የዛሬው የዘመን እንግዳችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኙ ከመጡ ሙሺዳዎች አንዱ የሆነ ወጣት ነው። ተወልዶ ያደገው በወሎዋ መናገሻ ደሴ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ዳውዶ በተባለ ትምህርት ቤት የተማረ ሲሆን፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ መምህር አካለወልድ ትምህርት ቤት ነው የተከታተለው። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቶም በሶሾሎጂና አንትሮፖሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። በተማረበት የሙያ መስክ የተለያዩ ተቋማት እየተዘዋወረ የሠራ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ልማትና እርዳታ ማህበር ተጠቃሽ ነው። በዚህ ማህበር ውስጥ ለአምስት አመታት በቆየባቸው ጊዜያት ውስጥም በርካታ ሙስሊሞች በሚገኙባቸው በርሃማ አካባቢዎች ድሆችን በመርዳትና በመደገፍ አወንታዊ ሚና ተጫውቷል። በተጨማሪም በኢትዮጵያ የዓለምአቀፉ ቀይመስቀል ማህበር ውስጥ ምዕራብ ወሎ መካነ-ሰላም በሚገኘው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፕሮጀክት ኃላፊ በመሆን ለሦስት ዓመታት ሠርቷል።
በአሁኑ ወቅት በግል ሥራ የሚተዳደረው እንግዳችን ከዚሁ ጎን ለጎን እስላማዊ የሆኑ ዜማዎችን (ነሺዳዎችን) በማዜም ከፍተኛ እውቅና እያገኙ ካሉ ወጣት ሙሺዳዎች መካከል አንዱ ሆኗል። የተለያዩ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን፤ መቻቻልን፤ ሰላምና የአገር ፍቅርን የሚያነሱ ከ40 በላይ ነሺዳዎችን ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ አበርክቷል። ከተለያዩ ሙሺዳዎች ጋር በመጣመርም ስለአገር፤ ስለሰላምና እርቅ የሚያወሱ ኅብረ-ዝማሬዎችን በማበርከት የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። አዲስ ዘመን ጋዜጣም ዘንድሮ ለ1ሺ443ኛ ጊዜ የሚከበረውን የኢድ-አልፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ ሙሺድ አስማማው አህመድን የዘመን እንግዳ አድርጎ ይዞ ቀርቧል።
አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ ወደ ነሺዳ አገልግሎት የገባህበትን አጋጣሚ አስታውሰንና ውይይታችንን እንጀምር?
ሙሺድ አስማማው፡- ደሴ የኢትዮጵያ ሙስሊም ሊቃውንት መፍለቂያ ናት። ጠንካራ የሆነ ማኅበረሳባዊ ትስስር ባለው ሕዝብ መካከል ነው ያደኩት። እምነትና ቋንቋ ሳይለይ ሁሉም በፍቅር የሚኖሩባት ከተማ ናት። ስለዚህ እንደማንኛውም ሙስሊም ማኅበረሰብ ቁርዓን መድረሳዎች ውስጥ እየቀራሁ ነው ያደኩት። በነገራችን ላይ ወደዚህ ሙያ ከመግባቴ በፊት ተማሪ ሳለሁ ወጣት አማተር ክበባት ውስጥ እሳተፍ ነበር። እንዳልኩሽ የደሴ ማኅበረሰብ በሁሉ ነገር የተጋመደና ያለልዩነት በፍቅር የሚኖር ሕዝብ ነው። ብዙዎቻችን የእምነት ልዩነታችን ትዝ የሚለን ለበዓል ቀን ብቻ ነው። በቤተሰብ ደረጃ የምናገኘው ሃይማኖታዊ እውቀቶች ቢኖሩንም እንዲህ እንደአሁኑ በጥልቀት የእምነቱን አስተምሮች አልተገነዘብንም ነበር። እኔ በተለይ በምሳተፍባቸው የአማተር ክበቦች ውስጥ ሙዚቃ የመሞከር ዕድል ነበረኝ። ዩኒቨርሲቲ እስከምገባ ድረስ አቢሲኒያ የስነ ተዋልዶ ክበብ፤ ጥበብ አምባ በተባሉ ክበቦች ውስጥ ሙዚቃ እሠራ ነበር። ያም ልምዴ ደግሞ ከመሠረታዊው የእምነት እውቀት ጋር ተዳምሮ ከዩኒቨርሲቲ ከወጣሁ በኋላ ወደ ሃይማኖታዊ ዜማዎች እያደላሁ መጣሁ።
በተለይም በርሃ አካባቢ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጋር በምሠራበት ወቅት ራስን የማዳመጥ ሰፊ ዕድል አግኝቼ ነበር። ግጥሞች መፃፍ እና ብስለት ያላቸውን ዜማዎችን ወደ መሥራት መጣሁኝ። እስከቅርብ ጊዜ የወጡ ሥራዎቼ ያኔ የተፃፉ ዜማዎች ናቸው። በትክክል ወደዚህ ሙያ በቀጥታ የገባሁበትን ቀን ባላስታውሰውም የመጀመሪያ አልበሜን የሠራሁት በ2009 ነው። በወቅቱ በአጋጣሚ አዲስ አበባ መጥቼ ነበርና እዚህ በግላቸው የሚሠሩና ስቱዲዮ ያቋቋሙ ጓደኞቼን ለመጠየቅ ስመጣ ለምን አትሞክርም የሚል ሃሳብ መጣና ክፍቶችን መሙላት ከቻልኩኝ ብዬ የጀመርኩት ነው።
ከሁሉ በላይ ግን ወደዚህ የአገልግሎት ዘርፍ እንድገባ ምክንያት የሆነኝና እንደአርዓያ የማየው መሃመድ አወል ሳላህን ነው። አላህ ይዘንለትና ለእኔ በጣም ቅርቤ የምለው ሰው ነበር። ተቀጥሬ በምሠራበት ጊዜ የሱን ሥራዎች ነበር የምሰማው። ብዙዎቻችንን ለአገራችን ነሺዳ መስፋፋት ፈርቀዳጅ የምንለው እሱን ነው። እንዳልኩሽ ደግሞ ወደ ነሺዳው እኔም ከገባሁ በኋላ ግን ከእኔ በጣም ተቀራርበን ነበር። እንደአባትና ልጅ ነበር የምንግባባው። እንግዲህ አላህ የፈቀደው ጊዜ ደርሶ ወስዶታል። በተመሳሳይ በመንዙማው ዘርፍ ደግሞ መሃመድ አወል ሃምዛ የሚባሉ ሰው ጥልቅ መልዕክቶችን የያዙ መንዙማዎቻቸውን እየሰማን ነው ያደግነው። አሁንም በሕይወት አሉ፤ አላህ ሃያታቸውን ያርዝምላቸው።
አዲስ ዘመን፡- እስካሁን ምንያህል የነሺዳ አልበሞችን ሠርተሃል?
ሙሺድ አስማማው፡- በነገራችን ላይ ነሺዳ የዳዕዋ (የትምህርት) ዘርፍ ነው። በዜማ አማካኝነት ነብያዊ ትፊውቶችን፣ የአላህን ቃል ለማኅበረሰቡ ማድረሻ መንገድ ነው። ስለዚህ እኔም በሆነ መንገድ ጉልበት ልሆን እችላለሁ ብዬ የሞርኩት ነው። በአልበም ደረጃ እስካሁን አንድ አልበም ብቻ ያወጣሁ ቢሆንም ከ40 በላይ ነሺዳዎችን ለሙስሊም ማኅበረሰብ ማድረስ ችያለሁ። ምክንያቱም ነሺዳ ገንዘብ ለማግኘት ታስቦ የሚሠራ ሳይሆን እምነቱን ለመደገፍ የሚከወን አንድ የአገልግሎት ዘርፍ ነው። ስለዚህ አልበም እያወጣን አንሸጥም። የመጀመሪያ አልበሜ ላይ ስድስት ነሺዳዎች ናቸው ያሉት፤ ከዚያ በኋላ ግን በነጠላ መልኩ በርካታ ሥራዎችን አበርክቻለሁ። እኔ በይበልጥ የምታወቀው ‹‹የምርኩዝ መድረክ›› በሚል ሜምበር መልቲ ሚድያ በየወሩ በሚያዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ ነው። በዚያ መድረክ ላይ በየወሩ ነሺዳ አቀርባለሁ፤ የተለያዩ እስላማዊ ክንውኖችና በዓላት፤ የይፍጠር ዝግጅቶች ላይ አዳዲስ ሥራዎችን ይዤ እቀርባለሁ። ከዚህም ባሻገር ዳዕዋ ወይም ትምህርት በሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ሁሉ እየገባን ትምህርቶችን በነሺዳ አማካኝነት እናቀርባለን። ይህንን ደግሞ የምናደርገው በዋናነት የእምነቱ ትልልቅ አባቶች የሚነግሩን ክፍቶች እየለየን በዚያ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ሥራዎችን ይዘን ነው የምንቀርበው።
አዲስ ዘመን፡- በነሺዳና በመንዙማ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?
ሙሺድ አስማማው፡– መንዙማ እንደሚታወቀው አገራዊ ትውፊት ነው። እስልምና ወደ አገራችን ከገባ ጊዜ ጀምሮ በየእውቀት ቦታዎች ላይ ነብያዊ የሆኑ ትምህርቶችን፣ የአላህን ቃል ጥሩ በሆነ ለዛ ለተተኪው ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ ነው። በተለይም ገጠር አካባቢ ጥልቅ በሆኑ ሃሊሞች የሚመራ፤ ጥልቅ የሆኑ የእምነት መርሆችና አስተምህሮችን የያዘ፤ የፈጣሪ ሃሳብ የሚተላለፉበት ነው። ነሺዳ ደግሞ የመንዙማ አንዱ ዘርፍ ነው። እኔ አሁን መንዙማ ወይም እንጉርጎሮ እሠራለሁ። ነሺዳ በመድረሳ ደረጃ የሚቀርቡና በጣም ቀለል ያሉ ሃሳቦች የሚተላለፉበት ነው። ከቃል ምጥቀት ይልቅ ቀለል ያሉ ሃሳቦች የሚያስተላልፍ ነው። የተማረውም ሆነ ያልተማረው የኅብረተሰብ ክፍል ሊሰማው የሚችል ቀለል ባለ አቀራረብ የሚዘጋጅ ነው።
የነሺዳ አመጣጥ ከውጭ ቢሆንም እንኳን አገራዊ ዘይቤና ውበት ተጨምሮበት ነው እየሠራን ያለነው። ቀለል ብሎ የሚቀርብ ቢሆንም የኪነጥበባዊ ይዘቱ በጣም ከፍ ያለ ነው። ስቱዲዮ ውስጥ ተገብቶ ሙዚቃዊ ቅኝት በደንብ ተቃኝቶ፤ ዜማዎች ተቀምብበው፤ ተለክቶ የሚቀርብ ነው። መንዙማ ሲሆን ግን የሃሊሞቻችን ወይም በጣም ጥልቅ የሆኑ አማኞች የሚፅፏቸው የእምነትም፤ የሃሳብም ጥልቀት ያላቸው ናቸው። ዜማቸውም እንደየመንዙማው ይለያያል። መንዙማ አንዳልኩሽ ከቦታ ቦታ በጽሑፍም ሆነ በዜማ ይዘቱ ይለያያል። ይህንን የሚያውቁት ግን በእምነቱ ጥልቅ እውቀት ያላቸው ሰዎች ናቸው። ነሺዳ ግን ሲሆን ሁሉም ሰው እንዲሰማው ተደርጎ የሚቀርብ ሲሆን ግን ደግሞ አገራዊ ትውፊቶች ገብተውበት ነው የሚዘጋጀው። በቅርቡ ደግሞ ነሺዳን ከመንዙማ ጋር እያጣመሩ መሥራት ተጀምሯል። የሁለቱ ጥምረት ደግሞ ሌላ ቀለም እና ውበት እየሰጠው ነው። ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ የአገራችን ቋንቋዎች በርካታ ነሺዳዎች እየተሠሩ ነው ያሉት። ሕፃናትም እንዲሳተፉ እየተደረገም ነው ያለው። ይህም ሙያው የበለጠ እንዲያድግ እያደረገው ነው ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ከሃይማኖቱ ሥርዓት ውጪ ያፈነገጠ ነው በሚል ነሺዳን የሚቃወሙ የእምነቱ ተከታዮች አሉ፤ በዚህ ላይ ያለህ ሃሳብ ምንድን ነው?
ሙሺድ አስማማው፡- ትክክል ነሽ፤ እንዳልሽው ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ። በተለይ ደግሞ በእምነቱ ውስጥ እንዳለ አንድ አማኝ ሰው ነገሮች ከሃይማኖቱ አስተምህሮ ውጪ ሆነው ይበላሻሉ ብሎ የሚያስብ ሰው ነሺዳን ላይቀበለው ይችላል። እኔ በግሌም በተለይም አሁን አሁን እየመጡ ያሉ አካሄዶችን አልደግፋቸውም። መንዙማን ካየሽው በድምፅ ብቻ ወይም በእንጉርጉሮ የሚሠራ ነው። ወይም ደግሞ ድቤዎችን ተጠቅሞ የሚሠራ ነው። ይሄ ከበፊት ጀምሮ የመጣ ትውፊት ነው። ነፍስ ከፈጣሪ ጋር ተስማምታ፤ ውስጡ ረጥቦ፤ ማንነቱን እንዲያስተካክል የሚያግዝ ነው። ወደ ነሺዳውም ስንመጣ እንደዘፈን ወጣ ያላለ ግን ደግሞ ዜማ ያላቸው የሙዚቃ ኖታ የሚረግጡ ናቸው። ይሄ ልዩነት ከጥንት ጀምሮ ያለ ነው።
አንቺ ያነሳሽው ክርክር ሄዶ ሄዶ ይህንን አለመግባባት የሚፈቱት የእምነቱ አባቶች ናቸው። እርግጥ እነዚህ የእምነት አባቶች ቁጭ ብለው የሚፈቀደውንና የማይፈቀደውን ስላላስተማሩ ‹‹ትክክል ነው፣ አልያም ትክክል አይደለም›› መከራከር ከባድ ነው። እኔ በግሌ የምደግፈው ግን ሪትም ባይገባበት ጥሩ ነው ብዬ ነው። ምክንያቱም ዛሬ እኛ በሙዚቃ መሣሪያ አሽተን የምንለው ነገር ነገ ከነገ ወዲያ ፈሩን ስቶ ወደ ዓለማዊ ሙዚቃ ሊያመራ ይችላል። ስለዚህ ሽንቁሩን ባናሰፋው ጥሩ ነው የሚል የእኔ የግል እምነት አለኝ። ግን ደግሞ በጠቅላላው ነሺዳ ክልክል ነው ማለቴ አይደለም። እንደአንድ ተራ አማኝ የሚሰማኝ ይሄ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ግን ደግሞ አሁን ያለውን ወጣት መዋጀት እና መድረስ የሚቻለው እሱን በሚያማክሉና ሊወዳቸው በሚችላቸው መንገዶች በመሆኑ የድሮውን መስመር ብቻ መከተሉ ትውልዱንለማጣት ምክንያት አይሆንም ትላለህ?
