የኢትዮጵያ ስድስተኛው ዙር ምርጫ በ2012 ዓ.ም እንደሚካሄድ ይታመናል፡፡ ከአገር ውጭ ሆነው በትጥቅም በሐሳብም ሲታገሉ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ጋር በተናጠልም ሆነ በቡድን ተገናኝተውም በአንዳንድ ጉዳዮች መክረዋል፡፡ ከትናን በስቲያ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሩን ሰብስበው ‹‹ውይይትን እንዴት እንምራው›› በሚል ጽንሰ ሐሳብ ዙሪያ አወያይተዋቸዋል፡፡ በዕለቱም ዋና ትኩረታቸው የነበረው ቀጣይ ስለሚካሄዱ ገንቢ ውይይቶች ግንዛቤ መያዝ ላይ ነው፡፡
በተለይ አገራዊ ምርጫ ሲታሰብ በተቻለ መጠን ሁሉ ያለ እንከን ማጠናቀቅ ላይም ያሰመሩ ሲሆን፣ ምርጫው ያለ እንከን ቢጠናቀቅ ከመካከላቸው የሚሸነፍ አንድም እንደማይኖር ጠቅሰዋል፡፡ ማሸነፍ ማለት ደግሞ ሁሉም ተስማምቶ ባስቀመጠው ህግ መገዛት እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ዶክተር ዐብይ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጋር ያካሄዱትን ውይይት በተመለከተ በአጭሩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
የውይይ መነሻ ሐሳብ
የውይይቱ ዋና መነሻ የሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣውን ለውጥ በቅርበት ማገዝ፣ በቅርበትም ማወቅና ሐሳብ መስጠት እንፈልጋለን የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ፤ ይሁን እንጂ ያን ለማስኬድ ያስቸገረን ነገር የመጀመሪያው ከለውጡ በኋላ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉ ፓርቲዎች ታጥቀውም ይሁን ሳይታጠቁ በተለያየ ዓለም ተበትነው ስለሚገኙ በተሟላ ሁኔታ አገር ውስጥ እስኪገቡ ድረስ መጠበቅ ነበረብን፡፡ አሁን ግን ታጥቀው የሚታገሉም ሆነ ሳይታጠቁ በሐሳብ የሚታገሉ ሁሉ ገብተዋልና ለውይይታችን አንዱ መነሻ ሐሳብ እሱ ነው፡፡፡ ዛሬ ላይ በተቃውሞ ወገን ተሰልፎ በውጭ የሚቃረን ቡድን የለም ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ካለም ደግሞ በጋራ በማፈላለግ እነርሱንም ማምጣት ይቻላል፡፡
ሁለተኛው የውይይቱ መነሻ የሆነውን ጉዳይ በርካታ ሊሻሻሉ የሚገባቸው አዋጆችና አሰራሮች ስለነበሩ እነሱን መነካካት ስለሚያስፈልግና የፍትህ ሪፎርሙን ማሳለጥ ያስፈልግ ስለነበርና ነው፡፡ ከሁሉ በላይ የምርጫ ቦርዱን በሚመለከት ለረጅም ጊዜ ገለልተኛ አይደለም የሚባል ወቀሳም ስለነበር ቢያንስ በሁላችንም የጋራ እምነት ሊጣልበት የሚችል ተቋም መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ነው፤ እንዲሁም በለውጥ ጊዜ ምክክርና ሐሳብ ካደረግን በኋላ ሐሳብን ማስፈጸም ለማስቻል የሚያግዝ መሆን ካልቻለ ውይይቱ ከንቱ ይሆናል፡፡
እስካሁን ድረስ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት አዲስ አይደለም፡፡ ዋናው ቁም ነገር ውይይቱ ውጤታማ ነበር ወይ የሚለው ነው፡፡ ውይይቱን ውጤታማ እንዳይሆን ከሚያደርገው ነገር አንዱ ከጅምሩ ውይይቱ ሲጀመር ልክ ስሩ እንደተቆረጠ ችግኝ ከመተከሉ እንዲጠወልግ ሆኖ ስለሚጀመር ነው፡፡ ተወያይቶና ተግባብቶ የጋራ ነገር እንዲይዝ ታስቦ የሚጀመር ስላልሆነ ስር የለውም፤ ስለዚህ ምንም እንኳ ቢጀመርም ወዲያው በቅጽበት የሚጠወልግ ይሆናል፡፡
አሁን የምንተክለው ችግኝ እንዳይጠወልግ የሚያደርገው የመጀመሪያው ነገር ስሩ አለመነቀሉን ማረጋገጥ ነው፡፡ ስርና መሰረቱ ህግ እንዲሁም የነበርንበት የፖለቲካ ልምምድ ያስገኘውን ውጤት በውል ማወቅና ከድካሞቻችን ተሻሽለንና ተምረን ወደ ላቀ ደረጃ ለመሸጋገር የሚያስችል ሁኔታ ላይ መሆናችንን ማረጋገጥ ነው፡፡ ሁሉም እንደሚያውቀው አገር ካለ ሰውና ካለ ፖለቲካ ፓርቲ መኖር ይችላል፤ ሰው ግን ካለ አገር መኖር አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ዛሬው መቶ ሚሊዮን ህዝብ ሳይኖራትም ኖራለች፡፡ መቶ ሚሊዮኑም ለቆ ቢወጣ አገር ምድሩ ይቀጥላል፡፡ እኛ ግን አገር ከሌለ መቋቋም አንችልም፡፡
አገር እያፈረሰ አገር ላይ መኖር የሚፈልግ ፓርቲ አሊያም የፖለቲካ አስተሳሰብ ያለው ማንኛውም ኃይል ዋና መሰረቱን ስሩን ስለሚቆርጥ የማያድግ ፖለቲካ ይፈጠራል፡፡ የሚሰራው ማንኛውም ስራ መቀመጫ የሆነውን አገር የማያፈርስ መሆኑን እርግጠኛ መሆን ይጠበቃል፡፡ ሂደቱ እያፈረሱ ከሆነ መቀመጫ ስለማይኖር ፖለቲካው አብቦ ፍሬያማ ሊሆን አይችልም፡፡ እስካሁን የነበረው ሁኔታ ይህን መልክ የያዘ ነበርና ከዚህ በመውጣት በቀጣይ የሚደረጉ ውይይቶች ፍሬያማ እንዲሆኑና ከዚህ ቀደም የነበረውን ሁኔታ የማያስተናግድ እንዲሆን በተባበረ ክንድ በጋራ መስራት ያስፈልጋል፡፡
የውይይቱ መንደርደሪያ
የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ አገርና ለአንድ ህዝብ የሚሰሩ እስከሆነ ድረስ መወያየት ግዴታ ነው፡፡ ዛሬ ተመርጦ አሸንፎ እየገዛ ያለ ፓርቲ ነገ ሊሸነፍ ስለሚችል ዛሬ የተሸነፈ ፓርቲ ነገ ማሸነፍ ስለሚችል ያሸነፈውም ሆነ የተሸነፈው የሚወያዩበት መድረክ ተፈጥሮ የጋራ አገርና የጋራ ሕዝብ እንዴት ማስኬድ እንዳለባቸው መምከር አስፈላጊ ነው፡፡ ያን ማድረግ ሲሳነን የገጠመንን ችግር ሁላችሁም ታውቁታላችሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ 30 እና 40 ዓመት የቆዩ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርትን የተማሩ ሰዎች አሉ፡፡
ይሁን እንጂ እነሱን ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ያ ፖለቲከኞች መገንዘብ ያለባቸው ዋናው ጉዳይ ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን ፖለቲካ ‹‹ሀ›› ብላ የምትማር አገር መሆኗን ነው፡፡ በፖለቲካ ረገድ የተሳካላት አገር አይደለችም፡፡ ተማርን የምንልም ሰዎች ብንሆን እነ ‹‹እንትና ምን አሉ፤ ምን ጻፉ›› የሚል ሐሳብ ከማምጣት በዘለለ የእኛ የሆነ ፈጥረን ይህን አገር ወደፊት ለመውሰድ የሚያስችልና በአፍሪካ ደረጃም ቀደምት አገርና መንግስት ያላት እንደመሆኗ ለሌሎች አርዓያ የምትሆንበትን እድል አልፈጠርንም፡፡ ቆይታችን ያልበሰለ የፖለቲካ ባህልን ከመፍጠር ያለፈ አይደለም፡፡ ስለዚህ ፖለቲካን ከመጀመሪያው በመነሳት መማር እንዳለብን ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ለመማርም ዝግጁነቱ ካለ ከእያንዳንዱ ሰው በሚነሳው ሐሳብ የበለጠ ነገር ለመውሰድ እድሉ አለ፡፡ እናውቃለን ብለን ከተነሳን ግን ለመማማር እንቸገራለን፡፡
ይህ ማለት የርዕዮት ዓለም፣ የፖለቲካ የስትራቴጂ ልዩነት የለም ማለት አይደለም፡፡ ልዩነቱ ግን ከህዝብና ከአገር በታች ስለሆነ በአገርና በህዝብ ጥላ ስር ሆነን በተለያየንባቸው ጉዳዮች በመወያየትና የጋራ ሐሳብ መያዝ እንችላለን የሚል ሐሳብ ነው ያለው፡፡ ይህ ሲሆን ግን አንዱ ሌላው አጥፊ፣ በታኝ እንዲሁም አሸባሪ የሚል ተቀጽላ ስም ከሰጠ ውይይቱ ፍሬያማ አይሆንም፡፡ ምንም ይሁን ሐሳብ ጠቃሚ ነውና ይደመጣል፡፡ ገዥ የሆነው ሐሳብ ደግሞ ስራ ላይ ይውላል ብለን ማሰብ ይኖርብናል፡፡
የምርጫ ውጤቶችን ጨምሮ በርካታ ነገሮች ላይ መግባባት የሚቻለው በጨዋታ ህጉና በዳኛው ላይ እምነት ሲፈጠር ነው፡፡ በህጉ የማንገዛ ከሆነ ማንኛውም ህግ በተሟላ ሁኔታ ሁላችንንም ሊያረካ ሆኖ አይሰራም፡፡ የእኛ የምርጫ ህግ ከተግባባንበት በኋላ በሆነ ምክንያት የማያስደስተው አሊያም የማያረካው ሰው ካለ እንኳ በዛ ህግ ግን መገዛት ግዴታው ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም አይነት ውዥንብር መፈጠር የለበትም፡፡ ባሉን ህጎች ተገዝቶ በህግ ጥላ ስር መስራት ግዴታ ነው፡፡ በጨዋታ ህጉ ማኖ የሚነካ ሰው ካለ መንግስት ብቻ ሳይሆን የውይይቱ አካል የሆነ ማኛውም የፖለቲካ ድርጅት ለአገርና ለህዝብ ሲል የጋራ አቋም መውሰድ አለበት፡፡
በምንግባባው ጉዳይ ላይ ስልጣን ያለውም ሆነ የሌለው መገዛት አለበት፡፡ ሳይገዛ ሲቀር አንድ አቋም ይዘን መከራከር ይኖርብናል፡፡ ሁልጊዜ የገዥና የተፎካካሪ ፓርቲ አይነት እሳቤ ሳይሆን በሐሳብ የምንሰባሰብ መሆን መቻል ይኖርብናል፡፡
በውይይቱ ወደ 70 ገደማ የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ተገኝታችኋል፡፡ በሚቀጥለው ውይይት ምናልባት ሐሳብ እየተቀያየርን ስንሄድ ወደ አምስትና ስድስት ዝቅ እንላለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ለ70 ፓርቲ 70 ቢሮ ማዘጋጀትና በፋይናንስ መደገፍ ሌላው ቢቀር 70 የምርጫ ምልክት ማዘጋጀት ችግር ነው፣ አዋጭም አይደለም፡፡ መሆን ያለበት የተቀራረበ ሐሳብ ያለን በሐሳብ በመቻቻል መሰብሰብ ነው፡፡ ይህ በቀጣይ ውይይት ይዳብራል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ለአንዲት ዴሞክራሲያዊት አገር ምርጫ ወሳኝ ነው፡፡ በህዝቡም በሚፎካከሩ ኃይሎችም እንደ አንድ መመዘኛ ይወሰዳል፡፡ ይሁንና ምርጫ ብቻውን በቂ ነው ማለት አይደለም፡፡
ስርዓት ግንባታ
ሌላው ስርዓት ግንባታ ሲሆን፣ ምርጫ አንዱ ጉዳይ እንጂ ስርዓት ገንቢ አይደለም፡፡ ስርዓት ለመገንባት ፍትህ፣ ነጻነትና ሌሎችም ነገሮች ሊሟሉ ይገባል፡፡ በፓርቲዎች መካከል የምናደርገው ውይይት ዋና ዋና የሚባሉ የማያግባቡን ነገሮች የምንፈትሽበት፣ በብዙዎቹ ተግባብተን ምላሽ የምንሰጥበት፣ ለጋራ ግብና ስራ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን የምንፈጥርበት እንደሚሆን ተስፋ ይደረግበታል፡፡ አንዱ ሁላችንንም የሚያግባባው አገር፣ ህዝብና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት የጋራ ኃላፊነት ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡
በመካከላችን የነበረውንና የነገሰውንና ያለመታመን ታሪክ የምንቀንስበት እናም እንደ አገር ሰዎች የምንተያይበት ሁኔታ ይፈጠራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ላይም ግልጽ አካሄድ ተከትለን ተቋማቱን ለመገንባት በጋራ ርብርብ እንደምናደርግ ይጠበቃል፡፡ የምርጫ ተሳታፊዎች እጩ፣ ታዛቢ፣ አመራር፣ መራጭ አካሄድ ላይ የበለጠ መግባባት ይፈጠራል ተብሎ ይታሰባል፡፡
የውይይቱ አካሄድ በተመለከተ አንደኛው የችግሮቹን አይነቶች አንድ በአንድ ዘርዝሮ መለየት ነው፡፡ ከተዘረዘሩ በኋላ አጣዳፊና ጫና ፈጣሪ ናቸው የሚባሉት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ይታያል፡፡ አቀራረቡም ከቀላል ወደ ውስብስብ ደረጃ በደረጃ እንዲሄድ ይደረጋል፡፡
መሰረታዊ መርህ
መሰረታዊ መርህ ያልናቸው የአገራችን መንግስት ምስረታ ሂደት ላይ በጣም በርካታ ታሪካዊ ችግሮችና ጸቦች አጋጥመዋል፡፡ በሂደቱ ብቸኛ ተጠቃሚ አሊያም ተጎጂ የለም፡፡ ብዙ ህዝቦች በየራሳቸው መንገድ ተጎድተናል ብለው ያስባሉ፡፡ እነዛን ቁርሾዎች መልሰን የምናነሳ ከሆነ የገነባነውን አገር መልሰን ጥያቄ ውስጥ እንከተዋለን፡፡ እንዴት ነው ታሪክን ወደኋላ ተመልሰን ሳናይ ዘግተን መጓዝ የምንችለው የሚለው ጉዳይ የፖለቲካ ልሂቃን ዋነኛ አጀንዳ መሆን አለበት፡፡ አለበለዚያ ያለፈውን በመሳብ የምንነጋገር ከሆነ ሳንግባባ ልንለያይ እንችላለን፡፡
ሌላው ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ የብዙ ብሄሮችና ብሄረሰቦች እንዲሁም እምነቶች ያሉባት አገር ናት፡፡ ብዙዎቻችን የእኛን ብሄር ወክለን ፓርቲ ስለሆንን የሌላውን ህልውናና ደህንነት እንዲሁም የሌላውን በአገሩ የመኖር መብት ማክበር ፈቃደኛ ካልሆንን መልሶ ውይይታችንና ንግግራችን ችግር ውስጥ ይገባል፡፡ በንግግራችን ሁሉ እኛ ለቆምንለት ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ህዝብ በጋራ የመኖር ኃላፊነት እንዳለብን እያሰብን በዚህ መርሆ ታጥረን መወያየት ይኖርብናል፡፡
እኛ የምንፈልገው ትናንትናችን ብዙ ድል እና ብዙ ችግር አለው፡፡ ድሎቹን ወስደን ለችግሮቹ መቋጫ አበጅተን ወደፊት መሄድ እንድንችል እንጂ እዛ ውስጥ እንድንቀር አይደለም፡፡ በትናንትና ውስጥ የሚኖሩ ሁሉም አገራት ወደፊት መሄድ ስለሚቸገሩ እኛ የምንወያያቸው ጉዳዮች ደግሞ አገር ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ስለሚወስን እንደ አንድ መርህ ይህም ታሳቢ መደረግ ይኖርበታል፡፡ እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚል እሳቤ በፍጹም መኖር የለበትም፡፡
ሌላው ህገ መንግስቱንም ህጎቹንም እናከብርና በህገ መንግስቱ አሊያም በህጎቹ ያሉ ማንኛውም የማይስማሙን ሐሳቦች ካሉ ግን እንወያይባቸዋለን፡፡ ተወያይተን ከተግባባን እናሻሽላለን፡፡ ካልተግባባን ደግሞ ህዝብ እንዲወስን እናደርጋለን፡፡ ከወዲሁ ግን ይኸኛውን ህግ አልቀበልም፤ ያኛው አንቀጽ እኔን አይገዛኝም የሚል አስተሳሰብ ካለ ግን አንግባባም ማለት ነው፡፡ ባለው ህግ እየተገዛን ከዛ ህጉን እያሻሻልን መሄድ እንዳለብን ሁላችንም እንደ መርህ መያዝ አለብን፡፡
አዳጊ አገርና ህዝብ ስለሆነ በርካታ ሊሻሻል የሚገባው የማያግባባን ሐሳብ ብዙ አለ፡፡ ይህ ግን በንግግርና ውይይት የጋራ እያደረግን መፍታት ነው የሚጠበቅብን እንጂ ከወዲሁ መርጠን የምንፈልገውን ወስደን የማይመቸንን ጥለን ከሆነ ውይይቱ ፍሬያማ ስለማይሆን ይህ ጉዳይ መያዝ አለበት፡፡ በሁሉ ሐሳቦች በተደማሪነት ኢትዮጵያና ህዝቦቿን ወደፊት የሚወስድና የሚያሳድግ መሆኑንም እንደ አንድ የመርህ አካል ማሰብ ጥሩ ነው፡፡ ከአንድ ትውልድ በላይ የሚሻገር አሁን የምናካሂደው ምርጫ መሰረት ሆኖ ከዚህ በኋላ በሚቀጥለው አምስት ዓመት እጅግ በጣም የተሻለ አስር ሃያ ዓመት ደግሞ የምንመኘውን አይነት ነገር የሚያመጣ ሆኖ እንዲሰራ ጅማሬ በጣም ወሳኝ ስለሆነ በተቻለ መጠን ወደ ትውልድ የሚሻገር ነገር ለመተው አስበን ብንሰራና እንደ መርህም ብንወስደው መልካም ነው፡፡
በውይይት ማመቻመች በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ሚስተር ኤክስ አንድ ሐሳብ አለው፤ ሚስተር ዋይ ደግሞ ሌላ ሐሳብ ይዞ መጥቷል፡፡ ሁለቱ ሐሳብ የማይገዛዙና አንዱ በአንዱ ውስጥ የማይወረስና አብረው መጓዝ የማይችሉ ከሆነ መለያየት ሳይሆን ሶስተኛ የላቀ ሐሳብ አማራጭ መፍጠር ነው፡፡ የሚያመቻምቹ የፖለቲካ ልሂቃን ሐሳብ ማምጣት ይችላሉ፡፡ አዲስ ነገርን መፍጠር ይችላሉ፡፡
በክርክር ወቅት የእኔ ሐሳብ ካልሆነ ብሎ ጥሎ መሄድ አማራጭ አይደለም፡፡ አንደኛው የሌላኛውን ሐሳብ አድምጦ ሶስተኛ አማራጭ እያየን የምንሄድበትን መንገድ መከተል ያስፈልጋል፡፡
ሚዲያ አጠቃቀም
በቀጣዩ ምርጫ እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ የራሱ የሆነ ሚዲያ የለውም፡፡ በጋራ የምንጠ ቀምባቸው ሚዲያዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ዘመን ያመጣው ቴክኖሎጂ እያንዳንዱ ድርጅት ብቻ ሳይሆን ግለሰብም እንደፈለገው ሊመራው የሚያስችል አቅምም ስለተፈጠረ ሁሉም ፓርቲ የራሱ ዓርማ ያለበት ግልጽ የሆነ ድረ ገጽ ያስፈልገዋል፡፡ ማንኛውም መረጃ መደበኛ በሆነ መልኩ የምንቀያየርበት ይሆናል ማለት ነው፡፡
ለምንድን ነው የአንደኛችንን ሐሳብ የሚደግፍ የሚመስል ሌላው የሚጠላ ሐሳብ ያለው ግለሰብ ወይም ቡድን በማህበራዊ ሚዲያ ሂደቱን እኛ እየተወያየን እያለንም ቢሆን ሊያበላሸው ይችላልና ነው፡፡ ህጋዊ ከሆነው ድረ ገጽ ውጭ እኛ የማናውቃቸው ግለሰቦች ስማቸውን ቀይረው ብሄርን ከብሄር፣ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ ሐሳብ ጽፈው ችግር ቢያመጡ የእኛ ውይይት ሙሉ ስለማይሆን መወያየታችን ዋነኛ ዓላማው ችግር ማስቀረት ሆኖ ሳለ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ግለሰቦች ወይም ቡድኖችን ግጭት እንዳያመጡ ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ተመካክረን አቅጣጫ የምናስቀምጥበት ይሆናል፡፡
እስካሁን በነበረው የምርጫ ሂደት ማህበራዊ ሚዲያ ራስምታት አልነበረም፡፡ በ97ቱ ምርጫ ማህበራዊ ሚዲያ ቢኖር ኖሮ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ ነው፡፡ ባለመኖሩም ችግሩ ቀንሷል ማለት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ምርጫ በብዙ መልኩ ፈተና የሚሆንብን አንዱ ማህበራዊ ሚዲያ ነው፡፡ ህዝባችንን እያስተማርን እያነቃን መረጃ ከፈለክ የእንትናን ፓርቲ በዛ በኩል የእንትናን ደግሞ በዚያኛው በኩል ታገኛለህ ብለን በመግለጽና ከዚህ ውጪ ያለውን እንደ መረጃ አትውሰድ ብለን ካልነገርነው በስተቀር በጣም በርካታ አሳሳችና ትክክል ያልሆኑ ፎቶሾፖች ተሰርተው ሰው ሲታረድ፣ ሲገደልና ሲጭበረበር ማሳየት ይቻላል፡፡ እኛ ደግሞ በባህሪያችን በጣም ስሜታዊ የሆንን ህዝቦች ስለሆንን በቀላሉ ግጭት ውስጥ እንገባለን፡፡
ስሜታዊ የሆኑ ህዝቦች ስሜታቸውን የሚገዙበት በርካታ ስልጠናዎችና ውይይቶች ያስፈልጋል፤ ይህ ለኛም ጨምሮ የሚያስፈልግ ነው፡፡ ያንን ማድረግ ካልቻልን በትንንሽ መረጃ ችግር ውስጥ ልንገባ እንችላለን፡፡ ብዙዎች እንደሚያነሱት ሰፋፊ ታሪክ ያላቸው አገራት በአፍሪካ እንደ ኢትዮጵያና ግብፅ፣ በአውሮፓም እንደ ግሪክና ቱርክ ያሉ አገራት ትናንትና ውስጥ ጊዜያቸውን ስለሚያጠፉ፣ በታሪክ ስለሚመጻደቁና ስለሚኖሩ ከፍተኛ ስሜታዊ ናቸው ይባላል፡፡
አፍሪካ ውስጥ ኢትዮጵያና ግብጽ ተወያይተው ተወያይተው ውይይታቸውን በትንሽ ነገር እንዲበላሽባቸው ከሚያደርገው አንዱ ስሜታዊነት ነው፡፡ በአውሮፖም እንዲሁ ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ አገራት የሚያስቡት የአክሰማዊት ግዛትን፣ የፈርኦንን ግዛትን እንዲሁም የኦቶማን ቱርክን ነው፡፡ ያንን ግዛት እያሰቡ በንዴትና በቁጭት ውስጥ ስለሚሆኑ ትክክለኛ ሆነውና ምክንያታዊ ሆነው ማሰብ ይቸገራሉ፡፡ ይህን አይነት አካሄድ ለመፍታት በጋራ ገብቶን ካልሰራን በስተቀረ በቀላሉ ጸብና ግጭት ይበዛል፡፡ ትውልድ የሚገነባው በሐሳብ ነው እንጂ በጉልበት አይደለም፡፡
መቶም ፣ሶስት ሺም ዓመት እያልን እንደ እንጭጭ አገር የሆንበት ምክንያት ዛሬም መንግስት የሚፈጠርበትን ጉልበት እንጂ ትውልድ የሚገነባበት ሐሳብ ላይ መድረስ ባለመቻላችን ነው፡፡ ይህንን ለማስተካከል ከሁሉ በላይ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በኃላፊነት ስሜት በጋራ መስራት ይኖርብናል፡፡
አስቴር ኤልያስ