የቀጣናውን አሮጌ የፖለቲካ ባህል ለመዋጀት!

የአፍሪካ ቀንድ ካለው ስትራቴጂክ ጠቀሜታ አኳያ የብዙዎች ዓይን እና ቀልብ ማረፊያ ነው። ይህን ተከትሎም አካባቢው ለረጅም ዓመታት ሰላም እና መረጋጋት ርቆት፤ በግጭት እና በጦርነት ሲታመስ ቆይቷል። የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦችም ካሉበት ድህነት እና ኋላቀርነት ለመውጣት ያላቸው መሻት፤ ከፍላጎቶቻቸው በላይ በሆኑ አስገዳጅ ሁኔታዎች ተጨባጭ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል።

በተለይም የቅኝ አገዛዝ ሥርዓቱ ይከተል የነበረው የከፋፍለህ ግዛ መርህ፤ አንድ አይነት ቋንቋ፣ ባህል እና ሃይማኖት ባላቸው አፍሪካውያን ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ሳይቀር የፈጠረው እለመተማመን፤ ከነጻነት ማግስት ጀምሮ የአህጉሪቱ ሕዝቦች ለአንድነት እና ለተሟላ ነጻነት የጀመሩትን የጋራ ትግል በብዙ ፈትኖታል።

ችግሩ አፍሪካውያን ከነጻነት ማግስት ጀምሮ ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት ግጭቶች በሚፈጥሯቸው አለመረጋጋቶች እንዲናጡ ሆነዋል። መልከ ብዙ የውጪ አጀንዳ በያዙ ግለሰቦች እና ቡድኖች ከዛም ባለፈ መንግሥታት ጋር በተያያዘ ሕዝቡ ያራሱ ባልሆነ አውዳሚ ጦርነቶች እና ግጭቶች ብዙ ያልተገባ ዋጋ ከፍለዋል፤ ዛሬም እየከፈሉ ነው።

አፍሪካውያን ከነጻነት ዋዜማ የጀመሩትን የዓላማ እና የትግል አንድነት በመሸርሸር፤ የተረጋገጠባቸውን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች ተሻግረው ለማለፍ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖባቸዋል። ራሳቸውን ሆነው በራሳቸው ዕጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን የነበራቸውን ህልም አደብዝዞባቸዋል።

የቅኝ አገዛዝ ከአፍሪካ መንኮታኮት ከጀመረበት ማግስት ጀምሮ አገዛዙ በአህጉሪቱ ሕዝቦች ላይ ፈጥሮት ያለፈው የመለያየት እና የጥርጣሬ መንፈስ፤ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በሚገኙ ወንድማማች ሕዝቦች ላይ በተመሳሳይ መልኩ ተከስቷል። አንድ ቋንቋ፣ ባህል እና ሃይማኖት ባላቸው ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ሳይቀር እንደ ሀገር መከፋፈልን ፈጥሯል።

የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች በብዙ መሥዋዕትነት በእጃቸው የገባውን ነጻነታቸውን አጽንተው ከመጓዝ እና በትግሉ ዋዜማ ያለሙትን ህልማቸውን ተጨባጭ ከማድረግ ይልቅ ለእርስ በርስ ግጭቶች እና ጦርነቶች ተዳርገዋል። በዚህም የተረጋጋ ማኅህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን መፍጠር ተስኗቸው ዓመታትን አስቆጥረዋል።

አብዛኛዎቹ የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች አንድ አይነት ባህል ሃይማኖት እና ቋንቋ የሚጋሩ ቢሆንም እነዚህን እንደ ሕዝብ የሚያስተሳስሯቸውን ሁኔታዎች ለጋራ እጣ ፈንታቸው አቅም አድርገው ለመውሰድ ሳይችሉ ቀርተዋል።

