ክላውድ ኮምፒውቲንግ- ዘመነኛው የመረጃ አያያዝ ዘይቤ

መረጃዎችን በማቆየት ወይም በማከመቻት በኩል ስልኮች፣ ኮምፒውተሮች፣ ፍላሾችና የመሳሰሉት ሀርድ ዲስኮች ሚና ከፍተኛ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ተቋማት፣ ግለሰቦች፣ ወዘተ. መረጃዎችን በማዕከላዊ የመረጃ ቋትነት /central database/ በሚገለገሉባቸው ኮምፒዩተሮች እያስቀመጡ ሲጠቀሙ ኖረዋል፤ ግለሰቦችም እንዲሁ በስልካቸው ወይም በላፕቶፖቻቸው አልያም በሲዲ እና ፍላሽን በመሳሰሉ ሀርድ ዲስኮች እያስቀመጡ ሲጠቀሙ ቆይተዋል፡፡ አሁንም ይህንኑ የሚያደርጉባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ሰርቨሮችን ሌሎች መረጃ የማከማቻ ቴክኖሎጂዎች ሆነው ቆይተዋል፡፡

ይሁንና እነዚህ የኤክትሮኒክ መሳሪያዎች ከተሰበሩ ወይም ከጠፉ መረጃውን /ዳታውን/ መልሶ ለማግኘት አማራጭ መንገድ አልነበረም። የቴክኖሎጂው መንደር ይህን ችግር የሚፈቱ የፈጠራ ውጤቶችን /ቴክኖሎጂዎችን/ መተግበር ከጀመረም ቆይቷል።

ቴክኖሎጂ ከዘመኑ ጋር አብረው ሊሄዱ የሚችሉ የቴክኖሎጂ መላዎች የሚያመነጭ በመሆኑ በተለምዶ መረጃ /Data/ የምንለው ትልቅ ሀብት የሚቀመጥበትን ዘዴ በማዘመን ቀይሮታል፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ የወለደው መረጃ /Data/ የሚቀመጥበት አዲስ ዘዴ ክላውድ ቴክኖሎጂ ይሰኛል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ክላውድ ኮምፒውቲንግ ቴክኖሎጂ በፈረንጆቹ 1960ዎቹ ነው የተፈጠረው፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶም ቴክኖሎጂውን መጠቀም የተጀመረ ሲሆን፣ እእአ በ2006 ደግሞ የአሜሪካው የቴክኖሎጂ ኩባንያ አማዞን የራሱን የክላውድ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ አገልግሎት እየተስፋፋ መጥቶ ቀስ በቀስም ታዋቂነትን አግኝቶ የዲጂታል ቴክኖሎጂው የመረጃ አቀማመጥ ዘዴን መለወጥ ያስቻለ ቴክኖሎጂ ለመሆን በቅቷል፡፡

መረጃን ከመጥፋት የሚታደገው ይህ ቴክኖሎጂ፣ የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች በበይነ መረብ /በኢንተርኔት/ አማካኝነት የሚፈልጉትን መረጃ ማስቀመጥና መገልገል የሚያስችላቸው ነው፡፡

ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች በርካታ መረጃዎችን ረዘም ላሉ ጊዜያት ዲጂታል በሆነ መንገድ ማስቀመጥና መገልገል የሚችሉበት ብቻም አይደለም፤ መረጃው በአጋጣሚ ከግል ኮምፒውተሮቻቸው ውስጥ ቢሰረዝ ወይም የተቀመጠበት የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ቢጠፋ እንኳን በሌላ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ከክላውድ ላይ በማግኘትም መጠቀም ይችላሉ፡፡

ስልክ ብንቀይር እንኳን በቀድሞ ስልካችን ፎቶዎች፣ ቪዲዮዎች፣ የጽሑፍ መልዕክቶች እና የስልክ ቁጥሮችን የመሳሰሉ ጠቃሚ መረጃዎቻችን ወደ አዲሱ ስልካችን እንዲሸጋገር ለማድረግ እንደሚጠቅምም የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ለዚህም ነው በዛሬው ‹‹ሳይንስና ቴክኖሎጂ›› አምድ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ስላለው ዘመነኛው የክላውድ ቴክኖሎጂ ምንነት አስመልክቶ ባለሙያ በማናገር ከዚህ የሚከተለውን ዝርዝር ዳሰሳ ያዘጋጀንላችሁ።

አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ መዋል እንዲሁም መረጃ ወይም ዳታ ዲጂታላይዝድ መሆን ከጀመረ በኋላ ኮምፒውተር የመረጃ ማከማቻና መተግበሪያ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ ቀጥሎም በዋናነት የሚያስፈልገው ሰርቨር መሆኑንም ጠቅሰው፣ ይህ ቴክኖሎጂ ለተለየ ጥቅም ሊውል የተዘጋጀ ኮምፒውተር ሆኖ ብቃትና አቅም ያለው ወይም ደግሞ በተለምዶ ለሌሎች ኮምፒዩተሮች አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል ነው ሲሉም ያብራራሉ፡፡

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ሰርቨሮች ሌሎች ኮምፒዩተሮችን ለማገዝ የሚውሉ አቅም ያላቸው የኮምፒውተር ዓይነቶች ከመሆናቸውም በላይ፣ የኮምፒውቲንግ ኃይልና አቅም የሚፈልጉ ስሌቶችን የሚያቀነባብሩ፣ ከፍተኛ የሆነ መረጃ የመያዝ ብቃት ያላቸው እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ የዲጂታል መረጃ አገልግሎቶችን የሚሰጡ የኮምፒዩተር ዓይነቶች ናቸው፡፡ በእነዚህ የኮምፒውተር ዓይነቶች የሚቀነ ባበሩትን መረጃዎችም በኢንተርኔት አማካኝነት ከእያንዳንዱ ግለሰብ የሚቀበሉበትም መንገድ አላቸው፡፡

ከሰርቨር ቀጥሎ ያለው የመረጃ ቋት (ዳታ ቤዝ) የሚባለው ነው፤ ይህን በሶፍት ዌር አማካኝነት በሰርቨር ላይ የሚከማች የመረጃ ጥርቅም ነው፤ በመረጃ አስተዳዳር /ዳታ ቤዝ አድሚኒስትሪተር/ በኩል የሚተዳደርና ተጠቃሚዎች መረጃን በቀላሉ የሚያከማቹበት፣ የሚቀንሱበት፣ የሚጨምሩበት እና የሚያርሙበት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የተለያዩ ስልቶች ተጠቅመው ያን መረጃ ፕሮሰስ የሚያደርጉበትና ለሚፈልጉት አላማ የሚጠቀሙበትም ነው፡፡

ትላልቅ የመረጃ ቋቶች አብዛኛውን ጊዜ የብዙ ሰርቨሮችን አቅም ይጠይቃሉ፡፡ የእነዚህ በርካታ ሰርቨሮች ስብሰብ ደግሞ የመረጃ ማዕከል /ዳታ ሴንተር/ ይባላል፡፡ የመረጃ ማዕከላት በውስጣቸው ከያዟቸው በርካታ የመረጃ ቋቶች የተነሳ ለሳይበርና ለተለያዩ ዓይነት ጥቃቶች ሊጋለጡ ስለሚችሉ ከፍተኛ የሆነ አካላዊ ጥበቃና ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል።

ያም ሆኖ እነዚህን ጥቃቶች መከላከል የማይቻልባቸው አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። የጥቃት መጠኑን ለመቀነስ በመረጃ አስተዳደር አሠራር ውስጥ መረጃዎች በአንድ መረጃ ቋት ብቻ እንዲቀመጡ አይፈለግም፤ መረጃዎቹ በተሰባጠረ ሁኔታ በተለያየ ቦታ ላይ እንዲቀመጡ ይደረጋል። ይህም አንዱ የመረጃ ማዕከል ጥቃት ቢደርስበት በሌላ መረጃ ማዕከል በተቀመጡት ተመሳሳይ የመረጃ ቋቶች አማካይነት አገልግሎት ሳይቋርጥ ሥራው እንዲከናወን እና የመረጃ ፍሰቱ ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚያስችል የቴክኖሎጂ አማካሪው ያስረዳሉ፡፡

የቴክኖሎጂ አማካሪው እንዳብራሩት፤ የዳታ ማዕከላት ብዙ ዓይነት ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል የመጀመሪያዎቹ የቴሌኮሙኒኬሽን ኩባንያዎች በሚያስተዳደራቸው የመረጃ ማዕከላት ያሉት ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ማዕከላት በአብዛኛዎቹ ጥቅም ላይ የሚውሉት ለቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶች ነው፡፡

ሁለተኛዎቹ የኢንተርፕራይዝ የመረጃ ማዕከላት የሚባሉት ናቸው፡፡ እነዚህ የዳታ ማዕከላት በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉና በኩባንያዎች /ኢንተርፕራይዞች/ ወይም ተቋማት ተገንብተው ለአገልግሎት የሚውሉ ናቸው፡፡

ሦስተኛዎቹ ሃይፐር ሴኬል ዳታ ሴንተር የሚባሉት ሲሆኑ፣ ከፍተኛ አቅም ያለው ዳታ ፕሮስስ ለማድረግ ጥቅም ላይ የሚውሉ የዳታ ማዕከላት ዓይነት ናቸው፡፡

እንደ ቴክኖሎጂ አማካሪው ማብራሪያ ሌላኛው የመረጃ ማዕከል ዛሬ በስፋት የምንዳስሰው ክላውድ ኮምፒውቲንግ ነው፡፡ ክላውድ ኮምፒውቲንግ ማዕከል በኢትዮ ቴሌኮም አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ሲሰራበት ቆይቷል፤ አሁን ላይ ደግሞ ሌሎች የግል ተቋማትም እየገነቡ ይገኛሉ፡፡

የክላውድ ኮምፒውቲንግ ማለት የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች መተግበሪያዎችን /ሶፍትዌሮችን/ እና የሀርድ ዌር የመረጃ ቋቱን የሲፒዮ ኮምፒውተር ኃይል እንዲሁም ደግሞ የመረጃና መተግበሪያ አፕሌኬሽኖችን በራሳቸው ኮምፒውተሮች፣ በራሳቸው ሰርቨሮች እና የዳታ ማዕከላት ከመጫንና የራሳቸው የዳታ ማዕከል ከመገንባት ይልቅ ያንን የዳታ ማዕከል ከገነባ አካል ጋር በመተሳሰር በበይነ መረብ አማካኝነት የሚፈልጉት አገልግሎት መጠቀም መሆኑን አማካሪው ያብራራሉ።

የመረጃ ማከማቻ ማዕከል ለሁሉም ተቋማት ቢያስፈልግም፣ ሁሉም ተመሳሳይ ማዕከል መገንባት አይጠበቅባቸውም የሚሉት የቴክኖሎጂ አማካሪው፤ ይህንን የማስተዳደርና የመገንባት አቅም ካላቸው ተቋማት አገልግሎት በማግኘት ለአገልግሎቱ የሚያስፈልገው ክፍያ በመክፍል በቀላሉ ሊጠቀሙ የሚችሉበት አማራጭ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ክላውድ ኮምፒውቲንግ በራስ ያልተገነባ የዳታ ማዕከል ሆኖ በበይነ መረብ አማካኝነት መጠቀም ሲቻል ነው የሚሉት የቴክኖሎጂ አማካሪው፤ ለምሳሌ ክላውድ በበይነ መረብ አማካኝነት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ፤ ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች በርካታ መረጃዎችን ረዘም ላሉ ጊዜያት ዲጂታል በሆነ መንገድ በማስቀመጥ መረጃው ቢሰረዝ ወይም የተቀመጠበት የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ቢጠፋ እንኳ በሌላ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ለማግኘት የሚያስችል እድል ያለው መሆኑን ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡

የክላውድ ቴክኖሎጂ እአአ ከ2006 ወዲህ ከፍተኛ እድገትና መሻሻል እያሳየ የመጣው እንደ ጉግል እና አማዞን የመሳሰሉት ትላልቅ ኩባንያዎች አሰራሩን ተግባራዊ ማድረጋቸውን ተከትሎ መሆኑን የሚጠቅሱት አማካሪው፤ አሁን በይነ መረብ (Inter­net) እስካለ ድረስ ማንኛውንም ኮምፒውተር ላይ ገብቶ የሚፈልገውን በማስቀመጥ የትኛውም ዓለም ላይ ሆኖ መረጃውን ማግኘት እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡

እንደ አቶ ሰለሞን ማብራሪያ፤ የክላውድ ኮምፒውቲንግ መረጃ ማዕከል ጠቀሜታ ብዙ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል አንደኛ ትላልቅ ፋይሎችን ለማስቀመጥና በኢሜል ለማስተዳደር ውድ የሆነ ሰርቨር መግዛት ሳይስፈልግ በክላውድ ኮምፒውቲንግ መረጃ ማዕከል ማከማቸት መቻል ነው፡፡

‹‹የክላውድ ዓይነቶች የተለያዩ ናቸው›› የሚሉት አቶ ሰለሞን አንደኛው የሕዝብ ክላውድ/pub­lic/ የሚባለው ሲሆን፤ በትልቅ መረጃ ማዕከላት ውስጥ የሚገኝና የተለያዩ ኢንተርፕራይዞች በአንድ ላይ በመጋራት እየከፈሉ አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉበት ነው፡፡ ሁለተኛው የግል ክላውድ /Pri­vate/ ይባላል፡፡ ይህ ክላውድ ቴክኖሎጂ ደግሞ አንድ ኩባንያ ብቻውን በአንድ ዳታ ማዕከል መጠቀም ሲፈልግ የሚጠቅምበት ነው፡፡ ሦስተኛው ሃይብሪድ /Hybrid/ የተባለውና የሕዝብና የግልን በአንድ ላይ አጣምሮ የሚይዝ ነው፡፡ አራተኛው ኮሚኒቲ/com­minute/ ሰርቪስ ክላውድ የሚባለው ነው፤ ይህም እንደ የዓይነቱ የተለያየ ጠቀሜታ ይሰጣል፡፡

አማካሪው እንደሚያብራሩት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመረጃ ክምችት እያደገ መጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ እንዲሁ የመንግሥትና የግል ተቋማት የመረጃ ክምችታቸው እያደገ መጥቷል፡፡ ይህ መረጃ እየጨመረ በመጣ ቁጥር የማከማቻ ፍላጎትም በዚያው ልክ እየጨመረ ይመጣል፡፡ ቴክኖሎጂው ይህን ፍላጎት ለማስተናገድ ትላልቅ አቅም ያላቸው የዳታ ማዕከላትን በመገንባት አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ያስችላል፡፡

አቶ ሰለሞን በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ፈር ቀዳጅ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም በቴክኖሎጂው ያለውን ልምድ ተጠቅሞ ከዓመት በፊት የክላውድ ኮምፒውቲንግ አገልግሎትን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ወደ ሥራ ማስገባቱን ያስታወሳሉ፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ኢትዮ ቴሌኮም የሚያቀርበው የክላውድ ኮምፒውቲንግ አገልግሎት መሠረተ ልማት አስፈላጊዎቹ ግብዓቶች የተሟሉለት ሲሆን፣ ይህም የእለት ተእለት እንቅስቃሴን ለማዘመን፣ ቢዝነስን ለማሳለጥ ያግዛል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም የክላውድ መረጃ ማዕከል በሦስት አማራጮች ለተጠቃሚዎች የቀረበ ነው፡፡ የመጀመሪያ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ባሉበት ሆነው የግል መረጃቸውን በማስቀመጥ፣ መቀመር የሚችሉበት እና ለደንበኞቻቸው የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችሉበት ነው፡፡ ሁለተኛው ፕላትፎርም አገልግሎት መስጠት ሲሆን፤ የሶፍትዌር አልሚዎች ባሉበት ሆነው ላበለጸጉት የተሟላ የመረጃ ቤዝ ሲስተም እና የማቀናበሪያ ብቃት አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት ነው፡፡

