
በአሁኑ ወቅት ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች ያሉ ወደ 70 በመቶ እንዲሁም ከ15 እስከ 24 ወደ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን የሚደርሱት ወጣቶች በአፍሪካ ውስጥ ይኖራሉ። ይህም ከዓለም ሕዝብ ወደ 13 በመቶ የሚይዝ ነው። በኢትዮጵያም ቢሆን 70 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በወጣት የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህ ወጣት ኃይል በአግባቡ ከተያዘ ለልማት እና ሰላም ዋስትና ነው። በአግባቡ ካልተያዘ ደግሞ የጥፋት እና የሰላም እጦት ምክንያት ሊሆን የሚችል ነው። አፍሪካ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነቡ ማኅበራዊና ባህላዊ ዕሴቶች፣ ታሪክ እና ጥበብ የበለፀገች የወጣቶች አኅጉር ብትሆንም፤ አኅጉሪቱ አንገብጋቢ የሰላም ማጣት እና የደኅንነት ችግር፤ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተግዳሮቶች የሚያጋጥሟት አኅጉር ናት።
በተለይም ለወጣቶች በቂ ትኩረት ያልሰጡ የአፍሪካ ሀገራት ለግጭት እና ሰላም እጦት ከመዳረጋቸውም ባሻገር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ከተወለዱበት ሀገር ወደ ተለያዩ ሀገራት ይፈልሳሉ። አስቸጋሪ የአየር ፀባይ እና የመሬት አቀማመጥ ያለባቸውን አካባቢዎች በማቆራረጥ ከተፈጥሮና ከድንበር ጠባቂዎች ጋር ግብግብ በመግጠም ከሀገር ሀገር ለመሻገር በሚያደርጉት ሙከራ በርካቶች በመንገድ ይቀራሉ፤ ለተለያየ ዓይነት የአካል እና የአዕምሮ ጉዳትም ይጋለጣሉ። በአሸባሪ ቡድኖች በመመልመልም የጥፋት ኃይል ይሆናሉ።
ለወጣቶች የተሻለ ትኩረት የሰጡ ሀገራት በአንጻሩ የተረጋጋ ሰላም እና ልማት በማረጋገጥ ላይ ይገኛሉ። ሀገራችን ኢትዮጵያም የወጣቶችን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማረጋገጥ የሚያስችል ብሔራዊ የወጣቶች ፖሊሲ አውጥታ በመተግበር ላይ ትገኛለች። ከዚሁ ጎን ለጎንም ወጣቶችን በሥነ-ምግባር በማነጽ ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ብሔራዊ የወጣቶች የዜግነት አገልግሎት አዋጅ እንዲሁም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህል ያደረገ ዜጋ መፍጠርን ራዕዩ ያደረገ ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር ተገብቷል።
የእነዚህ ፖሊሲዎች መውጣትም ወጣቶች የተሻለ ሥራ ዕድል እንዲያገኙ እና በአካባቢያቸው ልማት ውስጥም በባለቤትነት እንዲሳተፉ አስችሏቸዋል። በ2017 በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተፈጠረው 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሥራ ዕድል ውስጥ በአብዛኛው የሥራ ዕድሉ ባለቤት የሆኑት ወጣቶች ናቸው።
ከሥራ ዕድል ባሻገር በሠላም ግንባታና ግጭትን መከላከል፣ በአካባቢ ደኅንነት፣ በሰላም ጥበቃ እንዲሁም የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በማቋቋም ተግባር ወጣቶች በስፋት እንዲሳተፉ አስችሏቸዋል።
ሆኖም አሁንም ቢሆን በወጣቶች ዙሪያ በርካታ ያልተፈቱ ችግሮች አሉ። በኢትዮጵያ በየዓመቱ እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ወጣቶች ወደ ሥራው ዓለም ይቀላቀላሉ ወይም ሥራ ፈላጊ ይሆናሉ። ለዚህ ከፍተኛ ቁጥር ላለው ዜጋ በመንግሥት ወይም በግል ተቋማት እና ድርጅቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ባለመቻሉ አብዛኛው ቁጥር ያለው ወጣት ለሥራ-አጥነት ይዳረጋል። ወደ ሥራ ዓለም ለመግባት የሚነሳሱ ወጣቶችም በመሥሪያ ቦታ እጥረት፣ በብድር አቅርቦት አለመመቻቸት፣ በገበያ ትስስር አለመኖር እና በክህሎት ክፍተቶችና መሰል ችግሮች እንቅፋት ሆኖ ሲገጥማቸው ይስተዋላል።
ስለዚህም ቀጣይነት ባለው መልኩ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች መፍታት እና ማገዝ ያስፈልጋል። ወጣቶችን በማብቃት፣ ለሥራ እንዲተጉና የፈጠራ ባለቤት እንዲሆኑ በማድረግ እንዲሁም በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ በማሳተፍ ወጣቶች ለሰላም የሚደረጉ ጥረቶችን እንዲደግፉና ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግ ተገቢ ነው።
ወጣቶች የወደፊቱ መሪዎች እና የልማት አንቀሳቃሾች እንደመሆናቸው መጠንም በቂ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል። ሰላም የሰፈነባት እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ የሚቻለው ለወጣቶች ምቹ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ እና ወጣቶችም በተፈጠሩት ዕድሎች በሚገባ መጠቀም ሲችሉ ነው!
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም