አዲስ አበባ፡- ጋዜጠኞች ሐሰተኛ መረጃ እና ሐሰተኛ የመረጃ ምንጭን በመከላከል ሀገርን ከጥፋት ማዳን እንደሚገባቸው ተገለጸ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዝግጅት ክፍላችን ትናንት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ተአማኒነት የሌለው ዜና (Fake News) እና የእጅ ስልክ ጋዜጠኝነት (Mobile Journalism) የመለያ መንገዶች በሚል ርዕስ ከተለያዩ የአገሪቱ ሚዲያዎች ለተውጣጡ 30 ጋዜጠኞች በተቋሙ አስተባባሪነት ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በመርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት፤ መረጃን ከትክክለኛው ምንጭ በማግኘት በተገቢው መንገድ ለህብረተሰቡ ማድረስ ይገባል፡፡
እንደ አቶ መለስ ገለጻ፤ የሐሰት መረጃ አገርን ይጎዳል፤ እውነተኛ መረጃ ማስተላለፍ ህዝብን ከጥፋት አገርን ከውድመት ያድናል፡፡ መረጃን ከማስተላለፍ በፊት የተገኘበትን ምንጭ በሚገባ መመርመር እና የተቀነባበረ የሐሰት መረጃ አለመሆኑን መረዳት ከጋዜጠኞች ይጠበቃል፡፡
ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉ የተጋበዙት ጋዜጠኛ ሙንታስር ማራይ በበኩላቸው፤ የውሸት መረጃ እንደ ሶሪያ እና ሊቢያ ያሉ አገራትን እንዴት እንዳፈራረሳቸው በመጠቆም የማህበራዊ ሚዲያ፣ ውድ የሆነውን የሰው ሀብት ብሎም አገርን እንዳልነበረ እንደሚያደርግ ተጨባጭ ምሳሌዎችን በመጥቀስ አብራርተዋል፡፡ የሞባይልን ስልክ ብቻ በመጠቀም መረጃ የመሰብሰብ እና የማሰራጨት አሰራር እየተለመደ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችም ሊጠቀሙበት የሚችሉት አሰራር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የሚዲያ ባለሙያ መረጃውን ከማስተላለፉ በፊት ምንጩን በተለያየ መንገድ ማጣራት እና ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል ብለዋል ሙንታስር ማራይ፡፡
በማህበራዊ ሚዲያ የሐሰት መረጃን እውነተኛ ማስመሰል ከባድ አለመሆኑን በመጠቆም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እና ተዓማኒ ሚዲያ መሆን ከበሬታን ከማግኘት በተጨማሪ አድማጭ እና አንባቢን ማብዛት ያስችላል ብለዋል፡፡
ሠልጣኝ ጋዜጠኞች በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ የሐሰት ዜናዎችንና መልዕክቶችን በማንሳት የሃሳብ ልውውጥ ተደርጓል፡፡
የግል አስተያየታቸውን ከተቋሞቻቸው ኤዲቶሪያልና ትክክለኛ መረጃ መለየት እንደሚገባቸውም በሥልጠናው ወቅት ተገልጿል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 20/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር