ሀገር በህዝቦች አንድነትና ስምምነት የሚመሰረት እንደመሆኑ ህዝቦችን የሚያስተዳድር መንግሥትም ከህዝብ የሚወጣና በህዝብ የሚመረጥ ነው። መንግሥት ደግሞ ህዝቡን የሚያስተዳድርበት ህገ መንግሥት አውጥቶ ወደ ሥራ ይገባል። ይሄ በሁሉም የዓለም ሀገራት ተግባር ላይ የዋለ ነው። በኢትዮጵያም በአፄ ኃይለስላሴ ስርዓተ መንግሥት የመጀመሪያው ህገ መንግሥት መዘጋጀቱ ይነገራል። ከዛም በኋላ ሀገሪቱን ያስተዳደሩት መንግሥታት የራሳቸውን የአስተዳደር እሳቤ የሚያንፀባርቅ ህገ መንግሥት አዘጋጅተዋል። በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ የዋለው ህገ መንግሥት በ1987 ዓ.ም የተዘጋጀው ነው።
በኢፌዴሪ ህገመንግሥቱ አንቀፅ 32 (1) “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነፃነት አለው” ይላል:: አንቀፅ 40 (1) ደግሞ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራት፤ ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመስራት መብት አለው” ይላል። በተጨማሪም በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 30 ላይ ዜጎች ከሀገሪቱ የመንግሥት አካላት ማግኘት ስላለባቸው መሰረታዊ መብቶች ይዘረዝራል። የመኖር መብት፣ የአካል ደህንነት መብቶች፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቶች እንዲሁም ንብረት የማፍራትና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ይጠቀሳሉ።
በአንቀፅ 13 ንኡስ አንቀፅ አንድ ላይም በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌዴራል መንግሥትና የክልል ህግ አውጪ፣ ህግ አስፈፃሚና የህግ ተርጓሚ አካላት እነዚህን መብቶች እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ ኃላፊነትና ግዴታ ተጥሎባቸዋል። እነዚህ ጉዳዮች በህገ መንግሥቱ ይቀመጡ እንጂ በተግባር ግን በአስፈፃሚ አካላት ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰሩ አይደለም።
በሀገሪቱ የለውጥ አራማጅ መንግሥት ከመምጣቱ ሁለትና ሶስት ዓመታት በፊት ህብረተሰቡ በመልካም አስተዳደር እጦት ተማሮ እንደነበር አይዘነጋም። በወቅቱም መንግሥት ሰፊ ህዝባዊ ውይይቶች አድርጎ ሙስና፣ የኑሮ ውድነት እንዲሁም የሰላም እጦት መንሰራፋቱና መፍትሄ እንዲሰጣቸው በህብረተሰቡ በኩል በጥያቄነት ቀርቦ ነበር። መንግሥትም አፋጣኝ ርምጃ እንደሚወስድ ቃል ገብቶ፤ እቅድ አውጥቶ ወደ ተግባር ገብቻለው አለ። ነገር ግን መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ችግሩ በመባባሱ በለውጥ መንግሥት እንዲተካ ሆኗል።
የለውጥ መንግሥቱም የነበረውን ችግር በሂደት ፈትቶ መልካም አስተዳደር እንደሚያሰፍን ቃል በመግባትና ይቅርታ በመጠየቅ ወደ ማስተዳደሩ ገባ።
ከለውጡ ማግስት በሀገሪቱ በተካሄደው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫም የብልፅግና ፓርቲ መንግሥት መመስረቻ ድምፅ አግኝቶ በህጋዊ መንገድ ህዝብ በማስተዳደር ላይ ይገኛል። ፓርቲው የመጀመሪያውን ጉባኤ ባካሄደበት ወቅት ከህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንዳለበት በመወሰኑ ከጉባኤው ማግስት ጀምሮ ህዝባዊ ውይይቶች ተደርገዋል።
በውይይቶቹም የመንግሥት አካላት ህዝቡ በውይይቶቹ ያነሷቸውን የመሰረተ ልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የሰላምና ፀጥታ፣ የህግ የበላይነት እና የሥራ እድል ፈጠራ በቀዳሚነት ለመመለስ ጥረት እንደሚያደርጉ ጠቅሰዋል። በተጨማሪም የኑሮ ውድነትና የመልካም አስተዳደር እንዲሁም ሰላምና ፀጥታ ጉዳይ አስቸኳይ እልባት ለመስጠት እቅድ ማቀዳቸውን በሚሰጡት መግለጫዎች ማየት ይቻላል። ህዝቡ ያነሳቸው ጥያቄዎች እቅድን ሳይሆን ትግበራን የሚፈልጉ ስለመሆናቸው ነጋሪ አያሻም። ህብረተሰቡ ሰላምና መረጋጋትን አጥብቆ እንደሚፈልግ በየመድረኩ ሀሳቡን ገልጿል። በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የኑሮ ውድነትም እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች እንዲፈቱለትም ጠበቅ ያለ ጥቄውን አቅርቧል።