ሙሺድ አስማማው፡- ትክክል ነሽ፤ ነሺዳ ወጣቱን በመድረስ ረገድ ትልቅ አብዮት የማምጣት አቅም አለው። አሁን አሁን እኮ ብዙ ወጣት ነሺዳ አዳማጭ ነው። የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ ወጣቶች ሳይቀሩ በስፋት እያዳመጡ ይገኛሉ። በግሌ ብዙ አስተያየቶች ናቸው የሚደርሱኝ። በቅርቡ እንዲያውም ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ተሠርተዋል። አሁን ነሺዳው ላይ በጣም እያገዘ ያለው ወጣት በጣም ፈጣን በሚባል የነሺዳውን ባህሪ እየለወጠው ነው። በዚያው ልክ ደግሞ የሰው ተቀባይት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ነው። ይሄ ተቀባይነት ጥሩ ነው፤ ወጣቱን ይዟል፤ በተለይ እስከዛሬ ተደራሽ ያልነበረው ወጣት ይዟል። የቅድሙን ሃሳብ የሚያመጡት ሰዎች እንደሚመስለኝ ነገ ከነገወዲያ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ከመስጋት ነው። መንፈሳዊነቱን ለቆ ወደ ዘፈን ሊጠጋ ይችላል የሚል ፍራቻ ስላላቸው ነው። መንፈሳዊ የልብ ቋንቋ መሆኑ ይቀርና የስጋ ሃሴት ማግኛ ይሆናል የሚል ነው። ወደዚያ ነገር እንዳይገባ ከመጀመሪያው እዚህ ጋር እንግታው ከሚል ነው እንጂ አሁን ያለበት አካሄድ ብዙ የሚያሰጋ አይደለም። ብዙ ዳኢዮች እንደሚስማሙት ነሺዳ አሁን ያለበት ደረጃ ጥሩ የሚባልና ብዙ የወጣቶችን ጥያቄ የመለሰ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የነሺዳ መስፋፋት የኪነ-ጥበብ ፍቅርና ተሰጥኦው ያላቸውን የሙስሊም ወጣቶችን ወደፊት እንዲመጡና ተሰጥቷቸውን እንዲያወጡ ምንያህል ጠቅሟል ብለህ ታምናለህ?
ሙሺድ አስማማው፡- አስቀድሜ እንደነገርኩሽ እኔ በግሌ አማተር ክበባት ውስጥ ሙዚቃ ስሠራ ነበር፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳለሁም ባህል ማዕከል ውስጥም በተለይ ረቡዕ ረቡዕ ይቀርብ በነበረው የግጥም ምሽት ላይ እሳተፍ ነበር። ያኔም ቢሆን ግን የእስልምና መሠረታዊ እውቀቱ ስለነበረኝ በጣም ጥግ የሄዱ ሥራዎችን አልሠራም። ሃይማኖቴ እንደሚፈቅደው በአገር ጉዳይ እና የሞራል ከፍታን በሚገልፁ ሥራዎች ላይ እሳተፋለሁ። ያም ያለኝን ተሰጥኦ እንዳወጣ አግዞኛል የሚል እምነት አለኝ። ይህም ማለት የግድ ሙስሊም ሲኮን የሆነ አጥር ላይ ታጥረሽ ቁጭ የምትዪበት አይደለም። እንደአንድ ሙስሊም ኢትዮጵያዊ የአገሬን ሰላም እፈልጋለሁ፤ ስለሰላሟ ፤ ስለተፈጥሯዋ፤ ስለአየሯ ፤ ስለሰው ቅንነት በጎነት በተገኘው አጋጣሚ መስበክ አለብኝ። እዚያው እምነት ላይ ብቻ ትኩረት ተደርጎ የሚሠራ አይደለም።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ እንደዚህ የኪነ-ጥበብ ፍቅር ያላቸውን ተሰጧቸውን የሚያሳዩበት በየከተማው ትልልቅ መድረኮች መዘጋጀቱ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል። ለምሳሌ እኔ ደሴ፤ ኮምቦልቻ፤ አዳማ፤ ሻሸመኔ አስተባብራለሁ። በየወሩ ፕሮግራሞች አሉ። እዚያ መድረክ ላይ አቅሙ ያላቸው ልጆች መድረክ እንዲያገኙ ይደረጋሉ። ለምሳሌ ሻሸመኔ ያለ በጣም ግጥም የሚፅፍ አልያ ነሺዳ የሚፅፍና ድምፁ ጥሩ የሆነ ልጅ እዚያው አገሩ ላይ በየወሩ በሚዘጋጅ መድረክ ላይ እንዲቀርብ ይደረጋል። እንዳልኩሽ እምነቱን ብቻ አይደለም የምናጠናክረው፤ በተለይ አሁን ያለንበት ወቅት በጣም ህብር የሚፈልግ ነው። አንድነትን እና ፍቅርን ይፈልጋል። በያለንበት ህብረትን የሚያጠናክር፣ አገር የሚያፀና፣ ጥላቻን ሳይሆን ፍቅርን የሚሰብኩ ነገሮች ላይ ትኩረት አድርገን እንዲሠራ ነው እየሞከረን ያለነው። ኪነ-ጥበባዊ ፋይዳውም በጣም ሰፊ ነው ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በነሺዳዎች አማኝነት ምንዓይነት መልዕክት ያላቸው ሃሳቦች ናቸው የሚተላለፉት። ለአብነት ያህል ጥቀስልን?
ሙሺድ አስማማው፡- እንዳልኩሽ በነሺዳዎቻችን በብዛት የሚተላለፉት መልዕክቶች አብሮነትና መቻቻል ላይ ያጠነጠኑ መልዕክቶች ናቸው። እነዚህ ሁለት ጉዳዮች በቅዱስ ቁርዓንም፤ በሐዲሱም ትልቅ ትኩረት ነው የተሰጣቸው። ከሰው ሁሉ ጋር በሰላምና በፍቅር መኖር እንደሚገባ የሚያስገነዝቡ በርካታ ነሺዳዎች ተሠርተዋል። ከሁሉ በላይ እስልምና ዘረኝነት ይጠየፋል፤ ያወግዛል። አንዱ ጎሳ ከሌላው የሚበልጥ ወይም የማያንስ መሆኑን፤ በማንነት መኩራራት ሃጥያት እንደሆነ የሚያነሱ ሃሳቦችንም እናስተላልፋለን። እኔ ከሦስት ዓመት በፊት
‹‹ያኔ በመጨረሻው ቀን ስንጠራ
መዝገቡ ሲከፈት ሁሉም በየተራ
በብሔር አትቆምም በቀለም በዘርህ
ሥራህን አሳምር ጀነት የሚያስገባህ››
የሚል ስንኝ ያለው ነሺዳ አውጥቼ ነበር። ይህም የእገሌ ዘር ስለሆንን ጀነት (ገነት) መግባት እንደማንችል ያስረዳል። ይህንንም አላህ በቁርዓኑ ነግሮናል። እርስበርስ እንድንከባበርም አስገንዝቦናል።
ከዚህም ባሻገር
‹‹ከመልካም ሥራ ወይስ ከዘርህ
አፈር ስትለብስ የሚከተልህ››
እያለ የሚቀጥል ስንኝ ያለው ሲሆን ይህም የየትኛው ጎሳ ወይም ብሔር አባል ብንሆን ይዘነው እንደማንሄድ፤ ሁሉም ነገር ተመላሽ እንደሆነና መልካም ሥራ ብቻ ነው የሚቀረው የሚል ሃሳብ ነው ያለው። በሌላ ፅንፍ ይህንን ሃሳብ የማይደግፉ ሊኖሩ ይችላሉ። ግን ደግሞ የአላህ ትዕዛዝና ቅዱስ ቁርዓን ላይ ያለ ነገርን ነው የምታስታውሺው።
በተመሳሳይ ከሌሎች ጋር በጋራ የሠራናቸው የኅብረት ሥራዎች አሉ። አንድነትን እና ፍቅርን የሚሰብኩ በርካታ ሥራዎችን ሰርቻለሁ። ከእነዚህም መካከል፡-
‹‹የበጎነት ፍትህ መፍቻ
የፍትህ ራስኮርቻ
እምዬ ውዷ የእኔ እናት
ኢትዮጵያ የእውነት ምድር ናት›› በሚል
የእውነት ምድር ተብላ በረሱል የተመረጠች እንደሆነች የሚያነሳ ስንኝ ያለው ነሺዳም ተጠቃሽ ነው። ይህም አገራችን ፍትህ የተሟላበት አገር በመሆኗ ‹‹ሂዱ ወደ ሃበሻ ምድር›› የተባለውን በንጉሥ ነጃሺ ጊዜ የነበረውን ታሪክ አንስቶ የሚተነትን ነው። በተመሳሳይም እዚሁ ነሺዳ ላይ
‹‹ጊዜ ይሄዳል፤ ጊዜ ይመጣል
የገላሽ አፈር በወርቅ ይሸጣል
ማጣት ጎርፍ ነው ይሄዳል አልፎ
ቀን የወጣ ዕለት ጓዙን ሸክፎ››
የሚልም ስንኝ አለው። ይህም አንዳንድ ጊዜ ችግርና መከራ ይኖራል፤ ግን ችግሩ ያልፋል ስለዚህ አንድ ላይ ፀንተን እንቁም የሚል ሃሳብ ያለው በቅርቡ አራት ሆነን የሠራነው ነሺዳ አለ። በዚህ መልኩ የተሠሩ ብዙ ነሺዳዎች አሉ። እንዳልኩሽ ኢስላም መሠረቱ ልብ ላይ ብቻ የሚቀር ሳይሆን ኩሉ ማንነት የያዘ ነው። ለብቻችን ፈጣሪን ማምለካችን ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት ጋር እንዴት መኖር እንዳለብን፤ በአገር ላይ ሊኖር ስለሚገባ አቋም ቁርዓንን መሠረት በማድረግ የምንሠራቸው ናቸው። በነገራችን ላይ ጀሃድ ከታወጀባቸው ጉዳዮች መካከል ሚስትና አገር ናቸው። አገርሽ ላይ ወራሪ እየመጣ ጥለሽ ብትሸሺ ተጠያቂ ነሽ። ለአገርሽ የምትከፍይው ደም ነገ ፈጣሪ የሚከፍልልሽ ደም ነው። ይህም ቁርዓን ለአገር ትልቅ ስፍራ እንደሰጠ ያመለክታል። ስለዚህ የእኛ ሚና ያንን በዜማ ማጉላት ነው። እምነት ሲባል የግል ብቻ አድርጎ የማሰብ ጉዳይ እንዳልሆነ በነሺዳዎቻችን እያነሳን እንቀጥላለን።
አዲስ ዘመን፡- ረመዳን ላይ የሚዜሙት ነሺዳዎች በሌሎች ጊዜያት ከሚዜሙት ነሺዳዎች የሚለያቸው ነገር ምንድን ነው?
ሙሺድ አስማማው፡- ረመዳን ላይ የሚዜሙ ነሺዳዎች ይለያሉ። ምክንያቱም ረመዳን የእዝነት፤ የዱአ (የፀሎት) ወር ነው ፤ አላህ ዱኣችንን፤ ለመቀበል ወደ መሬት ወርዶ የሚጠይቅበት ወር ነው። በዚህ ጊዜ የሚዜሙ ነሺዳዎች ይህንን የሚያስገነዝቡ ናቸው። እኔ እንኳን በብዛት እንጉርጉሮ ነው የምሠራው። በቅርቡ የሠራሁት ስለሞት የሚያነሳ ነው። አማኙ ወደ ቀልቡ ተመልሶ ዛሬ የመጨረሻ ቀኔ ነው ብሎ ራሱን መፈተሽ እንዳለበት የሚያስገነዝብ ነው። ሌላ ደግሞ አንድ ትልቅ ሼህ የሰጡኝ ግጥም አለ። ይህ ግጥም በዋናነት ሞት ለሁላችንም አይቀሬ በመሆኑ በዚህ አላህ በመረጠው ወር ራሳችንን ከክፉ ሥራ እንድንመልስ ይሰብካል። በተመሳሳይ ሌሎችም ምዕመኑን ለንስሃ የሚያግዙ ሥራዎች ይሠራሉ። ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ሃሳብ ያላቸው ነሺዳዎች በረመዳን ጊዜ ይዘወተራሉ።
በነገራችን ላይ ነሺዳ በዓልን በማድመቅና ትልልቅ የድአዋ እንቅስቃሴዎች ላይ ወሳኝ ሚና ነው የሚጫወተው። አንድ ሰባኪ (ዳኢ) ሦስት ሰዓት የሚወራውን ሙሺዱ በነሺዳው በሦስት ደቂቃ ብቻ በኪነ-ጥበባዊ ለዛ እያዋዛ ለምዕመኑ ማድረስ ይችላል። በዚህም ምዕመኑን መማረክ ይቻላል። ምክንያቱም ኪነ-ጥበባዊ ይዘት ስላለው የሁሉንም ጆሮ ይወስዳል። በአጠቃላይ ግን ነሺዳ መልዕክትን ከማስተላለፍ አኳያ ፋይዳው የጎላ ነው። አሁን ላይ ዩቲብ ላይ ካየሽ በአንድ ወር ውስጥ ሁለትና ሦስት ሚሊዮን ተመልካች ነው የሚያገኙት። ጊዜው ዲጂታል በመሆኑ ተፅዕኖ ፈጣሪ እየሆኑ ነው ያሉት። በየማኅበራዊ ሚዲያው ቶሎ ነው ሰው የሚቀባበለው።
አዲስ ዘመን፡- ነሺዳ ትውልዱን ከመታደግና ከጥፋት ከመመለስ፤ አኳያ ምንዓይነት አበርክቶ አለው?
ሙሺድ አስማማው፡– እንዳልኩሽ አንድነቱ፣ ፍቅሩ፣ መተሳሰቡን ሁሉ ነው በነሺዳዎቻችን የምናነሳው። ስለሆነም ነሺዳ ላይ የሚተላለፉ መልዕክቶች ከመንፈሳዊ ይዘታቸው በዘለለ ትውልዱ ወደ ተሳሳተ መንገድ እንዳይሄድ የመታደግም አቅም አላቸው ብዬ ነው የማምነው። በተለይም ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን ቃል በቃል ከመንገር ይልቅ ወጣቱ በሚፈልገው መንገድ ለማስተማር ዕድል ይሰጣል። በሌላ በኩልም ይህች አገር ስትገነባ ደግሞ አነሰም፤ በዛም ጭቃ ያቦካም፤ ያቀበለም አለ። አያንዳንዱ ግን ባይተዋር ነኝ ብሎ ያስባል። እውነታው ግን ኢትዮጵያ ስንል እኛ ዜጎቿ ነን። ሰው ከሌለ አገር አይኖርም። እያንዳንዷ የእኛ ተሳትፎ ናት ይህችን አገር የምታቆያት። ስለዚህ እኛ በጎ አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚገባን የሚያስገነዝቡ ብዙ ነሺዳዎች ወጥተዋል።
በቅርቡ ከአንድ ወንድሜ ጋር የሠራሁት ነሺዳ
‹‹እልፍኝሽ የተንጣለለ፤
መሶብሽ ረድኤታም
ፍቅር ነው የራቀን እንጂ
ገበታሽ ማዕድ አላጣም››
እያለ ስለኢትዮጵያ ተፈጥሮ ሀብት፤ ሁሉ ሞልቶ ሳለ ፍቅር አጥተን አለመስማማታችን ገቢ አለመሆኑን ያወሳል። ሌሎችም ሁሉም ሰው ወደ መሬት ሲመጣ ለአገሩ አስተዋፅኦ አድርጎ ማለፍ እንዳለበት የሚያስገነዝቡ ይሠራሉ። ስለዚህ በጠቅላላው ነሺዳ ፋይዳው ብዙ ነው ማለት እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ጎሰኝነትና ሙስና በየእምነት ተቋማት በስፋት ይስተዋላል፤ ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከእምነት አባቶች ምን ይጠበቃል?
ሙሺድ አስማማው፡- እንዳልሽው አሁን ያለንበት ወቅት ብዙ ነገሮች የተበላሹበት ነው። የእምነት ተቋማት በፊት የተጣሉ ሰዎችን ለማስታረቅ ወይም ደግሞ አገር ሲበላሽ እንዲያስተካክሉ የእምነት አባቶች ሚና የጎላ ነበር። አሁን ግን ፖሊስ ሄዶ የሚያደራድረው የእምነት ተቋማት መሪዎችን ነው። በያለንበት ብንቆም የተሻለ ነው። አሁን እየሄድንበት ያለው መንገድ ስህተት ነው። ምክንያቱም ሁሉም የየራሱን ፍላጎት ብቻ ለማሳካት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ውጤቱን እያየነው ነው። ስለዚህ ባለንበት ቆመን ሕዝቡን ልናዳምጠው ይገባል። የእምነት ተቋማት ውስጥ ፖለቲካው መግባቱ ነው አንዱ ችግሩን ያከበደው። ስለዚህ የእምነት አባቶች ሁሉም ከእኔ ይቅር ብለው ሕዝቡን ሊታደጉ ይገባል።
በሌላ በኩል ጠንካራ ተቋም ስለሌለ ነው በእምነት ተቋማቶቻችን ችግር እየተፈጠረ ያለው። በየቦታው ዘርን መሠረት ተደርጎ ጭፍጨፋ ተካሂዷል፤ መስኪድና ቤተክርስቲያት ተቃጥለዋል፤ ወድመዋል፤ የእምነት ሰዎች ተገድለዋል። በነገራችን ላይ የትኛውም እምነት ይህንን አይፈቅድም። መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ቁርዓን የሚያዙት በጎ ሰው መሆንን እንጂ ክፋትን አይደለም። ጠንካራ የእምነት ተቋማት ቢኖሩን ኖሮ ጥቃቱን መከላከል በቻሉ ነበር። በመሆኑም ተቋማቶቻችንን ማጠናከር ለነገ የምንተወው ሥራ አይደለም ብዬ አምናለሁ።
ከሁሉ በላይ ግን እምነታችን እንደሚያዘው በሰላምና በፍቅር ከሁሉ ጋር ተስማምተን ለመኖር ፍቃደኛ መሆንና ልባችንን ማዘጋጀት አለብን ብዬ ነው የማስበው። በተለይ የእምነት አባቶች ስጋዊ ፍላጎታቸውን አሸንፈው ለሰላምና ለፍቅር መኖርን በሕይወታቸው ተርጉመው ሊያሳዩ ይገባል። ምክንያቱም ምዕመኑ የሚከተለውና የሚያምነው እነሱን በመሆኑ ነው። በሁሉም የእምነት ተቋም ያሉ መሪዎች አሁን ከያዙት አቋም ተመልሰው ሕዝቡን ማድመጥ ይገባቸዋል። አሁን ላይ እኮ በየእምነት ተቋሙ የፀጥታ አካል ካልቆመ አስተማማኝ ሰላም የማይኖር እየመሰለን ነው። የሚገርመው ደግሞ በተለያየ እምነት ተቋማት ብቻ ሳይሆን በአንድ ሃይማኖት ውስጥ እርስ በርስ ግጭት እየተፈጠረ አንዱ ሌላውን ለማሳሰር ሲሯሯጥ መታየቱ ነው። እንዲህ ዓይነቱ የሞራል ዝቅጠት ውስጥ እንዴት እንደገባን መፈተሽ አለብን።
ለዚህ መልስ የሚኖረው በዋናነት የእምነት አባቶቹ ጋር ነው። በአንድ በኩል እነዚህ አባቶች ወደው ወደዚህ ሁኔታ ገብተዋል ብዬ አላምንም። አብዛኞቹ አባቶች አጠገባቸው ያለውን ሁሉ በንፁህና ስለሚያምኑ ወደ ስህተት የሚመራቸውን ሰው ሃሳብ የሚቀበሉበት ሁኔታ አለ። ፖለቲካውን ስለማያውቁት በፖለቲከኞቹ ሴራ ሳያስቡት ይጠመዳሉ። ሄዶ የመከራቸው ሁሉ በጎ ነው የሚመስላቸው። አሁን ግን የእነዚህን ሰዎች ምክር ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ባይሰሟቸውና የፈጣሪን ፍቃድ ብቻ ለመፈፀም ቢተጉ ጥሩ ነው የሚል እምነት አለኝ። አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ ሁላችንም ተያይዘን ነው የምናልቀው።
በመሆኑም የመቻቻል እሴታችንን ለማስጠበቅ የእምነት አባቶች ተቀራርበው መነጋገር ይጠበቅባቸዋል። በየቀኑ የምንሰማው ነገር የተለመደና የብዙዎቻችን አመለካከት ሁሉ የቀየረ ሆኗል። ፈጣሪ ለሰው ልጅ የሰጠው ክብርም ተረስቷል። ከዚህ ቀደም እንስሳ እንኳን ባይሆንበት የምንመኘው ነገር በሰው ልጅ ሲሆን ግድ የማይሰጠን ሁኔታ ነው ያለው። በመሆኑም ከዚህ የስህተት መንገድ ሕዝቡን መመለስ የሚችሉት እነዚህ የእምነት አባቶች በመሆናቸው ራሳቸውን በመጀመሪያ መፈተሽንና ወደትክክለኛው ሃይማኖታዊ ልምምድ መግባት አለባቸው ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ ላመሰግን እወዳለሁ።
ሙሺድ፡- እኔም ለሰጣችሁኝ ዕድል እያመሰገንኩ ለመላው ሙስሊም ማኅበረሰብ መልካም የኢድ- አልፈጥር በዓል እመኛለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 /2014