እንደምን አላችሁልኝ ውድ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አንባቢዎች:: በቅድሚያ እንኳን ለፋሲካ በአል በሰላም አደረሳችሁ። ለዛሬው ከአንድ ወዳጄ ጋር በስልክ ባደረግነው ውይይትና ጨዋታ ላይ የቀረበልኝ ድንገቴ ጥያቄን በማንሳት ላይ አተኩራለሁ። ነገሩ እንዲህ ነው፤ ከዚህ ወዳጄ ጋር በስልክ እየተጨዋወትን ሳለ በመሃል ጨዋታዬን አቋረጠኝና “እውነት ምንድነው?” ሲል ድንገተኛ ጥያቄ አነሳልኝ። በቀጥታ ጥያቄውን ለመመለስ ብሞክርም እውነትን እንዲህ ነው ብሎ በአንድ አረፍተ ነገር ብቻ ቋጥሮ ለማስረዳት ባለመቻሌ፤ ጥያቄውን ወደ እናንተ ይዤው መጥቻለሁ። በእርግጥ “እውነት” ምንድ ነው?
እውነት ምን እንደሆነ በትክክል ለመረዳት፣ የሰው ልጅ ከአንድ ሚሊዮን አመት በላይ እንደፈጀበት የታሪክ ተመራማሪዎች ቢስማሙም፤ እውነት የተገለፀው በአንድ የፍርድ ወንበር ላይ ነበር። ለምሳሌ፣ አይሁዳውያን እየሱስ ክርስቶስን በመክሰስ በፍርድ አደባባይ ጲላጦስ ዘንድ ሲያቀርቡት እየሱስ መልስ አልሰጠም ነበረ። “ጲላጦስ ‘አንተ እንዲህ ሲከስሱህ ለምን ዝም ትላለህ? አንተ ንጉሥ ነህን? ንገረኝ’ አለው። ጌታ ኢየሱስም መልሶ፦ ‘እኔ ንጉሥ እንደ ሆንኩ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ፤ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል፤ አለው”። ጲላጦስም፣ እውነት ምንድነው? አለው።
የሰው ልጅ መልስ አጥቶ አንድ ሚሊዮን አመት የፈጀበትን ጥያቄ፣ እኔንም ጓደኛዬ እንደጠየቀኝ ሁሉ ጲላጦስም መልሶ እየሱስ ክርስቶስን “እውነት ምንድነው?” ብሎ ጠየቀው። እውነት በመስቀል ላይ፣ በመከራ ውስጥ መገኘቷን ብትሰቀልም ወደ ላይ ከፍ ከፍ የምትል፣ ብትቀበርም ሲኦልን የምትበረብር፣ ወደ ላይም የምታርግ፣ ፀንታም የምትኖር መሆኗን ከአንድ ሚሊዮን አመት በኋላ የሰው ልጅ እጅግ ዘግይቶ ቢያውቅም፤ አሁንም ድረስ “እውነት ምንድነው?” እያለ እንደ ጲላጦስ መጠየቁን ቀጥሏል። ምክንያቱም እውነት በደጋፊዎች ቁጥር ብዛት አትገለጽም። ለዚህም ማሳያው በኢየሱስ ላይ ከእውነታው የተቃረነ ፍርድ እንዲሰጥ ያጨበጨቡና የጮኹ ብዙዎች መሆናቸው ነው። ለዚህ ይመስለኛል የሰው ልጅ እውነት ምንድነው? የሚለው ጥያቄ ለመመለስ የሚቸገረው። እምነታችን አፋዊ እንጅ ልባዊ ባለመሆኑ ዛሬም ነገም እውነት ምንድ ነው እያልን መጠየቃችን ገና ይቀጥላል።
የእናንተን ባላውቅም በእኔ እምነት ግን የሰው ልጅ፣ በአዕምሮ ብቃቱና በስነ ልቦና አመለካከቱ፣ በፍላጎቱም ሆነ በልቦና መሻት አካባቢውን በራሱ ስሜትና ፍላጎት ተነሳስቶ ዓለምን ለመለወጥ ከፈጠረበት ምኞት ጀምሮ እስከ መቀየር፣ ከመፍጠር እስከ ማጥፋት፣ ደመ ነፍሳዊ እንቅስቃሴዎች፣ እንደሚያደርግ ግልፅ ቢሆንም፤ ከክፋት ደግነትን፣ ከመለያየት አንድነትን፣ ከጦርነት ሰላምን መምረጥ የአንድ ማሕበረስብ የስልጣኔ መለያው እውነት ነው ብዬ አምናለሁ።በዚህ ምክንያት በጋራም ሆነ በተናጠል የምናደርጋቸው ዘር ተኮር ጥላቻዎችና ፅንፈኝነት በሰው ልጆች ላይ ልናደርስ የምንችለውን የሞራል ልዕልናና ስነልቦናዊ ጉዳትንም አብረን ማሰብና መገመት ይኖርብናል።
ውድ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አንባቢዎቼ እናንተስ ምን ትላላችሁ?። በእርግጥ፣ የሰው ልጅ መቃብር እስኪዘጋበት፣ አፈር እስኪሸከም ድረስ ፍላጎቱን ለማርካት ሲል በማያቋርጥ ጉዞ የሚጓዝ መንገደኛ ቢሆንም፤ ሰው ራሱ በሰራውና በፈጠረው ውጤት የማይረካ፣ ያለኝ ይበቃኛል የማይል ለግል ዝና ሲል ስግብግብ በስጋዊም ሆነ በነፍሳዊ ፍላጎቱ እርካታን የማያገኝ እንደ ወንዝ ውሀ በጉዞ ላይ ያለ ፍጡር በመሆኑ እውነት ምንድ ነው? ብሎ ቢጠይቅ ብዙም ሊያስገርመን አይችልም።ታላላቅ የሚባሉ፣ በታሪክ መዛግብት ላይ ዛሬም ድረስ፣ ገና ወደፊትም ድረስ የሚዘከሩ ሰዎች ሳይቀሩ በአንድ ወቅት በሰሩት ሐገራዊ ስህተት እስከ መቃብር ድረስ ጥፋታቸው ተከትሎ በውኃ በተሞላው ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ታሪካቸው እንዳይገኝ ቀብሮ አስቀምጦታል።
እዚህ ላይ፣ ሰዎች አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ከሚያደርሱብን ህመም ለመፈወስ ብቸኛ ምርጫ ጥላቻና በቀል ሳይሆን ፍቅር አሸናፊ መሆንን አስመክረው የሰውን ልጅ ያስደመሙት የሩዋንዳ ሙሽሮችን ታሪክን ለአብነት ብጠቅሰው ደስ ይለኛል።እውነቱ እንደዚህ ነው ከ28 ዓመታት በፊት በሩዋንዳ በነበረው የዘር ፍጅት ባለቤቷን የገደለውን ሰው ይቅር በማለት አባቱ ሲገደል የ14 አመት ልጅ የነበረውን አልፍሬድና የዘር ማጥፋት በተፈፀመበት ወቅት የዘጠኝ ዓመት ታዳጊ የነበረችው የግራቲየን ሴት ልጅ የሷን ወንድ ልጅ እንድታገባ በመፍቀዷ በማህበረሰቡ ላይ የተዘራውን ጥላቻን ከስሩ ነቅለው ጥለውታል።
እአአ 1994 በ100 ቀናት ውስጥ 800 ሺህ የሚያህል ሩዋንዳውያን በተገደሉበት የዘር ጭፍጨፋ የተፈጠረውን የማህበረሰብ ቁስል እንዲሽር የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዕርቅና ሰላም ለማምጣት የራሷ ድርሻ ቢኖራትም፤ እነዚህን ሙሽሮች የሚያክል አለምን ያስደመመ ዜና ሊሆን ግን አልቻለም። ከዚህ የምንረዳው፣ “እውነት ማለት ከልብ ይቅር የመባባል ፍቅር” መሆኑን ነው።ፍቅር ማለት መከባበር፣ መለማመድ፣ መተሳሰብ፣ ይቅር መባባል መሆኑን ሩዋንዳውያን የሙሽሮቹ ወላጆች በልጆቻቸው ሰርግ ከእምነት ተቋማት እኩል ድርሻ በማበርከት ሐገራቸውን ከእርስ በእርስ እልቂት አትርፈዋታል።ለእኔ እውነት ማለት የሚሰጠኝ ትርጉም እንደዚህ ነው።
