ፕሮፌሰር ጠንክር ቦንገር የተወለዱት በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ ኢሽወይ የሚባል መንደር ሲሆን ወልቂጤ ከተማ አድገዋል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአምቦ ከተማ ጨርሰው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በጂኦግራፊ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በግብርና ኢኮኖሚክስ በሪዲንግ ዩኒቨርሲቲ እንግሊዝ፤ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን/ ፒኤችዲ/ ስኩል ኦፍ ኦሪየንታል ኤንድ አፍሪካን ስተዲስ ለንደን ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ፤ፒ ጂ ሲ ኢ(ፖስት ግራጁዌት ሰርተፍኬት ኢን ኢዱኬሽን) በቢዝነስ ማስተማር ዘዴ ከቴምስ ዩኒቨርሲቲ ለንደን ተምረው ጨርሰዋል።
በእንግሊዝ ሀገር በሰሜን ለንደን ዩኒቨርሲቲ፤ በሳውዝ ባንክና ብሪስቶል፤በዚምባቡዌ ዩኒቨርሲቲ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ሙሉ ጊዜ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ፤ በዛምቢያ ኮፐር ቤልት እና ሙሉንጊ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ አስተምረዋል፡፡ በኡጋንዳ ካምፓላ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምርምር ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ በመሆን ሰርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ እድገት ምርምር ተቋም መስራች አባል ናቸው፡፡ በሰር አርተር ሊዊስ የማሕበራዊና ኢኮኖሚ ምርምር ተቋም፤ በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዌስት ኢንዲስ፣ በብሪጅታውን በባርባዶስ ከፍተኛ ተመራማሪ ሆነው ሰርተዋል፡፡
የነጋድረስ ገብረህይወት ባይከዳኝን መጽሐፍ ወደ እንግሊዝኛ ተርጉመዋል፡፡ በዚህም ከአለም ታላላቅ ኢኮኖሚስቶች ተርታ እንዲሰለፉ እንዲነበቡ ለማድረግ የቻሉ ናቸው፡፡ በርካታ መጽሐፍትን ጽፈዋል፡፡ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በሚለው መጽሐፋቸው ላይ የኢትዮጵያ እድገትና ልማት ከየት ወዴት? እንዴት? የሚል ጽሁፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡ አዲስ ዘመን በወቅታዊ ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊና ተያያዥ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እነሆ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአብዛኛው የተመሰረተው በግብርናው ላይ ነው። የመሬት ላራሹ ንቅናቄ ግብ መሬትን ለአርሶ አደሩ የማድረግ ነበር፡፡ በቀደሙ ዓመታት መሬትን በኢንቨስትመንት ስም በስፋት ለውጭ ባለሀብቶች መስጠት እንዴት ይመለከቱታል ?
ፕሮፌሰር ጠንክር፡- ታሪክም ፖለቲካም የራሱ ሂደት አለው፡፡ ኢኮኖሚ ከዛም ጋር የተዛመደ ቢሆንም አብሮ ግን አይሄድም። እኛ ልጆች ሆነን ማርክሲስት ለውጥ ስንል ሁሉም ነገር በአንድ ላይ የሚመጣ ነበር የመሰለን። ግን አሁን ወደ ኋላ ዞር ብዬ ሳየው በአጼ ኃይለስላሴ ጊዜ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አምስት በመቶ ያድግ ነበር። ደርግ በ17 ዓመቱ ጊዜ ውስጥ በአንድ ነጥብ 5 በመቶ እድገት አስመዝግቧል። ሌላው ደግሞ እድገት ብቻ ሳይሆን ሂደት ነው፡፡
ከሐሮማያ የእርሻ ኮሌጅ የተመረቁ የኢትዮጵያ ወጣቶች አዋሽ ሸለቆ ገብተው ግብርናን እያለሙ ነበር። ልክ እንደዛሬዎቹ መንግሥት ስራ የሚሰጥ ሳይሆን የራሳቸውን ስራ በብርታት ሲሰሩ ነበር፡፡ በእዚህ ስራ የተሰማሩ በጣም የማውቃቸው ሰዎችም ጭምር ነበሩ፡፡ አርሲ ላይ ደግሞ አንድ ታዋቂ ሰው ዘመናዊ እርሻ እያካሄዱ ነበር። ይሄን እንግዲህ የሚመራው የሀገር ሰው ነው፡፡ የእራሳችን ናቸው። ሁለተኛም በጊዜው ወጣቶች ነበሩ፡፡ እነዛ ሰዎች በዚያን ጊዜ ያካሂዱት የነበረው ግብርና ዛሬ ድረስ ተያይዞ ቢዘልቅ ኖሮ የትና የት በሄድን ነበር። ምን ያህል ታላቅ ሀገራዊ ስኬት በተገኘም ነበር።
ጋምቤላ የሕንድ ባለሀብት ኢንቨስተር በግብርናው ዘርፍ አለማለሁ ብሎ ገብቶ ሰፊ መሬት ወስዶ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የልማት ባንክን አክስሮ ባንኩ ባለእዳ ሆኗል። የተበላሸ ብድር የሚሉት ነው። የኢትዮጵያ እድገት ትልቁ ችግር ቀጣይነት አለመኖሩ ነው። ደርግ መጣ በእርግጥም የመሬት አዋጁ አብዮተኛ ነበር። ነውም። የመሬት አዋጁን ዛሬም እደግፋለሁ። በጊዜው ሕዝባዊ ሰልፍም ወጥተንለታል።
እንዲያውም የግብርና ኢኮኖሚክስ ለመማር የበቃሁት አቶ ደሳለኝ ራህመቶ የሚባሉ ምሁር አሜሪካን ሀገር ሆነው መሬት ላራሹ ላይ የጻፉት ነገር ስለመሰጠኝ ነበር። ያ ፍላጎት አሳድሮብኝ ነው ወደ ትምህርቱ የገባሁት። መሬት ላራሹ የኢትዮጵያ እርሻና ልማት መሰረት ነው፡፡ ባለፉት አስር ዓመታት የኢትዮጵያ እርሻ በ6.5 በመቶ አድጓል። እድገቱ ደግሞ ከብዙ ሀገሮች የተለየ ነው።ለምን ቢባል ገበሬው የመሬት ባለቤት ነው፡፡ ይሄ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ ነው እድገቱ የመጣው፡፡ ሁሉንም አዳርሷል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- የገበሬው እርሻውን ጥሎ መውጣት መሰደድ መሬቱን ጾም አያሳድረውም? ከአቅም በላይ በሆነ ችግር መፈናቀል ሌላ ነገር ነው። ነገር ግን መስራት፣ ማረስ፣ ማምረት የሚችለው ትኩስ ኃይል ወደ ከተማ የሚያደርገው መጠነ ሰፊ ፍልሰት ከተሞችን ከማጨናነቁ ውጭ በግብርናው ላይ ጉዳት አያስከትልም ወይ?
ፕሮፌሰር ጠንክር፡- ከገጠር ወደ ከተማ በስፋት የሚፈልሱት ወጣቶች ከግብርና ስራቸው አንጻር ይጎዳል፡፡ ሆኖም ግን ደቡብ ክልል ላይ ከሚገመተው በላይ የሕዝብ ብዛት አለ። ሕዝቡ በጣም ብዙ ነው። መሬቱ ደግሞ ትንሽ ነው።መሬቱ(እርሻው) ላይ ያለው ሰው ስራውን ሊያካሂድ ይችላል፡፡ ሰሜን ብንሄድ ለምሳሌ ጎጃም ሰፋ ያለ በበሬ የሚታረስበት ሀገር ነው። ደቡብ ግን በእጅ የሚታረስ ነው። ይሄኛው ወደ ከተማ የሚፈልሰው የወጣት ኃይል አነሰም በዛ ትርፉ ጉልበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በእርሻው አጠቃላይ ግብአትና በሚያስገኘው ውጤት በምርታማነቱ ላይ መጥፎ ውጤት የሚያመጣ አይመስለኝም፡፡ የኢትዮጵያ እርሻ 6 ነጥብ 5 በመቶ አድጓል፡፡ ይህ በጣም ብዙ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የእርሻው እድገት በምን መልኩ ይገለጻል?
ፕሮፌሰር ጠንክር፡- እድገት ማለት ጠቅላላ ምርቱ በገንዘብ ተተምኖ አምናና ዘንድሮ ሲወዳደር ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አረንጓዴው በመባል በእርሻ ታሪክ ውስጥ በፓኪስታንና በሕንድ የሚታወቀው አብዮት ይሄን ያህል እድገት አላመጣም፡፡ የእነሱ እንዲያውም የትላልቅ ከበርቴዎች እርሻ ነው። በትራክተር ነው የሚታረሰው፡፡ መንግሥት ብዙ ድጋፍ ይሰጣቸዋል። ምክንያቱም ገበሬዎችና መንግሥት እጅና ጓንት ናቸው። በዚህ በኩል የመንግሥት ባለስልጣን ነው። በዚያ በኩል ያርሳል። ለራሱ ድጎማ ያደርጋል። የግል ድጋፍ ያደርጋል። ያ ደግሞ የሚታረሰው በመስኖ ነው።
በመስኖ ስራ በዓመት ውስጥ ሁለት ሶስቴ ማምረት ትችላለህ፡፡ የእኛን እርሻ ስትመለከት ገበሬው ዝናብን ጠብቆ ነው የሚያካሄደው። አሁን በአብዛኛው ገበሬው የመስኖ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆን በስፋት እየተሰራ ነው። የበለጠ ውጤታማ የሚያደርገውም እሱ ነው። ለውጦች እንዳሉ እያየንም አንቀበልም። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ በእኛ ሀገር ከማርክሲዝምም ጋር ተያይዞ የመጣ ይሁን ከባሕላችንም ጋር የተቆራኘ ይሁን መለወጥና መታረም ያለበት ጉዳይ ሁልጊዜም አሉታዊ ነገር ነው የምንፈልገው።
አዲስ ዘመን፡-እንዴት?
ፕሮፌሰር ጠንክር፡- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ብዙ መልካም ነገሮች አሉ። ለምሳሌ በአስር በመቶ ማደግ ራሱ ሰባትና ስምንት እንኳን ቢሆን ትልቅ እድገት ነው። ይሄ እድገት ደግሞ ከላይ እንደገለፅኩት 80 በመቶ የሆኑ ገበሬዎች በራሳቸው መሬት ለራሳቸው እያመረቱ ያስገኙት ለውጥና እድገት ነው። ይሄ ነው የሆነው። ገቢው በአብዛኛው ቀጥታ ወደ እነሱ ነው የሚሄደው፡፡ ሁለተኛው ነጥብ በየትኛውም አለም እኔ እስከማውቀው ድረስ የኢኮኖሚ ታሪክ አንብቤአለሁ በየትም ሀገር ላይ አማካይ ዓመታዊ ገቢው 700 ዶላር ሆኖ በሕይወት የመኖር የእድሜ ጣሪያው 64 ዓመት ላይ የደረሰ ሀገር የለም፡፡ የኢትዮጵያ አሁን በሕይወት የመኖር የዕድሜ አማካይ ጣሪያው 64 ዓመት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የአንድ ሰው ዓመታዊ አማካይ ገቢ ማለት ነው ?
ፕሮፌሰር ጠንክር፡-አዎን አማካይ ነው። የኢትዮጵያ አጠቃላይ የዓመት ምርት ለመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ሲካፈል የኢትዮጵያ በዓመት ሲተመን ወደ 70 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ በዚህ አጠቃላይ ገቢ መጠን በሕይወት የመኖር ጣሪያ 64 ዓመት የሆነበት በአለም የለም። ይሄ ራሱ ተአምር ነው። ለምንድነው ይሄ የሆነው፤ እዚህ ላይ እንዴት ደረስን፤ ውጤቱ እንዴት ነው የመጣው ካልን በየገጠሩ በየቀበሌው ያሉ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኛ የሆኑ ሴቶች የሰሩት ስራ ነው፡፡ በዚህ እጅግ በጣም ሰፊና መልክአ ምድራዊ አቀማመጡ አስቸጋሪ በሆነ ሀገር ውስጥ እነዛ ብርቱ ሴቶች የሰሩት ስራና የመንግሥት ፖሊሲ ነው ውጤቱን ያስገኘው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የመንግሥት የግብርና ፖሊሲው አዋጪና የሚደገፍ ነው ማለት ነው?
