‹‹አፋን ኦሮሞ›› የፌዴራል መንግስት የሥራ ቋንቋ ሆኖ እንዲያገለግል ጥያቄ እየቀረበ ይገኛል፡ ፡ ሰሞኑን ‹‹አፋን ኦሮሞ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ቢሆን ያለው ጠቀሜታ/ዕድሎች›› በሚል ርዕስ የአምቦ ዩኒቨርሲቲና የኦሮሚያ ቱሪዝም ቢሮ በጋራ የውይይት መድረክ አዘጋጅተዋል፡ ፡ በውይይቱ ላይም ምሁራን ጥናታዊ ጽሁፎችን አቅርበው ውይይት ተካሂዶበታል፡፡
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ አምስት ላይ አማርኛ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ እንደሆነ በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ ኢትዮጵያ በጽሁፍ የሰፈረ የቋንቋ ፖሊሲ አዘጋጅታ ተግባራዊ አላደረገችም፤ ይልቁኑ ፖሊሲው ገና በረቂቅ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም አፋን ኦሮሞ ተጨማሪ የፌደራል መንግስት ስራ ቋንቋ ይሁን የሚለው ሀሳብ ከህገ መንግስቱና ሌሎች ተያያዥ ጉዳች አንፃር እንዴት ይታያል የሚለውን በዚህ ፅሁፍ ለመተንተን ተሞክሯል፡፡
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ውይይት ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ካቀረቡት መካከል በዩኒቨርሲቲው የሥነጽሁፍ ትምህርት ክፍል የአፋን ኦሮሞ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ዱላ ከፈና አንዱ ናቸው፡፡ ‹‹ቋንቋ ባህልና የማህበረሰብ ግንኙነት›› (language culture society relationship) በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ እንዳስታወቁት ቋንቋ ባህልና ማህበረሰብን እንዴት እንደሚፈጥር፣ ማህበረሰብን በመፍጠርና ባህልን በማዳበር ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡
የረዳት ፕሮፌሰር ዱላ ጥናታዊ ጽሁፍ እንደሚያመለክተው ቋንቋ ለመግባቢያ ብቻ ሳይሆን፣ ባህልን ለማዳበርና የማህበረሰብን አንድነት ለማጠናከር ጥቅም ላይ የሚውል መሳሪያ ነው። በመሆኑም ቋንቋ በስፋት ጥቅም ላይ ካልዋለ ማህበራዊ ትስስር ይገደባል። ‹‹አፋን ኦሮሞ›› የሀገሪቷን የቆዳ ስፋት በብዛት የያዘ፣ በህዝብ ብዛቱም ከፍተኛ፣ አንዲሁም ብዙ ተናጋሪ ያለው መሆኑን በመጥቀስ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ቢሆን ፋይዳው የጎላ እንደሆነ በጥናታቸው አመላክተዋል። በሀገር ውስጥ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በተወሰኑ አካባቢዎች የሚጠቀሙት ፊደል ከ‹‹አፋን ኦሮሞ›› ፊደል ጋር ተመሳሳይ ያለው መሆኑን፣ በጎረቤት ሀገሮች ኬኒያና ታንዛኒያ ውስጥም የ‹‹አፋን ኦሮሞ›› ቋንቋ ተናጋሪዎች መኖራቸውን አስታውሰው በቋንቋው የሚጠቀም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኝ ህዝብ ሰፊ እንደሆነ ያስረዳሉ።
በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል አካባቢ ቦረና፣ ኮንሶ፣ጉጂና ጌዲኦ ብዙ የሚጋሯቸው ነገሮች እንዳሉና በአንድ ቋንቋ በተለይ ‹‹አፋን ኦሮሞን›› ቢጠቀሙ ባህላቸውን ማዳበር ይችላሉ፤ አስተርጓሚም አያስፈልጋቸውም ይላሉ፡፡ ረዳት ፕሮፌሰሩ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ እና በወለጋ ዩኒቨርሲቲዎች በ‹‹አፋን ኦሮሞ›› እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት መሰጠቱን እንዲሁም በሥነጽ ሁፍና በኪነጥበብ ውስጥ ያለው ሚና መጎልበት የቋንቋውን ማደግ እንደማሳያ አቅርበዋል።
በምሥራቅና በምዕራብ የሚነገረው ‹‹አፋን ኦሮሞ›› ዘዬ ወይም ቀበሌኛ በትምህርት እየተፈታ እንደሆነም ይገልጻሉ። መፍታት ያልተቻለው የአካባቢ የአነጋገር ዘዬ ‹‹accent›› እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹አፋን ኦሮሞ›› የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ቢሆን የሚያስገኘውን ጥቅም ያጎሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ተግዳሮት ብለው ያስቀመጡትም አለ፡፡
ባለፉት አመታት የነበሩትን አሰራሮች በአንዴ ለመቀየር አስቸጋሪ መሆኑን፣ ማህበረሰቡ ይጠቅመናል ብሎ እንዲነሳሳ ለማድረግ እንዴት መሰራት እንዳለበትና አጠቃላይ ተደራሽነቱ ላይ ክፍተት አለ ብለዋል። እንደመፍትሄም ያመላከቱት በህገመንግሥቱ ላይ ክልከላም ሆነ ፍቃድም ስለሌለው ‹‹አፋን ኦሮሞ›› የሥራ ቋንቋ መሆን ነው።
ረዳት ፕሮፌሰሩ የ‹‹አፋን ኦሮሞ›› የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሁን የሚለው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ስለመሆኑ ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሰንደቅ ዓላማ፣አንድ ማህበረሰብ ሲባል የኖረ በመሆኑ የብዙሃን ጥያቄ ይሆናል ብሎ መጠበቅ አይቻልም፡፡ ‹‹በንጉሱ ጊዜ በቤተ እምነት ሳይቀር አፋን ኦሮሞ ጥቅም ላይ እንዲውል አይፈቀድም ነበር። ከዚያ ወዲህ ባለው ሥርዓትም ለቋንቋው የተሰጠ ትኩረት የለም፡፡
ከ80 በላይ የሚሆን ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባለበት ሀገር ህዝቡ አፋን ኦሮሞ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ይሁን ይላል ተብሎም አይታሰብም። ሁሉም ጥቅሙን እስኪረዳ ጊዜ ይወስዳል። ጥያቄው ለጊዜው የኦሮሞ ህዝብ ነው›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ዶክተር ተፈራ አማረ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት በዚህ ረገድ የፖለቲካ ተዋናዮች ሚናቸው የጎላ በመሆኑ ጥያቄው የህዝብ አጀንዳ እንዲሆን ተጽዕኖ ይፈጥራሉ። አስፈላጊነቱ ላይም አንዳንድ ምሁራን በጽሁፍ በማሳተም፣በተለያዩ መድረኮች ላይም ‹‹አፋን ኦሮሞ›› የሥራ ቋንቋ ቢሆን አስፈላጊነቱን ሲያነሱ መስማታቸውን ያስታውሳሉ። እነዚህ ሁሉ ‹‹አፋን ኦሮሞ›› የፈዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ግፊት ይፈጥራል ብለዋል፡፡
እርሳቸው እንዳሉት ጥያቄውን ማን አነሳው? ሳይሆን መሆን ያለበት፣ ፋይዳው መታየት ያለበት። ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሀገር መሆኗ ይታወቃል። በሀገር ግንባታ ሂደት ደግሞ ዜጎች ስለሀገራቸው ያለፈ አመለካከት ያላቸው ምስልና በጋራ የሚያስማማቸው ነገር መኖር አለበት።
እንዲሁም ዜጎች በመንግሥታዊ መዋቅርና አሰራር ውስጥ የቋንቋውን አገልግሎት ማየት ይፈልጋሉ፡፡ ብሄሮች ከሚገለጡባቸው አንዱ ቋንቋ በመሆኑ።
ቋንቋ ህዝብና ህዝብን ለማቀራረብ አንዱ መንገድ ነው። ‹‹አፋን ኦሮሞ›› የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን እውቅና የማግኘት አንድምታ በተለይ ደግሞ ‹‹እበደል ነበር›› የሚል አስተሳሰብ ላለው ቡድን እንደ አንድ በጎ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል። ከአንድ በላይ የሥራ ቋንቋ ለኢትዮጵያ ገና አዲስ ጥያቄ ይሁን እንጂ ሶስትና ከዛም በላይ የሚተገብሩ ሀገሮች አሉ ሲሉም አለም አቀፍ ተሞክሮዎችን አስቀምጠዋል። ሲ
ውዘርላንድ፣ ካናዳን እና ሌሎች ሀገሮችንም በማሳያ ያነሳሉ። ከዚህ አንጻር ተጨማሪ ቋንቋ እንደሀገር ይጠቅማል። ተግዳሮት የሚሆነው ጤናማ ባልሆነና ልቅ በሆነ መንገድ ውድድር ውስጥ ሲገባ ነው። እንዲህ አይነት ችግሮች ከወዲሁ ካልታሰበባቸው ስጋት አለው። ለችግሮቹም መፍትሄ ያሉትን ጠቁመዋል።
