በትምህርት ቤቱ የተገኘው ከፍተኛ ውጤት የአስተማሪዎች እና የተማሪዎች የጥንካሬ ውጤት ነው

አዲስ አበባ፡በቓላሚኖ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለከፍተኛ ትምህርት መግቢያ የተገኘው ከፍተኛ ውጤት የአስተማሪዎች እና የተማሪዎች ጥንካሬ ማሳያ መሆኑን ተገለፀ።

የትምህርት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መምህር ታጋይ ዘበነ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ ትምህርት ቤቱ በ1990 ዓ.ም የተመሠረተ ሲሆን፤ እስከ አሁን ከሁለት ሺህ አምስት መቶ በላይ ተማሪዎችን አስተምሮ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማስገባት ችሏል፡፡ ዘንድሮች በትምህርት ቤቱ የተገኘው ከፍተኛ ውጤት የመምህራንና የተማሪዎቹ ጥንካሬ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

በክልሉ ከሚገኙት ትምህርት ቤቶች የስምንተኛ ክፍል ውጤታቸው ከፍተኛ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቱ ገብተው አራት ዓመት ነፃ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ እንደሚያደረግ የጠቀሱት ኃላፊው፤ ተማሪዎቹ የነበራቸው ዕውቀት በማዳበር የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ አመርቂ ውጤት እያመጡ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ በትግራይ ልማት ማህበር የተመሠረተ ሲሆን፤ ዋና ዓላማው የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት የሕዝብን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመቅረፍ እና ሀገርን በዕውቀት ከፍ ለማድረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ችግር ለመፍታት የተሻለ ዕውቀት እና ምርምር ላይ ትኩረት በማድረግ እና ትምህርት ቤቱ ለሌሎች አርአያ እንዲሆን እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ታስቦ መመስረቱን ተናግረዋል፡፡

በጦርነቱ ምክንያት ተማሪዎች ከባድ ችግር ቢያሳልፉም የመማር ማስተማር ሂደቱ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ላይ መጀመሩን ጠቅሰው፤ የሶስት ዓመት መርሃ ግብር በአንድ ዓመት በማስተማር በጥረት ከፍተኛ ውጤት ማምጣት መቻሉን አብራርተዋል፡፡

አሁንም ቢሆን አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ ከመጣ ወዲህ ዘንድሮ 284 ተማሪዎች መፈተናቸው ጠቅሰው፤

ከፍተኛ ውጤት 675 ወንዶችና 662 ሴቶች ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ሲሆን 92 ተማሪዎች ደግሞ 600 ማምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ 567 አማካይ ውጤት በማስመዝገብ የቆየ የብልጫ ታሪኩን አምናና ዘንድሮም ማስቀጠል መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በትምህርት ቤቱ ተምረው የወጡ ተማሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁት ኩባንያዎች ጎግል ማይክሮሶፍት፣ ናሳ፣ በሀገር ውስጥም በኢንሳ እንዲሁም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በማስተማር እና በምርምር ሥራዎች ተሠማርተው ይገኛሉ፡፡

የቓላሚኖ ተማሪዎች ውጤት ሲታይ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ጥረትና ዓላማ በመሰነቅ የአስተማሪዎች እና የተማሪዎች ይህን ውጤት ማስገኘቱ እጅግ የሚያስደስት ነው ብለዋል፡፡ የቀድሞ ተማሪዎች አሁን በተለያየ የሥራ መስክ የሚገኙ ውጤታማ ምሁሮች ከያሉበት የሚሰባሰቡበት መድረክ በማዘጋጀት ለሀገራቸው አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን  መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You