ለአንድ አገር የእድገትና የስልጣኔ ምንጭ ከሆኑ የማኅበረሰብ እሴቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ለበጎነት የሚያበቃው መልካም ሰብዕና ነው። መልካም ሰብዕና የሌለው አገርና ሕዝብ ነውር የሚያውቅ አዲስ ትውልድ መፍጠር አይቻለውም። ካለ መልካም ሰብዕና መልካም አገርና ትውልድ አይፈጠርም። ታላቅ አገርና ሕዝብ ለመፍጠር ከመነሳታችን በፊት መጀመሪያ እኛ የታላቅ አስተሳሰብና ስብዕና ባለቤቶች መሆን ይጠበቅብናል። እንደ ወላጅ አሁን ላይ ለልጆቻችን የምናስተምራቸው ምንድነው? ለታናናሾቻችን ምን ዓይነት ቤተሰብ ነን? ነገ ላይ በእኛ በኩል አገር የሚዋጁ ትውልዶች ይፈጠራሉ። አሁን የምንሆነው ነገር የነገዋን ኢትዮጵያ፣ የነገውን ትውልድ የመወሰን ጉልበት አለው። አገር እኮ የዜጎቿ የአስተሳሰብ ውጤት ናት። በየትኛውም እውቀት መዝኑት አገር ዜጎቿን ነው የምትመስለው ስለዚህም እኛ የኢትዮጵያ መልኮች ነን፤ ኢትዮጵያን የሳልናት እኛ ነን። አሁን ላይ እንደ ችግርም ሆነ እንደ መልካም ዕድል ከበውን ያሉ ነገሮች ሁሉ በእኛ ሰብዕና የተሳሉ ናቸው።
ሰብዕና ወንዝ ነው፤ ከግለሰብ ተነስቶ ወደ ማኅበረሰብ የሚፈስ። ከዜጎች ተነስቶ ወደ አገርና ትውልድ የሚጎርፍ። ኢትዮጵያም የትናንቶቹ አባቶቻችን ሥጦታችን ናት። እኛም በበጎና በተገባ የአባቶቻችን ሰብዕና የነገዋን ኢትዮጵያ የመፍጠር ግዴታ አለብን። በዘርና በጎሳ፣ በቋንቋና በቦታ እየተባላን የምናፈራው የጋራ ልዕልና የለም። በዓለም አቀፍ ደረጃ በአገራት መካከል የሚታየው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የስልጣኔ ልዩነት በዚያች አገር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች የፈጠሩት የአስተሳሰብ ልዩነት ነው። ሰብዕና ማረፊያው አስተሳሰብ ነው። በአስተሳሰቡ የላቀ ማኅበረሰብ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው የላቀ አገርና ሕዝብ ይፈጥራል። በሰብዕናው ምስጉን የሆነ የፖለቲካ ፓርቲ ነገ ላይ ታሪክ የማይረሳውን የአንድነት ግንብ ይገነባል እንጂ በሀሳብ ልዩነት ጦርነት አይከፍትም። በየትኛውም እውቀት መዝኑት አገራዊ ችግሮቻችን ከዜጎቻችንና ከፖለቲካ ፓርቲዎቻችን የሰብዕና ግድፈት የመነጩ ሆነው እናገኛቸዋለን። ዜጋ ጨዋነት ሲርቀው… አገር ሊመራ የተሰናዳ የፖለቲካ ፓርቲ ራስ ወዳድነትን ሲያስቀድም ትውልድ መረን ይሆናል። እነዚህ ሁሉ ችግሮች በአንድ ይሆኑና በጦርነትና በመለያየት የምታምንን አገር ይፈጥራሉ። ስለዚህ የሚያስፈልገን አገር ገንቢ ሰብዕና ነው። የሚያስፈልገን ከዛሬ አርቆ የሚያይ ዓይንና አእምሮ ነው።
