ብዙ ልንማርበት የሚገባው የኢዜማ አዲስ የፖለቲካ ባህል!

በአንድ ሀገር ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የተልዕኮ ማጠንጠኛቸው ሀገር እና ሕዝብ ነው። ፖለቲከኝነት የሀገርን ዕጣ ፈንታ የተሻለ እና ብሩህ ማድረግ፤ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ መታመን፤ ከመታመን የሚመነጭ መነቃቃት/ መነሳሳት መፍጠር፤ ሀገርን ከትናንት የሚያሻግሩ ተጨባጭ እውነታዎችን አስቦ መፈጸምን የሚጠይቅ ነው።

ሀገር የብዙ ትናንቶች ትርክት ድምር ውጤት ነችና፤ ከትናንት ጋር እርቅ መፍጠርን፤ ዛሬን በታረመ ትናንት አስቦ መንቀሳቀስን፤ ነገን ከትናንት መሠረት ላይ፤ ከዛሬ ተጨባጭ እውነታ ላይ ገምግሞ እና ተረድቶ፤ በብዙ ተስፋ የተሻለ አድርጎ ዛሬ ላይ የመሥራትን ኃላፊነት የመሸከም ተልዕኮ ነው።

የሕዝቦችን ፍላጎት፤ ሆኖ የመገኘት መሻት አውቆ፤ ለዚሁ እውነታ የተገዛ ማንነት መፍጠርን፤ የሕዝብን መጻኢ ተስፋ ብሩህ እና የሚጨበጥ የማድረግ የውስጥ መቃተትን፤ ለዚህ የሚሆን ከትናንት በመሻል የተለወጠ ማንነት መገንባትን፤ ስለ ሕዝብ ፍላጎት ራስን አሳልፎ ለመስጠት የተዘጋጀ ስብዕና ባለቤት መሆንንም የሚፈልግ ነው።

የትናንቶችን የአስተሳሰብ ጥላ መግፈፍ የሚያስችል የተለወጠ ስብዕና፤ ዘመኑን የሚዋጅ የአስተሳሰብ ልዕልናን፤ ለሕዝብ እና የሕዝብ ለሆኑ ተሻጋሪ አስተሳሰቦች እና ከእነርሱ ለመነጩ ዕሴቶች ተገዥ መሆንን የሚጠይቅ፤ የተገራ ማንነት የሚፈልግ፤ በሕዝቦች ፍላጎት መገዛትን የሚያስቀድም ነው።

በየትኛውም ሁኔታ፤ በየትኛውም መፈተን ውስጥ የሀገር እና የሕዝብን ፍላጎት ከፈተና ባሻገር ባለ ተስፈኛነት አሸንፎ መውጣት የሚያስችል የዓላማ ጽናት የሚፈልግ ነው። በብዙ ማሰብ እና መትጋት የሚገለጥ፤ በእያንዳንዷ ፈተና ጽናትን መገንባት የሚያስችል የአስተሳሰብ ልዕልና እና የተግባር ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ነው።

በሃሳብ ልዕልና ማመን እና ለዚህ የሚሆን አማራጭ ሃሳቦችን ይዞ በሕዝብ የፖለቲካ ፓርቲዎች መፈጠር እና ከመፈጠር ባሻገር ያለው እውነታም ይሄው ነው። የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ውልደት እና ተጨባጭ እንቅስቃሴ አስተሳሰብ ማጠንጠኛው በአንድም ይሁን በሌላ ከነዚህ እውነታዎች የመነጨ እና ለእነዚህም የተገዛ ነው። የመፈጠራቸው አልፋ እና ኦሜጋም ይሄው ነው።

እንዳለመታደል ሆኖ የሀገራችን የፓርቲ ፖለቲካዎች የታሪክ ትርክት ከዚህ የተለየ እና በተቃርኖ ሲታይ የኖረ ነው። ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት በሀገሪቱ የተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቋንቋ በአብዛኛው በሕዝቦች ፍላጎት ላይ የተመሠረተ እና ይህንኑ በስፋት የሚተርክ ነው።

ስለሕዝብ እና ስለ ሀገር በስፋት ይዘምሩ እንጂ፤ በተጨባጭ ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው ግን ከሕዝብ እና ከሀገር ፍላጎቶች ላይ በተቃርኖ የቆሙ ናቸው፤ በዚህም ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት ሕዝብ እና ሀገርን ለብዙ መከራ እና ስቃይ ዳርገዋል። ሕዝባችንን ለከፋ ሁከት እና ብጥብጥ፤ ጦርነት እና መገዳደሎች አሳልፈው ሰጥተዋል።

የፓርቲዎቹ አሰላለፍም ሆነ የፖለቲካ ጉዞ በግለሰቦች እና በቡድኖች ፍላጎት ላይ የተመሠረተ፤ ከሕዝባችን ፍላጎት እና የዘመናት መሻት ጋር በተቃርኖ የቆሙ፤ በሀገር ሕልውና እና ጥቅሞች ላይ በአደባባይ ያላገጡ፤ ይህንንም የፖለቲካ አማራጭ አድርገው የተንቀሳቀሱ እና እየተንቀሳቀሱ ያሉ ጥቂት አይደሉም።

አሁን ላይ ከዚህ የፖርቲ ፖለቲካ ልምምዳቸው እየወጣን እንደሆነ የሚያሳዩ፤ የሀገርን እና የሕዝብን ጥቅሞች ለየትኛውም የፖለቲካ ተልዕኮ መደራደሪያ ሊሆን እንደማይችል በተጨባጭ ያመላከቱ እውነታዎችን እያየን፤ እየሰማን ነው።

ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ-ኢዜማ የሀገር ጉዳይ እና ብሔራዊ ጥቅሞች የፖለቲካ መደራደሪያ እንደማይሆኑ ከቋንቋ በዘለለ በተጨባጭ እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት በብዙ ዕውቅና የሚሰጠው እና የሚበረታታ ነው። “በሀሳብ እንፎካከር ስለሀገር እንተባበር” የሚለው ወርቃማ መሪ ቃላቸውም ይህንኑ የሚያመላክት ነው፡፡

አሁን ላይ በሀገር እና በሕዝብ ጥቅሞች ላይ ለሚቆምሩ፤ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር ሳይቀር ሀገር በማፍረስ እና በማዳከም ሴራ ውስጥ ገብተው ለሚዳክሩ የፖለቲካ ኃይሎች ኢዜማ በአደባባይ ለሀገር እና ለሕዝብ ጥቅም በመቆም እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት በትውልድ እና በታሪክ ፊት ደምቆ የሚታይ የአዲስ ፖለቲካ ባህል ጅማሬ እና ውበት ነው!

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You