የፈራነውማ…
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገሬ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መቆዘምና መተከዝ ስጀምር የማላውቀው የፍርሃት ቆፈን እየጨመደደኝ በቃላት ልገልጸው የማልች ለው ውስጣዊ ብርድ ሲያንዘፈዝፈኝ ይታወቀኛል። ይሄ ስሜት የጸሐፊው ብቻ አይመስለኝም። ቢሆን ደስታውን አልችለውም። ግን አይመስለኝም። አገሬና ሕዝቤም ድምጻቸውን በጋራ አስተባብረው፡- “ፍርሃቱን የአንተ ብቻ ማን አደረገው? ቁዘማውንም ቢሆን ጠቅልለህ ለራስህ ብቻ አትውሰድ። እኛም እኮ በፍርሃት እንቅጥቅጥ እየተናጥን ነው፡፡” እያሉ የሚገስጹኝ እየመሰለኝ የራሴን ጥላ እስከ መፍራት እደርሳለሁ፡፡
“አስፈራኝ!” ያልኩትን ስሜቴን በሚገባ የሚገልጽልኝን በይዘቱ ጠነን፣ በርዝመቱ ዘለግ ካለው ከሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን ተወዳጅ ግጥሞች መካከል ጥቂት የግጥም ስንኞችን በመዋስ ብእሬ ራሱ እንዳይፈራ በማበረታት ጭምር “ጉልበቴ በርታ! በርታ!” እያልኩ ከጋራ ስጋቶቻችን መካከል በአንዱ ላይ ቁዘማዬን እንቀጥላለን፡፡
“ፍቅርን ፈራን፤ መቀራረብን ፈራን፣
እንዳልተዛመድን፤ እንዳልተዋደድን፣
ፈርተን መዋደድን፤ ጉርብትናን ናድን፡፡
ፍቅርን ፈራን፣ ጥላቻን ሰራን፣ ብቸኝነት ጠራን፣
በጋራ ቤታችን አጥር ድንበር ሰራን፡፡
መቻቻልን ንቀን፤ ለፀብ ተሟሟቅን፣
ለአመጽ ስንነሳ፤ ለሰላም ወደቅን፣
አገር ስትቃጠል ከዳር ሆነን ሞቅን፡፡
መወያየት ጠላን፤ መነጋገር ጠላን፣
መደማመጥ ጠፍቶ፤ መነቋቆር በዝቶ፣
መናናቅ በርክቶ፡፡
የተስፋ ሻማችን ተለኩሶ፣
ወጋገኑ መታዬት ሲጀምር አድማሱን ጥሶ፣
እኛ ግን ራቅን፤ ብሩኅ ነገን ራቅን፣
ዛሬን በመጣበቅ ትናንትን ናፈቅን፡፡
ይለናል ጠቢቡ ብእረኛችን። እንኳንም በዛሬው ቀናችን አልኖርክ ጋሼ!
እባብ ያየ በልጥ በረየ፤
ሰሞኑን ከሃይማኖት ጋር ተያይዘው በተፈጠሩ ሁከቶች፣ ሞቶችና የንብረት ውድመቶች ምክንያት ምዕመናን እንደየእምነታቸው በየደጀ ሰላማቸው አደባባዮች ላይ ተደፍተው እምባቸውን እያጎረፉ ፈጣሪን በመሞገት ላይ ናቸው። የየሃይማኖቶቹ “አበ ነፍሶችም” “መንጎቻቸውን” ከጠብና ከጥፋት ለመታደግ ከቅዱሳት መጻሕፍታቸው ላይ እየጠቀሱ ምክርም ውግዘትም እያሰሙ ነው፡፡
ፖለቲከኞችም አርፈው አልተቀመጡም፤ በይደር የተላለፈው የትናንቱ ዳፋ ወደ ዛሬ ጀምበር ዞሮ አገር እያተረማመሰ መሆኑን ደጋግመው በመግለጥ ናላቸው መዞሩን እየገለጹልን ነው። ከየስብሰባቸው መድረኮች በሚወጡት መግለጫዎችም እኩይ የሚሉትን የጥፋት ኃይል መልሰው መላልሰው በንግግር እየወቀጡ በልብ ስፋት እንድንታገስ እየመከሩን ነው። የአገር አውራ ሽማግሎችና እናቶችም በእንብርክክ ተደፍተውም ሆነ በጥበብ ቃል እያግባቡ አጥፊና ጠፊውን ለማቀራረብና እርቅ ለማውረድ በትጋት እየሰሩ እንደሆነ በየሚዲያዎቹ የዜና ሰዓት ብቅ እያሉ ተስፋ እንዳንቆርጥ እያበረታቱ ይመክሩናል።
የጸጥታ ክፍሎችም ጉዳዩ ከቁጥጥራቸው ውጭ ያለመውጣቱን አስረግጠው ቢነግሩንም የፈራነውና የተፈራራንበት “በላ” ግን እየተደጋገመ በፍርሃት ስለሚያንዘረዝረን “ፈራን!” ብለን ብንበረግግ አይፈረድብንም። ለምን ቢሉ “እባብ ያየ በልጥ በረየ” [በረየ፡- ፈራ፣ ደነገጠ፣ ሸሸ፣ በረገገ፣ ፈረጠጠ፣ ወገሸ ወዘተ.] እንዲል ብሂላችን “ብዙ መሰል ተናዳፊ አገራዊ እባቦች በታሪካችን ውስጥ ደጋግመው ሲነድፉን ስለኖሩ በልጥ በሚመስሉት ወቅታዊ ፈተናዎቻችን” ብንበረይ አንወቀስም።
ታሪካችንን ስላላከበርነው አኩርፎን ይሆን?
ኢትዮጵያ የዛሬዎቹን ታላላቅ ሃይማኖቶች “ቤት ለእንግዳ” ብላ ልቧን ከፍታ፣ እጆቿን ዘርግታ፣ በፍቅርና “በአንቱታ” ዝቅ በማለት አክብራ መቀበል ከጀመረች ሺህ ዓመታት ተቆጥረዋል። የአይሁድ እምነት ወደ አገራችን የገባው የእምነቱን ቅዱሳት መጻሕፍት ይዞ ብቻም ሳይሆን በዘውድና በንግሥና ከብሮ ጭምር ነው። ከንግሥት ሳባና ከንጉሥ ሰሎሞን የተወለደውንና “ለሞዓ አንበሳ ዘእምነገድ ይሁዳ” የዘር ሐረግ በአባትነት የሚጠቀሰውን የቀዳማዊ ምኒልክን ሥርወ መንግሥት ማስታወሱ ብቻ በቂ ይሆናል።
ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ የዚሁ የሞአ አንበሳ 225ኛው ወራሴ ዙፋን እንደሆኑ ሲታመን መኖሩ ያልመሸበት ታሪካችን ነው። [ምንጭ፡- 1ኛ ነገሥት ምዕ. 10 እና በቅርቡ በደራሲ አምሳሉ መሐሪ ተጽፎ ለንባብ የበቃውን “ቤተ-እስራኤል ከትናንት እስከ ዛሬ” የሚለውን ግሩም መጽሐፍ እና “ዝክረ ነገር” የተባለውን ታላቅ ሰነድ ማመሳከር ይቻላል፡፡] “አፈ ታሪኩ በማስረጃ ከሚመሳከሩት ሰነዶች ጋር ይቃረናል” – እያሉ አንዳንድ ምሁራን ፀጉር እየሰነጠቁ የሚከራከሩባቸውን ዝንጉርጉር መሟገቻዎች ለጊዜው በዚህ ጽሑፍ ለመጠቃቀስ ዐውዱ ስለማይፈቅድ እናልፈዋለን፡፡
ከአይሁድ እምነት ቀጥሎ ወደ ኢትዮጵያ የገባው የክርስትና ሃይማኖትም ቢሆን ዕድሜው ሁለት ሺህ ዓመት ሊሞላው የቀሩት ጥቂት ዓመታት ብቻ ናቸው። የወንጌሉን የምሥራች ይዞ ከእየሩሳሌም ወደ አገሩ የተመለሰውን ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ፊሊጶስን እንደ የክርስትና እምነት ዋና መግቢያ ምክንያት አድርገን ከተስማማን ሁለት ሺህ ዓመት ዕድሜውን የሚደፍነው ከሁለት ዐሠርት ዓመታት በኋላ መሆኑን የሚያረጋግጥልን የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ምዕራፍ 8 ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ የተጻፉ በርካታ ማጣቀሻዎች እንዳሉም ማስታወሱ አግባብ ይሆናል፡፡
በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (በ340 ዓ.ም ገደማ) ለመጀመሪያ ጊዜ አክሱም ላይ ወንጌል ሰብከው ክርስትናን ያስተዋወቁትን ግሪካዊውን ጳጳስ ፍሬምናጦስን (የክህነት ስማቸው ከሳቴ ብርሃን “ብርሃን ገላጭ”) ለኢትዮጵያ ክርስትና መነሻ እናድርግ ከተባለም የእምነቱን የዕድሜ ርዝመት እጅግም አይቀንሰውም። የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች ታሪክ እድሜም ከአንድ ክፍለ ዘመን ተኩል በላይ ስለሆነ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡
የእስልምና እምነት ወደ ኢትዮጵያ አገባብ ታሪክም እንዲሁ በሰላምና በታላቅ አክብሮት የሚዘከር እንደሆነ ከታሪኩ መረዳት ይቻላል። በ615 ዓ.ም ነብዩ መሐመድ 15ቱን ተከታይ ሱሀባዎች ከወቅቱ የቁረሾች ስደት ዞር እንዲሉ የላኳቸው አፍቃሬ ሰላም ንጉሥ ወደ አለበት የሐበሻ አገር እንደሆነ ታሪኩ በዝርዝር ይነግረናል። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢም ከጥቂት ዓመታት በፊት ትግራይ ውስጥ በሚገኘው በጥንታዊው አልነጃሺ መስጊድ ለጉብኝት በተገኘበት ወቅት የ15ቱ ሱሀባዎች አጽም በክብር አርፎበታል የሚባለውን የመስጊዱን የውስጠኛ ክፍል ለመጎብኘት ዕድል ገጥሞት ነበር፡፡
ይህን የመሰለ ደማቅ፣ ሰላማዊና ፍቅር የተሞላበትንና በሺህ ዘመናት ውስጥ ሃይማኖቶችን በእኩልነት የመቀበል ታሪክ ባለቤት ነች በምትባለዋ ኢትዮጵያችን ውስጥ “የፍቅር ወንጌል” የሚባለው ቅዱስ መጽሐፍ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እየተሰበከ ኖሮ፣ “የሰላም መሠረት ነው” የሚባለው የእስልምና እምነትም እንዲሁ የተመሠረተበት ቅዱስ ቁርዓንም እንዲሁ ለሺህ ዘመናት ሲቀራ ኖሮ” ምን ሆነንና ምን ቢነካን ነው አፍቃሬ ሃይማኖተኝነትን እንደ ሽፋን እየቆጠርን የምንገዳደለው? አደብ ገዝተን የኅሊናችንን ወቀሳ ብናደምጥ ምክንያቱ በሚገባ ይገለጽልናል።
በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች እየተደመጡና እየተስተዋሉ ያሉ እጅግ አሳዛኝና ዘግናኝ ድርጊቶች ምንጫቸውና መነሻቸው ግራ እስኪያጋባን ድረስ መስጊዶች ተቃጠሉ፣ አብያተ ክርስቲያናት የዶግ ዐመድ ሆኑ፣ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች ተገዳደሉ ወዘተ. የሚለው መርዶ ከቀን ወደ ቀን ፍርሃትና ስጋት ላይ ጥሎን ብንቆዝም፣ ብንብከነከን፣ ብንበረግግና ብንበረይ “ለምን ፈራችሁ?” ተብለን ልንጠየቅና ልንወቀስ በፍጹም አይገባም፡፡
ሃይማኖታዊ ምልከታችንን ትንሽ ከፍ አድርገን እናግዝፈውና የወንጌሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን አገራዊ መከራችንን ሲመለከትና ሲያስተውል ስሙን የተሸከሙትን “ክርስቲያኖች ነን ባዮችን” በርግጥ ልጆቼ ብሎ ይጠራቸዋል? አይመስለንም። “በሰላም አስተምህሮው” መታወቂያነት የሚገለጸው “እስልምና” ስሙ በክፉ እየተነሳ በዛኛውም ሃይማኖት ሆነ በዚህኛውም ገዳይ ሲፎክርበት፣ ሟች የደም ግብር ሲከፍልበትስ የነብዩ መሐመድ መንፈስ ምን እያለ ይወቅሰን ይሆን? ዐይኖቹ ሁሉ በምድር ላይ የጸኑት ቅዱሱ የሰው ልጆችና የፍጥረታት ሁሉ ገዢው ጌታ አምላክስ እንደምን ያዝንብን፤ ፊቱንም ያጠቁርብን፣ በፍርዱም እንደምን አይጨክንብን?
ከየትኛውም የሃይማኖት ወገን በግፍ የተገደሉት የንጹሐን ነፍሳትስ ወደ ፈጣሪ ዘንድ ሲደርሱ ስለተፈጸመባቸው የግፍ አገዳደል ቢፈረጅ ጌታ ፊት የሚመሰክሩት ምን እያሉ ይሆን? የጌታችን ስም ሲታወስባቸውና ጸሎታችን ወደ ላይ ሲያርግባቸው የሚውሉት አብያተ ክርስቲያናትና መስጂዶች በእሳት ጋዩ፣ በአመጸኞች እጆች ወደሙ መባል፤ እንኳን ለፈጣሪ ቀርቶ ለሰው ኅሊናስ ይመቻል? ፈራን ያሰኘን፣ ውስጣችንን ብርድ ብርድ ብሎ ያንቀጠቀጠን ክፉ ፍርሃትና መከራ ምክንያቱ ይህ ነው፡፡
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በዘመነ ደርግ የነበረውን የሃይማኖት ስደትና የአማኞችን የመከራና የግፍ ዓይነት ተንትኖ ባቀረበበት “ኤሎሄና ሃሌሉያ – 1992 ዓ.ም” በሚለው ዳጎስ ያለ መጽሐፉ ውስጥ በጨካኙና በእምነት የለሹ የደርግ መንግስት ፖሊሲ መሠረት በሺህዎች የሚቆጠሩ የጸሎት ቤቶች እንደተቃጠሉ፣ እጅግ በርካታ ምዕመናን ለሞት፣ ለአካላዊ ጉዳትና ለኅሊናዊ ስብራት እንደተዳረጉ በበቂ ማስረጃ አስደግፎ መረጃዎቹን ለኅትመት አብቅቷል። ይህንኑ አስጨናቂ የወታደራዊ አገዛዝ በመሸሽም እውቀትና አቅም የነበራቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያን ከአገር ወጥተው እንደኮበለሉ ጭምር ለማሳየት ተሞክሯል፡፡
ይህ ጸሐፊ ራሱም ቢሆን የመከራው ተካፋይ ስለነበር ጥናቱ የሚያካትተው የራሱንም ተሞክሮ በማሳየት ጭምር ነው። “ሥጋ ያንገፈገፈው ሰው ቀይ በሬ ሲያይ ይሸሻል” እንዲሉ፤ ጸሐፊው “ፈራን!” እያለ ጭንቀቱን የገለጸው ከሃይማኖት ጋር የተቆራኘ ይህንን መሰል ክፉ ትዝታ ስላለውና ትዝታው ደግሞ የደም ግብር ጭምር የተከፈለበት፣ የዜግነት መብቱ የተገፈፈበትና በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት ጭምር የትምህርት ዕድል እንዳያገኝ በግፍና በግፈኞች የተፈረደበት ስለነበር “እባብ ስላየ በልጥ ቢበረይ” ፍርሃቱ ሊጋነን አይገባውም፡፡
ዛሬ በጀብደኝነትና “የቀናኢ ሃይማኖትን ካባ በመደረብ” የሚፈጸሙ ድርጊቶች በሙሉ ነገ ዋጋ የሚያስከፍሉት “ተጠያቂ መሆን የሚገባቸው እነ እከሌ ናቸው” እየተባለ ጣት የሚቀሰርባቸውን ብቻ ሳይሆን ራስና የራስ የሆኑት ጭምር በምድራዊም ሆነ በሰማያዊ የፍትሕ ወንበር ፊት እንደሚቆሙ ሊታወቅ ይገባል። ትናንት ደም የተቃባንበት የእርስ በእርስ የጦርነት ጠባሳ ሳይጠግግና አገራዊ የሀዘን ማቃችንን ሳንለውጥ ይህም አነሰ ተብሎ በሃይማኖት ስም የሚፈጸሙ እኩይ ድርጊቶች ከወዲሁ ተገቢው እርምጃ ካልተወሰደባቸው በስተቀር ውሎ አድሮ መከራችንን ቧጠን ወደማንወጣበት አዘቅት መደፈቃቸው አይቀርም፡፡
መንግሥት ሆይ! “በትረ መኮንንህን” ወደ በትረ ፍትሕ ለውጠው። የሃይማኖት አባቶች ሆይ! በመንጋ መሃል ሆነው እንደሚበጠብጡ ኮርማዎች ምእመኖቻችሁን “ጃስ!” እያሉ ወደ ጥፋት የሚመሩትን “ፀረ ሰላም ተዋንያንን” አንድም በምክር አለያም በውግዘት አደብ አስገዙልን። የማሕበረሰቡ የሽበት ባለፀጋዎች ሆይ! ሽበታችሁን ወደ ሺህ ውበት ለውጣችሁ ለጥፋት የሚያገነግኑትን በምክር ቃል ወደ ኅሊናቸው መልሱልን። ያኔ ፍርሃታችን ተገፎ በአገራችን ተዘልለን እንኖራለን።
ጉልበታቸውን በሴራና በሸር ላደነደኑ፣ በአንደበታቸው ቅዱስ መጻሕፍትን እያጣቀሱ በተግባራቸው ግን የሞት ቀስት ለሚያስወነጭፉ “የደም ባለዕዳዎች” እባካችሁ ወደ ቀልብያችሁ ተመለሱ። በምድር ቆይታችሁ በፀፀት፣ በሰማይ ቤታችሁ በሲኦል ከመሰቃየት ዛሬ በንሰሃና በመመለስ ለሥጋችሁ እረፍትን ለመንፈሳችሁም እርካታን ምረጡ የመልእክቱ ማጠቃለያ ነው። ቀሪውን ጉዳይ ለመንግሥት እንተዋለን። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 /2014