ዓለማችንን ከጫፍ እስከ ጫፍ የሚያስተሳስሩ መሰረተ ልማቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል። ከዚህ የተነሳ ጊዜ፣ ጉልበትና ከፍተኛ መዋለ ንዋይ የሚጠይቁ አገልግሎቶች መፍትሄ እያገኙ ነው። ለምድራችን እድገትና ፈጣን ትስስር መፍትሄ ሆነው ከመጡት ውስጥ ደግሞ የዲጂታልና ኔትወርክ ቴክኖሎጂና መሰረተ ልማት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።
ለሞባይል ስልክ ግንኙነት፣ ለበይነ መረብ እንዲሁም የተለያዩ የቴክኖሎጂ ቁሶችን “ዲቫይስ” ለማስተሳሰር ደግሞ የኔትወርክ መሰረተ ልማት ጉልሁን ድርሻ ይወስዳል። ይህ መሰረተ ልማት ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት እያሳየ የመጣ ሲሆን፣ ፈጣንና በሰከንድ ልዩነት በምድራችን ላይ ያሉ መረጃዎች ደጃፋችን ላይ በፍጥነት እንዲደርሱ እያስቻለ ይገኛል። በተለይ የበይነ መረብና የስልክ ግንኙነት ከ2ጂ አንስቶ እስከ 5ጂ ትውልድ የደረሰ ሲሆን፣ ይህም በቴክኖሎጂ ረገድ በዚህ ዘመን ይመጣል ተብሎ ከሚታሰበው የእድገት ለውጥ በእጅጉ የፈጠነ እንደሆነ ይነገራል።
ኢትዮጵያ በየደረጃው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽ እንዲሆን እየሰራች ትገኛለች። ከዚህ ውስጥ የቴሌኮም ዘርፉ ቀዳሚውን ቦታ እንደሚይዝ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቴሌኮም አገልግሎት “የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይን ማሳካት” የሚል ግብ አስቀምጦ የ3ጂ እና 4ጂ ኔትዎርክ በማስፋፋትና 97 በመቶ የቴሌኮም አገልግሎት ሽፋን በማረጋገጥ ያሉትን ቀደምት ቴክኖሎጂዎችን ዘመን አፈራሽ ወደሆኑ ቴክኖሎጂዎች በማሳደግና በማሻሻል ላይ መሆኑን በኢትዮጵያ ዘርፉን እያስተዳደረ እና እየመራ የሚገኘው ኢትዮ ቴሌኮም በተለያዩ መድረኮች በሚያወጣቸው መረጃዎች ያሳውቃል።
ይህንኑ የኔትወርክ ቴክኖሎጂ አማራጭና እድገት ለተለያዩ አላማዎች በማዋል ተጨማሪ ምርትና አገልግሎቶችን ወደ ገበያ በማቅረብ፣ የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት እንዲሁም መሰል ዲጂታል አገልግሎቶችን በማስጀመር የዜጎችን አማራጮች ለማስፋት በሚደረገው ሂደት ላይ ሚናውን እያሰፋ መሆኑን ድርጅቱ በየጊዜው ይፋ ከሚያደርጋቸው መረጃዎቹ እንረዳለን።
ከሰሞኑ ደግሞ ኢትዮ ቴሌኮም የቴሌኮም አገልግሎቶችን የሚያቀላጥፈውን የ5ጂ የሞባይል ቴክኖሎጂ የሙከራ አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ በስድስት ጣቢያዎች ማስጀመሩን ሰምተናል። ይህ የ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት ዳታ የማስተላለፍ መዘግየትን እጅግ በላቀ ሁኔታ ይቀንሳል፤ በርካታ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን እርስ በርሳቸው ለማገናኘትም ያስችላል። ወሳኝ ተልዕኮ ላላቸው እና በተመሳሳይ ወቅት መከናወን የሚፈልጉ አገልግሎቶችን ለአብነትም የማምረቻ ፋብሪካዎችን፣ ግብርናን፣ ህክምናን ለመሳሰሉት እጅግ የላቀ ፋይዳ አለው።
የ5ጂ ኔትወርክ በኢትዮጵያ ለምን?
ኢትዮ ቴሌኮም የ5ኛ ትውልድ (5ጂ) የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት በአዲስ አበባ በይፋ ባስጀመረበት ወቅት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ “የ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ ለማህበራዊ ተቋማት ፈጣን አገልግሎትና ለኢንዱስትሪዎች ውጤታማነት የላቀ ሚና ይኖረዋል” ሲሉ ተናግረዋል። የ5G የሞባይል ኔትወርክ በኢትዮጵያ በይፋ መጀመሩ የጤና አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማፋጠን እንዲሁም ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ያስረዳሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት እስከ 10 ጂቢ የሚደርስ ከፍተኛ ፍጥነት አለው፤ ዳታ የማስተላለፍ መዘግየትን (Ultra low latency) በመቀነስ ወደ 1 ሚሊ ሰከንድ የሚያደርስ ነው። በተጨማሪም በአንድ ካሬ ኪሎ ሜትር ውስጥ እስከ 1 ሚሊዮን የሚደርሱ በርካታ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን እርስ በእርሳቸው ለማገናኘት የሚያስችል ዓለማችን የደረሰበት የመጨረሻ የገመድ አልባ ቴክኖሎጂ ነው፤ ይህን መሰረተ ልማት በኢትዮጵያ ውስጥ ማስጀመር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
በተለይ ይሄው ፈጣን ቴክኖሎጂ የማምረቻ ፋብሪካዎች፣ ግብርና፣ ህክምና፣ ለመሳሰሉ ኢንዱስትሪዎች እጅግ የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ ምክንያት ኩባንያው የ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ የቅድመ ገበያ የሙከራ አገልግሎት በአዲስ አበባ ያስጀመረ መሆኑን ተናግረዋል፤ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ከተሞች እስከ 150 ጣቢያዎች የመትከል እቅድ መያዙንም ይፋ አድርገዋል።
ከተለያዩ መረጃዎች መረዳት እንደምንችለው ኢትዮ ቴሌኮም የ5ጂ ቴክኖሎጂን እውን ማድረጉ ተመራጭ የቴሌኮም ኦፕሬተር ለመሆን ከቀረጸው የሦስት ዓመት የእድገት ስትራቴጂ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ነው።
የ5ጂ ኔትወርክ ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፋዊ ዳሰሳ
5ጂ የቀጣዩ የገመድ አልባ ትውልድ አውታረ መረብ ቴክኖሎጂ የሰዎችን አኗኗር እና አሠራሩን ይለውጣል ተብሎ ይጠበቃል። አሁን ካለው የ4ጂ (LTE) አውታረ መረብም የበለጠ ፈጣን እና እርስ በእርስ የተገናኙ እጅግ በርካታ መሳሪያዎችን ማስተናገድ የሚችል ይሆናል። ይህ ማሻሻያ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ምርቶችን እና ግልጋሎቶችን ከማስተዋወቅም ባለፈ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ ምርምር ለሚያደርጉ አያሌ ባለሙያዎች ሰፊ እድል ይከፍታል።
የ5ጂ አውታረ መረብ በዩናይትድ ስቴትስ እና በዓለም ዙሪያ መሰራጨት የጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 በመጀመሪያዎቹ ወራት ነበር። ይህ የአምስተኛው ትውልድ ኔትወርክ በሙሉ አቅም በዓለማችን ላይ ገና አልተሰራጨም። “ባለሙያዎች እምቅ አቅሙ ግዙፍ ነው” ይላሉ። በተለይ ታላላቅ ኩባንያዎች በጣም ፈጣን የሚባለውን ወይም ትልቁ የ5ጂ አውታረ መረብ እንዲኖራቸው እሽቅድምድም ላይ እንደሆኑ አያሌ መረጃዎች ያሳያሉ። አገሮችም በአገር አቀፍ ደረጃ 5ጂ ሙሉ በሙሉ የሚሰራ ኔትወርክ ለመዘርጋት ቀዳሚ ለመሆን እየተፎካከሩ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት የአዲሱ የ5ጂ ኔትወርክ ጥቅም ለግለሰብ ተጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆን ለንግድ፣ ለመሠረተ ልማት እና ለመከላከያ መተግበሪያዎችም ለውጥ አምጭ ቴክኖሎጂዎችን ያቀጣጥላሉ ተብሎ ስለሚጠበቅ ነው።
ከመረጃዎች መገንዘብ እንደምንችለው በ5ጂ ዙሪያ ያለው አብዛኛው ማበረታቻ ከፍጥነት ጋር ቢያያዝም፣ ሌሎች ጥቅማጥቅሞችም አሉት። 5ጂ ከቀደሙት የኔትወርክ ትውልዶች በተሻለ መልኩ የበለጠ የመተላለፊያ ይዘት ይኖረዋል፣ ይህም ማለት ከቀደሙት አውታረ መረቦች የበለጠ ብዙ የተገናኙ መሳሪያዎችን ማስተናገድ ይችላል። ምንም እንኳን በተጨናነቀ የኔትወርክ አካባቢ ውስጥ ቢሆኑም ከአሁን በኋላ አስቸጋሪ አገልግሎትና መጓተት አይኖርም ማለት ነው።
