በዓለም የፖለቲካ ታሪክ የሚጠላትን አገር የመምራት እድል ያገኘ ብቸኛው ፓርቲ ሕወሓት ነው። በጎሰኝነት አስተሳሰብ፣በመጥበብ ፖለቲካ የተካኑት አሻባሪው ሕወሓት አባላትና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ኢትዮጵያን ለመጥቀም ከተጓዙባቸው ይልቅ ለማፍረስ የሄዱባቸው ጎዳናዎች ረጅምና አሰልቺ መሆናቸው የማይካድ ሃቅ ነው።
የቡድኑ አመራሮችና ደጋፊዎችም፣የማእከላዊ መንግስቱን ስልጣን በተቆጣጠሩበት ሃያ ሰባት አመታት ውስጥ አረመኔና ጨካኝ መሆናቸው በሚያስመሰክር መልኩ ለማየት የመስማትም ሆነ ለመንገር የሚዘገንኑ ኢ – ሰብአዊ ድርጊቶችን ፈፅመዋል።
በተለይ በዘመድ አዝማድ በመቧደን በዘር በመመዳደብ፣ በሚያስገርም፣ በሚያስደነግጥና በሚያስተዛዝብ መልኩ ኢትዮጵያን መዝብረዋል። እንደመዥገር ተለጥፈው የኢትዮጵያን ደም በመምጠጥ በሃብት ላይ ሃብት አግበስብሰዋል። ከሃያ ዓመታት በፊት ያልነበራቸው ሃብት አካብተዋል።
አባላቱ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሃብት ከዘረፉባቸው በርካታ መንገዶች አንዱ እርዳታ ቀዳሚ ነው። እ ርዳታ ለአሸባሪው ሕወሓት መክበሪያው ነው። ወያኔ ከበረሃ ወጥታ አዲስ አበባ እንድትገባና በእግሯ እንድትቆም ያደረጋት በድርቅ ለተጎዳ ሕዝብ የመጣ እርዳታ ነው።
ወያኔ ለህዝብ የመጣን እርዳታ እህል ሳይቀር የሚዘርፍ ሌባ፣ዘራፊና በቅጥፈት የተሞላ የማፊያ ድርጅት ስለመሆኑን ዋነኛ ማሳያ ደግሞ እ.ኤ.አ በ1984 የተከሰተውና በወቅቱ የቢቢሲው ጋዜጠኛ ሚካኤል ቡርክ‹‹በመሬት ላይ ለሲኦል የቀረበ ‹‹the closest thing to hell on Earth››ሲል የገለፀው ረሃብ ዋነኛ ማሳያ ነው።
በወቅቱ የወያኔ አባላት በዚህ ደረጃ አሰቃቂ ሆኖ የተገለፀውን ረሃብና የረኃብ ሰለባዎች ወደ ጎን በመተው ለነብስ ማዳኛ የመጣውን የሰብአዊ እርዳታ እህል ከታለመለት ዓላማ ውጭ ከዓለም አቀፍ ለጋሾችና አበዳሪ ድርጅቶች ጋር በመሞዳሞድ ለጦር መሳሪያ ግዥና ለግል ጥቅም አውለውታል።
ይህም የቀድሞ የማእከላዊ አባላቱ ሳይቀር በተደጋጋሚ በግልፅ በአደባባይ መስክረዋል። ጋዜጠኛ ማርቲን ፕላውትም የዘረፋ ቅሌቱን ለዓለም አጋልጦታል። ፕሮፌሰር ሀሰን ሰይድ‹‹መንግስታዊ ጥቃት በኢትዮጵያ፣ ሰብአዊ እርዳታ እና ሙስና›› በሚል ርዕስ ባሰነዱት መፅሃፍ በጥልቀት አትተውታል።
ቡድኑ ጫካ በነበረበት ጊዜ የጀመረው የዓለም አቀፍ የእርዳታ ስርቆት፣ ዘረፋና ሙስና የማይላቀቀው መናጢ አመል ሆኖበት በስልጣን በቆየባቸው ሃያ ሰባት አመታት ለምግብ፣ለመጠጥ ውሃ፣ ለመድሃኒትና ለትምህርት እየተባለ ወደ ኢትዮጵያ የሚፈሰውን እርዳት ቅርጥፍ አድርጎ በልቷል።
በኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ስልጣኑን ከተነጠቀ በኋላም የስልጣን አባዜ የሚያመጣው እብደት ከእኛ በላይ ላሳር በሚል ትእቢት ተወጥሮ እኩይ ምግባሩን ሲያስቀጥል ቆይቷል። በተለይም ኢትዮጵያን መምራት የምችለው ብቸኛ ድርጅት ‹‹እኔ ነኝ›› በሚል መረጃ እያምታታና በሚዲያ የበላይነት ራሱን የተሻለ አድርጎ ሲያቀርብም ቆይቷል።
የሽብር ቡድኑ ከዚህ የባንዳ ተግባሩ ባሻገር ኢትዮጵያን የሚፈልጋት እርሱ እስከገዛትና የትግራይ ብሄርተኝነት የበላይነትን ይዞ እስከቀጠለ ብቻ በመሆኑ ለ20 አመታት ነፍሳቸውን ሰጥተው ሲጠብቁት የነበሩ የሰሜን እዝ አባላትን አስከፊ በሆነ መልኩ በመጨፍጨፍ እና በማዋረድ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ግልፅ ጦርነት ከፍቷል።
ጦርነቱን ወደ አፋርና ወደ አማራው ክልል በመግፋት ለበርካቶች እልቂት፤ ምክንያት ሆኗል። ወጣት፣ሴቶች፤ ህጻናትና አዝውንቶች ጨፍጭፏል። ደፍሯል። የእምነት ተቋማትን አቃጥሏል። ለመተካት የማይቻሉ ቅርሶች ሰርቋል። አውድሟል። በድሃ ህዝብ የተሰሩ ክሊኒኮች፤ ሆስፒታሎች ዘርፏል። አቃጥሏል። በርካቶችን ከቀያቸው አፈናቅሏል። ለረሃብ አጋልጧል።
ይሑንና የቋመጠለትን ስልጣን መቆጣጠር ተስኖት፣በመጨረሻ‹‹በማንኛውም ግዳጅ ወይም ተግባር የላቀ ውጤት››በሚል እሴት የተገነባው፣በየትኛውም ሁኔታ በማንኛውም የአየር ፀባይ ማንኛውም ግዳጅ በውጤት የማጠናቀቅ አንፀባራቂ ድል የማስመዝገብ አቋምና አቅም ያለው የኢትዮጵያ ሰራዊትና የቁርጥ ቀን ልጆች ተቀጥቅጦ ወደ መጣበት ተመልሷል።
ይሑንና የቡድኑ አባላትና ጋሻጃግሬዎቻቸው የስልጣን አባዜ የሚያመጣው እብደት ከእኛ በላይ ላሳር በሚል ትእቢት ተወጥረው ፣ጤንነታቸውን በሚያጠያይቅ መልኩ ስልታዊ ማፈግፈግ ከሚለው ጀምሮ የበሬ ወለደ አይን ያወጣ የውሸት ፕሮፖጋንዳቸውን መንዛታቸውን አላቋረጡም። አዲስ አበባ ለመግባት የሰዓታት ጊዜ ነው የቀረኝ” በሚል ሲያደናግር የከረመው የጥፋት ኃይል ቆየት ብሎ ደግሞ ሌሎች የማደናገሪያ ፕሮፖጋንዳዎችን ሲያሰራጭ ተስተውላል።
ፕሮፌሰር ጋሬዝ ጃውት እና ፕሮፌሰር ቪክቶሪያ ኦዶኔል‹‹Propaganda and Persuasion››በሚል ርእስ እኤአ በ2011 ለንባብ ባበቁት መጽሐፋቸው፣ፕሮፖጋንዳ መረጃዎችንና ሀሳቦችን ሆን ብሎ በስፋት በማሰራጨት አንድን ግለሰብ፣ቡድን፣ተቋም፣ድርጅትና አገር ለመደገፍ ወይም ለመቃወምና ለማጥላላት በድግግሞሽ የሚሰራጭ የመረጃ ቅስቀሳ ዘዴ እንደሆነ በስፋት ያትታሉ።
ሌሎች ስመጥር የኮሚኒኬሽን እና ፖለቲካ ፀሃፍት እና ምሁራንም፣ፕሮፖጋንዳን በአይነት እና በአላማው በመከፋፋል በሶስት ይመድቡታል። ከሶስቱ ፕሮፖጋንዳ አይነቶች አንዱና እጅግ አደገኛው ደግሞ‹‹ ጥቁር ፕሮፖጋንዳ ‹‹Black propaganda››የሚባለው ስለመሆኑ ይጠቁማሉ።
‹‹ትልቁ ውሸት››በሚል ሌላ ቅፅላው የሚታወቀው፣ ይሕ አይነቱ የፕሮፖጋንዳ ዘዴ መረጃ ምንጩ የማይታወቅና በሬ ወለደ የፈጠራ ውሸት፣ ወሬ፣ ሀሜትና አሉባልታዎች እውነት አስመስሎ የማናፈስና የማሰራጨት ዘዴ መሆኑን ያስገነዝባሉ።
የውሸት ፕሮፖጋንዳ በአንደኛው የአለም ጦርነት በጀርመን የተለመደ የፕሮፓጋንዳ ቴክኒክ መሆኑንም የተለያዩ መረጃዎች ይመሰክራሉ። የውሸት ፕሮፓጋንዳ ሲነሳም ዮሴፍ ጉብልስ ‹‹The Master of Lies››አብሮ ይነሳል። ሰውየው የጀርመኑ ናዚ ፓርቲ እና የመሪው አዶልፍ ሂትለር አፈ ቀላጤ ሆኖ ለአመታት አገልግሏል።
ጎብልስ የውሸት ተዋናይ ነው። የውሸት አቀናባሪ፣ ዲስኩር ደርዳሪ ነው። የውሸት ፈላስፋ ነው። የውሸትን ጥግ ያውቀዋል። በውሸት ፈጠራ እና ውሸት የመዋሸት ቴክኒክ የተካነ ነው። በውሸት መሰናዶ የተዋጣለት ነው። ውሸት ለእርሱ በጣም ቀላሉ ነው። ሙያው ነው። ስራው ነው። የዕለት ጉርሱ፣ እንጀራው ነው።
‹‹ውሸት በተደጋጋሚ ከተነገረ በመጨረሻ ሰዎች እውነት ነው ብለው ይታለላሉ የሚል እምነት ያለው ጎብልስ፣አይን ባወጣ ቅጥፈቱ የገዛ ህዝቡን ማሞኘት ይችልበታል። ህዝቡን ግራ አጋብቶ ማወናበድ፣ምንም ቢፈጠር ምንም እንዳልተፈጠረ ፣ተሸንፎ እንደአሸነፈ በመሆን ተከታዮቹን በደስታና በድል አድራጊነት የሚያስፈነጥዝ ሰው ነው። በዚህ ዋሾነቱም በስርዓተ መንግስቱ የፕሮፓጋንዳ ሚኒስትር እስከመሆን በቅቷል።
በእርግጥ ውሸት የእውነትን አቅጣጫ ሊያዛባ ይችላል። ይሑንና ይህ አይነቱ የበሬ ወለደ ውሸት ፕሮፓጋንዳ የተገነባ ድርጅትም ሆነ ማንነት የጊዜ ጉዳይ እንጂ ማነሱና ማፈሩ ብሎም መፈራረሱ አይቀሬ ነው። በአገሬ ሰው ‹‹እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል››እንደሚለው መሰል ፕሮፖጋንዳ ውሎ ሲያድር ፍፃሜው ሁሌም የተገላቢጦሽ ይሆናል።
ውሸት ለስልጣን ዕድሜ ማራዘሚያነት ይጠቅመኛል የሚለው ጎብልስም ሆነ መሪው ሂትለር የመጨረሻ የጠጡ በውሸታቸው የተጠመቀውን መራራ እና አሳፊሪ ፅዋ ማስታወስ ግን መቼም ቢሆን እውነትን ሸፍኖ ማስቀረት እንደማይቻል ማረጋገጫን የሚሰጥ ነው።
የአሸባሪው ወሃት አፈ ቀላጤዎችና ጋሻጃግሬቻቸው የጎብልስ ልጆችም ከትላንቱ የጎብልስ እና መሪው ውድቀት ሳይማሩ የውሸት ፕሮፖጋንዳን ዋነኛ ታክቲካቸው ማድረጋቸውን የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። በእርግጥ በዚህ ተግባራቸው ለጊዜውም ቢሆን ተጠቅመዋል።
ስለ ሰው ልጆች የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ተቆርቋሪ ነን የሚሉት አንዳንድ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የቡድኑን እኩይ ሥራ ከማውገዝ ይልቅ ከወልቃይት እስከ ማይካድራ ምድር ድረስ በድብቅና በገሃድ በፈጸማቸው የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ሁሉ አይተው እንዳላዩ ሰምተው እንዳልሰሙ ብሎም ከጎናቸው እንዲቆሙ ማድረግ ችለዋል።
በተለይ በእርዳታን በሚመለከት፣ኢትዮጵያ በየቦታው የቁጥጥር ኬላ አስቀምጣ እንቅስቃሴውን አጓተተችብን እያሉ በየትዊተሩ እና ዓለምዓቀፍ መድረክ ላይ እርግማን የሚያዘንቡ ተቋማትና ባለስልጣናትን ማፍራትም ችለዋል።
ይሑንና የቡድኑ አባላት በኢትዮጵያውያን የጋራ ተጋድሎ በደረሰብት አስከፊ ሽንፈት ቅጭት ዛሬም እንደትላንቱ ከየአቅጣጫው ውሸቶችን ማስተጋባቱን ተያይዞታል። አመራሮችም እንደ ትላንቱ ሁሉ በንጹህ እንባና ደም እየነገዱ ናቸው።
ዛሬም ድረስ በለመደው ውሸትና ማስመሰል ህዝብ ያጭበረብራሉ። ውሸቱ አያልቅም አንዱ አልሰራ ሲል በሌላ ውሸት ይመጣሉ። ተርበን እንድናልቅ ዕርዳታ ዘጉብን በሚል ከምዕራባውያን አፍቃሪዎቹ ጋር በመሆን የተዛቡ መረጃዎችን ማሠራጨት በረሃብ እና ባለፈው ጦርነት በደረሠበትን ሠብዓዊ ቀውስ ለማትረፍ እየዳከሩ ይገኛል።
ጆሴፍ ጎብልስ መቃብር ፈንቅሎ ቢነሳ ሊቀናባቸው የሚችሉ ውሸቶችን እያስተጋቡም ናቸው። ይሕን ሃላፊነት ደግሞ የሕወሓቱ ጆስፍ ጎብልስ ወይንም የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በፊት አውራሪነት እየመራው ይገኛል።
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ እንደሚወርድና በተለይም ከአማራ ህዝብ ጋር የምናወራርደው ሂሳብ አለ እያለ ሲናገር ቅንጣት ታክል እፍረት ያልታየበት ጌታቸው ጦርነቱን ወደ አማራና አፋር ክልል በማስፋት ለመናገር የሚዘገንን ጥፋት በህዝብ ላይ ከፈፀመ እንስሳትን ሳይቀር በጥይት ከጨፈጨፈ፣ዛፎችን ከረሸነ በኋላ ዛሬ ሳናውቅ ነው የገደልናችሁ፣ የዘርፍናችሁ የማለት ድፍረትን አግኝቷል።
ሰውየው‹‹ዝርፊያ መፈፀማችን ትክክል አልነበረም፤ ወደድንም ጠላንም አማራ ወገናችን ነው››ወዘተ›› ንግግር በመቀሌ ላይ አድርጓል። የዚህ ንግግር አላማ የአማራ ሕዝብ መቆርቆር አይደለም። ዶሮን ሲያታልሏት ዓይነት ነው።
የአፈ ቀላጤው ንግግር በተለመደ የቅጥፈት ፕሮፖጋንዳ ትላንት በመንበረ ስልጣን እያለ ግንባር ቀደም ጠላቴ የሚል ማኒፌስቶ ቀርፆ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የአማራም ህዝብ ሲያሰቃይ መክረሙ ሳያንስ ዳግም ወደ ስልጣን እንድንምጣ እርዳኝና እንደቀድሟችን እንሁን አይነት ነው።
በተደጋጋሚ ስለ ትግራይ ሕዝብ ረሃብ፣ ስለ ሰብዓዊ ዕርዳታ አስፈላጊነት የሚደሰኩሩት፣ጌታቸውና አጋሮቹ በጣም በሚያስገርምና በሚያስደነግጥ መልኩ ለክልል ህዝብ የመጣን የእርዳታ እህል ዛሬም እንደ ትላንቱ የግል ጥቅም እያዋሉት መሆኑ ነው።
ይሕንንም አፈና እና ጭቆናው አንገሽግሿቸው ወደ አማራ ክልል የተሰደዱ ዜጎች ሳይቀር የመሰከሩት ነው። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያነጋገራቸው የትግራይ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉብርሃን ኃይሌም፣ የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል የሚላክ ቢሆንም ለሕዝቡ የሚደርስ እርዳታ የለም››ሲሉ ይሕኑ አረጋግጠዋል። ለትግራይ ሕዝብ የሚላከው እርዳታ ለሕዝቡ ሳይሆን ሕወሓት ራሱ ላደራጃቸው መደቦችና ታጣቂዎች እየተሰጠ መሆኑን ፓርቲያቸው ከተለያዩ ምንጮች እንዳረጋገጠ ገልጸዋል።
በሰብአዊ እርዳታ ሰበብ የሚደሰኩሩትን ጀምሮ በእያንዳንዱ ተግባር የጎብልስ ልጆች አላማ ሕዝብ እና ሰራዊቱን በስነ ልቦና ዘመቻ ለመፍታት መሆኑ እርግጥ ነው። ይሑንና ደግሞ ጠላትን ለማሸነፍ በአስተሳሰብ በልጦ መገኘት የግድ ነው።
ስለ ረሃብ፣ ስለ ሰብዓዊ ዕርዳታ ቀን ከሌት ሲወተውቱ የሚደመጡትም ለህዝብ ተጨንቀው አይደለም። ይልቅስ ለዳግም ውግያ ትጥቅና የስንቁን ጉዳይ በዚህ መንገድ ለማሳካት የሚመስል ነው። ቡድኑ አሁን ላይ የሆነ ሴራ እያሴረ መሆኑም እርግጥ ነው። የቡድኑ መሪ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለተመድ ዋና ጸሐፊ የላኩት ደብዳቤም ይህን የሚያረጋገጥና ዛሬም ለስልጣን እንደሚቀምጡ ፍንጭ የሚሰጥ ነው። መልእክቱንም አፍቃሪ ሕወሓቶቹ ሊንዳ ቶማሥ እና ማርቲን ፕላውት በማህበራዊ ሚዲያው በኩል አጋርተውታል።
ይሕ ደግሞ ሕወሓት አሁንም ለሰላም እጁን የመዘርጋት ፍላጎት እንደሌለው የሚጠቁም ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት አጎራባቾቹ የአማራ ክልል እና የአፋር ክልል የጸጥታ ኃይሎች ትኩረታቸውን ከቡድኑ ባለመለየት፣ጠንካራ ዝግጅት ማድረግ የግድ ይላቸዋል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 /2014