ተረከ ዘመን፤
ትናንት የዛሬ መደላድል ነው። ዛሬ ትናንትን ደርቦ የነገ መሠረት ነው። ከሦስቱ የዘመን ምዕራፎች አንዱ ጎዶሎ ከሆነ ዛሬም ሆነ ነገ አንካሳ መሆናቸው የማይቀር ነው። የአንካሳነታቸው መገለጫ ዝርዝሩ ብዙ ነው። ቢያሻ ከፖለቲካ፣ ቢያሻ ከኢኮኖሚ፣ ከባህል፣ ወይንም ከዘርፈ ብዙው ማኅበራዊ ተራክቦ አንጻር የዘመናቱን ጥልፍልፍነት እንተርክ ብንል ብዙ ያጽፈናል። ትውልድ እንደየክፍለ ዘመን ድርሻው የሚጠናውና የሚመረመረው በዚሁ ጥልፍልፍ የጊዜ ቀመርና ስሌት መሠረት ነው።
ትናንትን የካደ የዛሬ ዘመንኛ «ትውልድ» እንደ ወፍ ዘራሽ ወይንም «ወላጅ አልባ» እንደሆነ የሙት ልጅ አስተዳደጉ ያለ ምክር፣ ሕይወቱም ታሪክ አልቦ መሆኑ አይቀርም። ዛሬን ከትናንት የሚያፋታ፣ ነገንም ከዛሬ የሚያኳርፍ ትውልድም ሆነ ሥርዓተ መንግሥት እንዲሁ መሠረቱ ያልጠበቀና በድቡሽት ላይ እንደተሠራ ቤት ጥንካሬም ሆነ ዕድሜው ላይረዝም ይችላል። ለምን? ቢሉ ፈታኙን ጊዜ ወለድ ጎርፍ ለመቋቋም የሚሞክረው በራሱ ልምድና ተሞክሮ እንጂ የኋላውን «ምን ነበር? እንዴትስ ፈተናዎች ታለፉ?» ብሎ ስለማይፈትሽና ስለማይበረብር መለኪያውና መመዘኛው ራሱ ብቻ ይሆናል። ራሱን በራሱ ምሉእ በኩለሄ የሚያደርግ መሪነትም ሆነ ተመሪነት ትናንትን እንደማያይ አንድ ዐይናማ ወይንም ሸውራራ ሊቆጠር ይችላል።
በዛሬው ውስጥ የትናንት ታሪክ በትምህርት ሰጪነቱ ካልታወሰ፤ ለነገ የሚሆን ስንቅም ዛሬ ላይ ካልተሰነቀ የአገር ሕይወት «ጣእም አልባ አልጫ» ከመሆንም አያመልጥም። የሦስቱ የዘመን መልኮችና ተደጋጋፊነታቸው ብዙ ስለሚያጽፍና ስለሚያወያይ የዚህን ጽሑፍ ወሰን ገድቦ መነሳት ግድ ይላል። በዚህ ወሳኝ መርህ መሠረትም ይህ ጽሑፍ ትኩረት ለማድረግ የሞከረው የአገራችን መሪዎች «በራሳቸው ብእር ጻፍን» በሚሉት ወይንም ያጻፏቸውን መጻሕፍት በመጠቃቀስ የዜና መዋዕላቸው ፋይዳ በማመላከት ይሆናል።
ዜና መዋዕል ለምን?
የትናንት አገራዊ ውሎና አምሽቶ ለተከታታይ ትውልዶች ከሚተላለፍባቸው መንገዶች አንዱ፤ ምናልባትም ረጂም ዘመን በማስቆጠሩ በአንቱታ እንደተከበረ ያለው፤ በጽሑፍ የሚተላለፍ ታሪክ ነው። እርግጥ ነው ፎቶግራፎች፣ ሐውልቶች፣ እንዲያው በጥቅሉ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ እየተባሉ በፈርጅ በፈርጃቸው የሚዘከሩት የአገር ቅርሶች የትናንትን መልክ ለማሳየት አስተዋጽዋቸው ቀላል የሚባል አይደለም። እንዲያም ቢሆን ግን ሌሎች ቅርሶች ታሪካቸው ለትውልድ የሚተላለፈው ዞሮ ዞሮ በጽሑፍ ስለሆነ ለመጽሐፍ የሚገባው ተገቢ «ከበሬታ» አይጓደልበትም።
በተለይም «የወር ተረኝነቱ ዕጣ ወድቆባቸው» ለመንበረ ሥልጣን ወግ የበቁና በተለያዩ የእርከን ደረጃዎች ላይ የሚገኙ መሪዎች «የትናንትን ሥዕል» ጥርት አድርገው እንዲያዩና የነበር ታሪኩን ውጣ ውረድ በሚገባ ተገንዝበው የዛሬውን የአመራር ጥበባቸውን ወይንም ክሽፈታቸውን በትናንቱ የታሪካችን ወንጠፍት እስካላበጠሩ ድረስ ከእውቀት ሊጎሉ መቻላቸውን ሊያምኑ ይገባል።
መሪዎች ተብለው የተገለጹት ከላይ ከቁንጮዎቹ ጀምሮ በዋና ዋና መሠረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በፖለቲካም ሆነ በመንግሥታዊ ሹመት «ክህነተ ሥልጣን» ተጎናጽፈው በሕዝብ ሕይወትና በአገር አስተዳደር ላይ እንዲወስኑ «በትረ ሙሴን» የጨበጡትን ለማመልከት ነው። ይህም ሲባል በጽሑፍ እየተላለፈ ለትውልድ የሚደርሰው የመሪዎች ዜና መዋዕል የትናንቱን ውሎና አዳር እና የሥርዓተ መንግሥታቸውን ጉዞ ከሀ-ፐ ጠቅልሎ ይወክላል ማለት አለመሆኑም ሊሰመርበትም ይገባል።
ከቅቡልነትና ከተዓማኒነት አንጻርም ቢሆን «የራስ ውሎና የራስ ዘመን» ሲተረክ ከአድልዎና ከውስንነት ሙሉ ለሙሉ ነፃ ነው ተብሎም አይታመንም። እንዲህም ቢሆን ግን «በቃል ያለ ይረሳል፤ በጽሑፍ ያለ ይወረሳል» እንዲል ብሂላችን፤ የቀዳሚዎቹን የሥርዓተ መንግሥታት መሪዎች ግለ ታሪክና ግለ ወግ ለተከታታይ ትውልዶች በጽሑፍ ማስተላለፉ ከጉዳቱ ይልቅ ጠቀሜታው ላቅ ያለ እንደሚሆን አይካድም።
በተለየ ሁኔታ ግን ዕድልና ጊዜ ተገጣጥሞላቸው አገርን ለማስተዳደርና ሕዝብን ለመምራት አደራው በጫንቃቸው ላይ ለሚወድቅባቸው ለዛሬዎቹና ለነገዎቹ መሪዎች የቀደምት መሪዎችን ዜና መዋዕል አክብሮት ሰጥቶ ማንበቡ ፋይዳው በቀላሉ የሚታይ እንደማይሆን ለመገመት አይከብድም።
የትናንቶቹን የጥንካሬ ፈለግ ለመከተልና ከድክመታቸው ለመማርም በጽሑፍ የሚተላለፍ የቀዳሚ መሪዎች ዜና መዋዕል ለዛሬዎቹ የሥልጣን ወንበረተኞች ትሩፋቱ ከመደበኛ ትምህርት የማይተናነስ እውቀትና ተሞክሮ ሊለግስ እንደሚችል በብዙ ይታመናል። ስለዚህም በስሱም ቢሆን ኢትዮጵያ «ዘመናዊነትን» መተዋወቅ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ አገር ለመምራት የቻሉትን ጥቂቶች ብቻ ለመዘከር መነሻችንን የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን በማድረግ ቅኝታችንን እንጀምራለን።
ለአገር ልጆች በቋንቋቸው፤ ለባእዳኑም በልሳናቸው፤
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ታሪካቸውን ያጻፉት በጸሓፌ ትእዛዛቸው በገብረ ሥላሴ አማካይነት ነበር። እኒህ ብርቱ የዜና መዋዕል ጸሐፊ የንጉሠ ነገሥቱ የቅርብ ሰውም ነበሩ። የተመጠነው ታሪካቸው እንዲህ ይነበባል።
«አለቃ ገብረ ሥላሴ በ1858 ዓ.ም ለወ/ሮ ባፈና ጸሐፊ ሆነው በሎሌነት አደሩ። ቀጥሎም በ1864 ዓ.ም የንጉሥ ምኒልክ ጸሓፌ ትእዛዝ ሆኑ። ጥር 18 ቀን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚኒስትሮች ሹመት ሲቋቋም የጽሕፈት ሚኒስትር ተባሉ። …በጸሓፌ ትእዛዝነት 40 ዓመታት ከኖሩ በኋላ ጥቅምት 27 ቀን 1905 ዓ.ም ሞተው እንጦጦ ራጉኤል ተቀበሩ።»
እኒህ ጎምቱ ባለውለታ በብራና ያዘጋጁት ጽሑፍ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ ሙሴ ደኮፔ የተባለ ፈረንሳዊ ኢትዮጵያዊውን አባ ተስፋ ሥላሴን በተርጓሚነት በመምረጥ «ታሪከ ዘመን ዘ ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ» በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ይህ ግለ ታሪክ በ1922 ዓ.ም በሁለት ቅጾች ፓሪስ ላይ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ታትሞ ተሰራጭቷል።
በ78 ምዕራፎች ተከፋፍሎ የቀረበው ይህ የታሪክ መጽሐፍ እጅግ በርካታ የሆኑ ታሪካዊ እውታዎችን አካቶ የያዘ ሲሆን አተራረኩም እጅግ ማራኪና ጣፋጭ ነው። አፋዊ ትርክትን እንደ መነሻ አድርጎ ቢንደረደርም እስከ ዘመነ ኢያሱ ያለው የፖለቲካ ሽቅብ ቁልቁል ጉዞ በአግባቡ ስለተሰነደ ጠቀሜታው እጅግ የላቀ ነው።
በተለይም አገሪቱ ያለፈችበት ውስጣዊ የፖለቲካ ሽኩቻና የውጭ ጠላቶች ሴራና ትንኮሳ በሚገባ ተተንትኖ ስለቀረበ የዛሬዎቹ መሪዎች ልብ ተቀልብ ሆነው ቢያነቡት ራሳቸውን ለመገምገም በእጅጉ ይጠቀሙበታል። ያልኖሩበትን ዘመን ለመተቸት ብራቸውን፣ ምላሳቸውንና ጣታቸውን የሚቀስሩ «ሳይሞቅ ፈላ» የዘመናችን ባለጊዜዎችም ይህን ቀደምት ሥርዓት ከሚፈረጁበት ጭፍን አመለካከት እንዲረጋጉ ሊያግዛቸው ይችል ይሆናል።
«ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ»፤
ሁለተኛው አብነታችን ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ናቸው። ቀኃሥ የግለ ታሪክ መጻሕፋቸውን ያቀረቡት «እኔ» በሚል የአንደኛ መደብ የትረካ ስልት ሆኖ በሁለት ቅጾች በማካተት ነው። የመጀመሪያው ቅጽ የሚሸፍነው ከንጉሡ የሕፃንነት ታሪክ ጀምሮ በስደት ወደ ሎንዶን እስካቀኑበት ድረስ ያለውን ጊዜ ሲሆን የታተመውም በ1929 ዓ.ም ነው።
በ1934 ዓ.ም ታትሞ ለንባብ የበቃው ሁለተኛው ቅጽ ደግሞ የፋሽስት ወረራን አስመልክቶ በሊግ ኦፍ ኔሽን ጉባኤ ላይ (ጄኔቫ) በኢትዮጵያ የልዑካን ቡድንና በእብሪተኞቹ ፋሽስቶችና በፋሽስቶቹ ወዳጅ አገራት መካከል የተፈጸመውን የተጧጧፈ ዲፕሎማሲ ጦርነት እንደ ሥዕል ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። እነዚህ ሁለት ቅጽ መጻሕፍት የወቅቷን ኢትዮጵያ «ማዲያት የለበሰ» መልክና ከውድቀቷ ለመነሳት ወፌ ቆመች እያለች የተውተረተረችበትን ጉዞ የሚያሳይ ስለሆነ ጠቃሚነቱ እጅግ የከበረ ነው። ንጉሡ መጻሕፍቱን ያጻፉት እነ እከሌን ነው፣ ይዘቱም የንጉሡን ሰብእና ለማድመቅ ነው ወዘተ. የሚለው መከራከሪያ ለጊዜው በዚህ ጽሑፍ ቦታ አልተሰጠውም።
በተለየ ሁኔታ ቴክኖሎጂው ሙሉ ለሙሉ አስገብሯቸው የፌስ ቡክ ሱሰኛ ለሆኑትና የአመራር ስልታቸውን «በምን ተባልን» ሀሜታና ቱማታ ለመምራት ለሚመርጡ ዘመንኞቹ «ባለስልጣኖቻችን» የፈተናን ውጣ ውረድ ተቋቁሞ ለማለፍ የሚያስከፍውን ዋጋና የመሪነትን ልበ ሰፊነት ለመረዳት መጻሕፍቱ በጥሞና ቢነበቡ ብዙ ትርፍ ይገኝባቸዋል። «ከታሪክ መሰዊያ ላይ አመዱን ሳይሆን እሳቱን ጫሩ» የሚለው ብሂል ግን ለየትኞቹም ዘመናት የታሪክ መጻሕፍት ንባብ እንደ ዋነኛ መርህ መታየት እንዳለበት ሊዘነጋ አይገባም።
«ትግላችን» – በደም የቀለመው የኢትዮጵያ አብዮት ታሪክ፤
የንጉሡን መንበረ ሥልጣን ገልብጦ «ዙፋኑን የወረሰው» የወታደራዊው ደርግ ቁንጮ መሪ ኮሎኔል መንግሥት ኃይለማርያምም እንዲሁ እንደ ቀዳሚዎቹ መሪዎች ግለ ታሪካቸውን የጻፉት «ትግላችን» በሚል ርዕስ በሁለት ቅጾች በመሰነድ ነው። ቅጽ አንድ 2006 ዓ.ም ታትሞ ለስርጭ ቢበቃም «ከታሪክ የማይማሩ፣ ጊዜና ዕድሜ የማይለውጣቸው የጥፋት መልእክተኞቹ [እነ እከሌ] ቅጽ አንድ የመጀመሪያ ህትመት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተሰራጭቶ እንዳይነበብ በፈጸሙት አሳዛኝና አሳፋሪ ሻጥር ምክንያት ከመጀመሪያው ህትመት አንድ አራተኛው እንኳን ለአንባቢ አልደረሰም» የሚለው የግለ ታሪክ መጻሕፍቱ ደራሲ የኮሎኔሉ ምክንያት በ2008 ዓ.ም በታተመው በሁለተኛው ቅጽ ላይ ሰፍሮ ይነበባል።
ዞሮ ዞሮ ግን በውጭ አገራትም ሆነ በአገር ውስጥ የተሰራጩት መጻሕፍት ቁጥር በርከት ስለሚል በአመራር ላይ ባሉት መሪዎች ተፈልጎ ቢነበብ የትናንቱን የኢትዮጵያ ሥዕል እንዲያዩ በሚገባ ይጠቅማቸዋል። ዛሬም ድረስ እያመረቀዘ የሚጠዘጥዝን የጦርነት «ክፉ ደዌ» እንደምን ተጸንሶ ተወልዶና ጎልምሶ ሥር እንደሰደደም በጥሩ ሁኔታ ተብራርቶ ስለቀረበ እየተንገዋለለ ቢነበብ በእጅጉ ይጠቅማል። የዘመነ ደርግ ዋና ዋና ባለስልጣኖችና የጦር መሪዎች ግለ ታሪካቸውን በመጻፉ ረገድ ግን እንደምን ብርቱዎች እንደሆኑ ወደፊት በስፋት ተንትነን ለማቅረብ እንሞክራልን።
በውሱን መጻሕፍት ዜና መዋዕላቸው የተጻፈላቸው የዘመነ ኢህአዴግ መሪዎች «እንደ መላእክት እንዲመለኩ፣ እንደ ጀግና እንዲወደሱ» ታቅዶ ስለሆነ እንዲህና እንዲያ ነው ብሎ ለመተንተን ሞራልን ይፈታተናል። ለእነርሱ «አብዮታዊ ዲሞክራሲ» ከምድር በላይ፤ ከሰማይ በታች ብቸኛው የኢትዮጵያ መፍትሔ ተደርጎ ስለቀረበ «ስድባቸውን ደግሞ መሳደብ» እንኳን ለሌሎች ለራስም አይጠቅምም። አንብቦ ስህተቱን መረዳት በራሱ ጠቃሚ አይደለም ወይ? ለሚለው የመሟገቻ ክርክር መድረኩን የምንከፍተው «እዬዬ ሲዳላ» ስለሆነ እስከዚያው መታገሱ ይበጃል።
ዘመነ ብልጽግና አልሰከነም። በዋናው የፖለቲካ ቁንጮ የተጻፉት መጻሕፍትም ቢሆኑ ከግለ ታሪክና ከውጣ ውረድ ተራኪ ዜና መዋዕል ይልቅ በሥርዓቱ አካሄድ ንድፍ ላይ ያተኮሩ ስለሆነ እጅግም ጫን ብለን አንፈትሻቸውም። ጊዜውም አያበረታታንም። ፖለቲካው ሰክኖ፣ አቅጣጫው ጥርት ባለ ብእር መሰነድ ሲጀምር ያኔ የምንለውን ስለምንል ጉዳዩን በይደር እናስተላልፋለን።
ቀደምት የዜና መዋዕል ተራኪ መጻሕፍት መነበብ ለምን እንደሚገባቸው ምክንያቶቹን ነካካን እንጂ ጫን ብለን አልጨመቅነውም። በአጭሩ የትናንትን መልክ እንደመስታወት ስለሚያሳዩ ብቻ ሳይሆን ዛሬንም ስለሚሞግቱ መነበባቸው ውዴታ ሳይሆን ግድም ነው። ወደፊት መንደርደሪያውን በዝርዝር ትንተና እንደምንመለስበት ቃል በመስጠት የዛሬውን የወፍ በረር ቅኝት በዚሁ እናጠናቅ። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 /2014