር ጀምሮ ፋብሪካው ሙሉ ለሙሉ ሥራ አቁሟል። መፍትሄ ይሆን ዘንድም ሁለተኛ ዘመናዊ ማጣሪያ እየተገነባ ነው። ሽታውን ማስቆም ከተቻለም ድርጅቱ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችና አማራጮች ይጠቀማል። ሆኖም በዚህ ቅሬታ መቀጠሉ ለፋብሪካውም ሆነ ለነዋሪዎች ጠቃሚ እንዳልሆነና መፍትሄ ለማግኘትም ከከተማ አስተዳደሩ እስከ ክልል ድረስ ጥረት መደረጉን አስታውሰዋል። ኃላፊዎች እየተቀያየሩ ዘላቂ መፍትሄ አለመገኘቱን አብራርተዋል።
ከዚህ ሁሉ እሰጣ ገባ ፋብሪካው መነሳት ካለበትም የማያወላዳ ውሳኔ ማሳለፍና ሕጋዊ ሥርዓቱን ተከትሎ መሄድ እንደሚበጅም ጠቁመዋል። ለፋብሪካው ቀጣይ ዕጣ ፈንታው ለመወሰን የከተማ አስተዳደሩ ቆራጥ ውሳኔ ያስፈልጋል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር