የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ሸዋ ዞን የምትገኝና በመካከለኛ ከተማ አስተዳደር ደረጃ ያለች ስትሆን፣ ከክልሉ ርዕሰ ከተማ ባሕር ዳር 695 ኪሎ ሜትር፤ ከፌዴራሉ ከተማ አዲስ አበባ ደግሞ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች:: ከተማዋ ከባሕር ጠለል በላይ 2ሺ 700 ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች::
የከተማዋ ስፋት 18ሺ ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን፣ በከተማው ፕላን የተካተተው ከማስፋፊያው ውጭ 5ሺ 711 ሄክታር ይሸፍናል:: የቦታውም አቀማመጥ 86 በመቶ ሜዳማ፤ 10 በመቶ ዳገታማ፣ አራት በመቶ ተራራማ የሆነ እና ከዚህም ውስጥ 95 በመቶ ለግንባታ ምቹ የሆነ ቦታ ነው::
የከተማዋን አየር ንብረት ስንመለከትም በቀዝቃዛማ አየር ንብረት ብትታወቅም አሁን ላይ ቀዝቃዛነቱ እየቀነሰ የመጣ፤ በአማካይ 14 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀትና 964 ሚሊ ሜትር አመታዊ የዝናብ መጠን ያላት ከተማ ነች::
ከአስተዳደራዊ አደረጃጀት አንጻር ሲታይም ከተማዋ በዘጠኝ የከተማና በአምስት የገጠር ቀበሌ አስተዳደርና በ19 ሴክተር መስሪያ ቤቶች ተዋቅራለች::
የከተማው ህዝብ የተሰማራበት የሥራ መስክ በአብዛኛው በንግድና በግብርና ሲሆን ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢንዱስትሪዎች እየተመሙባት የምትገኝ ከተማ እንደሆነች መረጃዎች ያመለክታሉ::
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት እንደሚገልጸው ከተማዋ ለአዲስ አበባ ካላት ቅርበት፤ ምቹ አየር ንብረት፤ ሠላማዊና ሥራ ወዳድ ሕዝብ የሚኖርባት ከተማ በመሆኗ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ በኢንቨስተሮች ተፈላጊ ከተማ ለመሆን ችላለች ።
እስከ 2012 ዓ.ም በጀት ዓመት መጨረሻ ብቻ በ504 ባለሀብቶች 31 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር ያህል ኢንቨስት እንዳደረጉም መረጃው ያመለክታል ::
ኢንቨስትመንቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ሌሎች ባለሀብቶች ወደ ከተማዋ በብዛት መምጣት እንዲችሉ መስተዳድሩ ከምንጊዜውም በላይ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በቅንነት በመስጠት ረገድ ከፍተኛ ሥራ እየሠራ ከመሆኑም በላይ የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ ነው::
ኢንቨስትመንቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ለበርካታ ዓመታት ሲጓተት የነበረው የመሠረተ ልማት አገልግሎት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ አዳዲስ የምስረታ ሠፈሮችን ከነባሩ ሠፈር ጋር ለማገናኘት የመሠረተ ልማት አውታሮችን በዋናነት መንገድ ዝርጋታ፤ ውሃና መብራት መስመር አቅርቦት እየሠራ ይገኛል ::
መሠረተ ልማት ለአንድ ሀገር ህዝብ ዕድገት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ እንደ ደም ሥር የሚታይ ቢሆንም ይህ መሰረተ ልማት የታለመለትን ግብ ይመታ ዘንድ ደግሞ ጸጥታና ሰላም ወሳኝነት አላቸው ::
በአጠቃላይ በደብረብርሃን ከተማና በዙሪያዋ እየተገነቡ በሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የከተማዋ ህብረተሰብ ታላቅ ተስፋን የሰነቀ በመሆኑ መስተዳድሩም አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገም ይገኛል ::
ደብረ ብርሃን ከተማ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በከተማ ካለው ሰላምና ጸጥታ አንጻር ተመራጭ እየሆነች ስለመምጣቷ ደግሞ በደብረብርሃን ከተማ የሰላምና ህዝብ ደህንነት መምሪያ ሃላፊ አቶ አበራ መኮንን ይናገራሉ:: እኛም በከተማዋ ስላለው የሰላም ሁኔታና ተያያዠ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርገናል::
አዲስ ዘመን ፦ ደብረ ብርሃን ከተማ በተለይም እንደ አገር ካለብን ፈተና አንጻር ያለው
የሰላምና ደህንነት ሁኔታ ምን መልክ አለው?
አቶ አበራ ፦ ደብረ ብርሃን ከተማ በቅርቡ አዲስ መዋቅር ተሰርቶ ወደ ሪጂዎ ፖሊታንት ከተማ አስተዳደር ተሸግራለች:: አሁን ላይ በሙሉ አቅማቸው የሚንቀሳቀሱ አራት ክፍለ ከተሞችንም እንዲያቅፍ ሆኗል:: ይህ ደግሞ የከተማዋን እድገት በማፋጠን ሌሎች እህት ከተሞች የሚያደርጉትን ድጋፍ ተንተርሶ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጭ እንዲኖራት በርካታ ባለሀብቶች እንዲሳቡና ያላትን የገጸምድርና ከርሰ ምድር ሃብት በቅጡ አውቀው ወደልማት በመቀየር በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ሚናዋን እንድትወጣ የሚያደርጋት ነው:: ይህ እንዲሆን ግን ከተማዋ ከዚህ ቀደም የምትታወቅበትን የሰላምና መረጋጋት ሁኔታ ማስጠበቅ የግድ ይላል::
ይህንን የሰላም ማስጠበቅ ስራ አጠናክሮ ለመቀጠልም ከዚህ ቀደምም ቢሆን ሰላም ወዳድ የሆነውን የከተማዋን ነዋሪ ይበልጥ በሰላም አስፈላጊነት ዙሪያ ግንዛቤው እንዲያድግ በማድረግ የከተማዬ ሰላም የእኔም፣ የቤተሰቤም ነው ብሎ እንዲያስብ በማድረግ በኩል ሰፊ ስራዎች ተሰርተው የተለያዩ ውጤቶችም እየተመዘገቡ ነው::
ህዝቡ የከተማዬ ሰላም የእኔና የቤተሰቤም በሰላም ወጥቶ መግባት ምክንያት ነው ብሎ በማመኑም በአሁኑ ወቅት የትኛውም ሃይል የሚሰጠው አጀንዳ በከተማችን ነዋሪዎች ዘንድ ምንም አይነት ተቀባይነት የሌለው ሆኗል:: በአሁኑ ወቅት ሲቃወምም ሆነ ሲደግፍ ምክንያታዊ የሆነ የከተማ ነዋሪም ለማፍራት ተችሏል::
አሁን ባለው ሁኔታ እንደ አገር በበርካታ ውጥረት ውስጥ ያለን ብንሆንም እንደ ደብረ ብርሃን ከተማ ግን አንጻራዊ ሰላም ያለበት ከተማ ነው:: ይህ ደግሞ የመጣው የጸጥታ መዋቅሩና ህዝቡ እጅና ጓንት ሆኖ አካባቢውን በንቃት በመጠበቁ የተፈጠረ ነው ማለት እችላለሁ::
ለምሳሌ ብነግርሽ እዚህ ከተማ ውስጥ የሚኖር ነዋሪ በሙሉ በከተማዋ በየእለቱ ምን እየተከናወነ እንደሆነ፣ እነማን ምን እየሰሩ እንደሆነ ያውቃል ከዚያ በላይም ደግሞ ለየት ያለ እንቅስቃሴ ሲያይ ወይንም ደግሞ ጸጉረ ልውጦች በከተማዋ መንቀሳቀስ ላይ ከሆኑ ጊዜ ሳያጠፋ ለፀጥታ ሀይሉ ያሳውቃል:: በዚህ ደግም የፀጥታ ሀይሉ በፍጥነት ወደ አካባቢው በመድረስ ብዙ ነገሮችን ማዳን የከተማዋንም ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲቆም ለማድረግ ችሏል::
አሁን ባሳለፍነው የትንሳኤ በዓል ወቅት እንኳን ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን በሰላምና በደስታ እንዲያከብር በሰራቸው ስራ በበዓሉ ዋዜማም ሆነ በእለቱ እንዲሁም በቀጣይ ባሉ ቀናት እንኳን ህዝቡን ስጋት ላይ የሚጥል ችግር ቀርቶ የእርስ በእርስ ድብድብ እንኳን ያልታየበት ሆኖ አልፏል:: ይህ ውጤት ሊገኝ የቻለው ደግሞ ህዝቡና የጸጥታ ሀይሉ በመናበብ በሰሩት ስራ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል::
አዲስ ዘመን ፦ አሁን ያለንበት ወቅት አስቸጋሪ ከመሆኑ የተነሳ በተለይም እንደ አማራ ክልል ችግሮች እዚህም እዚያም ብቅ ብቅ ይላሉና ደብረ ብርሃን ከተማ ሰላሟን በዚሁ መልክ አጠናክራ እንድትቀጥል በተለይም በእናንተ የጸጥታ መዋቅር ውስጥ ምን አይነት ስራዎች ይከናወናሉ?
አቶ አበራ ፦ የሰላም ጉዳይ ዋናና መሰረታዊ ነው:: ሰላም ከሌለ ከተማዋን ማልማት ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ ብሎም እንደ አንድ ዜጋ ወጥቶ መግባት በራሱ ትልቅ ፈተና ስለሚሆን ይህ እንዳይመጣና
የሰላሙ ሁኔታ በዚሁ መልኩ አስተማማኝ እንዲሁም ሌት ቀን ይሰራል:: ነገር ግን ሰላምን ማስጠበቅ ከላይ እንዳልኩት የፀጥታ መዋቅሩ ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ነዋሪ ሃላፊነት በመሆኑና ሁሉም ነቅቶ አካባቢውን መጠበቅ ስላለበት እንደ ቢሮ የምንሰራው የህዝቡን አስተሳሰብ መቀየር ላይ ነው:: በየደረጃው ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችም ማለትም ሰላምን በማስጠበቅ በኩል ወጣቱም፣ ሴቶችም፣ የሃይማኖት አባቶችም በጠቅላላው ሁሉም የየራሱ ድርሻ ስላለው ከእነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ሰፋፊ ወይይቶችን እናደርጋለን::
በቀጣይም ህዝብና መንግስት የተጠናከረ ስራን እንዲሰሩ እንዲሁም የተለያዩ የፖሊስ አደረጃጀቶችም ወደነበሩበት እንዲመለሱ በሌላም በኩል ፖሊስ በሌለበት ሁሉም የከተማው ፖሊስ ሆኖ እንዲሰራ በተለያዩ ጊዜያት ከእምነት ከአመለካከትና ከብሔር እንዲሁም ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተገናኘ የሚፈጠሩ ችግሮች እንዳይኖሩ፤ ሲኖሩም በምክንያት እንዲፈቱ በማድረግ በኩል የፀጥታ መዋቅሩ ሰፊ ስራ እየሰራ ነው ለማለት እችላለሁ ::
ነገር ግን እዚህ ላይ የጸጥታ መዋቅሩ የፈለገ ቢጠናከር ህዝብ ያልተሳተፈበት ስራ ውጤታማ ስለማይሆን እንደ ትልቅ የትኩረት አቅጣጫ የያዝነው የሰላም ማስከበሩን ጸጥታ የማስፈኑን ስራ ህዝቡ በበላይነት እንዲመራውና የነቃ ተሳትፎን እንዲያደርግ በክልሉ ልማት ስራ ለመስራት የመጡ ባለሀብቶችም ድጋፍ እንዲያደርጉ የማድረግ ስራም እየተሰራ ይገኛል::
አዲስ ዘመን ፦ በደብረ ብርሃን አቅራቢያ ያሉ የአማራ ክልል ከተሞች እንግዲህ በህወሃት ሀይሎችም እንዲሁም በኦነግ ሸኔ የተለያዩ ችግሮችን እያስተናገዱ ነውና እንደው ይህ የሰላም መደፍረስ ወደክልሉ እንዳይመጣ እየተሰራ ያለው የመከላከል ስራ ምን መልክ አለው?
