መንግስት የግሉ ዘርፍ በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ጉልህ ድርሻ በመረዳት ወደተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ለማድረግ የተለያዩ የድጋፍ ማእቀፎችን እያወጣ ተግብሯል፡፡ በሆቴል፣በግብርና ኢንቨስት መንት፣በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የግል ባለሀብቱ በስፋት እንዲሰማራ የሚያስ ችሉ የድጋፍ ማእቀፎች፣አደረጃጀቶች፣ወዘተ መተግበራቸውን ለእ ዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግም ተሰር ቷል፡፡
የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በዚህ በመጠቀም ኢኮኖሚውን እንዲያሳድጉ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ዘርፉ ግን የተፈጠረለትን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ኢኮኖሚውን በማሳደጉ ረገድ የሚጠበቅበትን ሚና መጫወት አልቻለም፡፡ የጥራት እና የገበያ መዳረሻ ችግሮች እንዲሁም የቴክኖሎጂና እውቀት ክፍተቶች ይስተዋልበታል፡፡ በዚህ የተነሳም በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን በሚያስችል ቁመና ላይ ሊገኝ አልቻለም፡፡ ዘርፉ በሚፈልገው ልክ ማደግ ቢችል በርካታ ትሩፋቶች ይኖሩታል፡፡ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ከፍታ የሚያደርስ መሰላል መሆኑ የሚታመን ሲሆን፣ የስራ እድልና የውጭ ምንዛሬ ማስገኘትም ሌሎች ዋና ዋና ፋይዳዎቹ ናቸው፡፡
እነዚህ የዘርፉ ፋይዳዎች የግሉን ዘርፍ በማነቃቃት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከፍ ለማድረግ መስራት እንደሚያስ ፈልግ ያስገነዝባሉ፡፡ ለእዚህም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የመሆን አቅሙን ማዳበር ይገባል፡፡ ከአገሮች ጋር ለሚካሄዱ የንግድ ልውውጦችና ግንኙነቶች የሚደረጉት ውይይቶች እና ስምምነቶችም ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል፡፡
አገሪቱም ከሀገሮች ጋር የምታደርገው የንግድ ሽርክና ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረ ህክታል፡ የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በቅርቡ የኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ከዋና ዋና የንግድ አጋሮች ጋር ያለበትን ሁኔታ የገመገመ አንድ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡ በመድረኩ ላይ የንግድ አጋሮችን በተመለከተ ፅሑፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ባለሙያ ዶክተር አጥናፉ ገብረመስቀል እንደተናሩት፤ ፅሁፉ ከአንድ እስከ አስር ከሚገኙት ዋና ዋና የኢትዮጵያ የንግድ ሸሪኮች ጋር አገሪቱ ያደረገችው የንግድ እንቅስቃሴ ያለበትን ሁኔታ ገምግሟል፡፡ በዚህም መሰረት ለአገራቱ ደረጃ ወጥቶላቸዋል፡፡
በጽሁፉ ከተዳሰሱት መካከል በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲሁም በውጭ ንግድ ዙሪያ ያሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ዶክተር አጥናፉ እንዳሉት፤ ሀገሪቱ ከቻይና ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት ከሌሎች አገራት ሸሪኮች ጋር እኩል አይደለም፡፡ ቻይና ለአፍሪካ አገራትና ለሌሎች የዓለም አገራት የምትቀርብበት መንገድ ይለያያል፤ ለምዕራባውያን አገሮች ያላት አቀራረብ ግን አንድ አይነት ነው ሊባል የሚችል ነው፡፡ ቻይና የአፍሪካ አገሮችን የምትቀርብበት መንገድ የተለየ ነው የሚሉት ዶክተር አጥናፉ፣ ቻይናውያኑ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡበት መንገድ ከኬንያ እንዲሁም የኬንያው ከሌላው የአፍሪካ ሀገር እንደሚለያይ ያብራራሉ፡፡
በየሀገሮቹ ለኢንቨስትመንት የሚያደርጉት አካሄድ የየራሱ ዓላማ እንዳለውም ነው የሚጠቁሙት፡፡ ‹‹እኛ አፍሪካውያን የካፒታል እጥረት ስላለብን ሁሌም የእነሱን ፖሊሲ ተጠቅመን እናድጋለን ብለን እናስባለን፡፡ በእርግጥ ይህ ስህተት አይደለም፡፡›› የሚሉት ዶክተር አጥናፉ፣ የእነሱን ፖሊሲና የልማት ስትራቴጂ ስንገለብጥ /ኮፒ ስናደርግ/ በትክክል መሆን እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ እነሱም አሁን ላሉበት ደረጃ የበቁት ይህን ፖሊሲ በትክክል ተጠቅመው መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል ነው የሚሉት፡፡ ፖሊሲው እነሱ ለዚህ ደረጃ የበቁበት ከሆነ እኛ ዘንድም ይሰራል ወይ የሚለውን መረዳትም ተገቢ ነው፡፡›› ሲሉ ይገልፃሉ፡፡
እንደ ዶክተር አጥናፉ ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ ማድረግ ያለባት ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጥ ሳይሆን በጥንቃቄ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይህን ለማለት የተፈለገበት ምክንያት አንደኛ ቻይናውያን ፕሮጀክቶች ወስደው ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ በኢትዮጵያ በኩል የሚያስፈልገው የፖለቲካ ውሳኔ ሳይሆን፣ በቴክኒካልና ኢኮኖሚያዊ አዋጭነት ላይ መመስረት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል በእነዚህ ላይ ለመከራከር የሚያስችል የስምምነት ጥበብ እንዲሁም ችሎታ መኖር አለበት፡፡ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ በኩል በጉዳዩ ላይ የሚደረገው ክርክር አነስተኛ ነው ሲሉ ያጣቅሳሉ፡፡
ዶክተር አጥናፉ እንደሚሉት፤ ከቻይና ጋር ያለው ግንኙነት አብዛኛው ውሳኔ የሚሰጠው በፖለቲካ ሰዎች ነው፡፡ የቻይናው ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ድረስ በቴክኒክ ረገድ ተገምግሞ ውሳኔ ተሰጥቶበት አያውቅም፡፡ የሚወስኑት ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳም ጥራት ወድቋል፡፡ ብዙ የቻይና ፕሮጀክቶች ከተሰሩ በኋላ ጥራታቸው አንሶ ይገኛል። ስለዚህ የኢትዮጵያ የሰው ኃይል ቴክኒካዊ በሆነ መልኩ ብቁ ሆኖ መገኘት ይኖርበታል፤ የመከራከርም ሆነ ከእነርሱ ጋር አብሮ የመስራት ችሎታን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡
የውጭ ንግዱን ማጠናከር የግድ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተለያየ ምርቶችን በማቅረብ ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት አማራጭ የሌለው ተግባር እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ተወዳዳሪ ለማድረግ ደግሞ መስፈርቶች አሉ፡፡ እነዚህም መስፈርቶች በመንግስትም ሆነ በግል ዘርፉም በኩል እኩል መወሰድ ያለባቸው የቤት ስራዎች መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ በኩል ሁሉንም ከመንግስት መጠበቅ እንደማ ይገባ በመግለጽ የግል ዘርፉም ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ነገሮችን አንደኛ ችሎታንና ቴክኖሎጂን መጠቀም እንዲሁም ፈጠራንም ማከል እንደሚጠበቅበት ያመለክታሉ፡፡
‹‹የእኛ ኢኮኖሚ እስካሁን ድረስ በግብዓት ላይ ብቻ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ነው፡፡ ሌሎች የአፍሪካ ጓደኞቻችን ብቃት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ወይም ሌሎች ደግሞ ፈጠራ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ›› ሲሉም ዶክተር አጥናፉ ይጠቁማሉ። እንደ ዶክተር አጥናፉ ገለጻ፤ የኢትዮጵያ የውጪ እና የአገር ውስጥ ምርት ግብዓት ላይ የተመሰረተ ነው። በግብዓት ብዛትና ጥራት ላይ ብቻ የተወሰነ ነው።
ኢኮኖሚ ተወዳዳሪ ነው የሚባለው በውጤታማነትና በፈጠራ ላይ የተመሰረተ ሲሆን ነው፡፡ ‹‹እኛ ግብዓት ላይ ነን፡፡ አፍሪካ ውስጥ ፈጠራ ላይ የገባ ኢኮኖሚ የለም ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ብቃትን መሰረት ያደረጉ ኢኮኖሚዎች ግን አሉ፡፡›› ሲሉ ይጠቅሳሉ፡፡ በአፍሪካም ብቃትን መሰረት ያደረገ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚገኙ አገራት እንዳሉ ተናግረው፣ ከእነዚህም መካከል ግብጽ፣ ሞሪሺየስ፣ ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ሲሸልስን ይጠቀሳሉ፡፡ ››ኢትዮጵያ ግብዓት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ብቻ ነው ያላት፡፡
