ታሪኩን ላልሰሙ ወይንም ለዘነጉ፤
ዲዮጋን ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ412 ዓ.ም ገደማ የኖረ የጥንታዊቷ ግሪክ ተወዳሽና ተጠቃሽ ዐይነ ሥውር ፈላስፋ ነበር:: ይህ ፈላስፋ በሰዎች አፍቃሬ ራስነት፣ ኃላፊነት ጠልነት፣ ስግብግብነትና እንደ ጀብድ ይቆጠር የነበረው የማኅበረሰቡ የአደባባይ ንቅዘት እያበሳጨው ውስጡን ጤና ስለነሳው ከሕብረተቡ ተገልሎ ቢኖርም፤ በበርካታ ተግባራቱ ግን “የብዙኃን ኅሊና ወኪል” ተደርጎ ይወሰድ እንደ ነበር ግለታሪኩ በዝርዝር ይነግረናል::
ዐይነ ስውሩ፤ ነገር ግን ልበ ብሩሁ ዲዮጋን፣ በአንድ ወቅት በጠራራ ፀሐይ የሚበራ ፋኖስ በእጁ አንጠልጥሎ የሰው ደን በሞላበት በደማቁ ከተማቸው ውስጥ ሲዘዋወር ያስተዋሉት የአካባቢው ሰዎች “ይኸ ሰው ለየለት!” እያሉ ሲያሙት በዝምታ እያዳመጠ ጉዞውን አላቋረጠም ነበር:: ጤንነቱን ለማረጋገጥ የፈለጉ ሰዎችም ቀረብ ብለው፤ “አንድም ዐይነ ስውር፣ አንድም ሰዓቱ የቀን እኩሌታ፤ ምን ይሁን ብለህ ነው ፋኖስ አብርተህ መንገድ ለመንገድ የምትንከላወሰው?” ብለው ሲሳለቁበት ቁጣውን ዋጥ በማድረግ፤ “እናንተ ዐይናማዎቹ የብርሃን ጌቶች! በመካከላችሁ ለሰው የሚተርፍ ታማኝ ሰው ጠፍቶ እየፈለግሁ ነው!” ብሎ ትዝብታቸውን በትዝብቱ አከሸፈባቸው::
ይህ ታሪክ ትዝ ያለው ተወዳጁ ገጣሚያችን የዲዮጋን ትዝብት የእራሱ አገር ትዝብት መሆኑን አረጋግጦ የውስጡን መራራ ስሜት በብእሩ የገለጠው እንዲህ በማለት ነበር::
“በዲዮጋን ጩኸት፤ በፀሐይ ጠራራ፣
አንድ ሰው ፈልገህ፤ ፋኖስ ብታበራ፣
… አለ ማለት ዘበት…
ከጎረምሳው አፍሮ፤ ካዛውንቱ ሽበት፣
ስንት ሺህ ሰው ቆጥረህ፤ አንድ የማትልበት፣
ሁሉም ባዶ ግርማ፤ ሁሉም ባዶ ውበት::”
የፈላስፋው የዲዮጋን “የሰው ያለህ ጩኸት” እና የገጣሚው ምፀታዊ ግጥም የሚያስተላልፉልን የጋራ መልእክት “ሰው የሚሰኝ ኅሊና አደር” የሰው ፍጡር መጥፋቱን ለመጠቆም ብቻ አይደለም:: ሰው ሆኖ በተሰጠው መንግሥታዊና ሕዝባዊ አደራ በቅንነት፣ በታማኝነትና በዝቅታ ለማገልገል ፈቃደኛ “ሰው” ያለመገኘቱን ለመግለጽ ጭምር እንጂ:: ሰው በምንፈልግበት ወቅት “ሰው ሆኖ በመገለጥ” ለሰውነታችን ክብር የሚሰጥ አገልጋይ መሪ እንኳንስ በፋኖስ ነበልባል ቀርቶ በተፈጥሮ የፀሐይ ብርሃን እየኳተንን ብንፈልግ ለማግኘት በእጅጉ መቸገራችን የጊዜያችንና የአገራችን እውነታ ነው::
ዲዮጋናዊ የመሪ ያለህ ጩኸታችን፤
እርግጥ ነው የልባችንንና የኅሊናችንን “ጆሮ” ሙሉ ለሙሉ ደፍነን ከሚሊዮኖች ጋር እየተተረማመስንና በሰው ጫካ ውስጥ እየኖርን “የሰው ያለህ!” እያልን መጮኹ “ጩኸታችንን ለለመዱት ምን ግዴዎች” እብደትም ቅብጠትም ተደርጎ ሊታሰብ ይችል ይሆናል:: “ከሰው መሃል ሰው ጠፍቷል” በሚል ተስፋ መቁረጥ ተውጠንና በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እየተደናበርን በዲዮጋን ፍልስፍና መቆዘማችንም ከበላያችን ለተኮፈሱት “ባለስልጣኖቻችን” ትርጉም ላይሰጥ ይችል ይሆናል::
ይሄን ስንል፡- በአመራር ብቃታቸው፣ በራእይ አቅማቸው፣ በህልማቸው ብሩህነት፣ በባህርያቸው ምስጉንነት “ነዎሩ!” የሚባልላቸው “ጥቂት የሰው ሰው ሹመኞች” ከገጸ-አገር ላይ ጠፍተው ጭርሱኑ “ዳዋ” ለብሰው አንቀላፍተዋል በማለትም በእዬዬ ማላዘን ፈልገንም አይደለም:: ቤተሰብን፣ አነስተኛ ቡድኖችን፣ ቤተ እምነቶችን፣ አገርንና ግዙፍ ተቋማትን መርተው የተጨበጨበላቸው፣ በምላሹም በአደባባይ ተከብረው አንቱታን ያተረፉ ኢምንት ምሳሌዎች ዛሬም በየሙያ መስኩ ብናስስ ይጠፋሉ ብሎ መደምደሙ ከእውነታ ጋር መጋጨት ይሆናል:: ዘመንና ታሪክን እያጣቀስን፣ ኅትመት ደጉንና ቴክኖሎጂውንም እያመሳከርን “ሰው በጠፋበት ዘመን ሰው ሆነው የተገኙ” አርአያ ሰብ ቅሪቶች ብናስስም ይጠፋሉ ማለት አይቻልም::
ይህ ጸሐፊ ሺህ ዘመናት ወደ ኋላ አፈግፍጎ ፈላስፋውን ዲዮጋንን ለማስታወስና የገጣሚውን ብእር ለማስረጃነት ሊያቀርብ ወደ ፈለገበት ዋና ምክንያት ዘው ብለን በድፍረት ስንዘልቅ፤ የአገልጋይ መሪነት እጦት ምን ያህል የከበደብን ሸክም እንደሆነ እንረዳለን:: የመሪነትን መንበረ ሥልጣን ተቆናጠው፣ በታጠቁት የፖለቲካ የብረት በትር እያስፈራሩ ማን ይነካናል ባይ “ጊዜ ወለዶች” መበራከታቸውን እያየን “ኡኡታችንን ብናቀልጥ” የሚቆጣን ይኖራል ብለን አንፈራም:: በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ይህን መሰሉ ሥር የሰደደ አገርና ሕዝብ ጎታች የሹመኞች ተግባር እንዲገታም ለእግዜሩና ለመንግሥታችን አቤቱታ ብናቀርብ መልስ ሰጭ ይጠፋ ካልሆነ በስተቀር አድማጭና “እውነት ነው” ባይ እናጣለን ብለን ግን በፍጹም አንጠረጥርም::
በጨበጡት ሹመት፤ “ሺህ ሞት ቢባል ይቀላል”፤ የሚመሯቸውን የበታቾችና የሚያገለግሉትን ሕዝብ ጩኸትና እዮታ ከቁብ ሳይቆጥሩ “መሪነት ተዋጥቶልናል፣ ግባችንም ሰምሮልናል” እያሉ በሕዝብ ብዙኃን መገናኛና በፓርላማው ፊት የሚዘባነኑትን በርካታ “ከረባት ለባሾች” መመልከት ብርቃችንም፤ ድንቃችንም አይደለም:: ተጽፎ የተሰጣቸውን ሪፖርት እንኳን በአግባቡ ማንበብ ተስኗቸው አንደበታቸው እየተሳሰረ፤ “የተሰጠንን ገንቢ ሃሳብ ለወደፊቱ አርመን እንመጣለን” በማለት በአንደበታቸው እየተናዘዙ በልባቸው የሚያፌዙ “ዘመን ከሎችን” ስንሰማ ውለን ስንሰማ ማደራችን የአገራችን ፖለቲካዊ ባህል ከሆነ ሰነባብቷል::
ፓርላማ ይሉት “ሥርዓት” በአገራችን ከተተከለበት ጊዜ ጀምሮ እንደ ስልጡኖቹ አገራት ተሞክሮ “በሥራ ሰንፈው፤ በስብሰባ የጀገኑ” ውጤት እርሙዎች “ኃላፊነቴን በአግባቡ አልተወጣሁም” ብለው ሲናዘዙ እንጂ ለመቀጣጫ ሲወገዱ ወይንም ራሳቸውን ሲያስወግዱ ሰምተንም ሆነ አይተን እንደማናውቅ ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ እጃችንን ጭነንም ቢሆን እውነታችንን በመሃላ ማረጋገጥ አይሳነንም::
እንኳንስ “ውጤት አልቦዎች” ከወንበራቸው ተገፍትረው ሊነሱ ቀርቶ እንዲያውም “ሕዝቡ ምን እንዳያመጣ ነው!” በሚል ውሳኔ ይመስላል፤ ወደ ተሻለ ከፍታ እየተወረወሩ “በውጭ አገራት ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴዎች” እየተባሉ ለየአገራቱ መንግሥታት የሹመት ደብዳቤያቸውን ሲያቀርቡ እያስተዋልን መንደድ መክሰላችን አልቀረም:: እኛ ዜጎች በንዴት በግነን ስንንጨረጨር አለቆቻችን እየሳቁ የልባቸውን ቢሰሩ አይገርመንም፤ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ መንግሥታዊ ባህላችን ነዋ!
አንድን ታላቅ አንጋፋ ተቋም አዘቅት ውስጥ ወርውሮ ያኮላሸ “የጊዜው ሰው” በሠራተኞቹ “ጾምና ጸሎት” ከቦታው በተነሳ ማግሥት አገርን በዲፕሎማሲው መስክ እንዲወክል መሾሙን ሲሰማ “ለምሳ ሊያደርጉኝ ሲያስቡ በቁርስ ተበቀልኳቸው” ብሎ የኮሎኔል መንግሥቱን ንግግር አወላግዶ ሲናገር የሰሙት የራሱ የቅርብ ብጤዎች ናቸው:: ከአንድ ታላቅ የትምህርት ተቋም ጋር ተያይዞ የተፈጸመ መሰል ታሪክም ተደጋግሞ በአደባባይ ሲወራ ስለከረመ ብዙዎች ያስታውሱታል::
ከደቡቡ የአገራችን ክፍል መንጭቶ በሁሉም አካባቢ ሕዝቦች ዘንድ ተወዳጅ የሆነውን “ሆያ ሰለሜ” የሚለው ባህላዊ ዜማና እንቅስቃሴ በዚህ ቦታ ቢታወስ ከጉዳያችን ጋር በሚገባ የሚገጥም ይመስለናል:: የሆያ ሰለሜ አቀንቃኝ ትእይንቱን የሚከውነው የመግረፊያ ጅራፍ በእጁ ይዞ በርካታ አጃቢዎችን ከኋላው በማስከተል ነው:: አጃቢዎቹ እሱ ካሰመረውና ከሚንቀሳቀስበት አቅጣጫ እንዳያፈነግጡ በዐይነ ቁራኛ መከታተል ብቻም ሳይሆን ያፈነገጡትን ሾጥ እያደረገ ወደ መስመር ያስገባቸዋል:: ማንኛውም አጃቢ የራሴ ነፃነት አለኝ ብሎ እንዳሻው በትእይንቱ አይሳተፍም:: ይህንን አደርጋለሁ የሚል ደፋር ከተገኘ የመጨረሻው ዕጣ ፈንታ ወይ ከጨዋታው መውጣት አለያም በጅራፉ መሸንቆጥ ይሆናል::
በዘርፈ ብዙው የአገራችን አመራር ውስጥ እየታየ ያለው ይህን መሰሉ የሆያ ሰለሜ ስልት ነው:: የሹሙ ርእይ ብቻ ካልሆነ በስተቀር የሌሎች ህልም እንዲነገርም ሆነ እንዲሰማ የማይፈለግባቸው ተቋማት በርካቶች ናቸው:: “የተሻለ ርእይና አሰራር ብንከተል ያዋጣል” ብለው ሃሳብ የሚያቀርቡ ሠራተኞች ወይንም ኤክስፐርቶች “ዐይናችሁ ላፈር” እየተባሉ ሲወገዙና በዘዴ ሲሸኙ ማስተዋልም የተለመደ ሆኗል::
በርካታ የአገራችን ፊት ቀደም መሪዎች ሁሌም የሚፈልጉት “እሶ እሶ” እየተባሉ እንዲካደሙ እንጂ፤ የሚመሩትን ሠራተኛና የተገልጋዮችን አስተያየቶች ለማድመጥና ለመታረም በፍጹም ዝግጁ ሲሆኑ አይስተዋልም:: ቀድሞውንስ ቢሯቸውን ማን ደፍሮት!? የቢሯቸውን ሥራ እንዲያግዙ ሳይሆን ለበረኝነት የተመረጡ በሚመሰሉ ጸሐፊዎቻቸው ወይንም ልዩ ረዳቶቻቸው አማካይነት ባለጉዳዮች ሲዋከቡ ማየትን ተላምደን እንደ ባህል ስለቆጠርነው ብንሰደብም ሆነ ብንንጓጠጥ የምናልፈው “ተው ቻለው ሆዴን” እያንጎራጎርን ነው:: የአንዳንድ ሹሞች የጥበቃ ጓዶች አስተያየትማ “አፈር ከመሬት የሚደባልቅ” ብጤ ስለሆነ በእነርሱ ግልምጫ ከመዋረድ “ክብርን ከጉዳይ ማስቀደሙ” በብዙ ይሻላል::
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ባለፉት ሁለት ዓመታት እግርና ጉዳይ ጥሎት ያንኳኳቸው መንግሥታዊ ቢሮዎችና የቢሮክራቶቹን ባህርይ በተመለከተ ምን መልክ እንደነበረው ጊዜው ሲደርስ ለዘመንና ለትውልድ ምስክርነት በሚበጅ መልኩ በመጽሐፍ ጥራዝ ሰንዶ ለማቅረብ እቅድ ስለያዘ ያኔ ዝርዝሩ በሚገባ ይተነተናል:: ያለ ምንም ማዳመቅና ግነት ዛሬ አሉን በምንላቸው የኢትዮጵያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና በየሥልጣን እርከኑ ደረጃ በሚገኙት መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ መብቴና ስብእናዬ ተከብሮልኝ ጉዳዬን ፈጸምኩ ብሎ የሚመሰክር አንድ ሰው ማግኘት ከተቻለ ይህ ጸሐፊ አድራሻና ባለ አድራሻውን በስም ጠቅሶ ለማመስገን ወደ ኋላ አይልም:: አርአያ ሰብ ብቻ ሳይሆን አርአያ ተቋም (Role model) ማግኘት በአገሬ ውስጥ የሰማይ ያህል እርቆናል የምንለውም ስለዚሁ ነው:: የዲዮጋንን ታሪክና የገጣሚያችንን ብእር አስታውሰን የዘከርናቸውም “እውነታችሁን ነው” ብለን ለማመስገን ጭምር ነው::
በጥንታዊው ግሪካዊ ልበ ብርሃን ፈላስፋ ታሪክ የተንደረደርንበትን ርእሰ ጉዳያችንን የምንቋጨው የዚያኔው የግሪክ አገር ሌላ አንድ ፈላስፋ ታሪክ በማስታወስ ይሆናል:: ይህ ፈላስፋ አርኪሜደስ በመባል ይታወቃል:: ብዙዎች የሚያውቁት የዘመናዊ ሂሳብ አባት መሆኑን እንጂ የፊዚክስ ሊቅ፣ ኢንጂነር፣ የክዋክብት አጥኚ እና የሌሎች የበርካታ ሳይንሳዊ ግኝቶችም ባለቤት መሆኑን ልብ አይሉም:: አርኪሜደስ በአንድ ወቅት ለአገሩ ንጉሠ ነገሥት የተሠራለት ዘውድ “ንጹሕ ወርቅ ነው አይደለም? ከሆነስ እንዴት ይረጋገጣል?” የሚል ፈታኝ ጥያቄ ቀርቦለት እንቆቅልሹን ለመፍታት ረጂም ቀናት ጠይቆት ነበር ይባላል::
አርኪሜደስን እረፍት የነሳው ይህ ፍቺ አልባ ውስብስብ ጥያቄ ቶሎ ምላሽ ሊገኝለት ባለመቻሉ ወደ ብስጭት መርቶት እንደነበርም ይነገራል:: አንድ ቀን ግን በገንዳ ውሃ ሞልቶ ሰውነቱን እየታጠበ እያለ ድንገት የእንቆቅልሹ ምሥጢር ስለተገለጠለት እንዳበደ ሰው ከገንዳው ውስጥ መለመላውን ዘሎ በመውጣት “Eureka! Eureka!”፤ “እንደተመኘሁሽ አገኘሁሽ”፤ እንዲሉ “መልሱን አገኘሁት! አገኘሁት!” እያለ እርቃኑን በከተማው ውስጥ እንደዞረ ታሪኩ በግልጽነት ይነግረናል::
እኛም በአገራችን ውስጥ እንቆቅልሽ አብዝተውብን ለእምባና ለምሬት የዳረጉን “እሽ አትበሉን የሹም ዶሮ ነን” ባይ “ባለሥልጣን” መሪዎቻችን ወደ አገልጋይ መሪነት ደረጃ ዝቅ ብለው የሚመሯቸውን ሠራተኞችና ተቋማቸውን በአርአያነት ማስመስገናቸውን ያየንና የሰማን እለት ስእለትና ምስጋና የምናቀርበው ተባብረን ነው:: እምባችን ፈስሶ ላለቀው ለእኛ ለተገልጋዮችም ዝቅ ብለው ማገልገልን ያሳዩን ዕለት ልክ እንደ አርኪሜደስ ይሉኝታ ሳይገድበን በየሚዲያው ገጾችና አየሩ ላይ እየፋነንን “Eureka! Eureka!” አገራችን አገልጋይ መሪዎችን አገኘች! ፈጣሪና መንግሥታችንም ብሶታችንንና ጸሎታችንን ሰምተው “እምባችንን አበሱልን!” እያልን መጮኻችን አይቀርም:: ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19 /2014