አቶ አበራ ፦ ትክክል ነው ፤ በቅርብ ርቀት ያሉ ከተሞች በተለያዩ አሸባሪ ቡድኖች ችግር ውስጥ እየገቡ ነው:: ይህ ወደከተማችን እንዳይመጣ ትልቅ ሀላፊነት ወስደን ህዝቡን በደጀንነት አሰልፈን ብዙ ስራዎችን እየሰራን ነው:: በቅርቡ በነበረው የህልውና ዘመቻ ላይ እንኳን የከተማዋ በርካታ ወጣቶች “ሆ” ብለው በመነሳት ክቡር የሆነውን ህይወታቸውን እስከመስጠት የደረሰ መስዋዕትነት ከፍለዋል::
በነገራችን ላይ ደብረ ብርሃን ከተማ በተግባር ጦርነት አይካሄድበት እንጂ የሁሉም ነዋሪ አእምሮ በጦርነት ውስጥ የከረመ ነው:: ከዚህ አንጻር አሸባሪው ቡድን እስከ ደብረ ሲና ሲመጣ እንኳን በከፍተኛ ወኔና ሞራል የክልልን እንዲሁም የከተማውን ሰላም ለማስጠበቅ ብዙ መስዋዕትነት ከፍሏል:: ከዚህ ጎን ለጎንም አሁን ላይ ደግሞ ወደጦርነት ልጆቻቸውን ባሎቻቸውን የሸኙ ቤተሰቦች የፋሲካ በዓልን ተደስተው እንዲውሉ በማሰብ በርካታ ድጋፎችንም አሰባስበው ለግሰዋል:: በመሆኑም አሁን ባለው ሁኔታ ከተማዋ በራሷ ዙሪያውን በተለያዩ ሀይሎች የተወጠረች ከመሆኑ እንዲሁም ሰላም መሆኗ የሚያናድዳቸው በርካታ የጥፋት መልዕክተኞች ያሉ በመሆኑ አሁን ከዚህ በፊቱ በተሻለ ሁኔታ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል::
እነዚህ የከተማዋ ሰላም መሆን የሚያናድዳቸው ሀይሎች በተለያየ ጊዜ አጀንዳዎችን ለመስጠት ሲሞክሩ ተገኝተዋል፤ በመሆኑም ህዝቡም የጸጥታ ሀይሉም በቅንጅት እነዚህን መጥፎ በድኖች ሲዋጋ ቀሪው የመንግስት ስራ አሰፈጻሚ ደግሞ በተለይም በከተማዋ ህዝቡን ለአመጽ ወይንም ደግሞ ለሌላ ሃሳብ የሚዳርጉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ከስር ከስር መፍታት ይኖርበታል ብለን በዚህም ላይ ተስማምተን ሁሉም የድርሻውን እንስቶ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው::
ይህንን ካደረግን በኋላ ዙሪያውን በሸኔም ይሁን የጁንታው ተላላኪዎች ሰርገው ሊገቡ ስለሚችሉ አከራይ ተከራይ የጸጉረ ልውጥ እንቅስቃሴ የሆቴሎች ፍተሻ በጣም በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ፤ አሁን ላይ ደግሞ በከተማዋ ያሉ ኢንዱስትሪዎችም ስራ በመጀመር ላይ ስለሆኑ የተለያየ ሰው ከመላው የአገሪቱ ጫፍ ወደከተማዋ ስለሚመጣ ይህንን በአግባቡ መምራትና ክትትል ማድረግ ላይ ከፍተኛ ስራን እንሰራለን:: ችግሮችም ሲገኙ ከስር ከስር የሚታረሙበትን ሁኔታ እንፈጥራለን::
አሁን ባለው ሁኔታ ግን ደብረ ብርሃን ከተማ ጥሩ የሚባል ሰላም ያለባት ነች፤ ነገር ግን ይህንን ሁኔታ አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን ፦በከተማዋ ከሚስተዋለው ነገር አንዱ ከተለያዩ የአማራ እንዲሁም የወለጋ አካባቢዎች ተፈናቅለው የመጡ ዜጎች ጉዳይ ነውና እንደው ከተማዋ በዚህን ያህል ስደተኞች ሲገቡባት ከሰላም ከጸጥታ አንጻር ስጋት የመሆኑ ሁኔታ ምን ያህል ነው፤ ይህንን በመቆጣጠሩና በማረጋጋቱ በኩልስ ሚናችሁ ምን ያህል ነው?
አቶ አበራ፦ አዎ በከተማችን ከተለያዩ የአማራና የኦሮሚያ አካባቢዎች ተፈናቅለው የመጡ ስደተኞች አሉ ፤ ቁጥራቸውም ከ 25 ሺ በላይ ነው፤ እነዚህ ሁሉ ሰዎች ደግሞ ወደከተማዋ የመጡት የደብረ ብርሃን ተወላጅ ስለሆኑ ሳይሆን በከተማዋ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ለመጠቀም በማሰብ ነው::
የገጠመንን ችግር መንግስት በዘለቄታዊ ሁኔታ እስከሚፈታው ድረስ ደግሞ እንደ ከተማ የተቻለንን እናደርጋለን:: ነገር ግን እነዚህ ከቤት ንብረታቸው አላግባብ የተፈናቀሉ ዜጎች ብዙ በውስጣቸው የሚመላለሱ ስሜቶች አሏቸው:: አሁን ያሉበት ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ ነው፤ ይህ ሁሉ ነገር ተደማምሮ እነሱም የከተማዋን ሰላም አደፍራሽ እንዳይሆኑ የራሳችንን ክትትል ከማድረግ የተለያዩ ድጋፎችን የሚያገኙበትን ሁኔታ ከማመቻቸት ጀምሮ ከራሳቸው ውስጥ ሰዎችን በመምረጥና እዛው የጸጥታ አደረጃጀትን በመፍጠር ክትትል እያደረግን እንገኛለን:: እስከ አሁን ለከተማዋ ስጋት የሚሆን ችግርም አልፈጠሩም:: እነሱም ላይ የተፈጠረ ችግር የለም::
አዲስ ዘመን ፦ እንግዲህ እንደ አማራ ክልል ክተት በታወጀበት ወቅት በርካታ ሰዎች የጦር መሳሪያን የማግኘት እድሉን ወይም አጋጣሚውን አግኝተዋል፤ እንደው እንደእናንተ ከተማ ይህንን የጦር መሳሪያ ላልተገባ አላማ እንዳይውል በመከላከሉ፣ በመቆጣጠሩና ፍቃድ በመስጠቱ በኩል እያከናወናችሁ ያላችሁት ነገር ምን ይመስላል?
አቶ አበራ ፦ አዎ ከተቃጣብን የጁንታው ወረራ ጋር ተያይዞ ለበርካታ ሰዎች ፍቃድ ተሰጥቶ የተያዙ የጦር መሳሪያዎች አሉ:: እነዚህ የጦር መሳሪያዎችን የሚያስተዳድርበት ደግሞ ክልልሉ የራሱ መመሪያ አለው፤ በዚህ መመሪያ መሰረትም እየተዳደረ ነው:: በመሆኑም የግል፣ የመንግስት፣ በሚሊሻ እጅ ያለ፣ በተመላሽ ሰራዊት እጅ ያለ፣ ትጥቅ እየተባለም አደረጃጀት ተፈጥሮለታል:: ይህንን በአግባቡ የመምራትና የማስተዳደር ስራም ይሰራል::
በነገራችን ላይ አሁን ለየትኛውም አካል የጦር መሳሪያ ፍቃድ መስጠት ተከልክሏል:: ለማንም ፍቃድ አይሰጥም:: በህገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀስ የሚገበያይ እንዲሁም ይዞ የሚገኝ ካለ ደግሞ በኬላ ፍተሻዎቻችን በደፈጣ ስራችን እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች በሚደረጉ ክትትሎች የሚገኙት ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እየተወሰደ ነው:: ምክንያቱም ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ በተበራከተ ቁጥር መጨረሻው ወይም ደግሞ ሄዶ ሄዶ የሚያርፍበት ሁኔታ ከባድ ስለሚሆን በዚህ በኩል የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር ጫን ያለ ነው:: ይህንንም ለህብረተሰቡ በሚገባ የማሳወቅ ስራ ተከናውኗል::
እዚህ ላይ ግን ልብ እንዲባል የምፈልገው ነገር አንድ ሰው የጦር መሳሪያውን ስላስመዘገበ ወይም ፍቃድ በእጁ ስለያዘ ብቻ ክትትል አይደረግበትም ማለት አይደለም:: በተለይም በዚህ ወቅት ፍቃድ ያለው የጦር መሳሪያም ቢሆን እንኳን ለምን አላማ እንደሚውል፣ ምን እንደሚሰራበት የመከታተሉ ስራ በከፍተኛ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል::
አዲስ ዘመን ፦ እንደ ከተማ ለምታደርጉት የሰላምና የጸጥታ ስራ በተለይም አጎራባች ከሆነው የኦሮሚያ ክልል ጋር ያላችሁ ጥምረትና አብሮ የመስራት ሁኔታ እንዴት ይገለጻል?
