የኮርፖሬሽኑ ተስፋ ሰጪ የከበሩ ማዕድናት እሴት መጨመር ሥራዎች

ኢትዮጵያ የበርካታ የከበሩ ማዕድናት መገኛ ናት። በዓለም በእጅጉ ከሚታወቁና ተፈላጊ ከሆኑት እንደ ሳፋየር፣ ኤምራልድ፣ ኦፓል፣ ጃስበር፣ ኦብሲዲያን፣ ጋርኔት፣ አሜቲስት እና ሲትሪን ከመሳሰሉት የከበሩ ማዕድናት ከ40 በላይ የሚሆኑትም ይገኙባታል፡፡ ለማዕድናቱ ትኩረት ሳይሰጥ ከመቆየቱ ጋር በተያያዘ እነዚህን ማዕድናት አልምቶና አሴት ጨምሮ በሚገባ ተጠቃሚ መሆን ሳይቻል ቆይቷል፡፡ የከበሩ ማዕድናት ሀብቶችን በአግባቡ አውቆና አጥንቶ ጥቅም ላይ በማዋል በኩል ውስንነቶች እንደነበሩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለአጠቃላይ የማዕድን ዘርፉ በመንግሥት በኩል ትኩረት የተሰጠው መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም ቢሆን ለወርቅና ሌሎች ማዕድናት የተሰጠውን ትኩረት ያህል ለከበሩ ማዕድናት ትኩረት አልተሰጠም ነበር ሲሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለከበሩ ማዕድናትም ትኩረት መስጠት መጀመሩን እነዚሁ ባለሙያዎች ጠቅሰው፣ ይህን ተከትሎ በከበሩ ማዕድናት ልማትና ግብይት ላይ መነቃቃት እየተፈጠረና ለውጦች እየተስተዋሉ መምጣታቸውንም ያመላክታሉ፡፡

እንደ ሀገር በከበሩ ማዕድናት ዘርፍ ኢትዮጵያ ያላትን ያልተነካ ሀብት በማውጣትና እሴት በመጨመር ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ሰፋፊ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠይቅ ይታመናል፡፡ በዚህ ዘርፍ የተፈጠረውን መነቃቃት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በግልም ሆነ በመንግሥት ደረጃ በከበሩ ማዕድናት ልማትና እሴት ጭመራ ላይ ተሰማርተው የሚሰሩ ተቋማት እየታዩ ናቸው፡፡

ከእነዚህ መካከል የኢትዮጵያ ማዕድን ኮርፖሬሽን አንዱ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ በከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር፣ ከዘመኑ ጋር አብረው የሚሄዱ ዲጂታል ፕላትፎርሞችን በመጠቀም የከበሩ ማዕድናትን በዓለም ገበያ እያስተዋወቀና እየሸጠ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት እየሰራ መሆኑን ይገልጻል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የጌጣጌጥ ማዕድናት ማምረቻ ክፍል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘካሪያስ ፍቃድ እንደሚሉት፤ እንደ ሀገር በማዕድን ዘርፍ ላይ በትኩረት ሲሰራ የቆየው ለኢንዱስትሪ ግብዓት በሚውሉ ማዕድናት እንዲሁም በወርቅ እና ተዛማጅ ማዕድናት ላይ ነው፡፡ በከበሩ ማዕድናት ላይ በትኩረት መሥራት የተጀመረው ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡

የከበሩ ማዕድናት ቢሰራባቸው ለሀገር ትልቅ የገቢ ምንጭ ማስገኘት እንደሚችሉ ሥራ አስኪያጁ ጠቅሰው፣ ማዕድናቱ አላቂ የማዕድን ሀብት መሆናቸው ታሳቢ ተደርጎ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ መደረግ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ዘካርያስ እንደሚሉት፤ ኮርፖሬሽኑ ከአመራረት ጀምሮ ያሉ ሂደቶች በሚገባ እንዲስተካከሉ ለማድረግ ከክልሎች ጋር በመሆን በሙያ የታገዙ ሥራዎች እንዲሰሩ ጥረቶች እያደረገ ይገኛል፡፡ ማዕድኑ በአብዛኛው ወደ ውጭ ሲላክ የኖረው በጥሬው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደ ሀገር ትልቅ ኪሳራ ሲደርስ ቆይቷል፡፡ ማዕድናቱን እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ማቅረብ ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው፡፡ እሴት መጨመር ሲባል በአጠቃላይ በተፈጥሮ የተገኘው ማዕድን ውበት እንዲላበስ የሚደረግበት መንገድ ነው።

ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት እሴት መጨመር ላይ በስፋት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በእሴት ማዕከሉ ሥራ የከበሩ ማዕድናቱ ከወርቅ እና ከብር ጋር ወደ ለጌጣጌጥነት ከመዋላቸው በፊት ያለው ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ የከበሩ ማዕድናት ከሚያመርቱ የክልል የከበሩ ማዕድናት አምራች ማህበራት ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር የከበሩ ማዕድናት በጥሬው እንደሚገዛ ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ማህበራት በሕጋዊ መልኩ የተደራጁ ሕጋዊ እውቅና ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ኮርፖሬሽኑ በጥሬው በገዛቸው በእነዚህ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር ለገበያ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ቀደም ሲል የከበሩ ማዕድናቱ ምንም ዓይነት እሴት ሳይታከልባቸው በጥሬው ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ ይደረግ ነበር፡፡ ማዕድኑ በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር አልፎ ውጭ ሀገር የሚወሰድበት ሁኔታ እንዳለም ገልጸዋል፡፡

ማዕድኑ በጥሬ መላኩ ሳያንስ በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር እንዲወጣ መደረጉ እንደ ሀገር ኪሳራ ሲያስከትል ቆይቷል ሲሉ ሥራ አስኪያጁ ይናገራሉ። አሁን መንግሥት ይህን ሕገ ወጥነት ለመቆጣጠር የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቱን ጠቅሰው፣ ቁጥጥሩ በደንብ እየተጠናከረ የመጣበት ሁኔታ እንዳለም ያመላክታሉ፡፡

ሥራ አስኪያጁ ኮርፖሬሽኑ በከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት የመጨመሩን ሥራ አጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው፣ ዘንድሮ የጌጣጌጥ ማዕድናት ሥራ ወርክሾፕ ለማቋቋም አቅዶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ የጌጣጌጥ ሥራ ማለት በወርክሾፑ የሚመረቱ ማዕድናትን ከወርቅ፣ ከብር እና ከሌሎች ነገሮች በማምረት ለአንገት፣ ለጆሮ፣ ለእጅ እና ለመሳሰሉት ጌጣጌጥነት ሙሉ ለሙሉ እንዲውሉ የሚደረግበት መሆኑን ያብራራሉ፡፡

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ይህን ለማድረግ ወርክሾፕ ያስፈልጋል፡፡ ወርክሾፑ እስከሚቋቋም ድረስም እሴት የመጨመር ሥራው እየተሰራ ነው። በወርቅና በብር ሥራ ላይ ከተሰማሩ ድርጅቶች ጋር ትስስር በመፍጠር በሕጋዊ መንገድ የወርቅና የብር ጌጣጌጥ የማስዋቡ ሥራዎች ይሰራሉ፡፡ ኮርፖሬሽኑ በዚህ መልኩ እሴት የመጨመሩን ሥራ በማስፋፋት ሌሎችም ወደ ሕጋዊ መንገድ እንዲመጡ እያደረገ ይገኛል፡፡

በሀገሪቱ ከ40 በላይ የከበሩ ማዕድናት ዓይነቶች ይገኛሉ፡፡ ምን ያህሉ ላይ በሚገባ ተሰርቷል የሚለው ግን በደንብ መታየትና መለየት ይኖርበታል፡፡ ዋንኛው ነገር እሴት መጨመሩ ላይ መሥራት ነው፤ ከዚህ ጎን ለጎን በማዕድን ልማቱ ላይ ትኩረት በመስጠት የአምራቾቹን አቅም ማሳደግና ባለሙያ ማፍራት ላይ ሊሰራበት ይገባል፡፡ በዚህም ላይ በሀገር ደረጃ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በመነጋጋር ሥራዎች የተጀመሩበት ሁኔታ እንዳለም ሥራ አስኪያጁ አመላክተዋል፡፡

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ኮርፖሬሽኑ ምርቶቹን የሚሸጥባቸው ቦታዎችም አሉት፡፡ አንደኛው መሸጫ በኮርፖሬሽኑ ግቢ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች ተርሚናል ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህም ማዕድናትን ከማስተዋወቅ እንዲሁም ያሉትን ክፍተቶች ለመሙላት የሚያስችል ግንዛቤ ለመፍጠርና በኢትዮጵያ ያሉ ማዕድናትን ለማስተዋወቅ ያግዛል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመትም ሌሎች ተጨማሪ የመሸጫ ቦታዎች በመክፈትና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸጥ እየተሰራ ነው፡፡

አሁን የከበሩ ማዕድናት ዘርፍ እንደ አዲስ እየተነቃቃ መሆኑን አመልክተው፣ የከበሩ ማዕድናትን ለማስተዋወቅ እንዲሁም የዲጂታል ገበያ ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችሉ ሥራዎችም እየተሰሩ ይገኛሉ። በቅርቡ በኢትዮጵያ ዲጂታል ማርኬቲንግ ላይ ለመግባት ኤግል ላይን ከሚባል ድርጅት ጋር በመተባበር ‹ኢትዮጵያንስ ሚኒራል› የሚል የዲጂታል መገበያያ ፕላትፎርም ተዘጋጅቶ ይፋ ሆናል፡፡ የዚህ ዋና ዓላማም በኦንላይን መንገድ ግብይት መፈጸም ነው፡፡ ይህም በአሊባባ እና አማዞን ደረጃ ምርቶቹን ለማስተዋወቅ የሚያስችል ሥራን ለመሥራት ፡፡

የክፍያ ሥርዓቱንም ለማቀላጠፍ ከዳሽን ባንክ ጋር እየተሰራ ሲሆን፣ በኦንላይን መክፈል የሚቻልበት ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ ከማስተር ካርድ ጋርም እንዲሁ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡

ግብዓቱ ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ በኦንላይን እንዲሆን ቢደረግም ማዕድናቱ እንደ ማንኛውም እቃ በሕገ ወጥ መንገድ የሚወጡበት ሁኔታ እንዳለ አመልክተው፣ ምርቶቹ ሕጋዊነትን በጠበቀ መልኩ ለደንበኞች እንዲደርሱ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ፖስታ ድርጅት ጋርም እየተሰራ መሆኑን ያስታወቁት፡፡

አሁን ገበያው ላይ የተወሰነ መቀዛቀዝ እንዳለም አቶ ዘካርያስ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያትነት የማዕድናት ሕገ ወጥ ግብይት መሆኑን ተናግረው፣ ሕገ ወጥ የማዕድናት ግብይቱን ለመቆጣጠር ከብሔራዊ ደህንነት ጋር የሚከናወኑ ተግባሮች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አስታውቀዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ምርቶች ፎቶ “ኢትዮጵያ ሚኒራል ዶት ኮም” ላይ መለቀቁን ጠቅሰው፣ ይህም ማንኛውም ደንበኛ ማዕድናቱን ለመግዛት ሲፈልግ ወደ ዌብሳይቱ ገብቶ በኦንላይን እንዲያዝ የሚያስችል መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ደንበኛው የሚፈልገውን ምርት ካዘዘ በኋላ ክፍያውንም በተቀመጡት አማራጮች ተጠቅሞ በመክፈል በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት አማካኝነት ንብረቱን መረከብ የሚችልበት አሰራር መዘርጋቱን አስታውቀዋል፡፡

የኦንላይን ገበያ እምብዛም ያልተለመደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጥርጣሬዎች መኖራቸው ግብይቱ በሚፈለገው ልክ እንዳይሄድ የሚያደርግ ተግዳሮት እንደነበር ሥራ አስኪያጁ አስታውሰው፣ ይህንን የኦንላይን ሥርዓት ለማጠናከርና እንደ ሀገር ለማስፋት ሌሎች የከበሩ ማዕድን ላኪዎችም እንዲሳተፉበት ክፍት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ እስካሁንም ብዙ ላኪዎች መመዝገባቸውንና ሁሉንም በማሳተፍ በጋራ እየተሰራ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡ ይህም አሰራር አንደኛ ማዕድናቱ በሕጋዊ መንገድ እንዲሸጡ ለማድረግ እንደሚረዳ ገልጸው፣ ሁለተኛ ማዕድናቱ ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲመረቱና ለደንበኞች እንዲደርሱ የሚያስችል መሆኑን አስገንዘበዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት፤ ኮርፖሬሽኑ ምርቶቹን በዲጂታል ገበያ ለማቅረብ የሚያስችሉ በቂ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው፡፡ አሁን በቂ የምርት ክምችትም አለው። ለምሳሌ ያለውን ክምችት ለማሳየት ያህል ጌጣጌጦችን ለሚሰሩ ድርጅቶች አንድ ጊዜ የሚሰጠው ትዕዛዝ ከአንድ ሺ እስከ ሁለት ሺ ነው፡፡ የገበያው ተደራሽነት እየሰፋ ሲሄድ ከዚህ በላይ ማምረት ስለሚያስፈልግ የማምረት ሥራውን ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የተለያዩ ማዕድናትን በተለያዩ ዲዛይኖች በዓይነትም ሆነ በብዛት አምርቶ ለገበያ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ እንደ ደንበኛው ፍላጎት ምርቶቹን ለማቅረብ ኮርፖሬሽኑ ሁሉም ማዕድናት ላይ ትኩረት አድርጎ እየተሰራ ይገኛል፡፡

