መንግሥት በቅርቡ ወደ ትግበራ ያስገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሀገሪቷ በተለያዩ መስኮች የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታስመዘግብ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል የሚል እምነት ተጥሎበታል። የዘርፎችን ምርታማነት ለማሳደግ እንዲሁም የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችልም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይናገራሉ።
አካታችና ዘላቂ ዕድገት ያለው ኢኮኖሚን ለመገንባት፣ ሀገራዊ ገቢን ለማሳደግ የሚኖረው አበርክቶም ጉልህ ስለመሆኑም ተነግሮለታል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ ካደረጋቸው ጉዳዮች መካከል የውጭ ምንዛሬ ግብይቱ ከብሔራዊ ባንክ እጅ ወጥቶ በገበያ የሚመራበት ሥርዓት መፈጠሩ አንዱ ሲሆን፤ ይህም በተለይ የወጪ ንግዱን ለማሳለጥ፣ በችርችሮና ጅምላ ንግድ የውጭ ባለሀብቶችን ወደ ሀገር ውስጥ በመሳብ ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል።
በዋናነት የንግዱን ዘርፍ እንደሚደግፍ የተነገረለት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው፣ በተለይም የወጪ ንግድን የሚያሳልጥና የተሻለ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። የጅምላና ችርቻሮ ንግድን ለውጭ ባለሀብቶች የሚፈቅድ ሕግ እንደ መውጣቱ ለዚሁ ትግበራ ማሻሻያው ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተመላክቷል።
በመሆኑም በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች የሚበረታቱበትና ሌሎች በርካታ የውጭ ባለሀብቶችም ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጠርበት እንደሚሆንም ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ የምታገኘው በርካታ ዓይነት የግብርና ምርቶችን በመላክ እንደሆነ ይታወቃል። ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ዋነኛ ምንጭ ከሆኑት የግብርና ምርቶች መካከልም ቡናን ጨምሮ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመሞች ይገኙበታል። ለወጪ ንግዱ ተስፋ ይዞ የመጣው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይም በጥራጥሬና የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞች ዘርፍ ለተሰማሩ ላኪዎች ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ ስለመሆኑ እየተገለጸ ነው።
በቅርቡ ማሻሻያው ለዘርፉ ባለው አበርክቶ እንዲሁም በተግዳሮቶቹና መፍትሔያቸው ላይ ያተኮረ ውይይት ተደርጓል። በውይይቱም በዘርፉ የተሰማሩ ላኪዎችን ጨምሮ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ያስሚን ዋሀብ ተገኝተዋል።
የንግዱን ዘርፍ ለማዘመን መንግሥት የተለያዩ ተግባሮችን እያከናወነ እንዲሁም የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስቴር ዴኤታዋ፤ መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የወጪ ንግዱን ለማሳለጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል። በተለይም የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና የቅመማ ቅመም የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ እና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል ሰፊ እድል እንዳለው አስታውቀዋል።
ማሻሻያው ዕድል ብቻ ይዞ አልመጣም፤ ተግዳሮቶችንም ይዞ ሊመጣ ይችላል ሲሉ ጠቅሰው፣ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ችግሮችን መቅረፍ እንደሚቻልም አመልክተዋል። ለዚህም የተለያዩ መድረኮችን በማመቻቸት መወያየት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
መንግሥት የወጪ ንግዱን ለማሳደግ በተለይም የጥራጥሬ፣ የቅባትና የቅመማ ቅመም እህሎች ምርታማነትን እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ የፖሊሲ ማሻሻያዎች አድርጓል። በቅርቡ የተደረገው ማሻሻያም የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ ያግዛል።
ማሻሻያው ለውጭ ባለሀብቶች አመቺ በመሆኑ ባለሀብቶቹን ወደ ሀገር ውስጥ በማምጣት ከግሉ ባለሀብት ጋር አብረው የሚሰሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር ያስችላል። በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያሉትን ተግዳሮቶች በመቅረፍ ከፍተኛ የገበያ ተወዳዳሪነት እንዲፈጠርም ጉልህ አበርክቶ ይኖረዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት ከጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ዘርፍ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ሶስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዶላር መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቅባትና የጥራጥሬ ምርት እያስገኘ ያለው የውጭ ምንዛሬ እየተሻሻለ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
ሀገሪቱ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው ቡና፣ አበባና ወርቅ ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያሰገኘ ያለው ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም እንደሆነም ሚኒስትር ዴኤታዋ አመልክተዋል። የግብርናው ዘርፍ ከአጠቃላይ የወጪ ንግድ 18 በመቶ እንደሚሸፍን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት በስፋት እየተላኩ ያሉት የቅመማ ቅመም ምርቶች ለእዚህ ሸፋን እድገት የበኩላቸውን እንደሚያበረክቱ ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ከዘርፉ በ2017 በጀት ዓመት ወደ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል። ለዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ነው። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይም ለጥራጥሬና ቅባት እህሎች እንዲሁም ለቅመማ ቅመም ዘርፍ ያለው አበርክቶ ምን ይመስላል የሚለውን የኢትዮጵያ ጥራጥሬ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ማህበርም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
ማህበሩ ከ500 በላይ አምራችና ላኪ ማህበራትን ያቀፈ በላኪዎች ዘርፍ ያለ ትልቅ ማህበር ነው፤ በመንግሥትና በአባላቱ መካከል ያለውን ግንኙነት በማሳለጥ ዘርፉ ለሀገሪቱ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ መቀጠል እንዲችልና ጥራቱን የጠበቀ የወጪ ምርትን በማሳደግ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እንዲጨምር ለማድረግ እየሰራ ይገኛል። ይሁንና የሀገሪቱ የወጪ ንግድ በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ በሚፈለገው ልክ አላደገም።
የዘርፉ የወጪ ንግድ በሚፈለገው ልክ ያለማደጉ ዋነኛው ምክንያት ዘርፉ የሚያተኩረው እሴት ያልተጨመረባቸው የግብርና ውጤቶችን ለወጪ ገበያ በማቅረብ ላይ ያተኮረ በመሆኑ ነው። የግብርና ምርቶች ለውጭ ገበያ የሚላኩት በአብዛኛው በጥሬው በመሆኑ ለውጭ ገበያ በሚቀርበው ምርት መጠንም በገቢም ዝቅተኛ ነው። ዘርፉ ለኢኮኖሚው ሊያበረክት የሚችለው አስተዋጽኦ ካለው አቅም አንጸር ሲታይ በቂ አይደለም።
ስለዚህ በዘርፉ ከተሰማሩ ላኪዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ችግሮቹን መለየትና ውጤታማ እንዲሆን መሥራት ተገቢ እንደመሆኑ አሁን ሥራው ተጀምሯል። ከተጀመሩ ተግባራት መካከል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራ አንዱ ሲሆን፤ ይህም በዋናነት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ትልቅ ድርሻ አለው።
መንግሥት ያወጣውን ፖሊሲ ውጤታማ ለማድረግ ከዘርፉ አባላት ጋር መወያየት የግድ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቅሰው፣ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። በ2016 ለውጭ ገበያ ከቀረበው ምርት የተገኘው ሶስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዶላር በመጠኑ በሚፈለገው ልክ እንዳይደለ አመልክተው፣ ከሌሎች ተቀራራቢ ሀገራት ጋር ሲነጻጸርም ዝቅተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።
ስለሆነም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ቀርፈን በገቢ እየጨመረ ያለውን የቅባት እህልና ጥራጥሬ እንዲሁም ቅመማ ቅመም የወጪ ንግድ ድርሻ እና የገቢ መጠን ከፍ ለማድረግ ይሰራል። ለዚህም ኢትዮጵያ በምርት ደረጃ አንደኛ የሆነችበት ጥሩ አጋጣሚና ዕድል አለ ብለዋል።
