በአገራችን ለበርካታ ተደጋጋሚ ዘመናት የመንግስት ስርዓቶች እንዲለዋወጡ በማድረግ ረገድ የወጣቶች ሚና የጎላ ነው፡፡ በተለይ ከ1960ዎቹ ወዲህ የወጣቱ የነቃ ተሳትፎ የፈረጠመ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በዚህ ሂደትም ከአፄው ስርዓት ጀምሮ አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ታሪክ አድርገዋል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ በኢህአዴግ ስርዓት ውስጥ የነበረውን ትግል በመምራትም ወጣቶች የነበራቸው ተሳትፎ የሚናቅ አይደለም፡፡ በዚህም በተለይ ደግሞ ከለውጥ በፊት የነበረውን ኢህአዴግ ገለል በማድረግ ዛሬም ድረስ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
እነዚህ ወጣቶች በየትኛውም ሀገራዊ ሁኔታ ውስጥ የለውጥ ማዕከል ሆነዋል፡፡ በተደረገው ለውጥም የለውጡ እንብርት ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህን ለውጥ ተከትሎ በሀገራችን በተለያዩ የክልል ከተሞችና አካባቢዎች የተለያየ ስያሜዎችን የያዙ አዳዲስ የወጣት አደረጃጀቶች ተፈጥረዋል፡፡ እነዚህ ወጣት አደረጃጀቶች በለውጥ ሂደቱ ንቁ ተሳታፊ በመሆንም በሁለንተናዊ አካባቢያዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ የጎላ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ወጣቶቹ የቀደመውን የመንግስት አሠራር በመቃወም ዛሬ አዲሱ አመራር ላሳያቸው የዴሞክራሲ ጭላንጭሎች የድርሻቸውን ተወጥተዋል፤ ይህ የሚመሰገን ተግባር ነው፡፡
ወጣቶቹ አሁን ለታየው ለውጥ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የሚጠራጠር አካል ባይኖርም ዛሬ ላይ አልፎ አልፎ በአንዳንዶቹ የሚታይባቸው የአድራጊ ፈጣሪነት ባህሪ በብዙዎች ዘንድ አደረጃጀቶቹ የሀገር ስጋት እስከሚመስሉ ድረስ በየከተሞቹ የሚፈጥሩት ጫና እየጎላ መጥቷል፡፡ አሁን አሁን በአንዳንድ አካባቢዎች ከመስመር የወጡና ሀገሪቱን አደጋ ላይ እየጣሉ ያሉ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች በወጣቱ እየተፈጸሙ እንዳሉም የሚታይ ሀቅ ነው፡፡
እንደውም በአንዳንድ አካባቢዎች የመንግስትን ሚና በመንጠቅ ጭምር የተለየ አመለካከትን ሲያራምዱ ይታያል፡፡ ወጣቶች የክልል አስተዳደሮችንና ከንቲባዎችን ሳይቀር እስከ ማዘዝ ሊደርሱ አይገባም፤ ይህ ተግባር ተገቢ አይደለም ብቻ ሳይሆን ህግ መጣስም ጭምር ነው፡፡ አካሄዱ በተለየ መልኩ ስሜታዊነትም እየታከለበት በመሆኑ የዜጎችን ሕይወት ከማጥፋት ባለፈ አገሪቱ ያፈራችውን ውስን ሀብት ያወድማል፤ ሂደቱ ከዚህ አልፎ ሥርዓት አልበኝነት ይሰፍንና በብሄሮች መካከል ያለውን መገፋፋት ሊያጦዝ አይገባም፡፡
በየአካባቢው የተደራጁት የእነዚህ ወጣቶች መደራጀታቸው ክፋት የለውም፤ ነገር ግን ላልተፈለገ ዓላማ እንዳይውሉ አስተውሎት ሊኖር ይገባል፡፡ በተያያዘ ይህን የተደራጀ ኃይል በማሳሳት የአገርን ሰላም ለማደፍረስ የሚሞክሩ ኃይሎችን ተንኮል በማጋለጥ ረገድ የወጣቶች ኃላፊነት ከፍተኛ ሊሆን ይገባል። ሁኔታቸው ሁሉ ኃላፊነት የተሞላበት ሊሆንም ይገባል፡፡ በተለይ ጥያቄያቸው ለልማትና ለሰላም ግንባታ በሚውል መልኩ መሆኑ ደግሞ የወጣቱን የቆየ ልማትና የተጠያቂነት ጥያቄ ሊመልስ ይችላል፡፡
በዚህ ረገድ ወጣቱ ባለፉት ዓመታት ተንሰራፍቶ የነበረው የተደራጀ ሌብነት፣ ሙስናና የብልሹ አሰራር ችግሮች የሀገሪቱን ልማት ብቻ ሳይሆን የወጣቱን የልማት ተጠቃሚነት ጭምር ጎድቶት መቆየቱን ከወጣቱ በላይ የሚያውቅ አለ ቢባል ፍፁም ሀሰት ይሆናል፡፡
ወጣቶቹ በየትም ክልልና አካባቢ ቢሆኑ የእንቅስቃሴያቸው ቁልፍ ዓላማ ልማትና ሰላም ሊሆን ይገባል፡፡ የተበላሹ አሰራሮችን በማስቆም የህዝቡን በተለይም የወጣቱን ተጠቀሚነት ለማረጋገጥ አዲሱ አመራር ጠንክሮ መምራት እንዲችል ወጣት አደረጃጀቶቹ አቅም እንጂ ስጋት ሊሆኑ አይገባም፡፡ በመሆኑም ወጣቱ ከለውጡ አመራር ጎን በመሰለፍ ዝግጁነቱን ሊያረጋግጥ ይገባል፤ ተገቢም ነው፡፡
አመራሩም ቢሆን ወጣቱን በአፍ ብቻ እየደለሉ የልማቱ ተጠቃሚ ሳይሆን የቆየበትን ሂደት መቀየር የሚቻለው ወጣቱ ራሱ ባለቤት እና አጋር ሲሆን ጭምር መሆኑን ተገንዝቦ ሊንቀሳቀስ ይገባል፡፡ በመሆኑም የለውጡ አመራር በአገር ልማትና ሰላም ግንባታ ዙሪያ ከአሁን በኋላ የቃላት ሽንገላን ሳይሆን ሰርተው በማሳየት አቅም መሆናቸውን ሊያስመሰክር ይገባል፡፡ በአጠቃላይ ወጣቱ የለውጡ ሞተር ነው የሚሆነው ማህበረሰባዊና ታሪካዊ ኃላፊነቱን በህጋዊ መንገድ መወጣት ሲችል ብቻ ነው፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2011