መስቀል በጉራጌ

ዜና ሐተታ

መስቀል ደርሷል፤ ብርድና ፀሐዩን ተቋቁሞ ጀብሎ ሠርቶ ጥቂት ጥሪት የያዘውም በአስመጪና ላኪነት ሚሊዮኖችን ያካበተውም በየፊናቸው በዓሉን ከቤተሰብና ጎረቤት ጋር ለማክበር ጉድ ጉድ የሚሉበት ወቅት ነው።

ሴቶች የበዓል ምግብ ማጣፈጫ ቅቤና የተለያዩ ቅመሞችን ዝግጅታቸውን አላስታጎሉም። ከተማ ያለውም ብርም ልብስም አሊያም የበዓል ስጦውን ይዞ ለመሄድ ተዘጋጅቷል። ከነዚህ መሃከል ደግሞ ማርታ ተመስገን አንዷ ነች።

በአዲስ አበባ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ እየሠራች ሕይወቷን ትመራለች። መስቀል ደርሷልና ልቧ ሁሉ በዓሉን እንዴት አከብራለሁ የሚለው ላይ ማተኮሩን አልሸሸገችም። ለበዓሉ በጉራጌ ዞን ወደሚገኘው የትውልድ መንደሯ ለመሄድ ዝግጅት እያደረገች ነው።

በዓሉን ለማክበር የምትሄደው አያቶቿ ቤት ነው፡፡ አባቷ በሕይወት ስለሌሉ እናቷ የእሷን ታናናሾች ይዛ እናት አባቷ ቤት ትመጣለች፡፡ በዚህ ምክንያት ብቻ ሳይሆን በዓሉ በአብሮነት ከመከበሩ ጋር ተያይዞ የአያቶቿ ቤት እዛ ላሉትም ሆነ እንደእሷ ለሥራ ከሄዱበት በዓሉን ለማክበር ለሚመጡ ቤተሰቦች መሰባሰቢያ ነው፡፡

በእርሷ በኩል ለዚሁ በዓል ብላ ባጠራቀመችው ገንዘብ ለመላው ቤተሰብ አልባሳት ከመግዛት ጀምሮ ለማብሰያ የሚሆን ነዳጅ ጋዝ፣ ዘይትና ሌሎችም ለቤተሰቦቿ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ይዛ ለመሄድ መዘጋጀቷን ትገልፃለች፡፡

ቀኑ ደርሶ ከቤተሰቦቼ ጋር ቆንጆ ጊዜ እስካሳልፍ በቂ እንቅልፍም አልተኛ ስትል መጓጓቷን አሳውቃለች። በዓላት ሲመጡ የሚታዩ ችግሮችን ለመቀነስ በተለይ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ታሪፉን ባማከለ ሁኔታ ህብረተሰቡን ሊያገለግሉ እንደሚገባ መልዕክቷን አስተላልፋለች።

በጉራጌ ዞን ቸሀ ወረዳ አውቃቅር ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ውባለም ደጉ በበኩላቸው፤ አሁን ላይ ዝግጅቱ ሁሉ አልቆ ቤት የማስዋብ፣ አካባቢን የማፅዳት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ በዓሉ መስከረም 14 ከሚኖረው የሴቶች መስቀል ወይም የጎመን ክትፎ እንደሚጀምር ያስረዳሉ፡፡

የበዓል ክትፎ፣ ቆጮና ማባያ ቅመሞችን ሁሉ የማዘጋጀቱ ኃላፊነት የሴቷ መሆኑን አንስተው፤ ወንዶች እርድ የማከናወንና ባህላዊ ሥርዓቶችን የመምራት ኃላፊነት እንዳለባቸው ይናገራሉ።

ከሕፃን እስከ አዋቂ በጉጉት በሚጠበቀው በዓል ሁሉም ባለው አጊጦና ተደስቶ ለማሳለፍ ዓመት ሙሉ ይዘጋጃል የሚሉት ወይዘሮዋ፤ እርሳቸውም በባህላዊ ልብሳቸው አጊጠው ከጎረቤትና ዘመዶቻቸው ጋር በፍቅር ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውን ይገልጻሉ።

በኃይማኖታዊና ባህላዊ ሁነቶችን የሚደምቀው በዓሉ ተራርቆ የነበረ ሰው ከወዳጅ ዘመድና ጎረቤት የሚገናኝበት ነው፤ ህብረተሰቡም ምንም ሳይለየው አብሮነቱና መተጋገዙን ያጠናክርበታል ይላሉ።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ወይዘሮ ብሩክታዊት ፀጋዬ በበኩላቸው፤ የበዓል ዝግጅቱ ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ መስከረም 11 እና 12 ለማክበር መዘጋጀታቸውን ይገልጻሉ፡፡

የመስቀል በዓል እስከ መስከረም 16 ቀን ድረስ እርድ እስከሚከናወንበት መከበሩ እንዳለ ሆኖ እስከ ጥቅምት አምስት ድረስ ደግሞ በዓሉን ተንተርሰው የሚመጡ የአዳብና ጨዋታ መኖሩን ይጠቁማሉ። አዳብና በልጃገረዶችና በወጣት ወንዶች የሚደረግ ጨዋታ በመሆኑ ዞኑ ሕዝቡ እንደሚያከብረው ያስረዳሉ።

በዓሉን የምናከብረው በዙሪያችን ከሚገኙ በርካታ አጎራባች ማህበረሰቦች ጋር በጋራ በመሆን ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ የመስቀል በዓል ቁርኝት የሚፈጥርና ለአንድነታችንም መሠረት የሚጥል መሆኑን ነው ያነሱት።

የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሠረት አመርጋ በበኩላቸው፤ በዞኑ በዓሉ “የመስቀል በዓላችን ለቱሪዝም ሀብታችን” በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል ይላሉ።

የመስቀል በዓል ከምግብና ባህላዊ ሥርዓቶቹ ባሻገር በቱሪዝሙ ዘርፍ ትልቅ የኢኮኖሚ ምንጭ አድርጎ ለመጠቀም የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ነው ያመላከቱት።

ከመስከረም 9 እስከ 11 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በዞኑ የተዘጋጀ የመስቀል በዓል ፌስቲቫል እንደሚካሄድ አስታውቀው፤ በዓሉ ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀና የቱሪስቶችን ቀልብ በሚስብ መልኩ ለማክበር የሚረዳ ገጠራማ ሥፍራ መመረጡን ይጠቁማሉ።

ለሰባተኛ ጊዜ በሚካሄደው ዞናዊ ፌስቲቫል ከጉንችሬ ከተማ 50 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው እኖር ወረዳ በሚገኝ ጋራድ ቀበሌ በተሰኘ ውብ ሥፍራ ላይ ይካሄዳል ብለዋል።

በዓሉ ጀፎረ በተሰኘውና በባህላዊ መንገድ የተዘጋጀ ሰፊ መንገድን በያዘ የጉራጌ ባህላዊ መንደር ውስጥ ይካሄዳል ሲሉ ተናግረዋል። ለፌስቲቫሉ አስፈላጊ የሆኑ የመስተንግዶ፣ አካባቢውን የማስዋብና ሌሎች ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ነው የገለጹት።

በፌስቲቫሉ የቁንጅና ውድድርና የባህላዊ ዕቃዎች አውደ ርዕይ እንደሚካሄድ አስታውቀው፤ የመስቀል ጎመን ክትፎ ዝግጅትን የሚያካትተው የከብት እርድና የባህላዊ ምግብ ፌስቲቫል፣ የኪነ- ጥበብ ዝግጅቶች እንዲሁም የጥያቄና መልስ ውድድሮች መዘጋጀታቸውንም ያስረዳሉ።

ፌስቲቫሉን ለማክበር ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት የተጋበዙ እንግዶች እንደሚሳተፉ ጠቁመው፤ ለሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች፣ ለሚዲያ አካላት፣ ለኪነ-ጥበብ ሰዎች፣ ለአስጎብኚ ድርጅቶች፣ በቱሪዝም ላይ ለሚሳተፉ አካላትና ለተለያዩ እንግዶች ጥሪ ተደርጓል ይላሉ።

ማህበረሰቡ በርካታ ታሪክ ያለው በመሆኑ የቱሪዝም መዳረሻዎችንም የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚከናወን ይገልጻሉ።

ለመስቀል በዓል የሚመጡ ባለሀብቶችና የዞኑን ተወላጆች በማስተባበር በትምህርት ቤት ግንባታ፣ በመንገድ ሥራ፣ በተለያዩ ተቋማት የልማት ሥራዎች ላይ ለማሳተፍ የሚረዳ ንቅናቄ እየተካሄደ መሆኑን አንስተዋል።

በዞኑ በሚገኙ እያንዳንዱ ወረዳዎች አንድና ከዚያም በላይ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማልማት ይገባል የሚል አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራበት ይገኛል ይላሉ።

ዞኑ እንግዶቹን ለመቀበል ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን ገልጸው፤ የበዓሉ ታዳሚዎች በሰላም አክብረው እንዲመለሱ አገልግሎት ሰጪዎች፣ የፀጥታ አካላትና ሌሎችም የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ነፃነት አለሙ

አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You