አለም በአሁኑ ሰአት የተለያየ ርዕዮተ አለምን በሚያራምዱ ሀገራት፣ መንግስታት፣ ግለሰቦች የተሞላች ነች:: የነዚህ ሁሉ የሀሳብ ማረፊያ ደግሞ ሀገርና ህዝብ ናቸው:: ሀገር የምርጥ ሀሳብ ማረፊያ ናት፣ ህዝብ የድንቅ እውነት ስፍራ ነው:: ሀገርና ህዝብ ከነዚህ ጥንድ ሀቆች ሲርቅ ሌላ መልክ ነው የሚይዘው:: ምርጥ ሀሳብ፣ ድንቅ እውነት ሀገር የሚያቆሙ ዋልታና ማገር ናቸው:: የእኛም ሆኑ የአብዛኞቹ ሀገራት አሁናዊ ስቃዮች ከነዚህ የሀሳብ ጅረቶች የሚፈሱ ናቸው:: ሀገርና ትውልድን ማረፊያ ያደረጉ ከግለሰብና ከመንግስት እየፈለቁ ወደ ነገ የሚፈሱ አያሌ ሀሳቦች፣ አያሌ ድርጊቶች አሉ:: እኚህ የሀሳብ መልኮች የእኔና የእናተ አሁናዊ ታሪኮች ናቸው:: መጪውን ከመቃኘት ረገድም የጎላ ድርሻ አላቸው:: ከትናንት ተንከባለው ወደ ዛሬ የመጡ፣ ከዛሬ ተሸቀንጥረው ወደ ነገ ለመሄድ የሚያኮበኩቡ የሀሳብ እንቶፈንቶዎች፤…
ሰው ያለሀገር፣ ሀገር ያለሰው ምንድናቸው ቢባል መልስ አይኖረውም:: ሀገር ያለ ሰው፣ ሰው ያለ ሀገር ባዶ ናቸው:: ለአንዱ ህልውና የአንዱ መኖር ግድ ይለዋል:: ሀገር ያለ ሰው ምድረ በዳ ነው፣ ጋራ ሸንተረሩ፣ ሜዳና ዱሩ ትርጉም አልባ ነው:: አፈሩ፣ ምድሩ፣ ቀዬ፣ አእዋፋቱ ምንም ናቸው:: ሰውም ያለ ሀገር እንዲሁ ነው…ፍቅር ተስፋና እምነት በሀገር የሚበቅሉ የሰውነት ጌጦች ናቸው:: ሰውነት በሀገር፣ ሀገር በሰውነት የተሸመኑ አንድ አይነት መልኮች ናቸው:: በዚህ አንድ አይነት ውስጥ የሚለመልሙ፣ የሚያብቡ፣ የሚያፈሩ የጋራ ታሪኮች አሉ:: በዚህ አንድ አይነት ውስጥ የሚፈጠሩ፣ የሚጎለብቱ የጋራ ባህልና ሥርዓቶች አሉ:: እንደዚሁም ደግሞ ይሄንን የሀገርና የሰውነት መስተጋብር ባለመረዳት የምናበላሻቸው በርካታ ሀገራዊ ታሪኮች ይኖራሉ:: አሁን ላይ እንደ ሀገር የተፈጠሩብን ችግሮች ሰውነትን ከሀገር፣ ሀገርን ከሰውነት የመለያየት ጣጣ የፈጠረው ነው:: የቱ ጋ ነን?
