በተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በአባልነትና በመሪነት ተሳትፎን አድ ርገዋል። በቅንጅት ለአንድነትና ለዴ ሞክራሲ፣ በሰማያዊ ፓርቲ እንዲሁም አሁን ላይ ራሳቸው ባቋቋሙት የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ነቅናቄ (ኢሀን) በሊቀመንበርነት አገልግለዋል፤ እያገለገሉም ይገኛሉ፡፡ ኢን ጅነር ይልቃል ጌትነት።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ካላቸው ፖለቲካዊ ተሳትፎ አንጻር ስለ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ፣ በለውጡ ሂደትና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርጓል።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ ፓርቲ መሰር ተዋል፤ በአሁኑ ወቅት የእርስዎ የሥራ ድርሻ ምን ድን ነው?
አዲስ ዘመን፡- አዲስ ፓርቲ መሰር ተዋል፤ በአሁኑ ወቅት የእርስዎ የሥራ ድርሻ ምን ድን ነው?
ኢንጂነር ይልቃል:- አዲሱ ፖርቲ የተመ ሰረተው ግንቦት 12 ቀን 2010 ዓ.ም ሲሆን እኔም የፓርቲው ሊቀመንበር ነኝ። ፓርቲው በምርጫ ቦርድ የተመዘገበ ነው። ሆኖም ባለፉት አስር ወራት ወደ አባ ላት ምልመላና የፓርቲ ሥራ አልሄደም። ምክንያቱም ውጭ አገር የቆዩ የዳያስፖራ ፓርቲዎች፣ በኤርትራ የነበሩትም ወደ አገራቸው ሲገቡ ነበር ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የድጋፍ ሰልፎችም ነበሩ፤ በአጠቃላይ እንደ አገር «በፈንጠዝያ ዘመን» ላይ ስለነበርን መገናኛ ብዙኃኑም ሆነ መላው ህዝብ ሌላ አማራጭ ድምጽ ለመስማት ዝግጁ አልነበረም ፤ እኛም በዚህ ምክንያት አማራጮቻችንን ህዝቡ ውስጥ ለማስረጽ ብዙ ርቀት አልሄድንም ከዚህ በኋላ በሰፊው እንሰራለን ።
አዲስ ዘመን፡- የፓርቲዎ ርዕዮተ ዓለም ምንድን ነው?
ኢንጂነር ይልቃል:- የፓርቲያችን መሰረ ታዊ ሀሳቦች የግለሰብ መብቶች ሲከበሩ የቡድን መብቶች ይከበራሉ የሚል ነው ፤ በዚህ የተነሳ ደግሞ ኢኮኖሚው ነጻ ይሆናል ባይ ነን፤ ግን ደግሞ አሁን ባለንበት ሁኔታ ጠንካራ መካከለኛ መደብ ስላልተፈጠረ የመንግሥት ሚና በኢኮኖሚው ውስጥ ትልቅ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አሁንም የመንግሥትን ድጋፍ የሚፈልጉ ማህበራዊ ፍትህ የሚያስፈልጋቸው በርካታ ድሃ ህዝቦች ስላሉ ሚናውም ከፍተኛ ነው። ስለዚህ የእኛ ፓርቲ ሀብታም ለመሆን በነጻነት መስራት ለሚፈልጉትም ሆነ ድሃ ሆነው የመንግሥትን ድጋፍ የሚሹትን ግምት ውስጥ ያስገባ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ የፖለቲካ ፖሊሲያችን «ሴንተር ራይት» የሚል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢሀን ከሰማያዊ ፓርቲ በምን ይለያል?
ኢንጂነር ይልቃል:- ከሰማያዊ ፓርቲ የሚለይበት ነገር የለም፤ ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ ፓርቲዎች በየጊዜው አንድ ይሆኑና ከዛ ይሰነጠቃሉ ይከፋፈላሉ፤ በአዲሱ ፓርቲ ላይ ይህ ነገር እንዳይፈጠር አደረጃጀቱ የፖለቲካ መዋቅሩና የሥነ ምግባር ህጎቹ ጠበቅ እንዲሉ ሆኗል። ከዚህ ውጪ ግን በፓርቲው መሰረታዊ ሃሳቦች ላይ ምንም ልዩነት የለም።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ጠንካራ ፓርቲን መስርተናል አሁን አንፈርስም እያሉ ነው፤ ግን ይህ የመፈራረስ ሁኔታ በአብዛኞቹ ፓርቲዎች ላይ የሚያጋጥም ነውና ለዚህ ምክንያቱ በእርስዎ ሀሳብ ምንድን ነው? መፍትሔውስ?
ኢንጂነር ይልቃል :- እዚህ ላይ የፖለቲካ ባህላችን ገና ኋላቀርና ቀኖናዊ መሆኑ ሁሉም ነገር እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን የሚልና የሌላውን ሃሳብ ያለማዳመጥ፣ ተነጋግሮ በልዩነት ውስጥ አብሮ ያለመስራት፣ በሚያግባቡ ነገሮች ላይ አብሮ እየሰሩ ልዩነትን እያስመዘገቡ የመሄድ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል አለመኖር አንዱ ምክንያት ነው። ሌላው ደግሞ ባለፉት 27 ዓመታት ገዢው ፓርቲ ደካሞችን የማበረታታት ጠንክረው ሲወጡ ደግሞ የማዳከም ነገር በስፋት መታየቱ ነው፤ ጠንከር ላሉ ፓርቲዎች መገናኛ ብዙኃንን መከልከል፣ በወንጀል መክሰስ፣ ማሰር፣ በፓርቲው ውስጥ ሰርጎ ገብ ማስገባትና መሰነጣጠቅ የድርጅቱ ባህል ነበር። እነዚህ ሁለት ነገሮች ሲደመሩ የተሻለ ተፎካካሪ ፓርቲ እንዳይኖረና በቀላሉ መሰነጣጠቅ እንዲፈጠር አደርጓል።
አዲስ ዘመን፡- ቀድሞ እርስዎ ሲመሩት የነበረው ሰማያዊ ፓርቲ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ ተቀባይነትን ያገኘ ነበር ማለት ይቻላል፤ ሆኖም ሳይታሰብ ፈራረሰ ፡፡ ከላይ ያነሱልኝ ችግሮች ተከስተውበት ነበር ማለት ይቻላል?
ኢንጂነር ይልቃል:- ለሰማያዊ ፓርቲ መፈራረስ ዋናው ተጠያቂ ገዢ የነበረው ፓርቲ ነው። ይህንን ለማለት ምክንያቴ ደግሞ እኔ ወደ አሜሪካን አገር መሄዴን ተከትሎ ፓርቲው ጉባዔ ሊያደርግ ዝግጅት አድርጎ ጠበቀኝ። በቀ ደመው ጊዜ ጉባዔ ለማድረግ ወጪ ደብዳቤዎች ላይ የምፈርም እኔ ነበርኩ፣ ለምርጫ ቦርድ የማሳውቀውም እንደዚያው፤ ሆኖም በወቅቱ ቢሮውን ቆልፈው ጉባዔውም በሌላ ቢሮ ተደረገ። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ በግሌ ሽማግሌ ተላከብኝ በተለይም አሜሪካን አገር ሆነህ «ባላደራ መን ግሥት ያስፈልጋል» ማለትህ መንግሥትን አስቆ ጥቷል፤ ይህንን ሀሳብህን አንሳና ከመንግሥት ጋር ተደራደር አሉኝ ። እኔ ደግሞ አቋሜ ነው ሀሳቤን አልቀይርም አልኩ፡፡ ሌላ ጉባዔ ተደርጎ ሰዎች ተመረጡ። እነዚህና ሌሎች ከገዢው ፓርቲ የሚመጡ ጫናዎች ናቸው ፓርቲውን ሊያፈርሱት፣ እኔንም ከኃላፊነቴ ሊያስነሱኝ የቻሉ ምክንያቶች። ሰማያዊ ፓርቲ በዛው ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ እኮ አሁን ላይ ተስፋችንን በመንግሥት ላይ ብቻ ጥለን አንቀመጥም ነበር፤ ጥሩ ተገዳዳሪ ፓርቲ ሆኖ ከመውጣቱም በላይ ህዝቡም የተለየ ድምጽ ይኖረው ነበር። ሌሎች ኃይሎችንም ለማሰባሰብ እርሾ ሆኖ የሚያገለግልበት ዕድል ሰፊ ይሆን ነበር።
አዲስ ዘመን፡- አዲሱ ፓርቲዎስ ለቀጣይ ምርጫ ዝግጁነቱ ምን ያህል ነው?
ኢንጂነር ይልቃል :- አይ ምርጫ አለ ብለሽ ነው? ምርጫማ ካለ ኢህአዴግ ተሸንፎ ያለ ድርጅት ነው። እኛ ደግሞ አሸናፊዎች ነን። ለዚህ ማሳያው ፖለቲካ ውስጥ መቆየታችን፣ ሰው ሁሉ ስለእኛ በቂ መረጃ ያለው መሆኑ ነው። አሁን ከእኛ የሚጠበቀው እንደ አዲስ መምጣታችንን ማስተዋወቅ ብቻ ነው። በኢህአዴግ ድክመትም በእኛ የበሰለ ፖለቲካዊ ልምድ ታግዘን ምርጫውን ስለማሸነፋችን አንዳችም ጥርጥር የለኝም።
አዲስ ዘመን፡- ወቅታዊውን የአገሪቱን ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
ኢንጂነር ይልቃል:- እውነቱን ለመናገር የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ በጣም ውስብስብና ከባድ ችግር ውስጥ ነው ያለው። ባለፉት 50 ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሲከፋፈል፣ ልዩነት ሲዘራ፣ የውሸት ታሪክ ሲፈበረክ ኖሮ አሁን ላይ ማንም ከማንም የማይተማመንበት፤ የፖለቲካ ኃይሎች ሁሉ እርስ በርሳቸው በጥርጣሬ የሚተያዩበት፤ የነገን ሁኔታ በራሳቸው አምሳል ለመቅረጽ ደጋፊዎቻቸውን በስሜት እየነዱ አገሪቱን በከፋ ሁኔታ ወደ ፍጅትና ብጥብጥ ሊወስዱ ዳር ላይ የደረሱበት ሁኔታ ነው የሚታየው። ለዚህ ማሳያው ደግሞ በየቦታው የሚታዩት የሰዎች መፈናቀሎች፣ የመንጋ ፍርድ፣ የሰዎች ያለአግባብ መገደል፣ ከአንድ ክልል ወደሌላ የመንቀሳቀስ ነጻነት ማጣት፣ የኢህአዴግ መዋቅር እንዳለ መቅረት (ከዶክተር አብይ መምጣት ውጪ) ፣ በክልሎች መካከል በወሰን ያለው ግጭት ወደ እርስ በርስ ጦርነት በሚያደርስ ሁኔታ ተፋፍሞ መቀጠል ፣ በመንግሥት አለመተማመን፣ የህግ የበላይነት አለመኖር፣ የዶክተር አብይ ተቀባይነት በፍጥነት እየወረደ መምጣት ይጠቀሳሉ። በመሆኑም ይህንን የሚቀለብስና የሚያስተካክል ሥራን መስራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ምን መሰራት አለበት?
ኢንጂነር ይልቃል:- ኢህአዴግ ሁሉንም ነገር በራሱ መወጣት እንደማይችል ታይቷል፤ አሁኑኑ ወደ ሽግግር መንግሥት እንዳይኬድ ደግሞ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተግባብተው ልዩነታቸውን አውቀው ሀሳባቸውን አንጥረው የወጡበት ጊዜ አይደለም፤ በመሆኑም ለጊዜው በፍጥነትና በትዕግስት ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ተቀራርበው ወይይት መጀመር አለባቸው። ውይይት ሲባል ግን 107 ፓርቲ እየተሰበሰበ ግማሽ ቀን እያወራ የሚበተንበት ዓይነት ሳይሆን ሀሳብን በትዕግስት፣ በሆደ ሰፊነትና በአርቆ አሳቢነት መንፈስ በሚገባ በማብላላት ለአገሪቱ የፖለቲካ ጥያቄዎችና ችግሮች መፍትሔ የሚሰጥ ሊሆን ይገባል። በቶሎ ይህንን ማድረግ ካልቻልን ግን በቅርበት የምናውቃቸውን አገሮች ዓይነት ዕጣ ፋንታ ሊገጥመን እንደሚችል የሚያሳዩ ብዙ ምልክቶች አሉ። ችግሮቹንስ ያስቀራሉ ወይ? እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች በቂ ናቸው ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች መታየት አለባቸው። ባለፈው አንድ ዓመት እኮ እኛ እንኳን በእናንተ የህት መት ውጤቶች ፣በሌሎች የመገናኛ ብዙኃን ላይ ቀርበን ሀሳባችንን ማስተላለፍ ችለናል፤ ተወጥረው የነበሩት የመገናኛ ብዙኃን ፈታ የማለት ነገር ታይቶባቸዋል፤ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በተለያዩ እስር ቤቶች የነበሩ ግለሰቦች ተለቅቀዋል፤ ከውጭ አገርም ገብተዋል፤ እነዚህ ነገሮች እንደ ተስፋ ሊታዩ ቢችሉም ለትልቁ ችግር መፍትሔ የሚሆን ነገር አላገኘንም በራሳቸውም ግብ አይደሉም።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ተፈናቅሏል፤ መፍትሔው ምንድን ነው? እንደ ፓርቲስ የእኔ ሚና ምን መሆን አለበት ይላሉ?
ኢንጂነር ይልቃል:- ኢትዮጵያ ከቻይና ቀጥላ ረጅም ዓመትን አብሮ የመኖር ታሪክ ያስመዘገበች አገር ናት። የራሷ የሆኑ በርካታ መገለጫዎች ያሏት፣ የጋራ ማንነት ገንብታ የቆየች ብትሆንም ባለፉት 27 ዓመታት የነ በረውን አንድነት የማጥፋት ልዩነት ላይ ያተኮረ ፖለቲካ የማወጅ በዚህ ምክንያት ደግሞ እኛና እነሱ የሚባል ነገር መፈጠር ተጀመረ። ይህ ደግሞ አሁን ላይ እያንዳንዱ መሬት መሬትነቱ ቀርቶ ብሔር ያለው ሆኗል። ሰዎችም በዛው ልክ ብዙ ማንነቶች እያሏቸው ከዚህኛው ብሔር ነው በሚል አንዱ አንዱን ስጋት አድርጎ እየኖረ ነው። ይህም ባለፉት ዓመታት ሁሉ ኮትኩተን ያሳደግነው በመሆኑ አሁን ላይ ፍሬውን ማየት ጀምረናል። ከዚህ የተነሳም እንደ ኢትዮጵያ ትልልቅ ሃይማኖቶች ሲሰበኩበት በኖረ ሀገር ላይ ለመስማት በሚዘገንን ሁኔታ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ዓይናችን እያየ ነው። በፊት በፊት አማራ ጨቁኖናል የሚል ነበር ፤ አሁን የጉጂና ኦሮሞን ጉዳይ ብናይ እንኳን ሁለቱም ብሔሮች አንዱ የሌላውን ቋንቋ አቀላጥፎ የሚናገር፣ አብሮ የኖረ፣ የተጋባ፣ የተዋለደ ሆኖ ሳለ እርስ በርስ እኔ እበልጥ እኔ በሚል ሺዎች እየተፈናቀሉ ነው፤ ይህ በሌሎችም ክልሎች የሚታይ ሀቅ ነው፤ በመሆኑም ይህ ሁኔታ የሚያሳየው ነገሮች ይዋሉ ይደሩ እንጂ ሁሉንም እንደሚያዳርስ ነው፤ ግን በዚህ ሂደት ውስጥ አንዱ አንዱን አጥፍቶ መኖር እንደማይችል አለመገንዘቡ ነው። አሁን ማድረግ ያለብን ኢትዮጵያ ለሁላ ችንም የምትበቃ አገር መሆኗን ተገንዝበን ከልዩነቶቻችን ይልቅ አንድ ወደሚያደርጉን ነገሮች አዘንብለን መስራት ነው ፤ እልህና ጥላቻ፣ ተረኛ አሸናፊ ነኝ፣ ሂሳብ አወራርዳለሁ የሚለው ስሜት መጨረሻው ጥሩ አይሆንም።
አዲስ ዘመን፡- የለውጥ ሂደት ግን ይህ ንን መሰሉን ችግር ያስከትላል ብለን ማለት እንችላለን?
ኢንጂነር ይልቃል:- የለውጥ ሂደት የሚ ባለው ለምሳሌ ነጻነት ያጣ ሰው ነጻነቱን ሲያገኝ እንደሚከሰተው ዓይነት የተናጠል ወንጀሎች ከልክ በላይ የሆነ ንግግር ምናልባትም የሌላውን መብት የሚነካ ሲሆን ነው። ይህ ግን ሲብላላ የኖረው እያደገ መጥቶ ፍሬውን ማየት ነው የጀመርነው። በለውጥ ሂደት እንደሚፈጠር «ገጭ ጓ» አይነት ስሜትም የሚወሰድ ሳይሆን ጠንከር ያለና ሊያፈራርሰን የተዘጋጀ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- 107 ተፎካካሪ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድን ተፈ ራርማችኋል፤ ይህ ሰነድ ቀጣዩን ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክ ራሲያዊና ፍትሀዊ ያደርገዋል ብለው ያስባሉ?
ኢንጂነር ይልቃል:- ሰነዱ ፓርቲዎች በራሳቸው ያቋቋሙት እንጂ በህግ አዋጅ የወጣ አይደለም፤ ልዩነቱ ምርጫ ቦርድና አማካሪዎቹ ሀሳቡን አመንጭተው ፓርቲዎች እየተወያየን በራሳችን ያጸደቅነው መሆኑ ነው። ሰነዱ የፓርቲዎችን የመነጋገር ባህል ያዳብራል፣ እርስ በርሳቸው ያስተዋውቃል፣ ወደ መንግሥት ህግና ወደ ፍርድ ቤት ሳይሄዱም ችግራቸውን በራሳቸው የመፍታት ፖለቲካዊ ባህልን ያዳብራል። ከዚህም ባሻገር በደጋፊዎቻቸውና በአባላት መካከል ያለውን ሽኩቻ በመጠኑም ቢሆን ይቀንሳል ። ነገር ግን በአገር ደረጃ ያንዣበበውን ስጋት ይፈታዋል ማለት አይቻልም።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻም እርስዎ መጨመር የሚፈልጉት ነገር ካለ?
ኢንጂነር ይልቃል:- አሁን ያለንበት ሁኔታ ኢትዮጵያ በታሪኳ አጋጥሟት የማያውቅና አደገኛ ነው። ይህን ደግሞ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ሳይቀሩ እየተናገሩት በመሆኑ መንግሥትም ቢሆን በየዕለቱ ስሜት ከሚኮረኩሩ ንግግሮች ወጥቶ እውነተኛውን ችግር ፍጥጥ ብሎ መጋፈጥና ተረጋግቶ ማሰብ ያለበት ጊዜ ላይ ነን። ተፎካካሪ ፖርቲዎችና የፖለቲካ ኃይሎች በቤተ መንግሥት ውስጥ በሚፈጠሩ ፖለቲካዎች ልባቸውን ከፍና ዝቅ ከማድረግ ተላቅቀው የራሳቸውን ሃሳብ ይዘው በጥሞናና በጥንቃቄ መራመድ ለአገር መፍትሔ ማሰብና አማራጭ ሀሳቦች ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል። ህዝቡም በጅምላ መደገፍ ወይም መቃወም ሳይሆን መጠየቅን መልመድ አለበት፤ የአገር የስልጣን ባለቤት እኔ ነኝ ችግር እንኳን ቢመጣ ከፖለቲከኞቹ በላይ ተጎጂ እሆናለሁ በማለት በኃላፊነት መንቀሳቀስ ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2011
እፀገነት አክሊሉ