ብቃትን መሰረት ያደረገ ኢኮኖሚ ላይ ለመድረስ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ የአገር ውስጥ አቅምን መገንባት ይጠይቃል፡፡›› ብለዋል፡፡ ዶክተር አጥናፉ እንዳሉት፤ ፈጠራ ላይ ለመድረስ ደግሞ ከዛ የተሻለ ጥረትና ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ይህ ከመንገስት ብቻ የሚጠበቅ ስራ አይደለም፤ የእያንዳንዱን ለስራው ብቁ ሆኖ መንቀሳቀስንይጠይቃል፡፡ የአገር ውስጥ አምራቾች እርስ በእርሳቸው መያያዝ ይኖርባ ቸዋል፤ ከውጭ በሚመጣ እቃ ላይ ብቻ መመስረት አይገባም፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ በአገራት መካከል በሚደረገው የንግድ ልውውጥ ውይይት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው በመጥቀስ የዶክተር አጥናፉን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡
በዚህም የተሻለ መስራት እንደሚያስችል ይጠቁማሉ፡፡ ፕሬዚዳንቷም በኢትዮጵያ ይህ አይነቱ አሰራር ብዙም እንዳልተለመደ በመጥቀስ፣ በዚህ በኩል የአሜሪካና የአውሮፓ ነጋዴዎች ከቻይና ጋር ፊት ለፊት የሚያደርጉት ውይይት በአብነት እንደሚነሳ ይናገራሉ፡፡ እንደ ወይዘሮ መሰንበት ገለጻ፤ ከተለያዩ አገሮች ጋር የንግድና ኢንቨስትመንት ልውውጥ ማድረግ ብዙ ጥቅም አለው፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው ፋይዳው የእውቀት ሽግግር ነው፡፡
የእውቀት ሽግግሩ ግን የአንድን አገር እውቀት ብቻ ለልጆቻችን ማስተላለፍ እምብዛም ተገቢ አለመሆኑን መረዳት እንደሚያስፈልግ ፕሬዚዳንቷ ያስገነዝባሉ ‹‹የተለያየ አይነት እውቀት ከተለያዩ አገራት ማግኘት ወሳኝ ነው፡፡ ሌሎች አገሮችስ የሚሰሩት ምን ይመስላል የሚለውንም ማስተዋል እንዲሁም ከጥራት አኳያስ እንዴት ነው የሚለውን ሁሉ ማወቅ ይገባል ባይ ነኝ።›› ይላሉ። እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለጻ፤ መማር የሚቻለው ከተለያዩ አገሮች ጋር የልምድ ልውውጥ ሲኖር ነው፡፡ ውድድሩስ ምን ይመስላል? በንግድ በኩል ጥሩ ባህል ያለው የቱ ነው? የሚለው ሁሉ ሊታይ ይገባል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ‹‹የእኛ የንግድ ማህበረሰብ አሁን የሚያስፈልገው የፖሊሲ ለውጥ ነው፡፡›› ይላሉ። አንዳንዴ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ በመጥቀስም፣ ለእዚህም ኢትዮጵያ ወደ ቻይና ብቻ ምርቶችን የምትልክበትን መንገድም ክፍተት አለው ማለት እንደሚያስደፍር ይናገራሉ፡፡ ‹‹የሚደረገው ነገር ሁሉ ሊበራል አይደለም፡፡ በዚህ መንገድ ሲሆን እኛ የምናውቀው አንድ አይነት አሰራር ይሆናል፡፡ እሱም የቻይና ባህል ነው፡፡›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ መሰንበት ከእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር አንጻርም ክፍተት እንዳለ ይጠቅሳሉ፡፡ ይህንንም ሲያስረዱ በቻይና ኩባንያዎች የስራ እድል ተፈጥሮላቸው ሰራተኞች ቻይናውያን እውቀታቸውንና ቴክኖሎጂውን ለማስተላለፍ ፍላጎቱ እንደሌላቸው የሚያነሱትን ቅሬታ ይጠቅሳሉ፡፡
ኮንትራት ሲፈረም ‹‹የእውቀት ሽግግር እናደርጋለን›› ያለው ወረቀት ላይ ብቻ ነው የሚሉት ወይዘሮ መሰንበት፣ የማሸጋጋሩ ሁኔታ እምብዛም እንደማይታይ ይጠቁማሉ፤ ይህንንም ከጉዳዩ ጋር ቅርብ ግንኙነት ካለውና ማረጋገጫ ከሚሰጠው በስራው ላይ ከተሰማራው ኢትዮጵያዊው ወጣት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ወጣቱ የእውቀት ሽግግር ላይ እንዳልነበር እንደሚናገርም ነው የሚገልጹት፡፡ ዶክተር አጥናፉም የወይዘሮ መሰንበትን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡
ቻይናውያኑ ኢትዮጵያውያን ሙያውን እንዲያውቁት ብዙም ፍላጎቱ እንደሌላቸው ይናገራሉ። የቻይናውያኑ ስጋት እውቀቱን ካሸጋገሩ ኢትዮጵያኑ ያድጋሉ፤ ይህም ቻይናውያኑ ኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ የማይቆዩበትን ሁኔታ ይፈጥራል የሚል ስጋት ያድርባቸዋል የሚሉት ዶክተር አጥናፉ፣ ይህ እንዳይሆን በሚልም ቻይናውያኑ ድብቅ የሆነ የስራ ባህል እንደሚከተሉ ነው የሚናገሩት፡፡
ወይዘሮ መሰንበት እንደሚሉት፤ በንግድና ኢንቨስትመንት በኩል የሚደረግ ግንኙነት በአንድ አገር ላይ ብቻ መወሰን የለበትም፡፡ ሌሎች አገራትም በግንኙነቱ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱ ሰፋ ሲል ውድድሩም የዚያኑ ያህል ከፍ ይላል፡፡ ሌላው ዓለም የት እንደደረሰ ማወቅም ተገቢ ነው፡፡ በዚህ መንገድ መሄድ ከተቻለ ግንኙነቱ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የራሱን ገንቢ ሚና እንዲጫወት ማድረግ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2011
አስቴር ኤልያስ