
– 24 ስማርት ኮሙኒኬሽን ክፍሎች ተመረቁ
አዲስ አበባ፦ ክልሎች ዲጂታል መሠረተ ልማትን በማጠናከር የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ። 24 ስማርት የኮሙኒኬሽን ክፍሎች ትናንት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል።
የኢኖቪሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ ዲጂታል ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ መሠረተ ልማትን ማሟላት አስፈላጊ ነው። ከእዚህ መነሻነትም በአሁኑ ጊዜ በርካታ የዲጂታል መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ ሲሆን፤ የተመረቁት 24 ስማርት የኮሙኒኬሽን ክፍሎች እየተሠሩ ላሉት ሥራዎች አንዱ ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡
በ10 የፌዴራል ተቋማት፣ በ12 ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተገነቡት 24 ስማርት የኮሙኒኬሽን ክፍሎች ዲጂታል ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ ከፍተኛ ጥቅም እንዳላቸው ገልጸው፤ ይህንን መሠረተ ልማት ክልሎች በአግባቡ ሊጠቀሙና ደህንነቱን ሊጠብቁ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ይህም የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትራንስፎርሜሽኑ አንዱ አካል መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር በለጠ (ዶ/ር)፤ክልሎች ዲጂታል መሠረተ ልማትን በማጠናከር የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን አበክረው ሊሠሩ ይገባል። ለእዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የስማርት ኮሙኒኬሽን ክፍሎች የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ አካል መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የመንግሥት ተቋማት የዲጂታል ቴክኖሎጂን በተገቢው መንገድ እንዲጠቀሙ አስፈላጊ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት ከስትራቴጂው ዓላማ ውስጥ መሆኑን ተናግረዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 እቅድ የታለመለትን ግብ በሚገባ ማሳካት መቻሉን እና የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 እቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ በለጠ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያን ዲጂታል ኢኮኖሚ በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የመንግሥት ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ሚና በተቀላጠፈ መንገድ እንዲወጡ ለማስቻል የኮሙኒኬሽን ክፍሎች መገንባታቸውን ገልጸዋል።
እነዚህንም የተሟሉ ዘመናዊ የመገልገያ ቁሳቁሶች እና ልዩ ልዩ የኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙላቸው መሆናቸውንም ገልጸው፤ የስማርት ኮሙኒኬሽን ክፍሎች ዓላማ በተቋማት ውስጥ እና በተቋማት መካከል ያለውን የሥራ ግንኙነት የተሳለጠ በማድረግ፣ ምቹ የሥራ አካባቢ በመፍጠር፣ ለሥራ ቅልጥፍና እና ለመልካም አስተዳደር መስፈን አስተዋጽኦ ማድረግ ነው ያሉት።
በክልሎች የዲጂታልና አጠቃላይ የቴክኖሎጂ እንቅስቃሴ ወጥ አለመሆኑን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የተገነቡት የስማርት ኮሙኒኬሽን ክፍሎች ለእውቀት ልውውጥ፣ ለትምህርት ጥራትና ለኢኮኖሚ ልማት እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የተገነቡት የስማርት ኮሙኒኬሽን ክፍሎች የዲጂታል ኢኮኖሚውን በመገንባትና በሀገር ጉዳይ የሚወሰኑ ውሳኔዎችን የጋራ ለማድረግ የሚጫወቱት ሚና ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
እንዲህ ዓይነት መሠረተ ልማቶች በጤና ፣በትምህርት፣ በግብርና እና መሰል ዘርፎች ያሉ ተሞክሮዎችን ለማስፋፋት እና አዳዲስ እውቀቶችን በቀላሉ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያግዙም አመልክተዋል።
የስማርት ኮሙኒኬሽን ክፍሎች ለኢኮኖሚው እድገት የሚጠቅሙ ውሳኔዎችን በጋራና በፍጥነት ለመወሰን፤ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡
ስማርት ኮሙኒኬሽን ክፍሎችን የታችኛው መዋቅር ድረስ በማስፋፋት ዲጂታል ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ መሥራት እንደሚገባ ገልጸው፤ ዜጎች አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲሁም መንግሥት ከዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን ሁሉም ያለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም