ለሰው ልጆች ህይወት ጠቃሚ ከሆኑና ፈጣን ለውጥ ካመጡ ዘርፎች መካከል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቀዳሚው ነው። ምድራችን በዘመናት ሂደት ውስጥ ያልተገመተና በእጅጉ የረቀቀ የእድገት ደረጃ ላይ እንድትደርስ ሳይንሳዊ ምርምሮች የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶች ጉልህ ድርሻ ይወስዳሉ። ይህን ሁነት በተመለከተ አንዳንዶች “ በዓለማችን ላይ ለተከሰቱ አስደናቂ ለውጦች የግለሰቦች የፈጠራ ክህሎትና ብሩህ አእምሮ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል” በማለት ሲሞግቱ፤ አንዳንዶች ደግሞ “የተቋማት ግንባታና የህብረት ትጋት ውጤት አሁን ለደረስንበት ውጤት እንድንበቃ አድርገውናል” የሚል መከራከሪያን ያነሳሉ። ሁለቱም ሃሳቦች እንደየፈርጃቸው ማስረጃዎች ያላቸው ቢሆንም በዛሬው ርእሰ ጉዳያችን ልናወሳው ለወደድነው “የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ክህሎት የግለሰብ ስኬት ግን የሚቀርበው “መጠየቂያ” የመጀመሪያው ይሆናል።
በእርግጥም በዘመን ሂደት ውስጥ ግለሰቦች ምድራችንን ከአንደኛው ፅንፍ ወደሌላኛው የተሻለ ለውጥ ያንደረደሩ አያሌ የቴክኖሎጂና የሳይንስ ፈጠራ ውጤቶችን ጀባ ብለውናል። አልበርት አንስታይን፣ አይዛክ ኒውተን፣ ቶማስ ኤዲሰን ከእነዚህ ታላላቅና ባለ ብሩህ የፈጠራ ባለሙያዎች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው። ይህ የሚያመላክተን ግለሰቦች አሁን ለምንገኝበት ፈጣን እድገትና ታላላቅ የፈጠራ ግኝቶች ግዙፉን ድርሻ እንደሚወስዱ ነው። ለዚህም ነው ተሰጦና ክህሎት ያላቸው ግለሰቦች በልዩ ሁኔታ ድጋፍ እንዲደረግላቸው የተፈለገው። ይህን ፖሊሲም አያሌ አገራት ተግባራዊ በማድረጋቸው ፈጣን እድገት ከማስመዝገባቸውም በላይ የፈረጠመ ጡንቻ፣ ዘመናዊነትን መገንባት ችለዋል። አካሄዱን አሁን አሁን በአገራችን እየተለመደ ይገኛል። ዓለማችን ከምትገኝበት ደረጃ አንፃር ግን “እዚህ ግባ” የማይባልና ትከሻን ደንደን አድርጎ መትጋት እንዳለብን የሚያስገነዝብ ነው።
ለዛሬ የዝግጅት ክፍላችን ታዳጊ የፈጠራ ባለሙያዎ ያላቸውን እውቀትና የፈጠራ ሃሳብ በሙሉ አቅም ማውጣት እንዲችሉ፣ ሃሳባቸውን የሚያስተዋውቁበት እድልን እንዲፈልጉ ያበረታታል ብለን በማሰብ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ ዓመት የፕሪ ኢንጂነሪንግ ተማሪ እንግዳችን አድርገን ይዘንላችሁ ቀርበናል። ይህ ታዳጊ አራት አይነት “የድሮን ቴክኖሎጂ”ን ጨምሮ በዓጠቃላይ 28 የሚደርሱ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማሳያ (ፕሮቶታይፕ) ውጤቶች ላይ ምርምር በማድረግ ላይ ይገኛል። ለአገሩ በዘርፉ ውጤታማ የፈጠራ ስራ ማበርከት የዘወትር ምኞቱ ነው። ይህ እንግዳችን ተማሪ ኢብራሂም አሊ ይባላል።
ምልሰት ወደ ልጅነት
ውልደቱና እድገቱ በአዲስ አበባ ኮልፌ አካባቢ ነው። በአካባቢው የሚገኙ ቁሳቁሶችን በመጠቀም የፈጠራ ስራዎችን መስራት የጀመረው ገና የአራተኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት ነው። በዚያን ጊዜ ከቀለም ትምህርት ይልቅ ወደ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች ላይ ማዘንበልን ምርጫ በማድረጉ በክፍል ውስጥ ያለው ውጤት ያን ያህል አልነበረም። የመጀመሪያ የፈጠራ ስራውን በተለምዶ 18 እየተባለ በሚጠራው ሰፈር በሚገኘው እውቀቴ ወገኔ ትምህርት ቤት አካባቢ ሄሊኮፕተር ለመስራት ሙከራ ያደረገው ተጠቃሽ ነው።
“በልጅነቴ በሰፈር ውስጥ ከልጆች ጋር ከምጫወት ለብቻዬ ሆኜ ስለ ተፈጥሮ ማሰብና ስለምሰራቸው የፈጠራ ስራዎች መመራመር ይቀናኝ ነበር” የሚለው ተማሪ ኢብራሂም ሙሉ ጊዜውን በዚህ ላይ እንደሚያሳልፍ ይናገራል። አሁን በሚያካሂደው የፈጠራ ምርምር ስራው ከተፈጥሮና ከባቢያዊ ተፅዕኖ መነሻ እንደመጣም ያምናል። ለዚያም ነው ሙሉ ግዜውን ስኬታማ እሆንበታለሁ ብሎ በሚያስበው የፈጠራ ክህሎት ላይ ያደረገው።
የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ወቅት ለፈጠራ ስራው እቃዎችን ሲሰበስብ ከቤተሰቡና ከሰፈሩ ሰው ተቀባይነት አላገኘም ነበር። በተለይ ደግሞ ትምህርቱ
ላይ መድከሙ ቤተሰቡን ያሳስብ ነበር። በዚህ ምክንያት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ህልሙን ለማሳካት ሲል በትምህርቱ ጎበዝ በመሆን በእርሱ ላይ አመኔታ እንዲያሳድሩ ማድረግ ቻለ። ከዚያን ወዲህ ከትምህርቱ ጎን ለጎን የፈጠራ ስራው ላይ ማተኮሩን ተያያዘው። የ9ኛ ክፍል ተማሪ እያለ ግን ሙሉ ለሙሉ የፈጠራ ምርምር ስራውን በመግታት ትምህርቱ ላይ ትኩረት አደረገ፤ በውጤቱም 10ኛ ክፍል የደረጃ ተማሪ ከመሆኑም በላይ ትምህርት ቤቱን ወክሎ ሁለተኛ እስከመውጣት ደረሰ።
የፈጠራ ተሰጦ
ተማሪ ኢብራሂም ለጊዜውም ቢሆን ገትቶት የነበረውን የፈጠራ ስራ በድጋሚ በመጀመር ይበልጥ ይገፋበት ጀመር። የብየዳና የተለያዩ ለሙያው የሚጠቅሙ ትምህርቶችንም ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ይማር ጀመር። ይህን ግዜ ነበር ድሮኖችን የመስራት ፍላጎት በውስጡ ያደረው። ለፍላጎቱ መሳካትም የተለያየ ጥረት በማድረግ በዘመናችን ተፈላጊነታቸው እየጨመረ የመጣውን ድሮኖች በአገር ልጅና በአገር በቀል እውቀት ለመስራት ተነሳሳ። በተለያየ ጊዜያትም አራት የሚደርሱ ድሮኖችን በመስራትና “በማሳያ” ደረጃ በማዘጋጀት ሙከራውን ይገፋበት ጀመር። ሶስተኛውን ድሮን በሰራበት ወቅት በልዩ ሁኔታ የአንበጣ ኬሚካል እርጭት ማድረግ የሚችል እንዲሆን ጥረት አድርጓል። ኢብራሂም አራተኛውን ድሮን በተለየ መንገድ ለመስራት ሙከራዎችን እያደረገ ይገኛል። በዋናነት በኢትዮጵያ ውስጥ መሰራቱ ልዩ እንዲሆን እና በአገር ውስጥ በሚገኝ ቁስ ማምረት እንዲቻል እየሰራ ነው። በቀጣይ ደግሞ ሶፍትዌሩን፣ ሞተሩንና ሌሎች እቃዎቹን ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲመረቱ ለማድረግ ምርምር እያደረገ እንደሆነ ይናገራል።
“የፈጠራ ስራዎቼን ቀደም ሲል የማስተዋወቅና የእውቅና ሰርተፍኬት የማግኘት ሂደት ላይ ትኩረት አላደርግም ነበር” አሁን ግን በማህበራዊ ድርገፅ ስራዎቼን እያስተዋወኩና ተገቢውን ድጋፍ እንዳገኝ እየሞከርኩ ነው፤ የሚለው ኢብራሂም ቀደም ብሎ ይሄን ማድረግ አለመቻሉ ትንሽ ወደ ኋላ ጎትቶት እንደነበር ይናገራል። መሰል የመፍጠር አቅም ካላቸው ታዳጊዎች ጋር በጋራ ስራዎችን የመስራት ፍላጎት ብኖረውም የእርሱን ያህል ቁርጠኝነቱና ፍላጎቱን ሊያገኝ ስላልቻለ እንዳልተሳከላለትም ይናገራል። ሆኖም ያለውን ክህሎት ተጠቅሞ ድጋፍ ለሚሹ በርካታ ጓደኞቹ እውቀቱን አጋርቷል።
ከፈጠራ ስራዎቹ መካከል
ተማሪ ኢብራሂም በዋናነት የድሮን ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይስራ እንጂ 28 የሚደርሱ የፈጠራ ውጤቶችን በማሳያነት መስራት ችሏል። ከዚያ ውስጥ የምንጣፍ መጥረጊያ ይገኝበታል።ይህም በኤሌክትሪክ ( በቻርርጅ ) የሚሰራ የምንጣፍ መጥረጊያ ይገኝበታል። ይህ መጥረጊያ ምንጣፉን ከማፅዳት ባለፈ ቆሻሻን የሚስብበትና የሚያጠራቅምበት ቴክኖሎጂ አለው። ሌላኛው የፈጠራ ስራው የቤት፣ የመኪናና የተለያዩ መብራቶችን የስልክ 2ጂ ኔትወርክ ሲስተምን ተጠቅሞ ማብራትና ማጥፋት የሚችል ቴክኖሎጂን ነበር የሰራው።
ኢብራሂም ከሰራቸው በርካታ የፈጠራ ውጤቶች መካከል የሆነው ሌላኛው ቴክኖሎጂ ደግሞ የራዲዮ ፍሪኪዌንሲን ተጠቅሞ በራሱ ግዜ “የእጅ ቆዳን” በመገንዘብ “ሴንስ” በማድረግ የሚሰራ የእጅ መታጠቢያን መስራት ችሏል። ገበያ ላይ ያለው ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ወጥቶበት የሚገዛው መታጠቢያ ብዙ ክፍተቶች አሉበት የሚለው የፈጠራ ባለሙያው ብዙ በተለይ የኢንፍራሬድና ሴንሰሩ ፀሃይ ላይ የማይሰራና፣ ሌሎች ቁሳቁሶችንም ስለሚገነዘብና ውሃ ስለሚለቅ ብክነትን የሚያስከትል እንደሆነና የእርሱ የፈጠራ ስራ ይሄን ችግር መቅረፍ እንደሚችል ይገልፃል።
በራሱ ጥረት በርካታ የፈጠራ ስራዎች ቢኖሩትም በድጋፍ እጥረት ምክንያት ወደ ምርትና ተግባራዊነት ያልገቡ ብዙ የቴክኖሎጂ ሃሳቦች አሉት። ከዚህ ውስጥ የኮቪድ ወረርሽኝ በተከሰተ ወቅት የሰራው ኤትኤም ማሽኖችን በእጅ ሳይነኩ የሰውን ጣት እና ፍላጎት
በመገንዘብ (ሴንስ) በማድረግ የፈለግነውን ኮድ ማስገባት የሚችል የፈጠራ ውጤት እና ገንዘብን በቫይረስ ማፅዳት የሚችል ተጨማሪ ቴክኖሎጂ መስራት ችሏል። ኢብራሂም እንደሚለው የሚደግፈው አካል ቢያገኝ አሻሽሎ በመስራት ወደ ተግባር መለወጥ እንደሚችል በሙሉ እምነት ይናገራል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና የተቋማት ድጋፍ
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፈጠራ ባለሙያዎች እንዲጎለብቱ የሚያደርጉት ድጋፍ ጉልህ ድርሻ ይወስዳል። አሁን ላይ ተማሪ ኢብራሂምም ሳይቸገር የምርምር ስራውን እንዲያከናውን በግቢው ነጻ የትምህርት ዕድል ከመስጠት ጀምሮ ወርክሾፕ በማመቻቸት አቅሙን አውጥቶ እንዲሰራ እያበረታታው እንደሆነ ነግሮናል። በተለይ በይነ መረብ የማግኘት፣ ለሚያስፈልገው ቁስ በጀት የመመደብ ፍላጎት እንዳለውና እንደሚደግፈውም የዩኒቨርስቲው አስተዳደር ቃል ገብቶለታል። እርሱ ድሮ ድሮ ሉላዊ (ግሎባላይዝድ) የሆነውን አለም የሚያስተሳስረውን ዲጂታል ቴክኖሎጂ የመጠቀም ፍላጎቱ እምብዛም ነበር። አሁን ግን ለስራው ስለሚያግዘው የሚማርበት ትምህርት ቤት ባመቻቸለት እድል አማካኝነት ጎን ለጎን ልምድ እያገኘበት እንደሆነ ነግሮናል።
በዩኒቨርስቲው አሁን የቅድመ ኢንጂነሪንግ ኮርሶችን እየወሰደ ይገኛል። የትምህርት ክፍል የመምረጫ ግዜው ሲደርስ ተሰጦውን የሚደግፍና ይበልጥ ለመስራት የሚያግዘው የሙያ መስክ መርጦ ለመማር እየተዘጋጀ እንደሆነ ነግሮናል። ይህ ባይሆንም ሙከራውን እንደማይገታበትና በሙሉ አቅሙ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ እንደሚሳተፍ ገልፆልናል።
ሌላው የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በፈጠራ ስራው እንዲገፋበት የቃል ማበረታቻ እንደሰጡት ይናገራል። ድጋፍ እንደሚያደርጉለትም ቃል ገብተውለት ነበር። ከዓመት በፊትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት የፈጠራ ባለሙያዎች ተመርጠው ድጋፍና ሽልማት ሊደረግላቸው ይፋ ሆኖ ከምርጥ አሸናፊ 20 ዎቹ መካከል መግባት የቻለ ቢሆንም በኮሮናና አገሪቱ በነበረችበት ወቅታዊ የፀጥታ ችግር ምክንያት እስካሁን ተግባራዊ እንዳልተደረገ ይገልጻል። ይሁን እንጂ እውቅና የመስጠት ፕሮግራሙ እንዳልተቋረጠና ግዜው ይፋ እስኪሆንእየተጠባበቀ መሆኑን ነግሮናል። ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በድሮን፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንትና በሶፍትዌር የፈጠራ ክህሎት ላላቸው ተወዳዳሪዎች ያዘጋጀው ፕሮግራም ላይ መመዝገቡንም ይናገራል።
“በኢትዮጵያ ውስጥ ጥርት ያለ ድሮን ሰርቶ በመገጣጠምና በብዛት በማምረት ተግባር ላይ ያዋለ ባለሙያ የለም” የሚለው ተማሪ ኢብራሂም እርሱ እየሰራ ያለው አራተኛው ድሮንም ለየት ያለ ቴክኖሎጂ በመሆኑ በግሉ የፈጠራ መብት ላይ ለማስመዝገብ፣ በአፍሪካ ድንቃድንቅ ላይ ለመወዳደር እንዲሁም ምርቱ በኢትዮጵያ የሚመረት ብቸኛ ቴክኖሎጂ እንዲሆን እየሰራ እንደሚገኝ ይገልፃል። ለዚህ የሚማርበት ትምህርት ቤት እና አንዳንድ አካላት ድጋፍ እንደሚያደርጉለት ቃል መግባታቸውንም ይገልፃል።
የተማሪ ኢብራሂም ራዕይ
ኢብራሂም በልጅነቱ የሰነቀውን የፈጠራ ባለሙያ የመሆን ህልም በትምህርትና በልምድ እያጎለበተ፣ የስራ ትጋቱን እያጠነከረና ከስህተቱ እየተማረ ዛሬ ላይ ደርሷል። አሁንም ህልሙ እስኪሳካ ድረስና ለአገርና ለማህበረሰብ የሚጠቅም ቴክኖሎጂን እስኪሰራ ድረስ እንቅልፍ እንደማይወስደውም ። “የሰው ልጅ ሊኖረው ከሚችለው ትልቁ ሀብት ሃሳብ ነው ። እናስብ!” የሚል ጠንካራ እምነትና ፍልስፍና ያለው ተማሪው በአጭር ጊዜ ውስጥ በፈጠራ ስራ ግዙፍ ንቅናቄ ፈጥሮ ለፈጠራ ባለሙያዎች መንገድ ሊጠርግ የሚችል ሃሳቦችን ሰንቆ ለመስራት ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን ይናገራል። በተለይ ድሮኖችን ከማሳያነት ባሻገር ወደ ምርት መግባት በሚችሉበት መንገድ ሰርቶ ገበያው ላይ የመቀላቀል ራእይን ሰንቆ በመትጋት ላይ መሆኑን ይናገራል። በተለይ ደግሞ እርሱ የሚሰራው ድሮን በአየር ላይ የሚኖረው ቆይታ ረጅም እንዲሆንና የዓለምን ሪከርድ የመስበር ህልም እንዳለው ለዝግጅት ክፍላችን ገልፆልናል።
እንደ ኢብራሂም ያሉ በርካታ የፈጠራ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚኖሩ የዝግጅት ክፍላችን ያምናል። እነዚህን ውድ ልጆች ማገዝና በቅንጅት እንዲሰሩ ማድረግ ቢቻል የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አመርቂ ውጤት ያመጣል እንላለን። ባለሃብቶች እንዲሁም የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት ታዳጊውን አግዙትና የእርሱም የአገርም ህልም ከግብ ይድረስ የሚል መልክት ልናስተላልፍ ወደድን።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2014