ሀገር ዋጋ የምታወጣው በግለሰቦች የጋራ ህልም ነው:: ግለሰቦች ለየብቻቸው እያለሙ የሚፈጥሯት የጋራ ሀገር የለችም:: አብዛኞቻችን ግራ የተጋባን ነን:: የጋራ ሀገር ከመፍጠር ይልቅ የግል ሀገር ለመፍጠር የምንለፋ ነን:: በጋራ ሀሳብ ከመስማማት ይልቅ የብቻ አጀንዳ ይዘን ለመለያየት የቆምን ነን:: በየትኛውም የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ለብቻ በመቆም፣ ለብቻ በማሰብ የተፈጠሩ ሀገርና ህዝቦች የሉም:: የጋራ በሆነች አንድ ሀገር ላይ የሚፈጠር የብቻ ህልምና ራዕይ የለም:: እንደ ግለሰብ ከሌላው የተለየ ሀሳብና ህልም ሊኖረን ይችላል በሀገር ጉዳይ ላይ ግን በጋራ ማሰብ፣ በጋራ ማረይ፣ በጋራ መቆም የዜጎች ግዴታ ነው:: ስልጡኖቹ አውሮፓውያን እንዴት ከዘመናዊነት ማማ ላይ እንደተሰቀሉ ብታጤኑ አንድ መልስ ነው የምታገኙት እርሱም…ለጋራ ሀገር በጋራ ማሰብ የሚል እውነት ላይ ትደርሳላችሁ:: ቢገባን ኖሮ ይሄ እውነት አስተማሪያችን ይሆን ነበር:: ለምን ለየብቻ እንደቆምን፣ ለምን ለየብቻ እንደምናስብ፣ ለምን ጎራ እንደለየን መልስ ይሰጠን ነበር::
በእኛ ሀገር የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ መንግስትና ህዝብ አንድ ሆነው አያውቁም:: ባለፉት በርካታ አመታት ውስጥ መንግስት ህዝቡን ሲያስተዳድር የነበረው በሀይል ነበር:: መንግስትና ህዝብ ያልተስማሙባት ሀገር ምን አይነት ትውልድ፣ ምን አይነት ማህበራዊ መስተጋብር እንደሚኖራት መገመት አይከብድም:: አብዛኞቹ ችግሮቻችን በፖለቲካው በኩል የመጡ ናቸው:: አሁን ድረስ ፍዳ እየበላንባቸው ያሉ መከራዎቻችን እነዛ በራስ ወዳድነት የተቃኙ የወየቡ
የፖለቲካ ሥርዓቶቻችን የፈጠሩት ናቸው:: አንድ ሀገርና አንድ ህዝብ ያስፈልገናል:: መንግስትን የሚያምን ህዝብ፣ በህዝብ የሚተማመን መንግስት ያስፈልገናል:: እንዲህ ሲሆን የብቻ ህልም አይኖረንም፣ እንዲህ ሲሆን የብቻ ሀገር ለመፍጠር አንለፋም:: እንዲህ ሲሆን ተነጋግሮ መግባባት አይከብደንም:: ለችግሮቻችን እጅ አንሰጥም:: እዚም እዛም የምንሰማቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ችግሮቻችን ያለፈው የፖለቲካ ስርዐት የፈጠራቸው እንደሆኑ እሙን ነው::
አሁን ያለው መንግስት እኚህን ትላንትናዊ ችግሮች በመለየትና መፍትሄ በመስጠት በመንግስት ላይ እምነት ያጣውን ህዝብ እንደ አዲስ መፍጠር ይጠበቅበታል:: ያለፉት የፖለቲካ ስርዐቶች የዛሬውን ትውልድ ያሽመደመዱ፣ በሀገር ላይ በርካታ አሉታዊ ችግሮችን የፈጠሩ ናቸው:: እኚህ ችግሮች ከዛሬ ወደ ነገ እንዳይሻገሩ ሁሉን ባቀፈ ሀገራዊ ምከክር እልባት ሊሰጥባቸው ይገባል:: ህዝብና መንግስት የሚግባቡባትን፣ አንድ የሚሆኑባትን ኢትዮጵያ መፍጠር የሁላችንም ግዴታ ነው:: እንዳለፈው ጊዜ በተለያየና በተንሸዋረረ የፖለቲካ ምህዳር የምንፈጥረው ሀገርና ህዝብ የለም:: ያለፈው ጊዜ ምን ይዞልን እንደመጣ ሁላችንም የምናውቀው ነው:: ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል፣ ለስልጣን ጥም ሲባል በህዝቦች መካከል መለያየትን የሚፈጥሩ የሀሰት ትርክቶች ሆን ተብለው ሲፈጠሩ ነበር:: ታስቦና ታልሞ በትውልዱ መካከል የጥላቻ ቁርሾ ሲነገር ነበር እኚህ ሁሉ የማስመሰል ድራማዎች ከትላንት ተሻግረው ዛሬም አሉ::
ይሄ ትውልድ እኚህን የጥላቻና የመለያየትን ግድግዳ ማፍረስ አለበት:: ይሄ ትውልድ ከዛሬ ወደ ነገ የሚሻገር የፍቅርና የእርቅ መሰላል መዘርጋት አለበት:: በመንግስት ላይ እምነት ያለው ህዝብ በመፍጠር ረገድ ሀይሉንና ጉልበቱን እውቀቱንም መስዋዕት ማድረግ ይጠበቅበታል:: ኢትዮጵያ ያጣችው ምንድነው? ይሄን ጥያቄ ራሳችሁን ጠይቃችሁት ታውቃላችሁ? ካላወቃችሁ አሁኑኑ ራሳችሁን ጠይቁት…:: ኢትዮጵያ ሀገራችን ያጣችው ምንም የለም:: የወጣት ሀይል አላት፣ በተፈጥሮ የታደለች ናት:: ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ሀብቶቿ ብዙ ናቸው:: አለም የሌለው ብዙ ነገር አላት:: የተማሩ፣ ፊደል የቆጠሩ ሙህራን አላት:: ታሪክ ብትሉ፣ ባህል ስርዐት ብትሉ በሁሉም ሙሉ ናት…አንድ ነገር ግን ጎሎናል:: እርሱም የጋራ ህልም ነው::
ሀገር የጋራ ህልም ከሌላት ምንም ቢሞላት ዋጋ የለውም:: አሁን ላይ የወጣት ሀይላችንን፣ የተፈጥሮ ሀብታችንን፣ እውቀታችንንና ብዙሀነታችንን እንዳንጠቀም ያደረገን የጋራ ህልም አለመኖራችን ነው:: የጋራ ህልም የጋራ ብልጽግና፣ የጋራ ታሪክ ነው:: የጋራ ህልም የጋራ ትውፊት፣ የጋራ ጥቅም ነው:: የክብርና የሞገስ ዘውድ ነው:: የመፈራትና የአንበሳነት ምልክት ነው:: በጋራ ሀገር ላይ በጋራ አለማሰባችን ይሄን ሁሉ አሳጥቶናል:: ክብርን፣ ሙላትን አስፈሪነትን ወስዶብናል:: እድገትን፣ ብልጽግናን አሳጥቶናል:: አብዛኞቹ የዓለም ሀገራት ከኋላችን ተፈጥረው፣ የእኛን ያክል ምንም ሳይኖራቸው አልፈውን የሄዱት ለምን ይመስላችኋል? እውነት ይሄን አስባችሁት ታውቃላችሁ? የጋራ ህልም ስላላቸው ነው:: የጋራ ህልም አንድነትን ይፈጥራል:: ምንምነትን ወደ ሙላት የሚቀይር ሀይል ነው:: አሁንም ቢሆን ወደተውንውና ወደሚጠቅመን የአንድነት ህልም መመለስ አለብን እላለው:: ይሄን ካላደረግን ከዚህም በኋላ የምናባክናቸው በርካታ ሀገራዊ እድሎች ይፈጠራሉ:: ይሄ እንዳይሆን አርነት ወደሚያወጣን፣ ከፍ ወደሚያደርገን የአንድነት ህልም እንመለስ::
ሁሉ ሞልቶን ምንም እንደሌለን መሆናችን ሊያበቃ ይገባል:: በግለኝነት የተጓዝንባቸውን የብቻ ጎዳናዎች መለስ ብለን ብናያቸው ለማንም ያልጠቀሙ ሆነው ነው የምናገኛቸው:: እንደ ሀገር የጋራ ህልም ያስፈልገናል:: የጋራ መንገድ፣ የጋራ እውነት ግድ ይለናል:: የእኔና የእናተ የሀገር ፍቅር የሚለካው ለሀገራችን በምናስበው በጎ ሀሳብ ልክ ነው:: የእኔና የእናተ እውቀትና ማስተዋል ፍሬ የሚያፈራው ከግለኝነት ወጥተን ሁሉን አቃፊ በሆነ ማህበራዊ እውነት ላይ ስንቆም ነው:: ለዘመናት ሳይገባን ባክነናል:: መግባባት እየቻልን ሳንግባባ፣ መለወጥ እየቻልን ሳንለወጥ ወንዝ በማያሻግር የእኔነት አባዜ ተጠፍንገን ባለንበት እየረገጥን ቀመናል:: ይሄ ምንም ካልጠቀመን ወደ ሚጠቅመን መራመድ አለብን:: ወደሚጠቅመን ማማተር አለብን:: የሚጠቅመን ደግሞ እስከዛሬ ያልሄድንበት የአንድነት መንገድ ነው:: የጋራ ሀሳብ ነው:: የጋራ ህልም ነው:: በዚህ እውነት ውስጥ ራሳችንን እንድንፈልገው እንደ አንድ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁላችንንም አደራ እላለው::
ከየትኛውም ጥበብ በላይ ትውልዱ ይቅር ባይነትን መማር አለበት:: ከየትኛውም እውቀት በላይ ዜጎች የአንድነትን መንፈስ ሊረዱት ይገባል:: ከየትኛውም ማስተዋል በላይ መንግስትና ፖለቲከኞች በዛሬ የፖለቲካ ክሽፈት የሚፈጠረውን ነገ አርቀው ማየት አለባቸው እላለው:: ዛሬ ላይ ዋጋ እያስከፈሉን ያሉ ነገሮች እነዛ ትላንትና አርቀን ያላየናቸው ነገሮች ናቸው:: አርቀን ብናይም ሀላፊነት በማይሰማቸውና እኔነት በተጠናወታቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ነው:: ትውልዱ የአባቶቹን ስርዐት ተቀብሎ ለእውነት ማጎብደድ አለበት:: ሀገርና ህዝብን ከሚጎዱ ሀሳቦች፣ ድርጊቶች በመራቅ ለሀገራችን ውለታ መዋል ይጠበቅብናል:: የሀገራችን ኋላ መቅረት ሊሰማን ይገባል:: የህዝባችን ከስልጣኔ መራቅ ሊያመን ይገባል:: ያለ እኛ..ያለ እኔና እናተ ሀገራችን ምንም ናት:: በበለጠ ሀሳብ በልጠን መገኘት ለድሀ ሀገራችን ልንሰጣት የሚገባ የመጨረሻ ስጦታ ነው እላለው:: በጋራ ህልም ወደ ፊት መራመድ ለድሀ ህዝባችን ልንውለው የሚገባ የመጨረሻ ውለታ ነው እላለው::
በጋራ ሀሳብ ላይ ህዝብ ከመንግስት ጋር አንድ አይነት ሀሳብ ማሰብ አለበት:: በጋራ ጉዳይ ላይ ዜጎች አንድ አይነት ህልም ማለም አለበት:: አላማውን ትልቅ ያደረገ ትውልድ ሁሌም ትልቅ ነገር ነው የሚያስበው:: ትልቅ ነገር እንድናገኝ ትልቅ ነገር ማሰብ አለብን:: እስከዛሬ በትንሽ ሀሳብ ትንሽ ሆነን ቆይተናል:: ለመለየየት ሰበብ እየፈለግን፣ ለመገፋፋት መንገድ እየጠረግን ብዙ ጊዜአችንን በከንቱ አባክነናል:: አሁን ጊዜው የእርቅ መሆን አለበት:: በራስ ወዳድነት የቆሸሹ፣ በፖለቲካ ጭቅቅት ያደፉ ታሪኮቻችንን የምናድስበት የምክክር እንዲሆን ሁላችንም የበኩላችንን እንወጣ:: ሀገራዊ ምክክሩ ፍሬ አፍርቶ የሰላምን ፍሬ እስክንበላ ድረስ፣ የአንድነትን ካባ እስክንጎናጸፍ ድረስ የሀገራችን ጉዳይ ያሳስበናል::
ተነጋግሮ እንደመግባባት ጥበብ አለ አልልም:: ተስማምቶ አብሮ እንደመቆም ማስተዋል አለ አልልም:: እኛ ግን ይሄን ማድረግ ከብዶናል:: በዘመናት ታሪክ ውስጥ ተነጋግረን ከተግባባንባቸው ይልቅ ተነጋግረን ጎራ የፈጠርንባቸው ታሪኮቻችን ይበዛሉ:: በጋራ ካሰብንው ይልቅ ለብቻ ቆመን ያሰብንው ይልቃል:: ለምን? ይሄ ጥያቄ አንድ መልስ ነው ያለው..ሁላችንም ራሳችንን ጀግና ማድረግ እንፈልጋለን፣ ባለመስማማት ጦርነት ከፍተን ሀሳባችንን በሀይል ለማሳክት እንጥራለን:: ሳንዋጋና ሳንገዳደል ታሪክ ያለ አይመስለንም፣ ለውጥ የሚመጣ አይመስለንም:: የክፍለ ዘመኑ አስቂኝ ሞኝነት እኔና እናተ በጦርነት ያሳለፍንው ጊዜ ነው:: የክፍለ ዘመኑ የማይደገም አላዋቂነት ተነጋግረን መግባባት እየቻልን በአልሸነፍም ባይነት ጦር የተማዘዝንበት ጊዜ ነው:: በታሪካችን ላይ እንደዚህ ጊዜ ያለ አስነዋሪ ጊዜ አልጻፍንም:: ቢገባን ኖሮ ጀግንነት ያለው ተነጋግሮ በመግናባት ውስጥ ነበር:: ብናውቅ ኖሮ ከብቻ ሀሳብ ይልቅ በጋራ ሀሳብ ውስጥ ነበር ልዕልና ነበር:: በእኛ መስማማት የሚለመልሙ፣ በእኛ አንድ መሆን የሚያፈሩ ታሪኮች ከፊታችን እየጠበቁን ነው:: ለነሱ ስንል የጋራ ህልም እናዳብር::
እስኪ ሁላችንም በአንድ ሀሳብ፣ በአንድ ልብ የጋራ ታሪክ እንጻፍ:: እስኪ ሁላችንም ዘመን የሚሻገር፣ ለትውልድ የሚቆይ የጋራ ሀገር እንፍጠር:: በአንድ ቀለም፣ በአንድ ብዕር ኢትዮጵያ ትቅደም የሚል መፈክር እንከትብ:: ዛሬ..አሁን ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ለህዝባችን አንድነት እንትጋ:: ስለሀገራችን ምርጡን የምናስብበት ጊዜ ይሁን::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)