ህዝብ ያስተዳድረኛል የሚለውን ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ሲመርጥ ያለበትን ችግሮች እንዲፈታለት እንጂ ተመራጮቹ ሲሽሞኖሞኑ ለማየት አይደለም። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች የፀጥታ ችግር እየተስፋፋ ነው። አንዳንዶቹ የህዝብ ተሿሚዎች በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ፅንፈኝነትን ሲያራግቡና ግጭት የሚፈጥሩ እንደሚውሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ስልጠና በሰጡበት ወቅት በግልፅ ተናግረዋል። ታድያ እነዚህን አይነት የተመራጭ ቀላጆች ባሉበት የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ እቅድ ቢቀመጥ ችግር ይፈታል ማለት ዘበት ነው። ምክንያቱም ችግር አምጪ አመራር ችግር ፈቺ መሆን ስለማይችል ነው።
ሌላው በየመድረኩ የህዝብ ጥያቄ የነበረው የኑሮ ውድነት ነው። በሀገሪቱ ኑሮ በየጊዜው እየጨመረ ነው። ለዚህ ደግሞ ከስግብግብ ነጋዴው እኩል የሰላም እጦት በምክንያትነት ይጠቀሳል። በዚህም መሰረታዊ የሚባሉ ሸቀጦች ዋጋቸው እየናረ ነው። አርሷአደሩ ከማሳው ጀምሮ በደላላዎች ዋጋ እየተተመነ ወደ ገበያ የሚቀርብበት አሰራር መንግሥት ካላቆመ ኑሮው ይበልጥ እንደሚወደድ ህዝብ ለመንግሥት በየመድረኩ ተናግሯል። መንግሥትም ችግሩን በግልፅ ያውቀዋል። ነገር ግን በእቅድ እፈታዋለው ብሎ ከማሰብ እቅዱን በተግባር ቢደግፈው ለውጥ ማምጣት ይችላል።
በሀገሪቱ ሰላም ለማምጣት ከመንግሥት እኩል የህብረተሰቡ ትብብር ይፈልጋል። ህብረተሰቡ እርስበርስ በመተባበር የጥፋት አላማ ያላቸውን ሰዎች መታገል ካልቻለ መረጋጋት ሊመጣ አይችልም። በሌላ በኩልም አንድነትን የሚሸረሽሩ ጉዳዮች ሲገጥሙት የመነጋገር ባህል ማዳበር ካልቻለ የሰላም እጦት ይፈጠራል። በዚህ ደግሞ ከኑሮ መወደድ ባሻገር የመኖሪያ ስፍራም የሚታጣበት ሁኔታም እንደሚኖር ግምት ውስጥ መግባት አለበት።
ባለፈው አንድ ዓመት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ብዙ ሰው ተፈናቅሏል። ለአካል ጉዳትም ተዳርጓል። ይህ ሁኔታ ቀድሞ የነበረውን የሀገሪቱ የድህነት ሁኔታን አባብሶታል። በተለይ የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር እየበዛ መምጣት በየጊዜው ለሚፈጠሩት የሰላም መደፍረሶች አንድ ምክንያት ይሆናል። ሀገር የመበጥበጥ ተግባር ውስጥ የተሰማሩ ሰዎች ወጣቶቹን መጠቀሚያ እያደረጉ ናቸው። በሌላ በኩልም የመልካም አስተዳደር እጦትና የህግ የበላይነት አለመኖር ወጣቱ ወደ ጥፋት እንዲገባ እየገፋው ይገኛል። የመልካም አስተዳደር ችግር መስፋፋቱ በማሳያነት የሚቀመጠው ሙስና ነው። በአሁኑ ወቅት ጉቦ ሰጥቶ ጉዳዮችን ማስፈፀም እንደ ግዴታ ተቆጥሯል። ይህ ሁኔታ ደግሞ በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙኃን በኩል የቅሬታ ዜና ቢሰራበትም መሰረታዊ የሆነ ለውጥ ግን አልታየም። በመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ እንደ ባህል እየተስፋፋ የሚገኘውን ‹‹እጅ መንሻ›› ገንዘብ መንግሥት አፋጣኝ የተግባር መፍትሄ ካልሰጠበት የሚያመጣው ጉዳት ከፍተኛ ነው።
እንደ አጠቃላይ በሀገሪቱ በሁሉም ቦታዎች የሚገኘው ህዝብ በአንድ ቃል ሰላም እንዲሰፍንለት ጥያቄውን አቅርቧል። በተጨማሪም የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የኑሮ ውድነት እንዲሁም ሙስና በአፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው አሳስቧል። ዝም ያለ ህዝብ ደግሞ ሲነሳ ምን ሊመጣ እንደሚችል መገመት ከባድ ስለማይሆን ተመራጩ መንግሥትም የህዝቡን ጥያቄ ተቀብሎ ወደ ተግባር መግባት አለበት።
አምኃየስ መርዕድ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 /2014