አንዳቸው ለሌላቸው ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅም በመሆን የጋራ እጣ ፈንታቸውን የተሻለ አድርገው ከመሄድ ይልቅ፤ ባልተገቡ ምክንያቶች ለግጭት እና ከዚያም አልፈው ለተለያዩ ጦርነቶች የተዳረጉበት ሁኔታ ጎልቶ የሚደመጥ ነው።

ከነጻነት ዋዜማ አንስቶ የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች የተሻሉ ነገዎችን አብዝተው ቢሹም፤ አካባቢውን በተቆጣጠረው የውጪ ጣላቃገብነት እና ኋቀር የፖለቲካ ባህል የሀገራቱ ሕዝቦች የራሳቸው ያልሆኑ ግጭቶች እና ጦርነቶች ውስጥ ዓመታትን ለማሳለፍ ተገደዋል።

ከችግሩ ለመውጣት የሚያደርጓቸው ጥረቶችም በአካባቢው የጥቅም ፍላጎት ባላቸው ኃይሎች ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል። “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው በቀጣናው በተፈጠሩ የጸጥታ ክፍተቶች አካባቢው የጽንፈኛ እና የአክራሪ ቡድኖች መፈልፈያ እና ማደጊያ የሆነባቸው ታሪካዊ አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል።

ችግሩ ከአካባቢው ሀገራት ባለፈ የዓለም ሰላም አና መረጋጋት ስጋት ሆኖ የዘለቀበት አሁናዊ እውነታም የአደባባይ ምስጢር ነው። ችግሩን ለመሻገር የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች የሕይወት መሥዋዕትነትን የጠየቁ ሰፊ ጥረቶች ቢያደርጉም፤ አልሸባብ እና ሌሎች አሸባሪ እና አክራሪ ቡድኖች ዛሬም ለአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት ስጋት እንደሆኑ ናቸው።

በርግጥ የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ሊረተርፍ የሚችል ያልተነካ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ናቸው። ሰላማቸውን፤ ከዚያም አልፎ የጋራ ተጠቃሚነታቸውን የሚያጎለብቱ ሰፊ መንፈሳዊ፤ ባህላዊ እና ማኅበራዊ እሴቶች የሚጋሩ፤ ዘመናት የተሻገሩ ዘርፈ ብዙ መስተጋብሮችም ያላቸው ናቸው።

የሀገራቱ ፖለቲከኞች እነዚህን መልካም ዕድሎች ወደ ሚጨበጥ የጋራ ተስፋ መለወጥ የሚያስችል የተረጋጋ እና የሰከነ አካባቢያዊ ፖለቲካ መፍጠር ባለመቻላቸው ዕድሎቹ መክነዋል። የሀገራቱ ሕዝቦች መሻት የሆነውን ሰላም እና ብልፅግና ተጨባጭ ማድረግ ሳይቻል ቀርቷል።

ይህንን አስርት ዓመታት የዘለቀ ቀጣናዊ እውነታ ለመቀየር የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች፤ መንግሥታት እና ፖለቲከኞች ከባከኑ ትናንቶቻችን በመማር እና በመታረም ለአዲስ ቀጣናዊ የትብብር የታሪክ ጅማሮ ራሳቸውን ማዘጋጀት ብሎም ለዚህ የሚሆን የአስተሳሰብ ተሀድሶ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ እየሄደችበት ላለው የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው፡፡

በአጠቃላይ ካለመተማመን፤ በጠላትነት ከመፈላለግ እና ከሴራ ፖለቲካ፤ ከመልከ ብዙ የውጪ አጀንዳ ተሸካሚነት ተወጥቶ፤ የሀገራቱን ሕዝቦች የጋራ እጣ ፈንታ ወደተሻለ የታሪክ ምዕራፍ ማሸጋገር የሚያስችል አዲስ የፖለቲካ ባህል፤ የቀጣናውን አሮጌ የፖለቲካ ባህል የሚዋጅ አሻጋሪ የፖለቲካ አስተሳሰብ መላበስ፤ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ፋይዳው ብዙ ይሆናል!

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You