አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር ‹‹ወ.ወ.ክ.ማ›› ከፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ለአደጋ አጋላጭ ናቸው ተብለው በተመረጡ ሶስቱ ወረዳዎች የመብራት አገልግሎት እንዲሰጥ ፖል እየተተከለ መሆኑን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር ‹‹ወ.ወ.ክ.ማ› የአራት ኪሎ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር አቶ ነጋሽ ከበደ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ማኅበሩ ‹‹ምቹና አካታች ከተማን መፍጠር›› በሚል የፕሮጀክት መርሃ ግብር በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት፣ ሰባትና አስር ላይ ለዝርፊያና ሌሎች ወንጀሎች አጋላጭ በሆኑ ስፍራዎች 48 የመብራት ፖሎችን በመትከል ላይ መሆኑን አስታውቀዋል። የመብራት ፖል ተከላው ረጃጅም ደረጃ ያላቸውን መንገዶችና ለረጅም ጊዜ የመብራት አገልግሎት ያላገኙ መንደሮችን ያካተተ መሆኑንም ገልጸዋል።
እንደ አቶ ነጋሽ ገለጻ፤ በማኅበሩ እየተተገበረ የሚገኘው ‹‹ምቹና አካታች ከተማን መፍጠር›› የተሰኘው ፕሮጀክት ለአደጋ አጋላጭ ስፍራዎችን ለእንቅስቃሴ ምቹ የሚያደርግ፣ የኢ መደበኛ ህገ ወጥ ንግድንና የትራንስፖርት ችግርን ሊቀርፉ የሚችሉ ሀሳቦች ወደ ተግባር መለወጥ የሚችል ጽንሰ ሀሳብ ነው። በዚህም በከተማ ደረጃ በተለይም ለህብረተሰቡ የአደጋ ስጋት ተብለው ከተመረጡ ሥፍራዎች ውስጥ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት፣ ሰባትና አስር ውስጥ የሚገኙና በጨለማ ወቅት የኅብረተሰቡን እንቅስቃሴ ሊገቱ የሚችሉ አካባቢዎች ላይ ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣ የመብራት ፖል ተከላ እየተከናወነ ይገኛል። ሥራዎቹ የሚከናወኑት ከፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በኩል በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን፤ ከከተማ አስተዳደሩ፣ አራዳ ክፍለ ከተማና ሦስቱ ወረዳዎች ጋር በተደረገ ስምምነት ከ150 በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን በማሠልጠን በሥራው እንዲሳተፉ ተደርጓል።
የአራት ኪሎ ‹‹ወ.ወ.ክ.ማ›› ቅርንጫፍ ፕሮግራም ኦፊሰር ወጣት ታምራት እሸቱ በበኩሉ፤ በሥራው ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ከወጣቶችና ስፖርት፣ ወጣት ማኅበራት ከመሳሰሉት ሴክተሮች የተወጣጡ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ በፕሮጀክቱ ዙሪያ ለወጣቶች ግንዛቤ በመፍጠር በየአካባቢያቸው ለአደጋ አጋላጭና ምቹ ያልሆኑ ስፍራችን ለይተው እንዲያቀርቡ መደረጉን ተናግሯል። አክሎም በተለይ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት በተለምዶ መቶ፣ ሰባና አርባ ደረጃ በሚባሉት አካባቢዎች ላይ የመብራት አገልግሎት አለመኖሩ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በተለያየ ጊዜ ለችግር መዳረጉን አስታውሷል።
በአሁኑ ወቅት በስፍራው ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግሉ ጥራታቸው የጠበቁ የብረት ፖሎች እንዲተከሉ መደረጋቸው ህጻናትን፣ ሴቶችንና አረጋዊያን ብሎም በሥራ ላይ ቆይተው ምሽት ወደ ቤታቸው የሚገቡ ሰዎችን ከወንጀል ለመከላከልና በየትኛውም ሰዓት በነጻነት ለመንቀሳቀስ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ነው ወጣት ታምራት የሚናገረው። የፖል ተከላውና የመስመር ዝርጋታው እየተጠናቀቀ በመሆኑ በቀጣይ ወረዳዎች ከኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ጋር በሚኖራቸው ስምምነት መሰረት መብራት እንዲለቀቅ ይደረጋልም ብሏል። ለወጣቶች የተሰጠውን ሥልጠና ሳያካትት በሦስቱም ወረዳ እየተሠሩ ላሉት ተግባራት ወደ 286 ሺ ብር የሚደርስ ወጪ መደረጉንም ገልጿል።
የፖል ተከላው እየተካሄዳበቸው ያሉት ስፍራዎች፤ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ላይ የቀበና ወንዝ ተከትሎ በሚገኝ በቀድሞ ቦታ ቀበሌ 16 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ በወረዳ ስድስት (መቶ፣ ሰባ እና አርባ ደረጃ) ተብለው በሚጠሩት ስፍራዎች እንዲሁም በወረዳ አስር ዶሮ ማነቂያ አካባቢ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2011
አዲሱ ገረመው