አቶ አበራ ፦ አዎ፤ ከኦሮሚያ ክልል በተለይም መንዲዳ ከሚባለው አካባቢ ጋር እንዋሰናለን፤ ከዚህ አንጻር ደግሞ የሁለቱንም አካባቢዎች ሰላም ለማስጠበቅ ብዙ ስራዎችን እንሰራለን፤ ጥሩ ግንኙነትም ነው ያለን፤ በቅርቡም የጋራ ውይይት ተደርጓል:: የጸጥታ ስራ ድንበር ተሻጋሪ እንደመሆኑም በውስጣችን ያሉ ችግሮችን ለማረም ለመፍታትና ቀጣይ አቅጣጫችንም ለማሳመር ትብብር አይነተኛ ሚና ያለው ከመሆኑም አንጻር ብዙ ስራዎችን እንሰራበታለን:: ይህ ስራ ደግሞ በውጤትም መታጀብ ያለበት በመሆኑ በርካታ ውጤቶች መጥተዋል:: በዚህም ሰርጎ ገቦችን የመያዝ አንዳንድ ተላላኪዎች የሚሰሩትን እኩይ ተግባር የማክሸፍ ስራዎችም ተሰርተዋል::
አዲስ ዘመን ፦እንደ አገር ሰላማችንን የማይፈልጉ አፍራሽ ሀይሎች በተለያዩ ክልልች ላይ የፈጽሙት እኩይ ተግባር ብዙ ነገሮችን እያሳጣን ነው፤ ከዚህ አንጻር ደብረ ብርሃን እስከ አሁን ሰላም ናትና እንደው ይህንን ሰላም ወደፊትም አጠናክሮ ለመቀጠል ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?
አቶ አበራ ፦ አሁን ያለንበት ሁኔታ እንደ አገር እየፈተነን ነው ያለው:: የአገራችንን ሰላም የማይፈልጉ አካላትን ለተላላኪዎቻቸው ብዙ አጀንዳዎችን ነው የሚሰጡት ፤ይህንን እኩይ ተግባራቸውን ለማስፈጸምም የተጠናከረና የተጠና እቅድ ይዘው አማራጭ አስቀምጠው ነው የሚንቀሳቀሱት፤ በመሆኑም ይህንን ህልማቸውን ለማክሸፍ እኛም በበኩላችን አጀንዳ ሰጪ እንጂ ተቀባይ ሆነን መቀጠል የሌለብን ከመሆኑም በላይ አመራሩና ህዝቡ እንደከዚህ ቀደሙ በበለጠ ሁኔታ መቀናጀትና መናበብ ይኖርበታል::
የሰላም ጉዳይ የማይመለከታቸው የለም:: ሁሉም ይመለከተዋል:: ሰላም ከሌለ ማንም ወጥቶ መግባት ልጆቹን ማሳደግ ራሱን ማስተዳደር እንደማይችል ግልጽ ነው:: በመሆኑም የሰላምን ዋጋ ካጣነው በኋላ ሳይሆን መረዳት ያለብን አሁን በእጃችን እንዳለ መሆኑን ማወቅ መገንዘብ ያስፈልጋል:: ከተማችንም እስከ አሁን በመጣችበት አግባብ ሰላሟ ተጠብቆ እንድትቀጥልና የሰላም አምባሳደር እንድትሆን መላው የከተማው ነዋሪ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል::
የሰላምና ጸጥታ ቢሮውም የተለያዩ እቅዶች አቅዶ እየሰራ በመሆኑም ይህንንም ሀይል ማገዝ ያስፈልጋል፤ ያለ ህዝብ የሚሰራ የጸጥታ ስራ ዋጋ የለውም ምክንያቱም የቱንም ያህል ብርጌድ ቢቆም የጸጥታ መዋቅሩም በከፍተኛ ሁኔታ ቢደራጅ ያለህዝብ ተሳትፎ የትም መድረስ ስለማይቻል ከወጣቱ፣ ከአገር ሽማግሌ፣ ከሀይማኖት አባቶች ጋር የጀመርናቸውን ውይይቶች አጠናክረን እንሰራለን::
በሌላ በኩል ደግሞ ህዝቡ በተለይም የትንሳኤ በዓል በሚከበርበት ወቅት ያሳየውን አንድነት፣ ትብብርና ሰላም ወዳድነት በማስቀጠል የከተማችንን ስም በሰላም ማስጠራቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት::
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ::
አቶ አበራ ፦ እኔም አመሰግናለሁ