አብዛኛዎቹ የሀገራችን አርሶ አደሮች አረምን የሚያስወግዱት ሰብሉ ከበቀለ በኋላ በእጃቸው ካልሆነም አነስተኛ የጸረ አረም መርዝ መርጫ እቃዎችን በጀርባቸው ላይ በማድረግ በእግራቸው እየተዟዟሩ ሰብሉ ላይ በመርጨት ነው፡፡
ምንም እንኳን በሰፋፊ እርሻዎች በተሽከርካሪ ማሽኖችና በአነስተኛ አውሮፕላኖች የጸረ አረም እና ተባይ መርዞችን የመርጨት ልምድ እንዳለ ብናውቅም፤ አርሶ አደሩ ግን በግሉ የሚያርሳቸው ቁርጥራጭ መሬቶችን በመሆኑ ይህን ቴክኖሎጂ ለመተግበር አስቸጋሪ ሆኗል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አርሶ አደሮች የኩታ ገጠም እርሻን እየተላመዱ መምጣታቸው ዘመናዊ ማሽኖችን በመጠቀም መዝራት፣ ጸረ አረምና ተባይ መርዝ መርጨትን ጨምሮ ሙሉ የግብርና ፓኬጆችን እንዲጠቀሙ እድል ፈጥሮላቸዋል፡፡
ከሰሞኑ ባደረግነው የመስክ ምልከታ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ በሚገኘው በቡልቡላ ደንበል መስኖ ልማት ኅብረት ሥራ ዩኒየን እና በኦሮሚያ ግብርና ኅብረት ሥራ ማህበራት ፌዴሬሽን መካከል ቀደም ብሎ በተደረገው የኮንትራት ፋርም ስምምነት መሠረት፤ የተከናወነው የዘር መዝራት፣ የጸረ አረምና ጸረ ተባይ መርዝ ርጭት ይህንኑ እውነታ ያረጋግጣል፡፡
ግብርናን ከኋላ ቀር አሠራር አላቆ በምግብ ራስን ለማቻል በሚደረገው ጥረት እንደሀገር የግብርና ፓኬጆችን በሙሉ ለመጠቀም እየተሞከረ ነው፡፡ በእዚህም አርሶ አደሩ የኩታ ገጠም እርሻዎችን የማስፋፋት፣ የእርሻ ሥራን በሜካናይዝድ የማከናወን፣ በመስመር የመዝራት ፣ ምርጥ ዘርን የመዝራት፣ የአፈር እና የፈሳሽ ማዳበሪያዎችን የመጠቀም፣ ጸረ አረምና ጸረ ተባይ መርዞችን የመርጨት ልምዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡
በመስክ ምልከታችን እንዳስተዋልነው በ300 ሄክታር መሬት ላይ እየተዘራ የነበረው የበቆሎና የቦሎቄ ምርጥ ዘር ከሰላሳ ደቂቃ በኋላ እግር በእግር የጸረ አረም መድኃኒት ተረጭቶበታል፡፡ ቴክኖሎጂው ቀደም ሲል የነበረ ቢሆንም አርሶ አደሩ ግን እምብዛም ሲተገብረው እንዳልነበር በቦታው ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች እና የግብርና ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአረም ዳይሬክተር ከፍተኛ ባለሙያ ካሳሁን ዘውዴ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳስረዱት፤ ጸረ አረም መድኃኒት በሦስት ዓይነት መንገድ ሊረጭ ይችላል፤ እነዚህም ዘር ከመዘራቱ በፊት፣ ዘር እየተዘራ እያለ እና ዘር ከተዘራ በኋላ (በቡቃያነቱ) ናቸው፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ እንደ ኬም ቴክስን የመሳሳሉ ጸረ አረምና ጸረ ተባይ መድኃኒትን የሚያስገቡ ድርጅቶች በየጊዜው ዓለም የደረሰባቸውን መድኃኒቶች ለሀገራችን ያስተዋውቃሉ፡፡ ይህ መድኃኒት በቀጥታ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ከሀገሪቱ የአየር ጸባይ ፣ ከአፈሩ ባህሪ ፣ በአጠቃላይ ከአግሮ ኢኮሎጂው ጋር የተጣጣመ መሆኑ በጥናት ይረጋገጣል፡፡ የንጥረ ነገር ይዘቱ፣ መጠኑ፣ የሚኖረው አስተዋጽኦና የሚያሳድረው ተጽእኖም እንዲሁ በጥናት ይለያል፡፡
ካሳሁን (ዶ/ር) የጥናት ልምዳቸውን ሲያካፍሉ “ከውጭ የሚገቡ በርካታ የጸረ አረም መድኃኒቶች ወደ ኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት መጥተው ወደ ተመራማሪዎች ሳይላኩና እውቅና ሳይሰጣቸው ጥቅም ላይ አይውሉም፡፡ እኔም በዘርፉ ተመራማሪ እንደመሆኔ የአሠራር ሂደቶችን ተከትዬ ከኢኮሎጂው ጋር እንዲጣጣሙ ምርምር እና ጥናት አደርጋለሁ፤ በጥናት ሂደቱ በመርዙ ላይ የተቀመጠው መመሪያ እንደ ሀገሪቱና አካባቢው ኢኮሎጂ መሠረት ተጠንቶ መጠኑ እንዲጨምርም እንዲቀንስም ሊደረግ ይችላል፡፡ ይህን ለማድረግ በሰብሎች ላይ የሚያመጣው ተፅእኖ ምንድነው? መርዙ አረሞችን መቆጣጠር ችሏል ወይስ አልቻለም? ኢኮኖሚያዊ አዋጭነቱ ምን ያህል ነው? በእዚህ መልክ ተጠንቶ ሙከራ ከተደረገ እና ውጤታማ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል፡፡ ይህን አሠራር ደግሞ መድኃኒቱን ያመረተው ኩባንያ ቢሆን የሚደግፈው ነው፡፡
ለምን ቢባል ለምሳሌ አውሮፓ ያለው የአፈር አይነት፣ የአረም አይነት እና የአየር ጸባይ እዚህ ካለው ጋር ሊለያይ ይችላልና ነው፡፡
ለአርሶ አደሩ እንዲደርሰው የሚደረገውና ጥቅም ላይ የሚውለው በእዚህ መልክ ሲያልፍ ነው ይላሉ፡፡
ዛሬ በተረጨው የጸረ አረም መርዝ ላይ ምርምር ያደረግኩት ራሴው በመሆኔ የአረም መርዙ ይሄን ሂደት አልፎ የመጣ መሆኑን ላረጋግጥ እችላለሁ፡፡ ከአካባቢው ኢኮሎጂ ጋር እንዲጣጣም አድርጌ ጥናት ያደረግሁበት ይህ የጸረ አረም መርዝ ስሙ “ሹር ስታር” ይባላል ነው ያሉት፡፡
ከምርምራችን ውጤት ተነስተን በሰጠነው ምክንያታዊ አስተያየት (ሪኮማንዴሽን)መሠረት በሄክታር ሦስት ሊትር የሚረጭ ነው፡፡ መርዙ ሰፋፊ ቅጠል ያላቸውን እና የሳር አረሞች በተመሳሳይ ጊዜ ከመብቀላቸው በፊት የሚቆጣጠር ነው፡፡ በአፈር ውስጥ ያሉ አረሞች ከመብቀላቸው በፊት እዚያው አድርቆ ያስቀራቸዋል፡፡
ካሳሁን (ዶ/ር)፤ የጸረ አረም መርዝ አምራች ሀገራት ጤፍን የማምረት ልምድ ስለሌላቸው እንደ በቆሎና ስንዴ ሁሉ ለጤፍ የሚሆን ጸረ አረም መርዝ አያመርቱም ይላሉ፡፡ ነገር ኬም ቴክስ የተባለው ድርጅት ፓላስ የሚባለውን ጸረ አረም እና ጸረ ተባይ መርዝ በማስገባት በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች ዳግም ምርምር እና ጥናት እየተደረገበት ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡ በእዚህም ከፍተኛ ውጤት ታይቷል፡፡
አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም እርሻ መሬቱን እና አቅሙን ወደ አንድ አምጥቶ የመሥራቱን ልምምድ የበለጠ ቢያሳድግ፤ የግብርና ፓኬጆችን የመጠቀም እድሉ ይሰፋል። የግብርና ፓኬጆችን መጠቀም ደግሞ ምርታማነትን ያሳድጋል” ይላሉ፡፡
ግብርናውን ግንባር ቀደም የኢኮኖሚ ምሰሶ ማድረግ ከታሰበ ሙሉ ፓኬጆችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ለእዚህም የመጀመሪያው ርምጃ ኩታ ገጠም እርሻን ማስፋፋት እንደሆነ ካሳሁን (ዶ/ር) ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
የቡልቡላ ደንበል መስኖ ልማት ኅብረት ሥራ ዩኒየን ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኡካ ገመቹ በበኩላቸው ሲያስረዱ፤ ማህበሩ አራት መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማህበራት ተጣምረው የፈጠሩት፤ 201 አባላት የታቀፉበት እና መነሻ ካፒታሉም 633 ሺህ ብር ነው፡፡ መሬቱን ከተረከቡ ወራት እንዳስቆጠሩ ገልጸው፤ በአጭር ጊዜ አርሰው የመኸር ምርት ለማምረት እንደ ዘሩ ይናገራሉ፡፡ መደራጀታቸው የግብርና ፓኬጆችን ለመጠቀም እንዳስቻላቸው ይገልጻሉ፡፡
እየተዘራ ያለው በቆሎ ሳይንሳዊ መንገድን ተከትሎ ማሽን በመጠቀም መሆኑና ማዳበሪያም አብሮ የሚፈስ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ከ30 ደቂቃ በኋላም የጸረ አረም መርዝ በማሽን ይረጫል ይላሉ፡፡ የበቆሎ ቡቃያው ሲበቅል የአረም ተጽእኖ ሳይኖርበት ብቻውን ይበቅላል፡፡ ይህም ድካምና ወጪን ይቀንሳል፤ ምርታማነትን ያሳድጋል ሲሉ አቶ ኡካ ገልጸዋል፡፡
ኢያሱ መሰለ