ፕሮፌሰር ጠንክር፡-ያቀፋቸውን ክፍሎ ችና ያስገኘውን ውጤት አይቶ መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡-በአለም ስንተኛ ደረጃ ላይ ነን ?
ፕሮፌሰር ጠንክር፡- እንደማስበው 172 ደረጃ ላይ ትገኛለች። ያ እንግዲህ አይለካም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰው እድገት መለኪያ ሰንጠረዥ የሚለው አለው። ሌሎች ኢኮኖሚስቶች ደግሞ በአማካይ የሚያወጡት አለ። በዚህ መለኪያ መሰረት ከአለም 172ኛ ከአፍሪካ 30 ውስጥ ነች። እኔ ብዙ ጊዜ የምመለከተው ከአለም አንጻር ነው። አንድ የሕይወት ጣሪያን በተመለከተ ከድህነት በታች የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር 25 በመቶ ነበር። የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ድህነትንም እየቀነሰ የሄደ ፖሊሲ ነው የነበረው። የኢትዮጵያ መንገዶች እየተስፋፉ ነው። ለምሳሌ እኔ የተወለድኩበት አካባቢ በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ ድሮ ምንም አልነበረም፡፡ ከወልቂጤ አያቴ እየያዘችኝ ከከተማ ወደ ገጠር ትሄድ ነበር። ምክንያቱም የሀገርህን ቋንቋ ዘመዶችህን ማወቅ አለብህ እያለች ትወስደኝ ነበረ፡፡ አሁን ወደ ኋላ ሳይ በጣም አደንቃታለሁ፡፡ አመሰግናታለሁ። ያኔ እዛ መንደር ለመሄድ አካባቢው ውሀማና ጭቃ ጨፈጨፍ የበዛበት ስለሆነ ፀጉራችንና ፊታችን ላይ ጭቃ እየተጠራቀመ ዘመዶቻችን ጋር ስንደርስ አንለይም ነበር፡፡ ማነህ አንተ ይባላል። በመጀመሪያ መታጠብ አለብህ ለመለየት፡፡ አሁን ወልቁጤ ዩኒቨርሲቲ ያለበት ቦታ ማለት ነው፡፡ ዛሬ ጥሩ አስፋልት ሆኗል፡፡
ቅኝ ገዢ ለመሆን ያሰበውም በዛ አካባቢ መንገድ አልሰራም፡፡ ከአዲስ አበባ መውጫ የሆኑትን አምስት በሮች ላይ ያሉትን መንገዶች የሰራው ጣሊያን ነው፡፡ አሁን በነሱ ላይ ብዙ ተሰርቷል። ደርግ በመጠኑ ሰርቷል፡፡ እነዚህ ደግሞ በጣም አስፋፍተውታል። ጉራጌ ሀገር የልማትና የመንገድ ስራ በትንሹም ቢሆን በፊት ተጀምሮ ነበር፡፡ እነጀነራል ወልደስላሴ በረካ ልማት በጀመሩት ስራ ለሁሉም የአየር ንብረት የሚሆነው መንገድ ከአምስት ኪሎ ሜትር አይበልጥም ነበር፡፡ አሁን ከአምስት ኪሎሜትር በኋላ ለሁሉም የአየር ንብረት የሚሆኑ መንገዶች አሉ። እኔ መልካሙን እየተናገርኩ ነው፡፡ መመስከርም አለብኝ፡፡ ይሄን መናገር መጥፎ ነገሮች የሉም ማለት አይደለም። ፖለቲካ ደግሞ የራሱ አካሄድ አለው። ኢኮኖሚ ውጤቱ እስኪታይ ይቆያል።
አዲስ ዘመን፡- መሬት ለውጪ ኢንቨስተሮች በሊዝ መስጠት በሀገሪቱ ኢኮኖሚና በግብርናው ላይ ምን አይነት ተጽእኖ አለው ብለው ያስባሉ ?
ፕሮፌሰር ጠንክር፡- ስንናገር ይሄን የምናያ ይዘው ዛሬ በአለም ላይ ሁለት እውነታዎች አሉ። ማንም የማይቃወማቸው፡፡አንደኛው ሙሉ በሙሉ መንግሥት የሚመራው ኢኮኖሚ ነው። ለፍጥነት አይጠቅምም። ብዙ ሀብት አያፈራም። ሁለተኛው ገበያ መር ኢኮኖሚ ነው፡፡ ይሄኛው ኢኮኖሚን ለመምራት እጅግ በጣም ጠቃሚ መሳሪያ ነው። የግል ቢሆንም ትንሽ ልዩነት አለው፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያን አየር መንገድን እንመልከት፡፡ ሙሉ በሙሉ በመንግሥት የተያዘ ነው። የሚሰራው በገበያ መርህ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአለምን ገበያ የተመረኮዘ ስለሆነ በአለም ላይ የሚሸጥ ምርት ነው፡፡ ገበያ አለው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ወይም የገበያ የሚባል አይደለም፡፡ ገበያው በሁለቱም ይሰራል፡፡ መርሁ ብቻ በተግባር እንዲውል ነው የሚፈለገው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን በሀገሪቱ ላይ ያሉ የኢኮኖሚ እድገት እንቅፋቶች ምንድናቸው፤ ለወደፊቱ ኢኮኖሚው እየተሻሻለ እንዲቀጥል ምንድነው መሰራት ያለበት?
ፕሮፌሰር ጠንክር፡- በኢትዮጵያዊነቴ ናሽናሊስት ሆኜ ከሳይንስ እንዳልወጣ ሁልጊዜ እጠነቀቃለሁ። ናሽናሊዝም እንደምታውቀው አንዳንድ ጊዜ ከሳይንስ ያወጣሀል፡፡ ሙሶሎኒን ወደ ፋሽዝም መራው። ሂትለርን ናዚዝም ውስጥ ዘፈቀው።ናሽናሊዝም ካለም ትወስደዋለህ፡፡
በኢኮኖሚክስ አለመልማት (አንደር ዴቨሎፕ መንት) የሚባል ቃል አለ፡፡ እኔ የምሰጠው ፍቺ ደግሞ ይለያል። ውዝፍ ነው የምለው፡፡ በም እራቡ አለም አገላለጽ ብዙ ሰው አልተማረም፤ ጤና የለውም፤ ገቢው ዝቅተኛ ነው…ወዘተ የሚል ትርጉሞችን ይይዛል፡፡ይሄ ውዝፍ ነው፡፡ ውዝፍ ከሆነ ደግሞ ልታጠራው ትችላለህ፡፡ ለጠየከኝ ጥያቄ ለችግሩ መፍትሄ በኢትዮጵያ ፖለቲካና የመንግሥት አስተዳደር መለያየት አለበት፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲመሰረት ኃይለ ስላሴ ሙሉ ራስን በራስ የማስተዳደር ስልጣኑን ሰጥተውታል፡፡ ድሮ የትግራይ ገዢ የነበሩት ራስ መንገሻ ስዩም የመጀመሪያው ቦርድ ሰብሳቢ ነበሩ፡፡ በኮሎኔል መንግሥቱ ጊዜም የኮሎኔል ፍስሀ መጽሀፍ ላይ አለ፡፡ ምንድነው የነበረው በወቅቱ ሩሲያ ኢትዮጵያ ስለገባች ሩሲያኖች ለኮሎኔል መንግሥቱ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የእኛን አንቶኖቭ ይግዙ አሏቸው፡፡ ሩሲያዎቹ አየር መንገዳችንን በእነሱ አውሮፕላን ለመተካት አስበው ነው፡፡ ማንኛውም የአፍሪካ መሪ ቢሆን ኖሮ በዚህ ስልጣን ላይ ሆኖ እሺ ነበረ የሚለው፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ በወቅቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊ የነበሩትን ኮሎኔል መሐመድን ጠሩ፡፡ የትኛው ይሻለናል ብለው ጠየቁ። እኛ የጀመርነው በቦይንግ ነው፤,ይሄ ነው ይሄ ነው ብለው መልስ ሰጡ፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ለሩሲያዎቹ በሙሉ ልብና ድፍረት ይቅርታ እኛ የምንሄደው መጀመሪያ በጀመርነው መንገድ ነው የሚል መልስ ሰጡ፡፡ ይሄ ምንድነው የሚያሳየው ብንል በሀገርና በራስ መተማመንን ድፍረትን ቁርጠኝነትን ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም አየር መንገዱን ለውጭ ባለሀብቶች መሸጥ አለብህ ሲባሉ በሙሉ ድፍረት አይሆንም ነው ያሉዋቸው፡፡ የበዛ ድፍረትም ጭካኔም ነበረው፡፡ ድንበሩ ይሄ ነው። አሁን እንግዲህ አየር መንገዳችንን ለመግዛት እያንዣንበቡ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ እንግዲህ እናያለን። እስከዛም ድረስ ሳይኬድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ገበያ፤ እምቅ የማኔጅመንት ችሎታና አቅም ያለው ሕዝብ ነው፡፡ ኤሊቱንም (ምሁሩን) ጨምሮ። ሆኖም ግን የፖለቲካ አመራሩና ባለሙያዎቹ መለያየት አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- መሬት ለውጪ ኢንቨስተሮች በመንግሥት በስፋት በሊዝ መሰጠቱ ሀገራዊ ጉዳት የለውም ወይ?
ፕሮፌሰር ጠንክር፡- መሬት ትልቅ የተፈጥሮ ሀብት ነው፡፡ እንደ ኢኮኖሚስት ስናየው፡፡ በሌላው ጎን በባሕላችን ስናየው ርስት ጉልት የሚል ጥብቅ የሆነ ባህላዊ አመለካከት አለ፡፡ አሁን እኛ በዛሬው አለም ላይ ምርታማነትን ለመጨመር ነው የምንፈልገው። በሀገራችን በስራ ላይ ያልዋለ ብዙ ሰፊ መሬት አለ። ለምሳሌ ጋምቤላ ሰፊ መሬት ይዞ የነበረው ሕንዳዊ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ወደ ሱዳንም ምርት እልክ ነበር ብሏል፡፡ ብሩን ሰብስቦ አሁን የልማት ባንክ እዳ አለበት። የፖለቲካ ስራም ይሰራበታል፡፡
ለምሳሌ አቶ ደሳለኝ ራህመቶ በጣም የማከብረው ሰው ነው። ሕዝቡ ከመሬቱ ተነስቶ ለሌሎች ግዙፍ ለሆኑ የውጭ ነጋዴ ገበሬዎች መሰጠቱን ይቃወማል፡፡ ባሕላዊው ስሜት እዚህ ውስጥ መግባት የለበትም ባይ ነኝ በእኔ አስተያየት፡፡
መሬት ብዙ ቦታ ላይ ዝም ብሎ የተቀመጠ ያልተጠቀምንበት ሀብት ነው፡፡ ታክሳችንን በደንብ እንሰበስባለን ወይ የሚለውም መታየት አለበት። የከተማ መሬት የመንግሥት ነው ተብሎ እናውቃለን። በአርከበ ጊዜ ቤት ይስሩ ተብሎ ቦታ ተሰጥቷል፡፡ 70 ካሬ ሜትር። ዛሬ ያ መሬት የሚያወጣው በጣም ሰፊ ዋጋና ለገበሬው የተሰጠው ካሳ ሲታይ አይገናኝም፡፡ በመሀል ላይ ያለው ጣልቃ ገቢ ቢሮክራሲው ምኑ ምኑ ብዙ ዘርፎበታል፡፡
አዲስ ዘመን፡-ፖለቲካው በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደረ ነው የሚሉ አስተያየቶች አሉ፡፡ ይሄ እንዴት ነው መፈታት ያለበት ?
ፕሮፌሰር ጠንክር፡-ማንም ለዚህ የሚሆን ቀላል መፍትሄ የለውም፡፡ ኢኮኖሚው እያደገ በሄደ ቁጥር ሀብት ያመነጫል፡፡ ሀብቱ በሚመነጭበት ጊዜ ዝግጁ ሆነው የተቀመጡ ሰዎች አሉ፡፡ ከዚህ ይጠቀማሉ፡፡ አሁን የአዲስ አበባ ፎቆች ምን ያህል ትልቅ እንደሆኑ፤ማን በባለቤትነት እንደያዛቸው ሕዝቡ ያውቃል፡፡ ከሕዝብ የሚደበቅ የሚሰወር ነገር የለም፡፡
ሀገራዊ ሀብቱ ወደ ተወሰኑ ሰዎች ነው የሄደው። ያን ደግሞ ቅናት፤ ምቀኝነት፤ ጥላቻ፤ የፖለቲካ ጫናን ያመጣል፡፡አይተነዋል፡፡ ከየቦታው የተባረሩ ሰዎች ይሄ እከሌ የሚለውን ያመጣል፡፡ የፖለቲካ ሰው አይደለሁም። እንደ ኢኮኖሚስት ደግሞ የፖለቲካ ስፔሱን መዳሰስ አለብኝ፡፡ መጽሐፌም ላይ አንድ ቦታ ላይ አንስቼዋለሁ።
እኛ ኢኮኖሚስቶች በተቻለን መጠን ስሜታ ዊነት ጥላቻና የመሳሰሉት ውስጥ አንገባም። በተጨባጭ ቁጥሮችና አሀዞች ነው የምንናገረው። ግብይትን ተመልከት፡፡ በኢኮኖሚ ውስጥ በቢሊዮን ብር የሚቆጠሩ ግብይቶች አሉ። ያንን ግብይት የሚያካሂደው ማነው፤ ኮንትራት ተቀባይ ኮንትራት ሰጪ ብንል ይህን ስራ የሚሰሩት ሰዎች በፖለቲካው የተቀመጡ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ ትኩሳት ኢኮኖሚው ላይ ጫና እየፈጠረ ነው። የዋጋ ንረት፤ የሸቀጦች እጥረት ፤ስጋት፤ አለመረጋጋት ወዘተ ከዚህ መውጫው መንገድ ምንድነው ?
ፕሮፌሰር ጠንክር፡- ለየትኛውም ችግር ቢሆን በማንኪያ ተዘጋጅቶ የሚቀርብ መፍትሄ የለም። እንደ ኢትዮጵያዊ አሁን የምንኖርበትን ጊዜ እጅግ አስደማሚ አድርጌ ነው የማየው፡፡ ለችግሮቹ መፍትሄ ብዬ የምለው በአማርኛ የጻፍኩት መጽሀፍ ላይ ይገኛል። ገልጬዋለሁ፡፡ ወደ ዲሞክራሲና ሁሉንም ወደሚያረካ መንገድ መሄድ አንዱ ነው፡፡
ሌላውን አማራጭ ለማሰብ እንኳን ይሰቀጥ ጠኛል፡፡ አሁን ሀገሪቱ መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት። አንደኛው እሳቤ በመስቀለኛ መንገዱ ላይ ሁለት ታሪካዊ ፈተናዎቿን መፍታት ማቃለል ትችላለች ወይ የሚለው ነው፡፡ ሌላው ስልጣን በጠመንጃ ከሚለው ቡድንና ስብስብ አስተሳሰብ ከእዛ ትወጣለች ወይ የሚለው ነው፡፡ ሶስተኛው ዲሞክራሲ የሚለው ደግሞ በሰው ድምጽና ምርጫ ይሁን ባይ ነው፡፡ ምርጫው ሁልጊዜ ጥሩ ላይሆን ይችላል፡፡ አነሱም በዛ ይሄ ራሱ ምርጫን ሕጋዊና እኔ የመረጥኩት ነው እንዲል ያደርገዋል፡፡
ዛሬ ደግሞ በአለም ላይ ያለው ገበያ መር ኢኮኖሚና መንግሥት ብቻውን የሚመራው ኢኮኖሚ ነው፡፡ በመንግሥት ብቻ የሚመራው ኢኮኖሚ ከስሯል። ቻይና በካፒታሊስት መንገድ ነው በአብዛኛው የምትራመደው፡፡ ቻይና ኮሚኒስት ናት፡፡ ግን ገበያውን ክፍት አድርጋ ትሰራለች፡፡ እናም ቻይና ኮሚኒስት ሆና ገበያውን ክፍት ያደረገችው መንግሥት ብቻውን የሚመራው ኢኮኖሚ ስለከሰረ ነው፡፡ ሶስተኛው ደግሞ በአለም ላይ ያለው ሕዝብ ይሄ የእኔ መንግሥት ነው የሚለው ስሜት የሚሰማው መኖር ነው፡፡ ለምን መጥፎ ስራ አይሆንም እኔ የመረጥኩት ነው እኔ በማልፈልግበት ጊዜ ደግሞ አወርደዋለሁ የሚል ነው፡፡ይሄንን ኢትዮጵያ ሞክራው አታውቅም። የወደፊቱን ለመተንበይ ያስቸግራል፡፡ ብዙ ሀገሮች ወደ ዲሞክራሲ ሲሸጋገሩ ስብዕናቸው የገዘፈ ትላልቅ ግለሰቦችም ነበሯቸው፡፡ የሕንዱን ማሕተመ ጋንዲ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሕንድ ነጻ በወጣችበት ጊዜ ወሳኝ ነበር፡፡ በዲሞክራሲ መንገድ ተራመደች። ጀዋህርላ ኔህሮም ነበረ፡፡ ደቡብ አፍሪካ ኔልሰን ማንዴላ ነበራት፡፡ አንዳንዴ ሳስብ ዶ/ር አብይን በሶስት ሰዎች እወስደዋለሁ፡፡ ሚካኤል ጎርባቾቭ ከፓርቲው ወጥቶ ነው ፕሬስቶሪካና ግላስኖስት የተባለውን ለውጥ የመራው፡፡ የመጨረሻው አያደርስባቸው እንጂ፡፡
ፈራረሰች፡፡ ግን ከዛው ፓርቲ ነው የወጣው።
ሁለተኛው ማርቲን ሉተር ኪንግና እነ ጋንዲ ደግሞ በሰላማዊ መንገድ ይሄ መደመር የሚባለው አይነት ማለት ነው፡፡ እኛ በፖለቲካዊ ባህላችን ውስጥ ለዘመናት ነግሶ የኖረውና ያለው ምንድነው ካልን አጥፍተህ መጥፋት ነው፡፡ ልክ እንደ ድሮው እንደ ጉልተኞች። አንዱ አንዱን አጥፍቶ ስልጣን ይይዛል፡፡ ሁለት መንገድ የለም፡ ፡ እንደገና ለሌላ ዙር ደግሞ ትሄዳለህ። አጥፍተህ መጥፋት ነው። ያንን ስርዓት ቀይረን ዶ/ር አቢይ የዲሞክራሲን መንገድ እንደሚከተሉ ከሌሎቹም ተምረው እንዲሳካላቸው እመኛለሁ። እንደዛ ማድረግ ከቻሉ ትልቅ የኢትዮጵያ ሰው ይሆናሉ፡ ፡ ከቀደሙት ከነብርሀነ መስቀል፤ ከነኃይሌ ፊዳ፤ በጊዚያቸው እንደ ገነኑት ሰዎች ይገዝፋል፡፡ ግዙፍ ክፍለ አለም ነው ሕንድ። ጋንዲ በፍቅርና በሰላም ነው ወደ አንድ ያመጣው፡፡ የእኛም ዶ/ር አቢይ ታሪክን አሸጋግሮ ወደ ዲሞክራሲ መንገድ እንዲያስገባን እመኝለታለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡-ለነበረን ቆይታ እናመሰ ግናለን።
ፕሮፌሰር ጠንክር፡-እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2011