የሰው ልጅ የመጀመሪያው ጥበብ፣ እግዚአብሔርን መፍራት ነው። እግዚአብሔርን መፍራት ደግሞ ከበጎ ስነ ምግባር የሚጀምር የአእምሮ ርምጃ ነው። ሰው ከሥርዓት ሲርቅ አውሬ ነው። ሰው በራስ ወዳድነት ሲረታ ምንም ነው። ለዚያም ነው አገር መታደግ አቅቶን አውሬም ምንምም የሆንነው። ሰብዕና ከግለሰብ የሚጀምር ሰፈርና መንደርን አካሎ አገር ላይ የሚያርፍ የዘመናዊ አስተሳሰብ ውጤት ነው። ዘመናዊነት መነሻውም መድረሻውም ማኅበረሰብ ነው። ማሰብ ስንጀምር..በእውቀትና በማስተዋል ስንበረታ ከማንም በፊት ቀድመን የምናየው ማኅበረሰባችንን ነው። ከምንም በፊት የምንረዳው የአንድነትን ኃይል ነው። በሥነ ምግባር ለታነጸና አርቆ ለሚያይ ባለአእምሮ ሕዝብ የምንም ነገር ቀዳሚ ጉዳዩ ነው። ብዙዎቻችን ግን ይሄን እውነት አናውቀውም፤ ለብዙዎቻችን ስልጣኔ ከራስ እውነትና እሴት መራቅ ነው የሚመስለን። ከራስ እውነት መሸሽ፣ ከራስ ማህበራዊ ልማድ ማፈንገጥ ነው የሚመስለን። ዘርና ብሔርን መሠረት ባደረገ የእኔነት ስሜት አገር የሚገነባ የሚመስለንም ሞልተናል። እንደ ዜጋም፣ እንደ ፖለቲካ ፓርቲም ከዚህ አፍራሽ አመለካከት መውጣት አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ቀዳሚው መስፈርት ነው።
ስልጣኔ በምንም መልኩ ራስን አያስክድም። በምንም መልኩ ባህልና ሥርዓትን አይደፍርም። በምንም መልኩ መረንና ራስ ወዳድ አያደርግም። በምንም መልኩ ተነጋግሮ የመስማማትን ጥበብ አይሰውርም። የዘመነ ጭንቅላት ከሥርዓትና ከነውር ወጥቶ አያውቅም። ራሳችንን መፈተሽ ይኖርብናል። ትልቅ አገርና ሕዝብ ይዘን በአንድነት መቆም ያልቻልነው ለምንድነው ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። ሰፊ ታሪክ፣ ጥልቅ ባህል ከቦን የማንረባ ሆነን የቆምነው ለምንድነው ስንል እንጠይቅ። ለብዙዎቻችን አራዳነት ሥርዓትን መተው፣ ነውር አለማወቅ ወይም ደግሞ ከባህልና ወግ ያፈነገጡ ድርጊቶችን መከወን ነው። ይሄ ግን የዘመናዊነት ባህሪ አይደለም። ይሄ በማኅበረሰባችን ተረት «ከርሞ ጥጃነት» ነው። ስልጣኔ ከትናንት ሌላ መሆን፣ ከአምናው አንድ ርምጃ ፈቀቅ ማለት ነው። አሁን ላይ ብዙዎቻችን ስልጣኔ ሳይገባን በከንቱ የምንኖር ነን። መልካም ስብዕናን ሳንላበስ ብሩህ ነገን የምንናፍቅ ነን። ተነጋግረን ሳንግባባ ትልቅ ተስፋ የምንጠብቅ ነን። መልካም ነገሮች ያሉት በመልካም አመለካከት ውስጥ እንደሆነ ገና አልገባንም።
በአንድ አገር ላይ ለውጥ ለማምጣት ትምህርትና የመሳሰሉ ዋጋ ያላቸው ነገሮች ብቻቸውን በቂዎች አይደሉም። እውቀት ያለ መልካም ሰብዕና ዋጋ የለውም። አሁን ላይ ለአገራችን ችግር እየሆኑ ያሉት የተማሩ ግለሰቦች ናቸው። ከትናንት እስከዛሬ የስጋታችን ምንጮች ፊደል የቆጠሩ እናውቃለን ባዮች ናቸው። ብዙ ያልገቡን ነገሮች እንዳሉ ይሄ አንዱ ማሳያ ነው። ትምህርት ለአንድ አገር የስልጣኔ ዋልታና ማገር ሆኖ ሳለ እኛ ግን ለችግርና ለመከራ እንጠቀምበታለን። መማር ከትናንት እስከዛሬ አበሳ የሆነባት አገር ላይ ነን። መማር እኮ ክፉ ነገር ሆኖ አይደለም፤ መማር መቼም የትም ክፉ ሆኖ አያውቅም፤ እንዲያውም ዓለም የአሁኑን ስልጣኔ ያገኘችው ፊደል በቆጠሩ ባለ አእምሮዎች ነው። ችግሩ ያለው ከእኛ ነው። ምክንያቱም ስንማር በኩረጃ ነው፣ ስናልፍ በሙስና ነው። ወደ ስልጣን ስንመጣ በብሔር ነው። አገርና ትውልድን መሠረት አድርገን የተራመድንበት አንድም የፍትህ ጎዳና የለንም። በጣም የሚገርመው ደግሞ ዛሬም ያን ትናንትና ብዙ ዋጋ የከፈልንበትንና የተወለካከፍንበትን ጎርባጣ ጎዳና መድገማችን ነው። ልባችንን ለክፋት እያስገዛን የምናስበው ሀሳብ፣ የምንቀመጠው ስብሰባ፣ የምንመራው ሰልፍ፣ የምንማረው ትምህርት ያጠፋናል እንጂ አይጠቅመንም። ከምንም በፊት ጥሩነትን መማር አለብን፤ ከምንም በፊት ሰውነትን እንልመድ። ከምንም በፊት አገርና ትውልድን እናስብ። ከምንም በፊት ፈጣሪን እንፍራ። ይሄ ሁሉ በሌለበት ሁኔታ ተምረንም ሆነ ባንማር የምናመጣው ለውጥ የለም።
ውስጣችሁ ርህራሄ ይኑር፤ በመልካምነት ካልታገዘ መማር ብቻውን ጥቅም የለውም። ከሚሠሩ እጆች እኩል፣ ከሚያስቡ ጭንቅላቶች እኩል መልካም ሰብዕና ያስፈልገናል። ሁላችንንም የሚያስማማ አንድ እውነት ቢኖር ኢትዮጵያ ተምረናል በሚሉ ክፉ ልቦች እየደማች መሆኗ ነው። ከእንግዲህ ለምትፈጠረው አዲሲቷ ምድር ግን መባረክን እናስቀድም። የተባረከ ልብ ባይማርም የተማረ ነው። የተባረከ ልብ በወዳጁ ላይ ክፉ አያደርግም። የተባረከ ልብ ለሥርዓት የተገዛ ነው። ድሮነትን ሳስብ እደነቃለሁ፤ ፈጣሪ አምላክ በአባቶቻችን ልብ ውስጥ በዝቶና ተትረፍርፎ ነበር እላለሁ። እንደዛማ ባይሆን ባልሰለጠነ ዓለም ላይ ቆመው ለዘመናዊው ዓለም ትዕንግርት የሆኑ አክሱምና ላሊበላን አያንጹልንም ነበር። እንደዛ እማ ባይሆን በጦርና ጎራዴ ታንክና መድፍ አይማርኩም ነበር። እንደዛማ ባይሆን ከእኔና ከእናንተ ተሽለው ዛሬም ድረስ በመልካምነት አይጠሩም ነበር። እነርሱ የጥሩ ሰብዕና ባለቤቶች ነበሩ። ነውር የሚያውቁ በባህላቸው የተገሩ የመልካም ነፍስ ባለቤቶች ነበሩ። ለትውልድ የሚቀር መልካም ሥራ እንሠራ ዘንድ የዋሆቹን አባቶቻችንን መምሰል አለብን።
ብዙዎቻችን አሁን ላይ የምንማረው አገር ከመጥቀም ይልቅ አገር ለመጉዳት እየሆነ ነው። ስለሚያበላ ሥራ፣ ስለሚያተርፍ ንግድ እንጂ፤ እንዴት አድርገን አገራችንን እንደምንጠቅም አናስብም። መጀመሪያ ለአገራችን እንኑር፤ መጀመሪያ ቅደም ተከተላችንን እንወቅ።
ለአገራችን መኖር ከጀመርን አገራችን የምትከፍለን ብዙ ነገር አላት። ችግሩ ከፈረሱ ጋሪው ሆኖ ማስቀደም ያለብንን አለማወቃችን ነው። ሕይወት በሁኔታዎችና በሀሳብ የተቃኘ ቅደም ተከተል አላት። በእዚያ ቅደም ተከተል ውስጥ መጓዝ ስንችል ብቻ ነው ለራሳችንም ለሌሎችም ልክ የምንሆነው። አሁን ላይ እንደ አገር ቅደም ተከተላችን ተዛብቷል። ወደ ኋላ ተመልሰን የተውነውን፣ የረሳነውን ነገር ማስተካከል አለብን። መጀመር ካለብን መጀመር ይኖርብናል። እንደ አገር መቅደም ያለበትን ማስቀደም ካልቻልን ውስብስብ ችግሮችን እየፈጠርን ነው የምንሄደው። በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ምድር መቅደም ያለበት ሰላም ነው። እርቅ ነው። አንድነትና ወንድማማችነት ነው። እኚህ የህልውና በኩሮች እውቅና ባላገኙበት ሁኔታ ላይ የምናመጣው ለውጥ አለ ብዬ አላስብም።
እስኪ ይሄን ጊዜ ለኢትዮጵያ እንስጥ። ችግሮቻችንን የምናስተካክልበት፣ ተነጋግረን የምንግባባበት ይሁን። እስኪ ከእንግዲህ ባለው ጊዜአችን፣ ከእንግዲህ ባለው ወጣትነታችን፣ ከእንግዲህ ባለው የስልጣን ዘመናችን ከእኔነት ሸሽተን አገራችንን እናስቀድም። ያኔ የምንፈልገው ነገር ሁሉ በራሱ ጊዜ መስተካከል የሚጀምር ይመስለኛል። ምክንያቱም ማስቀደም ያለብንን አስቀድመናልና። መልካም አስተሳሰብን ሳንይዝ የምንሻገረው ወንዝ፣ የምናሳካው ህልምና ራዕይ የለም። ራሳችንን በሰብዕና ሳንገነባ የምንጀምረው ማንኛውም ነገር ጊዜአዊ ነው። ሰብዕና የማንነት መስተዋት ነው። ራሳችንን የምናይበትና የምናሳይበት ነጸብራቃችን ነው። ማን እንደሆንን፣ ከየት ተነስተን ወዴት እንደምንሄድ የምንመራበት አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያችን ነው። የዚህ የሰብእና ማረፊያ ደግሞ አገርና ሕዝብ ከፍ ሲል ደግሞ ትውልድ ነው።
በሕይወት መንገድ ላይ የሚወድቁ ሰዎች ራሳቸውን በሰብና ያልገነቡ ናቸው። ራሳቸውን በሰብዕና የገነቡ ሰዎች አይወድቁም፤ ቢወድቁ እንኳን ዳግም ለመነሳት የሚያስችል ሙሉ ኃይል አላቸው። አሁን ላይ አገራችን እየተቸገረች ያለችው በወጣቱ የሰብዕና ግድፈት ነው። ከአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር ከፍተኛው ወጣት በሆነባት አገር የሰብዕና ግንባታ የአንበሳውን ድርሻ መያዝ አለበት። በአእምሮና በስነልቦና ያልተገነባ ወጣት ጥፋት እንጂ ልማት አያውቅም። አላማችን ታላቅ አገርና ሕዝብ መፍጠር ከሆነ ወጣቱ በስነ ምግባር መታነጽ አለበት። የፖለቲካ ፓርቲዎች ከክሽፈት ወጥተው መታደስን ይማሩ። ያ ካልሆነ ህልማችን ፍሬ አያፈራም። በሕይወታችን፣ በኑሯችን መላቅ ከፈለግን መጀመሪያ ልናደርገው የሚገባን በስነ ምግባራችን ተመስጋኞች መሆን ነው። ህልማችን ከሕይወት መላቅ ከሆነ ከሁሉ በፊት ራሳችንን ለማኅበረሰቡ የተገባ ነፍስና ስጋን እናልብሰው። አገር የማኅበረሰብ መፈጠሪያ ናትና።
ማኅበረሰብ የማያውቀው፣ አገርና ሕዝብ ያልተቀበለው ሰውነት ምን ቢያምር ዋጋ አያወጣም። ዋጋችን ያለው ማኅበረሰባችን ጋ ነው። ሕዝብ እንዲወደን ሕዝብ እንዲመርቀን ሆነን እንኑር። ሕዝብ ከጠላን የምንሄድበት የሕይወት ጎዳና አይቀናንም። ለዚህ ደግሞ የመልካም ሰብዕና ባለቤት ሆኖ መኖር ከፍ ያለ ዋጋ አለው። ከትናንት እስከዛሬ ዓለም ላይ ያሉ ስኬታማ ሰዎች ከስኬት ለመድረስ ከትጋታቸው እኩል አንጸባራቂ ሰብዕናን የተላበሱ እንደሆኑ ይነገራል። እንደዚሁም በሳይንሱ ዘርፍ የሚገኙ በርካታ ፈላስፎች መልካም ሰብዕና ወደፈለግንበት ስፍራ የምንጓዝበት እንቅፋት አልባ ጎዳና ነው ይላሉ። እዚህ ጋ ሰብዕና ስንል እያንዳንዱን ድርጊታችንን ያጠቃልላል። አለባበስ፣ አመጋገብ፣ አነጋገር፣ ከሰዎች ጋር ያለን መስተጋብር ለባህልና እሴት የምንሰጠው ዋጋ፣ ለታላላቆቻችን ያለን ክብር፣ ለቤተሰቦቻችን በአጠቃላይ ለማኅበረሰቡ ያለንን አተያይ የሚያጠቃልል ነው። አገር ወደ ፊት እንድትቀጥል በጥሩ ስነምግባር የታነጹ ህልም ያላቸው ዜጎች ያስፈልጓታል። ይሄ ባልሆነባት አገር ላይ ሕዝብም ሆነ መንግሥት ያለትውልድ የሚሆን አመርቂ ሞራል አይኖረውም።
የብዙዎቻችን ነገ የሰመረ ይሆን ዘንድ በራዕይ መኖር ግድ ይለናል። ለዚህ ደግሞ የተባረከ ልብ ያስፈልገናል። መባረክ መማር አይደለም፣ መባረክ ብልጠት አይደለም፤ መባረክ በእኛ መኖር ሌሎች እንዲኖሩ መፍቀድ ነው። መባረክ በደግነትና በቅንነት ወደ ፊት መራመድ ነው። መባረክ ለአገርና ለሕዝብ ሲሉ ሁሉን መተው ነው። ወዴትም ይሁን ለምናደርገው ጉዞ ጥሩ ሰው መሆን ከፍ ያለ ዋጋ አለው። የምንራመደው በእግራችን ቢሆንም፣ የምናስበው በጭንቅላታችን ቢሆንም የምንመራው ግን ውስጣችን በተከልነው ማህበረሰባዊ እሴት ነው፤ እርሱም ሥርዓት ይባላል። መልካም ሰብዕና በዙሪያው በርካታ ንቦችን እንደሚሰበስብ ሸጋ ጠረን እንዳለው አበባ ነው። የመጨረሻው የውበት ጥግ፣ የመጨረሻው የስልጣኔ መገለጫም ነው። እርሱ መልካም የሚሸት የነፍስ ሽቶ ነው። ውብ..ውብ የምንሸትበት፣ ቆንጆ…ቆንጆ የምንጠርንበት እጹብ የሕይወት መዐዛ እለዋለሁ። ኢትዮጵያን የምንወድ ወጣቶች በዚህ እውነት እንኑር። ነጋችንን በዚህ ዘለዓለማዊ እውነት እንገንባ።
ያለ እኛ ኢትዮጵያ ምንም ናት፤ መኖራችን ለአገር ይጠቅማልና ስንኖር በምክንያትና በስሌት ይሁን። በተገራ ማኅበረሰባዊ ሥርዓት መራመድ ድሀዋን አገራችንን ወደ ፊት ያራምዳታልና የሚጠቅመንን ለይተን እንወቅ። ሰብዕናችሁ ላይ እክል ካለ አሁኑኑ ቆም ብላችሁ ራሳችሁን ለማስተካከል ሞክሩ እንጂ ከነ ግድፈታችሁ ወደ ፊት ለመሄድ አትሞክሩ። ልሂድ ብትሉ እንኳን አይቻላችሁም። ልሂድ ብትሉ እንኳን መንገድ ላይ ነው የምትቀሩት። ፍሬኑ የተበላሸ መኪና ታውቃላችሁ? ሰብዕናው የተበላሸ ሰው ፍሬኑ እንደተበላሸ መኪና ነው። ሁለቱም ሩቅ መሄድ አይችሉም፤ ቢሄዱ እንኳን ፍጻሜአቸው ገደል መግባት ነው። የአገራችን አሁናዊ ችግሮችም እንዲህ ናቸው። ዛሬ ላይ አገራችንን ገደል እየከተቱ ያሉ አስተሳሰቦች፣ ድርጊቶች የዚህ ፍሬ ውጤቶች ናቸው። ሰብዕናው የተበላሸ ወጣት፣ ሰብእናው የተበላሸ የመንግሥት ባለስልጣን፣ ሰብእናው የተበላሸ ተማሪ ይዘን ወዴትም መሄድ አንችልም። መጀመሪያ ፈርሰን እንሠራ። እየሄድን የምንቆመው፣ እየገነባን የምናፈርሰው፣ እየሳቅን የምናለቅሰው መሠረታችን ስለተበላሸ ነውና ገደል ከመግባታችን በፊት የሕይወታችንን መሪ ሰብዕናችንን እናስተካክል እያልኩ ላብቃ። ሰላም!
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 /2014