በሦስተኛው ደግሞ የተለያዩ ክፍያ የሚፈጸምባ ቸውን ውድ የሆኑ ሶፍትዌሮችን በክላውድ ኮምፒውቲንግ ማዕከሉ እንዲቀመጡ በማድረግ እነዚህ ሶፍት ዌሮች በበይነ መረብ አማካኝነት መጠቀም የሚያስችለው ብቃት ያለው አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ሁሉ በግሉ ዘርፍ የክላውድ ኮምፒውቲንግ መረጃ ማከማቻ ማዕከል እየገነቡ ያሉ የግል የቴክኖሎጂ ተቋማት አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነው አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ነው፡፡ ድርጅቱ ከሦስት ወር በፊት ነው ይህን የክላውድ ሰርቪስ መስጠት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይዞ የመጣው፡፡

የአሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳንኤል በቀለ እንደገለጹት፤ አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን የማኅበረሰቡን ችግሮች የሚፈቱ፣ ቢዝነሶችን የሚያግዙ እና በሀገር ደረጃ ለሚደረገው ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ የበኩሉን ትልቅ መሠረትን እየጣለ ነው፡፡ ተግባራዊ ያደረገው የክላውድ ሰርቪስ ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ለያዘችው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እቅድ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

የአሸዋ ቴክኖሎጂ የክላውድ አገልግሎት በበይነ መረብ ላይ የሚገኙ እና በሦስተኛ ወገን አቅራቢነት የሚተዳደሩ ሲስተሞችን በአካል መገኘት ሳያስፈልግ ካሉበት ቦታ ሆነው የተቋሙን መረጃ ቴክኖሎጂዎችን ብቻ ተጠቅመው ማስተዳደር እንዲችሉ እንደሚያደርግ ይገልጻሉ፡፡ አገልግሎቱ የድርጅቶችን ወጪ መቀነስ፣ የመረጃ ደኅንነትን መጠበቅ፣ የፈጠራ ክህሎት መጨመር እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቡድኖችን የሥራ ጫና መቀነስ እንደሚያስችል ይጠቁማሉ፡፡

ለደንበኞቹ የዶሜይን ምዝገባ እና ዝውውር፣ ማከማቻ፣ ራም ሲፒዩ፣ በቅርበት የቴክኒክ ድጋፍ መስጠት፣ ተወዳዳሪ የሆኑ የዋጋ አማራጮች፣ በየትኛቸውም የገንዘብ ኖቶችና ምንዛሪዎች ክፍያ እንዲፈጽሙ ማድረግ፣ የመረጃዎችን ደኅንነት መጠበቅ፣ ግልጽ የሆኑ ዋጋዎችን ማስቀመጥ እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን የያዘ መሆኑን አቶ ዳንኤል ይናገራሉ፡፡ የክላውድ አገልግሎት ፈጣን፣ ለአጠቃቀም ቀላል፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ወቅቱን የዋጀ፣ በ24 ሰዓታት ውስጥ 99ነጥብ9 በመቶ የአገልግሎት አቅርቦት ያለው እና ደንበኞች ራሳቸውን ማስተናገድ የሚችሉበት፣ የዕለት ተዕለት ሕይወትን በማቅለል ዓይነተኛ ሚና የሚጫወት ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

 አዲስ ዘመን መስከረም 7/2017 ዓ.ም

Recommended For You