የቋንቋ ፖሊሲ የሚቀርጹ ባለሙያዎች ጥያቄውን ታሳቢ ያደረገ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሥራ ቋንቋን ከሀገሪቷ ብሄራዊ ቋንቋ ለይቶ ማየት ወይም መረዳት እንደሚያስፈልግም ረዳት ፕሮፌሰር ዱላ ይናገራሉ። የፈዴራል የሥራ ቋንቋ ማለት የፌዴራል መንግሥቱ ከክልል አስተዳደሮች ጋር የሚነጋገሩበት ወይም የሚገናኙበት ቋንቋ እንደሆነ ነው የገለጹት።
ዶክተር ተፈራ በበኩላቸው ማብራሪያ በፌዴራል መንግሥቱ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ መኖሩ አስፈላጊነቱና ሀገራዊ ፋይዳም እንዳለው ቢታመንበትም ሀገሪቷ በምትተዳደርበት ህገ መንግሥትና የቋንቋ ፖሊሲ አለመደገፉ ሌላ ጥያቄ ሆኖ ይቀርባል። በኢትዮጵያ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋና ባህል እሴቶች ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ጌታቸው እንዳሉት ሀገሪቷ በጽሁፍ የሰፈረ የቋንቋ ፖሊሲ የላትም። ቋንቋ በባህል ፖሊሲ ውስጥ ሆኖ ነው ሲሰራበት የቆየው።
አንዳንድ ጥናት አጥኝዎችም ይህንኑ መሰረት አድርገው ነው ሲያንጸባርቁ የቆዩት። እንደ ሀገር የቋንቋ ልማት ሥራ ይሰራል። በዚሁ መሰረትም አጠቃላይ የሀገሪቱን ቋንቋዎች በህገመንግሥቱና በባህል ፖሊሲው ላይ በተቀመጡት መሰረት ቋንቋዎች የሚመሩበትንና የሚለሙበትን አቅጣጫ የሚያመላክት ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጅቷል። እንደ አቶ ዓለማየሁ ማብራሪያ በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቷ ወደ 52 ቋንቋዎች የትምህርት ሥርአት ውስጥ ገብተዋል።
በመገናኛ ብዙሃንም እንዲሁ በተለያዩ ቋንቋዎች እየተሰራ ነው። ከዛሬ 30 አመታት በፊት ከቋንቋ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በንጽጽር ሲታይ ለውጡ ከፍተኛ ነው። አማርኛም የሥራ ቋንቋ ሆኖ እንዲያገለግል ሲደረግ የወቅቱ ሁኔታ ግምት ውስጥ ገብቶ ሊሆን እንደሚችልም መታሰብ አለበት። የቋንቋ ልማቱ እያደገ ሲሄድ አሁን የሚነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉበት ዕድል ይፈጠራል።
ሌሎች ሀገሮች የተለያየ ቋንቋ እንደሚ ጠቀሙት በኢትዮጵያም ጥቅም ላይ ቢውል ክፋት እንደሌለው የሚናገሩት አቶ ዓለማየሁ ‹‹‹ፍጹም ነው። ተግዳሮት የለውም›› ብሎ መውሰድም ተገቢነት እንደሌለው ይገልጻሉ። በአሁኑ ጊዜ ደቡብ አፍሪካ 11የሥራ ቋንቋ እንዳላት በህገመንግሥቷ ማስፈሯንና ነገር ግን የምትጠቀመው በእንግሊዝኛ ቋንቋ እንደሆነ ለአብነት ጠቅሰዋል።
በኢፌዲሪ ህገመንግሥት ላይም የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑን ከመደንገጉ በስተቀር ሌላ ቋንቋ ስለመኖሩ የገለጸው ነገር ባለመኖሩ የቋንቋ ረቂቅ ፖሊሲው መነሻ የተደረገው ከሀገሪቷ ህገመንግሥት ነው። ረቂቁ ለውይይት በቀረበበት ውቅትም ‹‹አፋን ኦሮሞ›› የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ሆኖ እንዲያገለግል ሀሳብ መቅረቡን አስታውሰዋል፡፡
በወቅቱም በየደረጃው በተካሄዱ ውይይቶች ላይ ረቂቅ ፖሊሲው ህገመንግሥቱን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ምላሽ በመስጠት ከተወያዮች ጋር መተማመን ላይ መደረሱን አቶ ዓለማየሁ አስረድተዋል። እርሳቸው እንዳሉት ስልጣኑ የአስፈ ጻሚው አካል ነው። የተጠናው የቋንቋ ፖሊሲ ረቂቅ እየተተቸ በመሆኑ አስፈጻሚው አካል የሚያሻሽለው ነገር ካለ የማይታይበት ምክንያት አይኖርም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2011
ለምለም መንግሥቱ