የከበሩ ማዕድናትን በጥሬ ለገበያ ማቅረብ የሚበረታታ እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ በጥሬው ለገበያ ማቅረብ ይህ እንደ ቢዝነስ አዋጭ ሳይሆን አክሳሪ ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ይህንንም ምሳሌ ጠቅሰው ሲያብራሩ ‹‹አንድ ማዕድን በግራም 50 ሺ ብር መሸጥ እየተቻለ አምስትና ስድስት ሺ ብር መሸጥ ትክክል አይደለም›› ይላሉ፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፤ አንድ ማዕድን እሴት ሲታከልበት እና ሳይታከልበት ያለው የገበያ ልዩነት ሰፊ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ በተያዘው በጀት ዓመት እሴት የመጨመሩን ሥራ አጠናክሮ ለመቀጠል አቅዶ እየሰራ ነው፡፡ የማዕድናቱን ደህንነት በማስጠበቅ ረገድም በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው፡፡

ኮርፖሬሽኑ በተያዘው ዓመት አንዱ ስትራቴጂ አድርጎ እየሰራ ያለው ሥራ የማዕድን ልየታ ላብራቶሪ ማቋቋም መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት 80 በመቶ ያህል የመመርመሪያ መሳሪያዎች እንዳሉት ተናግረው፣ ቀሪዎቹን ጥቂት መሳሪያዎች ከውጭ በማስገባት ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጠው የአይኤስኦ ሰርተፊኬትን በመውስድ ለሁሉም አገልግሎት ፈላጊዎች አገልግሎት ለመስጠት ይሰራል ብለዋል፡፡ በከበሩ ማዕድናት ዘርፍ ብዙ ፍላጎት እንዳለም ጠቅሰው፣ ሰው ግንዛቤው ኖሮት ማዕድኑን እንዲገዛ ለማድረግ ስልጠናው በመስጠት የባለሙያ ክፍተቶች የመሟላት ሥራዎች እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡

እንደ አቶ ዘካርያስ ገለጻ፤ በከበሩ ማዕድናት ዘርፍ ከአመራረቱ ጀምሮ ለፍጻሜ እስከሚደርስ ያለውን ሂደት በተመለከተ እውቀት የሚያስጨብጥበት የጆኦሞሎጂ ትምህርት ቤት ለማቋቋም የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ ትምህርቱን ለመማርና ስልጠና ለመወሰድ ብዙዎች ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውን ተከትሎ ያለውን የመማር ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ በቅርቡ አጫጭር ስልጠናዎች መስጠት ተጀምሯል። በመጀመሪያ ዙር ስልጠናም ከ30 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ስልጠናውን ወስደዋል፡፡ ስልጠናው ስለማዕድናት አጠቃላይ ግንዛቤን የሚያገኙበት የተሻለ አረዳድ እንዲኖራቸው ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት እሴት በመጨመር የጌጣጌጥ ማዕድናትን ለማምረት ከተያዘው እቅድ ከ85 ከመቶ በላይ የሚሆነውን መፈጸም ተችሏል፡፡ የእቅዱ መቶ በመቶ እንዳይሳካ ካደረጉ ዋንኛ ምክንያቶች መካከል የኃይል መቆራረጥ እና ማዕድናቱ በሚመጡባቸው የተለያዩ አካባቢዎች የታዩ የጸጥታ ችግሮች ናቸው፡፡ በተያዘው በጀት ዓመትም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትና ከጸጥታ አካላት ጋር እየተሰራ ነው፡፡

የማዕድናት ልየታ ላብራቶሪም የሚቋቋም ይሆናል። የጌጣጌጥ ወርክሾፑንም በማቋቋም ሙሉ በሙሉ የወርቅና የብር ማስጌጥ ሥራው በውስጥ አቅም እንዲሰራ ይደረጋል፡፡ ለጌጣጌጥ ማዕድናት መቆረጥና ማለስለስ /የላፒደሪ/ ወርክሾፑ ባለሙያዎችንም ሆነ መሳሪያዎችን በመጨመር አቅሙን የማሳደግና ማጠናከር ሥራ ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል። ለእዚህም ባለሙያዎች የመቅጠሩ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን መስከረም 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You