የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያውና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተወዳዳሪነት

ከ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ ወዲህ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት፣ መንግሥት ለሀገሪቱ መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመፈለግ ያስችላሉ ያላቸውን ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ መርሃ ግብሮች አንዱ፣ ሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብር (Homegrown Eco­nomic Reform Program) ነው። የመርሃ ግብሩ ዓላማ አምራች የሆነውን የሰው ኃይል የሚሸከም የሥራ እድል እና የተረጋጋ የማክሮ-ኢኮኖሚ ከባቢ በመፍጠር እንዲሁም የግል ዘርፍ መር (Private Sector-Led) የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመገንባት ዘላቂና ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት ማስመዝገብ ነው፡፡

የኢንቨስትመንት አዋጅና የንግድ ሕግ ማሻሻያዎች፣ ብሔራዊ የንግድና ቢዝነስ ሥራ አመቺነት ማሻሻያ መርሃ ግብር (National Ease of Doing Business Initiative) እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የግብይት ሥርዓት ጋር ዘመናዊ ትስስር ለመፍጠር የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆን የተላለፈውን ውሳኔ ለመተግበር እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶች የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሩ አካል ናቸው፡፡

በ2011 የበጀት ዓመት ወደ ትግበራ የገባው የመጀመሪያው ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም፣ ብዙ የፖሊሲ ሃሳቦችን በውስጡ ያካተተ እና መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ዓላማዎችንና ግቦችን ያሳካ ነበር። ቀሪ ሥራዎች ቢኖሩም፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባትን ለማረም፣ የዕዳ ጫናን ለማቃለል፣ የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማሳደግ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጮችን ለማስፋፋት፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እና መዋቅራዊ ማነቆዎችን ለማረም በተደረገው ጥረት ውጤቶች መገኘታቸውን መንግሥት ገልጿል። በቅርቡ የጸደቀው ሁለተኛው ምዕራፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ቀሪ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ግብዓት እንደሚሆን ታምኖበታል።

እነዚህ የፖሊሲና የሕግጋት ማሻሻያዎች እና ሕጋዊ ማዕቀፎቹን መሰረት በማድረግም የተወሰዱ ተግባራዊ ርምጃዎች ኢኮኖሚው ወደተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲሸጋገር አዲስ ተስፋ ፈንጥቀዋል፡፡ በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ በቅርቡ ወደተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ትግበራ ገብታለች፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ በአራት ምሶሶዎች ላይ የተገነባ ነው፡፡ እነዚህም ምሶሶዎች የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን እና ዘላቂነትን የሚደግፍ ዘመናዊ እና ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማዕቀፍ መመሥረት፤ ፈጠራን የሚያበረታታ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ከባቢ እና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣ የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት አቅምን ማጠናከር እና ጥራት ያለው አገልግሎትን በብቃት ለማቅረብ የመንግሥትን አቅም ማሳደግ ናቸው።

በመንግሥት ይፋ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ማብራሪያ እንደሚያሳየው፣ የፕሮግራሙ ዋና ዋና ቁልፍ ዓላማዎችና ግቦች የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ማስተካከል እና የረጅም ጊዜ የውጭ ክፍያ ሚዛን ጉድለት ችግሮችን መፍታት፤ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉን በማዘመን የዋጋ ንረትን መቀነስ፤ የዕዳ ተጋላጭነትን በመፍታት እና የሀገር ውስጥ ገቢን በማሳደግ ሀገራዊ የልማት ፍላጎቶቻችንን በሀገር ውስጥ አቅም ለማሳካት ምቹ መደላድል መፍጠር፤ የፋይናንስ ዘርፉን አካታችነት፣ ተወዳዳሪነትና ጤናማነት ማጠናከር እንዲሁም የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም እና የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ጠንካራ፣ አካታች እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ሥርዓትን መገንባት ናቸው።

ማሻሻያው ለጠንካራ፣ በግሉ ዘርፍ ለሚመራ፣ ሁሉን አቀፍ ለሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ መሠረት እንዲሆን ታቅዷል፡፡ ፕሮግራሙ በሚተገበርበት ወቅት ከፍተኛ እና የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ባለ ነጠላ አሃዝ የዋጋ ግሽበት ይኖራል ተብሎ ግብ ተጥሏል። ከዚህ በተጨማሪም የማሻሻያው ትግበራ የውጭ ምንዛሪ መዛባትን በማስተካከል፣ የፋይናንስ ዘርፉን ይበልጥ በማጠናከር፣ የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር፣ የታክስ ገቢን በማሳደግ፣ የመንግሥትን ኢንቨስትመንት ውጤታማነት በማሻሻል፣ የባንክ ዘርፍን ተወዳዳሪነትና ጤናማነት በማጎልበት እና የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን በማሻሻል በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘመናዊና ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ሥርዓት የመገንባትን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት እንደሚያስችል ተገልጿል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዋና ዋና የፖሊሲ ርምጃዎች በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት፣ የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያ፣ በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ሥርዓት፣ የልማት ፋይናንስ ዕድሎች እና የመንግሥት ዕዳ አስተዳደር ማሻሻያ ናቸው፡፡ የማሻሻያ መርሃ ግብሩ በእነዚህ የፖሊሲ ርምጃዎች አማካኝነት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ ታምኖበታል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል አንዱ ኢንቨስትመንትን ማሳደግ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ከማሻሻያ መርሃ ግብሩ ዋና ዋና የፖሊሲ ርምጃዎች መካከል አንዱ በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን (Floating Ex­change Rate) ሥርዓት ትግበራ ነው፡፡ ይህ የፖሊሲ ርምጃ የውጭ ኢንቨስተሮችን በመሳብ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ እና የሀገሪቱን የንግድ ሥርዓት ከአጎራባችና ከአቻ ሀገራት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኢንቨስትመንት ሥራዎች ከሚከናወኑባቸው ስፍራዎች መካከል በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳሉ፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የመሳብ፣ የሥራ እድል ፈጠራን የማስፋት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን የማድረግ ዋና ዋና መሠረታዊ ተልዕኮዎች አሏቸው፡፡ የሕግ ማዕቀፎች ዝግጅትና ትግበራ ከእነዚህ ፓርኮች ውጤታማነት ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው፡፡ ፈጠራን የሚያበረታታ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ከባቢና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ እና የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት አቅምን ማጠናከር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ ከተገነባባቸው ምሶሶዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ስለሆነም የኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ውጤታማነት ለማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍስሃ ይታገሱ (ዶ/ር)፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለአምራች ዘርፉ፣ በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የተሰማሩ ባለሀብቶች ምርታማነታቸው እንዲያድግና በሀገራዊ ኢኮኖሚው ላይ ያላቸው ድርሻ እንዲጨምር የሚያስችሉ እድሎችን እንደያዘ ይገልፃሉ።

ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንደሚሉት፣ መንግሥት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የወሰዳቸው የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ርምጃዎች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ። ማሻሻያዎቹን በብቃት በመተግበር ተጨማሪ ኢንቨስትመንትን መሳብ እንደሚገባም ይገልፃሉ፡፡ ‹‹በቅርቡ መተግበር የጀመረው በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለተሰማሩ /ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል፡፡ የውጭ ባለሀብቶች በጅምላና ችርቻሮ ንግድ እንዲሰማሩ መፈቀዱም የውጭ ባለሀብቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለመሳብ ተጨማሪ እድል ይፈጥራል፡፡ የካፒታል ገበያ እንዲጀመር የሚደረጉ ዝግጅቶች ከዚህ ቀደም በባንኮች ላይ ተንጠልጥሎ የነበረውን ካፒታል ለማግኘት ያስችላል›› ይላሉ፡፡

ከኢኮኖሚ ማሻሻያው ዓላማዎች አንዱ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ማሳደግ እንደሆነ የሚጠቁሙት የብሔራዊ ባንክ ገዥው አቶ ማሞ ምህረቱ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለሚገኙም ሆነ ከፓርኮች ውጭ ለሚያመርቱ አምራቾች ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ በመሆን ምርትን፣ የወጪ ንግድንና ተወዳዳሪነትን እንደሚጨምርም ያብራራሉ። ‹‹ማሻሻያው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን ያበረታታል፤ የማምረት ሥራቸውን እንዲያስፋፉና የገበያ ድርሻቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል፡፡ በኢንዱስትሪና በፍጆታ ዕቃዎች ምርት ዘርፎች የተሠማሩ ተኪ ኢንዱስትሪዎች፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት ‹ኢትዮጵያ ታምርት› በተሰኘው ንቅናቄ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ከማሻሻያው ተጠቃሚ ይሆናሉ›› ይላሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ፣ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ሌሎች የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ የወጡ በርካታ የለውጥ ርምጃዎችን ለማጠናከር እንደሚረዳም አቶ ማሞ ያስረዳሉ፡፡

የፐብሊክ ፖሊሲ ጥናት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ፣ ዶ/ር ‹‹የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለኢንዱስትሪ ልማት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው መገመት አይከብድም፡፡ ማሻሻያው ለኢንዱስትሪው አቅም የሚሆን የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል፡፡ ትልልቅ ኩባንያዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ እድል ይፈጥራል። እነዚህ ኩባንያዎች ትልቅ የካፒታል አቅምና ሰፊ የገበያ መዳረሻ ያላቸው በመሆናቸው ሸማቹ ተጠቃሚ ይሆናል። ኪራይ ሰብሳቢነትን መጠንቀቅ ይገባል፡፡ በዚህ ችግር ምክንያት የግሉ ዘርፍ የተሰናከለባቸው ብዙ የአፍሪካ ሀገራት አሉ፡፡ በአጠቃላይ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ከተቻለ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እድል እየተፈጠረ ነው›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፣ መንግሥት በወሰዳቸው ርምጃዎች የአምራች ዘርፉ ተጠቃሚነትና እድገት እየተሻሻለ ስለመምጣቱ ይገልፃሉ። እሳቸው እንደሚሉት፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ የአምራች ዘርፉን ብሎም ሀገራዊ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት የአምራች ዘርፉን አፈፃፀም በማሻሻል በሀገር ውስጥና በውጭ ተወዳዳሪ ለመሆን በርካታ ተግባሮች ተከናውነዋል፡፡ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፤ ቅንጅታዊ አሰራሮችና የባለድርሻ አካላት ትብብሮች እንዲጠናከሩ፣ የኃይል አቅርቦት እንዲሻሻል፣ የሎጂስቲክስ ሥርዓቱ እንዲዘምን እና ለአምራች ዘርፍ የሚቀርበው የፋይናንስ መጠን እንዲጨምር ተደርጓል።

12 በመቶ የነበረው የአምራቾች የብድር ድርሻ ወደ 24 በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ የተከናወኑት ተግባራት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የሆኑ የአምራች ዘርፍ ተግዳሮቶችን ለማቃለል አስተዋጽኦ ነበራቸው፤ የዘርፉ ዓመታዊ እድገት 10 ነጥብ አንድ በመቶ እንዲሆን አስችለዋል፡፡ በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፎችና ተቋማት የተደረጉ ማሻሻያዎች በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ላይ የተቀመጡትን እቅዶች ለማሳካት በሚያስችል መልኩ የተከናወኑ ናቸው። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የተሰማሩ ባለሀብቶች የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኙ እንዲሁም የገበያ መዳረሻዎቻቸውን እንዲያሰፉ እድል እንደሚፈጥርላቸውም ሚኒስትሩ ይናገራሉ፡፡

አቶ መላኩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርቶች እሴት ተጨምሮባቸው ለገበያ እንዲቀርቡ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በ2016 የበጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላከው ምርት ውስጥ 78 በመቶ የሚሆነው በጥሬ የተላከ ነው፡፡ በምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ይገባል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ በአምራች ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱሰትሪ ፓርኮች መግባት እና ኢንዱስትሪ ፓርኮችም በሙሉ አቅማቸው ማምረት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎችን የሚጠቀም ባለሀብት ያስፈልጋል፡፡ ባለሀብት ገብቶ ካልሰራበት ፖሊሲውም ሆነ መሠረተ ልማቱ ብቻውን ለውጥ አያመጣም፡፡ በተለይ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የተለየ ኃላፊነት አለባቸው›› ሲሉ አመልክተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር (ዶ/ር) ዐቢይ አሕመድ ማሻሻያውን በተመለከተ ሲያብራሩ ‹‹በቅርቡ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የግሉ ዘርፍ በብዛት ኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት ላይ እንዲሰማራ በር ይከፍታል። የምንዛሬ ገበያው እንዲስተካከል እያደረገ እንዲሁም ብዙ ሕገ ወጥ ሥራዎችን ወደ ሕጋዊነት እያመጣ ነው። በዶላርና በብር መካከል ያለውን ያልተገባ ዝምድና ለማረቅ ያግዛል›› ሲሉ ገልጸው ነበር፡፡

‹‹ኤክስፖርት በማድረግ፣ ገቢን በማስገባትና በማስፋት፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንት በመሳብ፣ ከውጭ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) በሕጋዊ መንገድ እንዲመጣ በማድረግ ኢኮኖሚያችንን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያነቃቃ ይጠበቃል፡፡ በግሉ ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃት እየታየ ነው›› በማለት ተናግረዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ በሌሎች መስኮች ላሉ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎች በርካታ ፋይዳዎች ያሉት ትልቅ ርምጃ ነው፡፡ የማሻሻያ ፕሮግራሙን በብቃት እና በውጤታማነት ለመተግበር መንግሥት ቁልፍ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን ገልጿል። እነዚህ አቅጣጫዎች በላቀ አፈፃፀም እንዲተገበሩ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥና በሌሎች መስኮች ያሉ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎች ለሚያጋጥሟቸው መሰናክሎች ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት ይገባል፡፡

አንተነህ ቸሬ

 አዲስ ዘመን መስከረም 9/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You