ሀገሪቱ ትልቅ ኢኮኖሚ ያላት እንደመሆኗ የወጪ ንግድን ተወዳዳሪ ለማድረግ ማሻሻያው ትልቅ አቅም እንደሚሆን የጠቀሱት ሚኒስቴር ዴኤታዋ፤ እስካሁን ባለው ሂደት የወጪ ንግዱ በገቢ ንግዱ ተደግፎ መቆየቱን ገልጸው፣ አሁን ግን የወጪ ንግዱ ራሱን ችሎ መጓዝ እንዲችል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱንና በር ከፋች መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመም ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ኤዳኦ አብዲ፤ በበኩላቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይ ለወጪ ንግዱ ከፍተኛ ጉልበት እንደሚጨምርለት አመልክተዋል፤ ማሻሻያው በውጭ ንግድ የተሰማራውን የንግዱን ማህበረሰብ በቀጥታ የሚመለከት ቢሆንም፤ የእያንዳንዱን ግለሰብ ሕይወትም ይነካል ብለዋል። በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችን በቀጥታ የሚመለከት መሆኑን ጠቅሰው፣ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል። በዋነኛነት የወጪ ንግዱ ከኪሳራ ይወጣል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ባለፉት አስርት ዓመታትና ከዛም በላይ ከውጭ ምንዛሪ ግኝት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመቅረፍ አብዛኛው ላኪ ምርቶቹን የሚሸጠው በኪሳራ ነበር፤ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ በዓለም ገበያ እጅግ በጣም ተፈላጊና ተመራጭ ናቸው። ይሁንና ምርቶቹ ሲሸጡ የነበረው በኪሳራ ነው። ሁሉም የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች በዓለም ላይ ምርጥ ከሚባሉ ምርቶች መካከል የሚጠቀሱ ቢሆንም፤ አጠቃላይ የወጪ ንግዱ በኪሳራ ሲሠራ ነበር። ላኪው ምርቱን በውድ ዋጋ ገዝቶ ወጪውን በማይሸፍን ዋጋ በኪሳራ ሲልክ ቆይቷል።
አሁን ደግሞ በማክሮ ማሻሻያው የጥራጥሬ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ዘርፍ የመነቃቃት ዕድል አግኝቷል። ከዚህ ቀደም በኪሳራ ሲሰራ የቆየው የወጪ ንግድ ዘርፍ በማሻሻያው አትራፊ እንደሚሆን ይጠበቃል። አብዛኛው የኢትዮጵያ ግብርና ምርት ከሀገሪቱ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ገቢ /ጂዲፒ/ ከ35 በመቶ በላይ መያዙን ከወጪ ንግዱም እንዲሁ ከ75 በመቶ በላይ የያዘው ይሄው የግብርና ምርት ነው። ይህ ዘርፍ በኪሳራ ሲላክ ቆይቷል። ለዚህም የፖሊሲ ለውጥ አስፈልጓል። አሁን የተደረገው የፖሊሲ ማሻሻያም የወጪ ንግዱ ትርፋማ እንዲሆንና የተሻለ እንዲሆን ያደርገዋል።
ፕሬዚዳንቱ እንዳብራሩት፤ ላኪው ከስሮ ያገኘውን የውጭ ምንዛሪ ሌሎች ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ኪሳራውን ሲያጣጣ ቆይቷል። ይህም ማህበረሰቡ ላይ ለሚፈጠር የኑሮ ውድነት ትልቅ ድርሻ አለው። ስለዚህ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የወጪ ንግዱና የገቢ ንግዱ ተለያይተው እንዲጓዙ ያደርጋል። ፕሬዚዳንቱ ማሻሻያው የወጪ ንግዱ እንዲስፋፋ ዕድል ይሰጣል። ከዚህ ባለፈም ተወዳዳሪ ያደርጋል፤ በርካታ ነገሮችን ለማሻሻል ትልቅ አቅም ይፈጥራል የሚል እምነት አላቸው።
ማሻሻያው በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት የሚታይበት እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ ውጤቱ በሂደት የሚታይ መሆኑን አስታውቀዋል። በዘርፉ የተሰማሩ ሁሉ የሚያደርጉት ተሳትፎ በውጤቱ ላይ የራሱን ተጽእኖ እንደሚያሳርፍም ተናግረዋል። በቀጣይ የኮንትሮባንድ ንግዱን ሲቀንስ፣ ለውጭ ገበያ የሚላከውን መጠን ሲጨምርና የውጭ ምንዛሪው ግኝቱ ሲሰፋ የተሻለ ውጤት ይመዘገባል ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያ በ30 ዓመት ታሪኳ ውስጥ ያደረገችው ትልቅ ለውጥ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለውጥ ሲባል በራሱ ስጋት እንዳለው ተናግረዋል። አንዳንድ ስጋቶች ሊኖሩ እንደሚችሉና ጠቀሜታው ግን የጎላ መሆኑን አመልክተዋል። የበለጠ ተወዳዳሪ የመሆን ትልቅ ዕድል እንደሚመጣ አስታውቀው፣ ተወዳዳሪ ለመሆን የበለጠ መሥራት፣ በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ራስን ማዘጋጀት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና የቅመማ ቅመም ኢንዱስትሪው እሴት በመጨመርና ምርትና ምርታማነትን እንዲሁም ጥራትን በማሳደግ ተወዳዳሪ እንደሚሆን ገልጸው፣ ውድድሩ እየሰፋ በሄደ ቁጥር ተወዳዳሪ የመሆን ዕድሉም በዚያው ልክ ከፍ እንደሚል ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ጥራጥሬና የቅባት እህሎች እንዲሁም የቅመማ ቅመም ምርቶች በስፋት እንደሚመርቱ በመድረኩ ተነስቷል። ከምርቶች የሚጠበቀውን ያህል ገቢ እየተገኘ እንዳልሆነም ተጠቅሷል። የውይይቱ ተሳታፊዎችን የዘርፉ ተዋንያንና ባለሙያዎች እንደተናገሩት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዘርፉን ተወዳዳሪ ከማድረግ ባለፈ የኮንትሮባንድና ሕገ ወጥ ንግዱን በመከላከል ረገድ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ጠቅሰው፣ በዚህም ከዘርፉ ምርት 20 በመቶ ያህሉን ማዳን እንደሚያስችል አመላክተዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2017 ዓ.ም