ሌላው በቀደሙት የኔትወርክ ትውልዶች ሊከወኑ አስቸጋሪ የሆኑ አገልግሎቶችን ለማቀላጠፍ ከማገዙም በላይ ከሰው ንክኪ ውጭ የሚሽከረከሩ መኪኖችንና የመሳሰሉትን ተጨማሪ የተገናኙ መሳሪያዎችንም በሚፈለገው መንገድ ግንኙነታቸውን ለማቀላጠፍ ያስችላል። 5ጂ መዘግየትን ይቀንሳል። በተለይ ደግሞ የሞባይል ስልክ (ወይም ሌላ የተገናኘ መሳሪያ) ከአገልጋይ ጥያቄ ለማቅረብ እና ምላሽ ለማግኘት የሚፈጀው ጊዜ ወደ ዜሮ እንደሚቀንስ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከደመና መድረኮች (ክላውድ ቴክኖሎጂ) ግንኙነትን፣ የአማዞን ድር አገልግሎቶችን እና ማይክሮሶፍት መሰል ግልጋሎቶችን ፈጣን እና ቀላል ያደርጋቸዋል።
የ5ጂ መሰረተ ልማት እንዴት ይሰራል
በ5ጂ፣ ሲግናሎች በአዲስ የሬዲዮ ድግግሞሾች (ራዲዮ ፍሪኪዌንሲ) እንደሚሰሩ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህም በተንቀሳቃሽ ስልኮችና የኔትወርክ አስተላላፊ ማማዎችን እና ሌሎች መሳሪያዎችን ማዘመን ይፈልጋል። የ5ጂ አውታረ መረብን ለመገንባት ሶስት የተለያዩ ዘዴዎች እንዳሉም ባለሙያዎች ይናገራሉ። አንደኛው ገመድ አልባ አገልግሎት አቅራቢው ባለው የንብረት አይነት ላይ በመመስረት ዝቅተኛ-ባንድ አውታረ መረብ (ሰፊ የሽፋን ቦታ ግን ደግሞ ከ4ጂ በ20 በመቶ ፍጥነት ብቻ) የሚጠቀም ሲሆን ፣ ሁለተኛው ባለ ከፍተኛ ባንድ አውታረ መረብ ሲሆን (እጅግ በጣም ፈጣን፣ ግን ደግሞ በሲግናል አማካኝነት የሚሰራ ነው) ሶስተኛው ደግሞ የመሃከለኛ ባንድ ኔትወርክ (ፍጥነትን እና ሽፋንን መሰረት ያደረገ) ነው።
አገልግሎቱን ለማሰራጨትና ተደራሽ ለማድረግ እጅግ በጣም ፈጣን የ5ጂ ኔትወርኮችን የሚገነቡ ተሸካሚዎች እንዲሁም ብዙ ቶን የሚይዙ አነስተኛ የሕዋስ ጣቢያዎችን መጫን እንደሚኖርባቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ለምሳሌ በአሜሪካ በዚህ ምክንያት፣ እጅግ በጣም ፈጣን ኔትወርኮች በብዛት በከተማ እየተሰማሩ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። ውሎ አድሮ፣ አብዛኛዎቹ የአሜሪካ አገልግሎት አቅራቢዎች ሰፊ ሽፋን ያላቸውና እና ፈጣን የተለያዩ የኔትወርክ መሰረተ ልማቶች እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።
ኢትዮጵያም ይህንን መሰረተ ልማት በቀጣዮቹ አመታት በመገንባት ተደራሽ ለማድረግ እየሰራች መሆኑን ለማንሳት ሞክረናል። የ5ጂ ኔትወርክን በአፍሪካ በቀዳሚነት በማስገባትም የቴሌኮም ዘርፉን ለማዘመን ከመንግስት በኩል ቁርጠኝነት መኖሩን መገንዘብ ይቻላል።
በጣም ፈጣኑ የ5ጂ ኔትወርኮች ከ4ጂ ኤልቲኢ ቢያንስ በ10 እጥፍ ፈጣን እንደሚሆኑ ይጠበቃል ሲል የገመድ አልባ ኢንዱስትሪ ንግድ ቡድን ጂ ኤስኤምኤ አስታውቋል። አንዳንድ ባለሙያዎች ደግሞ አምስተኛው ትውልድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዘመነና እየተሻሻለ ሲመጣ 100 እጥፍ ፈጣን ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ። ይህ ማለት የሁለት ሰዓት ፊልም ከ10 ሰከንድ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማውረድ በቂ ይሆናል እንደማለት ነው። በ7 ደቂቃ አካባቢ ደግሞ በ4ጂ መጠን ያለው ፋይል ከበይነ መረብ ላይ ማውረድ ያስችላል። ትክክለኛው ፋይሎችን ወደ ኮምፒውተር አሊያም ሞባይል ለማውረድ ፍጥነቶች በበርካታ ሁኔታዎች ላይ እንደሚሞረኮዙ መገንዘብ ይቻላል። ከዚህ ውስጥ ዋናው የአካባቢ እና የአውታረ መረብ ትራፊክ አንዱ ነው።
ዜጎች እንዴት ሊጠቀሙበት ይችላሉ?
ዜጎች ከ5ጂ ኔትወርክ ጋር ለመገናኘት እና ጥቅማጥቅሞችን ለማግኘት ለ5ጂ ኔትወርክ የነቁና ብቁ የሆኑ መሳሪያዎች ሊኖራቸው ይገባል። ለምሳሌ ያህል ሳምሰንግ፣ ሞቶሮላ፣ ሁዋዌ፣ ኤልጂ፣ ዋንፕላስ እና ሌሎች በርካታ የሞባይልና ኮምፒውተር አምራቾች ለ5ጂ የሚሆኑ ስልኮችን አስተዋውቀዋል። የአፕል ካምፓኒ 5ጂ አይፎን ከፈረንጆቹ 2020 በኋላ መልቀቁ የሚታወስ ነው።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2014