ፈውስ ያገኙ ልቦች

ዜና ሀተታ

አክሊለ በቀለ ትባላለች፡፡ ቤተሰቦቿ የልብ ችግር እንዳለባት ያወቁት የስድስት ወር ህጻን እያለች ነው። የነበረብኝ የልብ ችግር የልብ ቀዶ ህክምና ማድረግ እንዳብኝ የሚያስገድድ ነበር የምትለው አክሊለ የዛሬ 23 ዓመት ገደማ የሁለት ዓመት ከስድስት ወር ህጻን እያለች በእስራኤል ሀገር በሚገኝ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት አማካኝነት የቀዶ የህክምና ማድረጓን ትገልጻለች፡፡

ወደ እስራኤል ሀገር ሄዳ የቀዶ ጥገናውን ከማግኘቷ በፊት በሀገር ውስጥ የተለያዩ መድሃኒቶችን ስትወስድ መቆየቷን የምትናገረው አክሊለ፤ ስትወለድ ጀምሮ የነበረው የልብ ክፍተት ችግር ክብደት አለመጨመር፣ ምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ እንዲሁም ቶሎ ቶሎ ለሳንባና ለሌሎች ኢንፌክሽኖች ያጋልጣት እንደነበር ታነሳለች።

አክሊለ በወቅቱ በኢትዮጵያ የልብ ቀዶ ህክምና ሃኪም አለመኖሩን ገልጻ፤ ነገር ግን የልብ ካርዲዎሎጂስቶች ባደረጉልኝ ህክምና የልብ ችግሩ እንዳብኝና ከሀገር ውጭ ወጥቼ ቀዶ ህክምናውን ማድረግ እንዳብኝ አሳውቀውኛል ትላለች፡፡

ከዛም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አማካኝነት እስራኤል ካለው ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሴቭ ዘ ቺልድረን ጋር መገናኘት በመቻሏ በእስራኤል ሀገር የልብ ቀዶ ህምናውን ማድረጓን ታስታውሳለች፡፡

አሁን ላይ አክሊለ በተደረገላት ህክምና ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ጤነኛ መሆኗንና ነርሲንግ ትምህርት ተምራ በአሁኑ ጊዜ በልብ ቀዶ ህክምና ወቅት ልብና ሳንባን ተክቶ የሚሠራ ማሽን ላይ ለመሥራት የውጭ የትምህርት እድል አግኝታ ለመሄድ ዝግጅት ላይ መሆኗን ተናግራለች፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ወላጆች በዚህ ህመም ምክንያት ከልጆቻቸው ጋር እየተቸገሩ መሆናቸውን የምትገልጸው አክሊለ፤ በኢትዮጵያ ልብ ህሙማ ህጻናት መርጃ ማዕከል ብቻ ከስምንት ሺህ በላይ ህጻናት ወረፋ እየጠበቁ እንደሚገኙ ትጠቁማለች፡፡

እኔ ያገኘሁትን አይነት እድል ሁሉም ህጻናት እንዲያገኙም ምኞቴ ነው ያለችው አክሊለ፤ የእስራኤል መንግሥት በጤናው ዘርፍ የሚያደርገው ድጋፍ የህክምና አገልግሎት ብቻ ሳይሆን የጤና ባለሙያዎችን ማሰልጠንም ጭምር የሚያካትት መሆኑን ገልጻለች። ይህም በቀጣይ ልብ ቀዶ ህክምናዎች በሀገር ውስጥ እንዲሠሩ የሚረዳ ነው ትላለች፡፡

ልዑልሰገድ ደሳለኝ ፤ የልብ ችግር እንዳለበት ያወቀው በ13 ዓመቱ ነው፡፡ ችግሩ እንዳለበት እንዳወቀም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ክትትል ያደርግ እንደነበርና ሆስፒታሉ ከሴቭ ዘ ቺልድረን ግብረሰናይ ድርጅት ጋር ባለው ግንኙነት የዛሬ 14 ዓመት በፊት በ14 ዓመቱ እስራኤል ሀገር ሄዶ መታከሙን ያስታውሳል፡፡

በወቅቱ የነበረው የልብ ችግር ቫልቭ መሆኑን የሚናገረው ልዑልሰገድ፤ ህክምናው ተደርጎለት ከተመለሰ በኋላ ጤነኛ መሆኑን ይናገራል። ከህክምናው በኋላም ቅርጫት ኳስ ሲጫወት እንደቆየና በኋላ ማሠልጠን መጀመሩን ይናገራል፡፡

በሂደት ግን እንደገና የልብ መድከም ችግር እንዳጋጠመው የሚያስታውሰው ልዑልሰገድ፤ ድርጅቱም የዛሬ ሶስት ዓመት በድጋሚ ወደ እስራኤል ሀገር ወስዶ አሳክሞኛል ይላል፡፡

ልዑልሰገድ፤ ለህክምና እስራኤል በሄድኩበት ወቅት የሚደረግልኝ እንክብካቤ የሚያስደስት ነው። እንደኔ አይነት የልብ ችግር ካላቸው ህጻናት ጋርም ተገናኝቼ ሃሳባችንን እንድጋራ ተደርጓል፡፡ አሁን ላይም በሙሉ ጤንነት በሂልተን ሆቴል እየሠራ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡

ሴቭ ዘ ቺልድረን ግብረ ሰናይ ድርጅት መቀመጫውን በእስራኤል ያደረገ ተቋም ነው፡፡ ድርጅቱ በተለያዩ 70 የዓለም ሀገራት በልብ ህመም ሲሰቃዩ የቆዩ ከሰባት ሺህ በላይ ህጻናት ሕይወትን ታድጓል፡፡ ከሰሞኑም በእስራኤል መንግሥት አማካኝነት በአራት የህክምና ዘርፎች የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የሴቭ ዘ ቺልድረን ተወካይ ሪኪ ሮዘንቤል እንደገለጸችው፤ ግብረሰናይ ድርጅቱ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ለ200 ከፍተኛ የልብ ችግር ላለባቸው ህጻናት ህክምና ለመስጠት ማቀዱን ገልጸዋል፡፡

የህክምና ልዑክ ቡድኑ ሥራውን መጀመሩን የገለጹት ሪኪ፤ ከፍተኛ የልብ ችግር ያለባቸው ህጻናትን ለይቶ ህክምና ካደረገ በኋላ ብዙዎቹን ወደ እስራኤል ሀገር ወስዶ ለማከም እቅድ እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You