በኦሊምፒክ፣ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና ሌሎች ውድድሮች ላይ የሃገራቸውን መልካም ገጽታ የገነቡ ድንቅ አትሌቶች የጀርባ አጥንትና የውድድር መሐንዲሶች አሰልጣኞቻቸው ናቸው። ኢትዮጵያ ደግሞ ምርጥና ዓለምን ያስደመመ ብቃት ያሳዩ አትሌቶችን ብቻ ሳይሆን፣ በልምድና በእውቀት አንቱ የተሰኙ አሰልጣኞችንም ማፍራት የቻለች ሃገር ናት።
በመላው ዓለም አድናቆትና ከበሬታን ካገኙ ኢትዮጵያውያን የአትሌቲክስ አሰልጣኞች መካከል ደግሞ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ከቀዳሚዎቹ መካከል ይሰለፋሉ። እኚህ ታላቅ አሰልጣኝ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ግንቦት 7 ቀን 2008 ዓ.ም በዛሬው እለት ነው፤ የዛሬው የአዲስ ዘመን ስፖርት ማህደርም እኚህን ታላቅ የአትሌቲክስ ባለውለታ ሊያስታውስ ወዷል።
አሰልጣኝ ወልደመስቀል ኮስትሬ በ1939 ዓም በሰሜን ሸዋ ተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ልዩ ስሙ ወንፈስ በተባለ ስፍራ ከአባታቸው አቶ ኮስትሬ ሰበሬ እና ከእናታቸው ወይዘሮ እናትገብርኤል ደስታ መወለዳቸውን በሕይወት ታሪካቸው ላይ ተሰንዷል። በትውልድ ስፍራቸው የቤተክህነት ትምህርት ከተከታተሉ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በቀንና ማታ መርሐ ግብር ዘመናዊ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ከትምህርት ጎን ለጎን በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ተሳታፊ የነበሩት የያኔው ታዳጊ ወልደመስቀል ከእግር ኳስ በተጨማሪ በ400፣ 800 እና 1ሺ500 ሜትር ውድድሮች ተካፋይ ነበሩ።
የስፖርት ፍቅር የሰረጸባቸው አሰልጣኙ በስፖርቱ ትምህርትም ገፍተው በመቀጠል ከመምህራን ማሰልጠኛ በስፖርት መምህርነት ተመርቀዋል። በመምህርነት ሙያ ላይ እያሉም ከሃንጋሪ ነጻ የትምህርት እድል በማግኘታቸው ወደዚያው አቅንተው በአካዳሚክስ ሳይንስ በምርምርና ጥናት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
ወደ ሃገራቸው ተመልሰውም በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ እንዲሁም በወቅቱ በነበረው የአካል ማሰልጠኛና ስፖርት ኮሚሽን ሠርተዋል። የአትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ በመሆን የሚወዱትን ስፖርት በ1970ዎቹ የተቀላቀሉት አሰልጣኙ፣ ስማቸውን ከመቃብር በላይ ያዋሉ በርካታ ገድሎችን በመፈጸም ሃገራቸውንም ጭምር አኩርተዋል።
አሰልጣኝ ንጉሴ ሮባን ተክተው ለሶስት አሥርት ዓመታት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን አሰልጣኝ በመሆን ያገለገሉት አሰልጣኙ፤ በዓለም አደባባይ ማንጸባረቅ የቻሉትን ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ፣ ስለሺ ስህን፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ታሪኩ በቀለ፣ ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም እና ጥሩነሽ ዲባባን የመሳሰሉ አትሌቶች አፍርተዋል።
ከውጤታማነታቸው ባለፈ በአሰልጣኝነት ዘመናቸው በተለይ የሚታወቁት በስነምግባር የታነጹ አትሌቶችን በማውጣት ነው። በሙኒክ ኦሊምፒክ በረዳትነት እንዲሁም በአምስት ኦሊምፒኮች በዋና አሰልጣኝነት (ባርሴሎና፣ አትላንታ፣ ሲድኒ፣ አቴንስ እና ቤጂንግ) ኦሊምፒኮች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን መርተዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ካስመዘገበቻቸው 58 ሜዳሊያዎች ውስጥ 28ቱን (13 የወርቅ፣ 6የብር እና 9 የነሐስ ሜዳሊያዎች) ማስመዝገብ የተቻለው በእሳቸው የአሰልጣኝነት ዘመን ነው። በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ ትልቁ የሜዳሊያ ቁጥር በተመዘገበበት የሲድኒ ኦሊምፒክ (4የወርቅ፣ 6 የብር እና 8 የነሃስ በጥቅሉ 8 ሜዳሊያዎች) ድል ላይም አሰልጣኙ ከፍተኛ ሚና በታሪክ ይዘከራል።
አሰልጣኝ ወልደመስቀል በስምንት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ላይም በዋና አሰልጣኝነት ተሳትፈዋል። በተለይ የሚታወቁትና በአትሌቲክስ ስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ አክብሮትን ያገኙት ደግሞ ኢትዮጵያ በተለይም በምትታወቅበት የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር አትሌቶችን ለውጤት በማብቃታቸው ነው።
‹‹የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አርክቴክት›› የሚሰኙት እኚህ ታላቅ አሰልጣኝ ታላቅነታቸውን የሚመሰክሩት ኢትዮጵያውያን እና አፍሪካውያን ብቻ አይደሉም፤ መላው ዓለምም ነው። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ደግሞ እአአ በ2006 በዓለም አቀፍ ደረጃ ያገኙት የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝነት ሽልማት ነው። በዓለም አትሌቲክስ የሚዘጋጀውን ይህንን ሽልማት በመቀዳጀት ብቸኛው ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝም ናቸው።
አሰልጣኝ ወልደመስቀል ኮስትሬ ከ1970ዎቹ አንስቶ ለኢትዮጵያ ታላቅ ክብርን ባጎናጸፈው የአትሌቲክስ ስፖርት በዋና አሰልጣኝነት እስከ 2008ዓ.ም አገልግለዋል። አሰልጣኙ በደረሰባቸው የመኪና አደጋ ለረጅም ጊዜ በውጪ እና በሃገር ውስጥ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው፣ በዛሬው ዕለት ግንቦት 07 ቀን 2008 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። የቀብር ሥነሥርዓታቸውም አትሌቶች፣ የስፖርቱ ባለሙያዎች፣ የመንግሥት ባለስልጣናት እንዲሁም የስፖርቱ ወዳጆች በተገኙበት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2014 ዓ.ም