አብሮነትንና ሰላምን የሚያውጀው የእርቅ በዓል “ያሆዴ”

ዜና ሀተታ

ወርሃ መስከረም ለኢትዮጵያውያን የግል ስጦታ ናት። የአዲስ ዓመት መባቻ፣ የብሩህ ተስፋ፣ የአዲስ ሕይወት፣ የአዲስ ምኞት፣ የምህረትና የቸርነት ደጆች የሚከፈቱባት የወሮች አውራ ናት። ምን ይህ ብቻ የሰዎች ግንኙነት የሚያይልበትና የሠብዓዊነት ምህዋር የሚጠነሰስባት ወርሃ በኩር እንደሆነች በብዙሃኑ ኢትዮጵያውያን ልብ ታትማለች።

በወርሃ መስከረም ሰማይ የክረምት ጠባይዋን ረስታ ከደመናው፣ ከጉምጉምታው ተላቃ ፣ መሬትም ከጭቃ ተላቃ፣ የውሃ ማማዎች ጠርተው፣ አበባዎች ፈክተው፤ ቡቃያዎችም ለምልመው በመልካም ወዘና ለፈጣሪያቸው የሚያረግዱ ይመስላሉ። ታዲያ በዚህ ጊዜ ሰዎች ለፈጣሪቸው ምስጋና የሚያቀርቡባት ወር ናት። በኢትዮጵያን የዘመን ቀመር መስከረም አንድ “ሀ” ብሎ የጀመረው ዘመን መለወጫ በወሩ አጋማሽ ቀናት በአደባባይ በዓላት ይዋባሉ።

በተለይ በደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍለ ግዛት አጀብ የሚያሰኙ በዓላት መስከረም ወር ላይ ጎልተው ይደምቃሉ፡፡ መስቀል፣ ጊፋታ፣ ያሆዴ፣ መሰላ ከብዙዎቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው። በዓላቱ ባህላዊ እሴታቸው ተላብሰው የአዲስ ዓመት መቀበያ በመሆናቸው ልዩ ስሜትን ይፈጥራሉ። የአካባቢው ማህበረሰቦችም አሮጌውን ዓመት በመሸኘት ተናፋቂውን አዲስ ዓመት ለመቀበል ሽርጉድ ሲሉ ይታያሉ።

የሀድያ ብሔር የራሱ የሆኑና ተለይተው የሚታወቁ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፉ የመጡና ጠብቆ ያቆያቸው የበርካታ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ሲሆን በተለያዩ ክዋኔዎች በመታጀብ በየዓመቱ በወርሃ መስከረም በድምቀት የሚከበረውን የ “ያሆዴ” የሀዲያ ዘመን መለወጫ በዓልን አንዱ ነው። “ያሆዴ” ዘመድ አዝማድና ቤተሰብ የሚገናኝበት የተጣሉ እርቅ በማውረድ ሰላምን የሚያጸኑበትና ከጨለማው ክረምት ወደ ፈካው ፀደይ መሸጋገርን ማብሰሪያም ነው።

የሀድያ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ በፍቃዱ ገብረሃና (ዶ/ር)፤ “ያሆዴ” የብሔሩ ተወላጆች የሚገናኙበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ ሰላምና ደስታ የሚያብብበት በዓል መሆኑን ይገልጻሉ። ያሆዴ በብሔሩ የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ፣ ብሩህ ተስፋ፣ ፍቅርና መልካም ነገር የሚሰነቅበት እንሆነም ያብራራሉ።

በያሆዴ በዓል የተጣላ ሳይታረቅ በዓሉ አያከበርም የሚሉት በፍቃዱ (ዶ/ር)፤ በዓሉ የተረራቁ ዘመዶች የሚጠያየቁበት፣ የሰላም ማስተሳሰሪያ ትልቅ ባህል ስለመሆኑም ይናገራሉ። ያሆዴን የመሰሉ የብሔሩ ባህላዊ እሴቶች ተጠብቆ እንዲኖር፤ እንዲተዋወቅና የበዓሉ ክዋኔዎች ሳይበረዙ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ባይ ናቸው።

በቀጣይ ጊዜያት የያሆዴ በዓልን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች መካከል አንዱ ሆኖ እንዲመዘገብ ከተለያዩ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ይጠቁማሉ።

የሀድያ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን በጋለ በበኩላቸው፤ በያሆዴ በዓል ያለው ለሌለው አካፍሎ በመተሳሰብ እና በፍቅር አዲሱ ዓመት በደስታ የሚቀበልበት ሀዲያ ሕዝብ መገለጫ መሆኑ ይናገራሉ።

እንደ መምሪያ ኃላፊው ገለጻ፤ ያሆዴ ሰላምን፣ ወንድማማችነትን፣ አብሮነትን የሚያንጸባርቅ በዓል ነው። በቀጣይ የያሆዴ በዓልን ይበልጥ በማጉላትና በማጎልበት፣ ወደ አካባቢው የሚመጡ ጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ መምሪያው ከባለድርሻ አካላት ጋር ይሠራል።

በበዓሉ ወጣት ልጃገረዶች የቤቱን ወለል ቆፍረው በመደልደልና የተለያዩ ውበት የሚሠጡ ቀለማት ያላቸውን ኖራዎችን በመጠቀም የቤቱን ውስጥና የውጭ ግርግዳን በመቀባት የተለያዩ ጌጥ ሠርተው ያስውባሉ ይላሉ።

ወጣት ወንዶች በበኩላቸው ከነሃሴ መግቢያ አንስተው አባቶቻቸው የሚያሳዩዋቸውን ግንድ ቆርጠው ለምግብ ማብስያ እንዲውል ፈልጠው ያደርቃሉ የሚሉት ኃላፊው፤ ለችቦ የሚሆኑ እንጨቶች ከጫካ በመልቀም አስረው እንደሚያዘጋጁ ያብራራሉ። በተጨማሪም ወጣት ወንድ ልጆች ያሆዴ /ኦሌ/ ጭፈራ ሲጫወቱ ያነጋሉ፤ ይህ ጭፈራ ከያሆዴ በዓል ውጭ አይጨፈርም ነው ያሉት፡፡

በዕለቱ ለእርድ የተዘጋጀው ሠንጋ ከቀረበ በኋላ የባህል ሽማግሌዎች የበሬውን ሻኛ በለጋ ቅቤና በሠርዶ ሳር ይቀቡታል፤ ወተት ያፈሱበታል፡፡ ይህም በሚከናወንበት ወቅትም ክፉ ቀን አይምጣ፣ ርሃብ ሰቀቀን ይጥፋ፣ ጥጋብ ይስፈን፣ በአካባቢው በሀገሩ ጥጃ ይቦርቅ፣ ልጅ ይፈንጭበት፣ ሀገር ሰላም፣ ገበያ ጥጋብ ይሁን፣ ሰማይና ምድሩ ይታረቁን በማለት ምረቃቱን ፈጽመው በሬው ይጣልና የእርድ ሥርዓት እንደሚካሄድ ያመላክታሉ፡፡

በዓሉ የሚከውኑበት ቦታ (ነፈራ) የሚባል ሲሆን ቦታው በማህበረሰቡ ዘንድ በአባወራ ጊቢ የተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎችን ለመከወን እንዲመች በተለያዩ የጥላ ዛፎች ተውቦና ተከልሎ የተዘጋጀ ሥፍራ ነው፡፡ በዚህ መሠረት (ሀዲይ ነፈራ) የሚለውን ስያሜ አግኝቶ በዓሉ ሁሉም የብሔሩ ተወላጆች በሥፍራው ላይ ተሰባስበው በድምቀት ያከብራሉ ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

በሀድያ ብሔር ሩቅ ያሉ ልጆች ወላጆችንና ዘመዶችን ለመጠየቅ ለመመረቅ ቀጠሮ የሚይዙለት በያሆዴ ክብረ በዓል በመሆኑ በዓሉ ዘመድ አዝማድ ተገናኝቶ ይጠያየቃል ይመራረቃል ይላሉ። በተጨማሪም በዓሉን ለማክበር አቅም ለሌላቸውን ያላቸው ካላቸው በማካፈል በሥራም በመርዳት ከሁሉም ጋር እኩል በዓሉን ተደስተው እንዲያከብሩ በማድረግ የመረዳዳትና የሥራ ባህልን ለማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ያስረዳሉ።

የ2017 ዓ.ም “ያሆዴ” የሀዲያ ዘመን መለወጫ በዓል በሀዲይ ነፈራ በርካታ የብሔሩ ተወላጆች በተገኙበት በትናትናው ዕለት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You