ዛሬ ስለ ተስፋ እነግራችኋለሁ:: ተስፋ ስላችሁ ግን በምንምነት ውስጥ ያለውን ህልም እልም ዓይነቱን ተስፋ እያልኳችሁ አይደለም:: በራዕይ ውስጥ ስላለው፣ ለለውጥ በተነሱ ልቦች ውስጥ ያለውን እሱን ማለቴ ነው:: ትልቅነት መብቀያው በአንድ ሀሳብ በተስማሙ ልቦች ውስጥ ነው:: ኢትዮጵያ አገራችን የአንድነት ተስፋ ርቋት ለዘመናት ኖራለች::
አሁን እነዛን ተስፋ ማጣቶች በተስፋ የምናድስበት ሰሞን ላይ ነን:: የተስፋ ወደብ ፍቅር ነው:: ፀሐይ በምሥራቅ በኩል ብልጭ እንደምትል ሁሉ የአገርም ተስፋ በምክረ ሀሳብ ውስጥ ፍሬ የሚያፈራ ነው:: ያጣናቸው እነዛ ትናንትናዊ ጣፋጭ ፍሬዎች በአንድነትና በፍቅር ማጣት የደረቁ ናቸው:: በወንድማማቾች ጥል የጎመዘዙ ናቸው:: ትልቅ አገር እንዲኖረን ከሁሉም በፊት በትልቅ ልብ ውስጥ የተጻፈ ትልቅ ተስፋ ሊኖረን ይገባል:: ትልቅ ልብ ነውር አያውቅም:: የእስከዛሬ ነውራችን በትንሽ ልብና በትንሽ ሀሳቦቻችን የፈጠርናቸው ናቸው:: ችግሮቻችንን ቁጭት በወለደው የኅብረብሔራዊነት ተስፋ መግደል አለብን::
የቆማችሁት በምን ይመስላችኋል? ወጥታችሁ የምትገቡት በምን ኃይል በምን ብርታት ቢሆን ነው? እዚህ ዓለም ላይ በሕይወት ለመኖር እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ኃይሎች ውስጥ አንዱ የተስፋ ኃይል ነው:: የተስፋ ኃይል ደግሞ በአንድነትና በወንድማማችነት የተቃኘ ኃይል ነው:: አገር ተስፋ ያለው ወጣት፣ ተስፋ ያለው ዜጋ፣ ተስፋ ያለው መሪ በአጠቃላይ ተስፋ ያለው ትውልድ ያስፈልጋታል::
ይሄ የሚሆነው ደግሞ በጋራ መስራትን፣ በጋራ ማሰብን ባህል ስናደርግ ነው:: ሕይወት ከተሠራችባቸው ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ አምላካዊ ቀመሮች ውስጥ ተስፋ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል:: በሃይማኖት አስተምህሮ ላይ እንኳን ተስፋ ለሕይወት ያለውን የላቀ ዋጋ ማየት እንችላለን:: ተስፋውን የገደለ፣ ተስፋውን ያጣ ሰውነት ለመኖር አቅም አያገኝም:: ትልቁ መኖራችን ያለው በትልቁ ተስፋችን ውስጥ ነው::
እንደ አገር ወደ ፊት እንድንሄድ፣ ወደ ፊት እንድናይ ልባዊ ተስፋ ያስፈልገናል:: ያለ ሙልዕተ ተስፋ ምንም ነን:: ተስፋ በራዕይ ውስጥ ያለ ለለውጥና ለአዲስ ነገር በሚጓጓ መንፈስ ውስጥ የሚፈጠር የመልካም ነገሮች ፍኖት ነው:: ከግለሰባዊነት ባለፈ ለአንድ አገርና ሕዝብ ያለው ሁለንተናዊ ፋይዳ እንዳለ ሆኖ እድገትና ስልጣኔ ከሚፈበረኩባቸው አእምሮአዊ የልማት ኃይል አንዱና ዋነኛው ነው ባይ ነኝ:: በተለይ እንደኛ አገር ባሉ በትናንት የውሸት ትርክት ዛሬን መኖር ያልቻሉ ሕዝቦች ባሉበት አገር ላይ ትናንትን የሚሽር ሁሉን አቀፍ አገራዊ ተስፋ ግድ ይላል:: መኖር መተንፈስ ብቻ አይደለም፣ መኖር መተንፈስ ብቻ ነው ብንል እንኳን እንድንተነፍስ የሚያበረቱን ኃይሎች እንዳሉ መዘንጋት የለብንም:: እንድንኖር፣ እንድንተነፍስ አቅምን ከሚፈጥሩልን ኃይሎች ውስጥ አንዱ ጸዐዳ ተስፋ ነው::
ተስፋ ከስኬትና የምንፈልገውን እንድናገኝ ከማድረግ ባለፈ እንዳንሞት የሚያደርግ ታላቅ ሰውነታዊ ኃይል አለው:: ሰዎች ሁሉ የሚወድቁት፣ ሰዎች ሁሉ የሚሞቱት ተስፋ ሲያጡ እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ ነው:: በሕክምናው ዓለም ብናይ እንኳን የአንድ ህመምተኛ የመዳንና የመሞት ልኬት የሚወሰነው በተስፋ ነው:: ተስፋ አለው..ተስፋ የለውም ሲባል ሰምታችኋል ብዬ አስባለሁ:: ተስፋ በመኖርና በመሞት መካከል የተሰመረ የህላዊ ድንበር ነው:: በተስፋ ማጣት ውስጥ ሆነን የምናሳካው ህልም፣ የምናሳካው ራዕይ የለም::
በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆነን የምንማረው ትምህርት፣ የምንይዘው ትዳር በአጠቃላይ የምንኖረው ሕይወት ዋጋ ቢስ ነው:: ለምንም ነገር በተስፋ የተሞላ ልብና መንፈስ ያስፈልገናል:: ለምንም ነገር ወደፊት ሊያስኬደን የሚችል ብርቱ መነቃቃት ግድ ይለናል:: አሁን ላይ እንደ አገር ተስፋ ያስፈልገናል:: ከዛሬ የተሻለ ነገን የማየት፣ ከትናንት የበረታ ዛሬን የመኖር ተስፋ ያስፈልገናል:: ተስፋ ዝም ብሎ አይፈጠርም..ተስፋ ከአንድነትና ከአብሮነት የሚነሳ መድረሻውንም አገርና ሕዝብ ያደረገ ኃይል ነው:: እየተገፋፋን፣ እየተናቆርን ከዛሬ አርቀን ማየት አንችልም:: እንደ አገር ለጋራ ጥቅም የሚታትሩ አእምሮና ልብ ሳንገነባ ወደ ፊት ፈቀቅ ማለት አይቻለንም::
በሕይወት ውስጥ በእያንዳንዱ ነገራችን ላይ ግፍና ጸዐዳ መልኩን ይዞ ተስፋ አብሮን አለ:: ዛሬ ላይ በብዙ ችግርና ማጣት የምንሰቃየው ውስጣችን ተስፋ ባለመኖሩ ነው:: ወይም ደግሞ ሳንሠራና ሳንለፋ በአጉል ተስፋ በመጠበቅ ውስጥ ስለቆምን ነው:: በነገራችን ሁለት ዓይነት ተስፋዎች አሉ:: አንደኛው የበረከት..የልዕልና ተስፋ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የማጣት..የድህነትና የእኩይ ነገሮች ተስፋ ነው:: አሁን ላይ ብዙዎቻችን በሁለተኛው የተስፋ ጎዳና ላይ የቆምን ነን:: ሁለተኛው ተስፋ ማለትም የድህነትና የማጣት ተስፋ ያልኳችሁ ውስጣችን ምንም ዓይነት ራዕይና መነሳሳት ሳይኖር በስሜት..በደመነፍስ እንዳው ዝም ብለን ከመሬት ተነስተን በብዙ ልፋት የሚገኝን አንድን ነገር የእኛ እንዲሆን መጠበቅ ማለት ነው::
ይሄ የተስፋ ዓይነት ሰዎችን ከመጉዳትና እኔ ከንቱና የማልረባ ነኝ፣ ለመልካም ነገር አልተፈጠርኩም ብለን ራሳችንን እንድንጠላ ከማድረግ ባለፈ የሚጠቅመን አንዳች ነገር የለም:: በዚህ የተስፋ ዓይነት ውስጥ መኖር ጉዳቱ ይሄ ብቻ አይደለም በሕይወት ውስጥ ለብዙ ግራ መጋባትና ለብዙ ያልተገቡ እኩይ አመለካከቶች በመዳረግ አቅማችንን በመግደል ለሱስና ለመሰል አላስፈላጊ ድርጊቶች እንድንጋለጥ በር ይከፍትብናል::
ዛሬ ላይ ብዙ ህልማችን ብዙ ራዕዮቻችን የመከኑብን በዚህ የሞት ተስፋ ላይ ስለቆምን ነው:: እውቀትና ጉልበት ይዘን ከንቱ ሆነን የምንኖረው በዚህ የውሸት ተስፋ ላይ ስለተደገፍን ነው:: አገርና ሕዝብ ከመጥቀም ይልቅ የወጣት ጡረተኛ ሆነን ከአያቶቻችን እጅ ላይ የምንበላውም በዚህ የተነሳ ነው:: በተስፋ ለመኖር እንዴት ተስፋ ማድረግ እንዳለብን ማወቅ ይኖርብናል:: በነገራችን ላይ ይህ የተስፋ ዓይነት የሞት ተስፋም ሊባል ይችላል::
በሕይወታችን የመጨረሻው ክፉ ነገር ላይ የምንደርሰው በዚህ ተስፋ ውስጥ አልፈን ነው:: በዚህ ተስፋ ውስጥ ለውጥ የለም፣ በዚህ ተስፋ ውስጥ ደስታ የለም:: እርሱ ሕይወታችን የሚባክንበት፣ ህልም ራዕያችን የሚመክንበት የውድቀት ጥግ ነው:: ብዙዎቻችን ባለመንቃት ባለማሰብና ባለማወቅ ምርጡን የተስፋ ዓይነት ትተን በዚህ የሞት ተስፋ ውስጥ እንኖራለን:: እናም አሁኑኑ ያለንበትን የተስፋ ሁኔታ ዞር ብለን ማየቱ ጥሩ ነው:: ያለዛ እየባከንን ነው:: ምንም ጥሩ ነገር ላንፈጥር የማይመጣን፣ የማይሆንን ነገር እየጠበቅንነው::
ሁለተኛው የተስፋ ዓይነት የምርጦች ተስፋ ይባላል:: ምክንያቱም ምርጥ ነገር ሁሉ ለምርጥ ጭንቅላት የተቀመጠ ስለሆነ ነው የምርጦች ተስፋ ያልኩት:: በዚህ የተስፋ ዓይነት ውስጥ ሞትና ርኩሰት የለም:: በዚህ የተስፋ ዓይነት ውስጥ መውደቅ የለም:: ብንወድቅ እንኳን እንድንነሳ የሚያስችል ኃይል ይኖረናል:: በዚህ የተስፋ ዓይነት ውስጥ አሁን ላይ ብዙ ነገራችን ልክ እየመጣ ነው እላለሁ:: ደስታችን፣ ሰላማችን እንዲሆንልን የምንፈልገው ነገር ሁሉ በዚህ የተስፋ ሥርዓት ውስጥ ያለፈ ነው:: በወጣትነታችን በጎ ሥራ እየሥራን ያለን ሁሉ፣ በሥራችን ስኬታማ የሆንን ሁሉ፣ በምንፈልገው ነገር ላይ ውጤታማ የሆንን ሁሉ ውስጣችን በገነባነው የለውጥ ተስፋ ላይ ስለቆምን ነው:: እንደ ዜጋ ለአገራችን መልካም ከሠራን፣ እንደ መንግሥት፣ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ተነጋግሮ መግባባትን ካስቀደምን በምርጥ ተስፋ ስር ነን ማለት ነው:: ምርጥነት ከማሰብ ይጀምራል:: የሚያስብ ጭንቅላት ተስፋ የሚያደርገው ነገር ይኖራል:: በማሰብና ተስፋ በማድረግ ውስጥ ደግሞ ራዕይና ህልም እውን ይሆናል ማለት ነው::
ብዙዎቻችን ሳናስብ ተስፋ የምናደርግ ነን:: ሳናስተውል ተስፋ ያደረግንው ነገር ደግሞ ከመሆን ይልቅ ላለመሆን የቀረበ ነው:: ምክንያቱም ሁሉም ነገር ማስብን ስለሚፈልግ ነው:: ምንም ነገር ከማድረጋችን በፊት ማሰብ ይቀድማል:: እስካሁን ድረስ የተበላሹ ሕይወታዊ አጋጣሚዎች ሁሉ ካለማሰብ በቀቢጸ ተስፋ የተከወኑ ስለሆኑ ነው:: እንደ አገር የጋራ ተስፋ ቢኖረን ኖሮ አሁን ላይ በችግሮቻችን ላይ ተነጋግሮ መግባባት ባልከበደን ነበር:: የአገራዊ ምክክሩ ዋና አላማ እኮ ተስፋን መፍጠር ነው:: በተግባቦት አንድነትን ማምጣት ነው:: ተስፋ የሚፈጠረው ደግሞ በእርቅና በውይይት ነው:: የጋራ ተስፋን ለመፍጠር የጋራ ውይይት የጋራ እርቅ ያስፈልገናል:: ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ ላይ የምንፈጥረው ተዐምር አይኖርም::
ሁሌም ወደ ትልቅ ነጋችን..ወደምንፈልገው የከፍታ ምዕራፍ ለመሸጋገር በማሰብ የታገዘውን፣ በመነጋገር የተቃኘውን እኛን መፍጠር ይኖርብናል:: እግር የሚራመደው በማሰብ ነው:: እጅ የሚሠራው፣ አይን የሚያየው፣ ጆሮ የሚሰማው ሁሉ ነገራችን ጥቅም እየሰጠን የሚገኘው ከማሰብ ቀጥሎ ነው:: አንