ወለጋ፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የህዝቡን የዓመታት ጥያቄ ለመመለስ ሙሉ በሙሉ ፊቱን ወደ ልማት ማዞሩን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ጠይባ ሃሰን አስታወቁ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በሳምንቱ መጨረሻ በክልሉ ከመቶ አስራ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡትን በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን የጉዱሩ ወረዳ ሆስፒታልና በዞኑ አቤ ደንጎሮ ወረዳ ሆስፒታል መርቀዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ እንደገለፁትም፤ ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ክልሉ በፖለቲካ ትግል ውስጥ ቆይቷል። በእነዚህ ዓመታት የህዝቡ ጥያቄም ሆነ የመንግስት ትኩረት የነበረው የፖለቲካ ጥያቄዎችን መመለስ በመሆኑም ለልማት ጥያቄዎች የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ሆኖ ቆይቷል። ከዋነኛ የህብረተሰብ ጥያቄዎች መካከልም የንፁህ መጠጥ ውሃ፤ የመንገድ የህክምና ተቋማት ተደራሽነት ዋነኞቹ መሆናቸውን የጠቆሙት ምክትል ፐሬዚዳንቷ፤ አሁን ላይ የተገኘውን የፖለቲካ ድል ተከትሎ ክልሉ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ወደ መመለስ መሸጋገሩንና ሙሉ ትኩረቱን ወደ ልማት መመለሱን አብራርተዋል።
«ህዝቡ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት የማግኘት መብት አለው ይህን ማድረግም የመንግስት ሚና ሳይሆን ግዴታም ጭምር መሆኑን በመረዳት በየአካባቢው የጤና ተቋማት ተደራሽነት ለማስፋት በመትጋት ላይ እንገኛለን” ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ፤ የተመረቁት ሆስፒታሎችም የዚህ ማሳያ መሆናቸውን አመላክተዋል።
በቀጣይም፤ የልማት ፍላጎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ከሁሉ በላይ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ህዝቡ አሁን ላይ የያዘውን ሰላም አጠናክሮ መያዝንና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታትን ምርጫው እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በበኩላቸው፤ ክልሉ የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ፤ በተለይም በጤናው ረገድ የተቋማትን ተደራሽነትና ጥራት ለማጎልበት በርካታ ስራዎች በመስራት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በዚህም በክልሉ 1400 ጤና ጣቢያዎችና 79 ሆስፒታሎች መገንባታቸውን ጠቁመው፤ ሰላሳ ሆስፒታሎች በግንባታ ላይ እንደሚገኙም አስገንዝበዋል። እያንዳንዳቸው 56 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸውና ከአራት መቶ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አገልግሎት የሚሰጡት ሁለቱ ሆስፒታሎችም የዚሁ ማሳያ» ናቸው፤ ያሉት ዶክተር ደረጄ፤ ክልሉ ሆስፒታሎቹን ከመገንባት ባለፈ አስፈላጊ የሆነ ግብዓትና ባለሙያዎችን ለማማሏት ትኩረት መስጠቱንና ጤማና አምራች ዜጋ የማፍራት ጥረትም በቀጣይ የመንግስት ቀዳሚ ተግባር እንደሚሆን አመላክተዋል።
ህብረተሰቡም የራሱ ሃብት ለሆኑት ሆስፒታሎች ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያደርግላቸው ጥሪ አቅርበዋል። ወይዘሮ ልኬ ዴሳና አቶ ቡሎ ዋቁማ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪዎችም ከዚህ ቀደም በጤና ተቋማት እጥረት የተነሳ እስከሞት የሚደርስ ከፍተኛ እንግልት ይደርስባቸው እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ የሆስፒታሎቹ መገንባት ከቀደመ ስቃይና እንግልት እንደሚገላግላቸው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2011
ታምራት ተስፋዬ