በእርግጥ እያንዳንዳችን ስጋ ለባሽ “ሰው” በመሆናችን ብዙ ስህተቶች ልንፈፅም ብንችልም፤ በመቻቻልና በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ባህል ካዳበርን በወዳጅነት ሰበብ ጥፋቶች ሁሉ በይቅርታ ይሰረዛሉ። ከታላላቅ በጎነቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ፍቅርም የሁላችንም ህግ አስከባሪ ዳኛ አሸናፊ ይሆናል። ፍቅር እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ የሚባሉ ውድድሮችን የማይደግፍ በመሆኑ እውነተኛ ስሜታችንን በቅንነት ስለምንገልፅበት ለጋራ ችግሮቻችን ሁሉ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት እውነቶች አንዱ ይሆናል። ብዙ ጊዜ በተሳሳተ አመለካከት ህዝብ በፍቅር እንዳይኖር እራሱ የሰው ልጅ ዋና ጠላት ቢሆንም፤ አንዳችን ለአንዳችን አስፈላጊ መሆናችንን አምነን በመቀበል ጠንካራ መተማመን ፈጥረን መልካም ግንኙነት እንድንመሰርት ይረዳናል።
ሰላምን ከወደድን ጦርነትን እንጠላለን። ሥርዓት አልበኝነትን ከጠላን ሥርዓትን እንወዳለን። በሌላ አነጋገር የፍቅር ተቃራኒ የሆነውን ጥላቻን እንጠላለን። ተቃርኖውን ሊፈታ የሚችለውን ውጥረት ማስወገድ ከቻል ደግሞ እውነት የሚለውን የሰው ልጅ የሞራል ልዕልና የበላይነትን ለማረጋገጥ ጥጉ ላይ ደርሰናል ማለት ነው። ሰሞኑን የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ ለጎዳና ተዳዳሪና ቤተሰብ ለሌላቸው ህፃናትና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አቅመ ደካሞ አረጋውያን በቤተ መንግሥትም ሆነ በከተማ አስተዳደሩ እንዲሁም ቅን ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው ያደረጉት ማዕድን የማጋራት መርሀ ግብር የዚሁ የአገራዊ መግባባቱ፣ የመተሳሰብና የመቻቻል ባሕል ምልክት በመሆኑ የሚበረታታ የሰባዕዊነት ተግባር ነውና መቀጠል ይኖርበታል።
እንደ ሩዋንዳዎቹ ዘር ተኮር ትንኮሳንና ጥላቻን ተፀይፈን የአካባቢያችንን መጥፎ ባህሪን ለመቀየር፣ ቂም በቀልን ቀብረን በመተሳሰብ ብሔራዊ ውይይት በማድረግ ችግሮቻችንን መፍታት እንደምንችል ካረጋገጥን አለም በእርግጥ ያከብረናል። አገራዊ አጀንዳችንን እውነት ለማድረግ ከገባንበት የጦርነት ቀጠና እንዴት ወደ ሰላም ድርድር ለመሸጋገርና ለመመካከር ቅን የሐይማኖት አባቶች፣ የበሳል ፖለቲካ አመራሮች፣ ታዋቂ ሰዎችና ምሁራኖች እንዲሁም የሞያ ስነ ምግባር የገዛቸው ጋዜጠኞች ያስፈልጉናል።ያስፈልጉናል ብቻ ሳይሆን የዝግጅቱ አስተባባሪ የመፍትሔው አካል ሆነው ለሃገራዊ መግባባት መሰለፍ ይኖርባቸዋል። ለእኔ እውነት ማለት ይህው ነው። እናንተስ ምን ትላላችሁ? ለዛሬው አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን።
ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 /2014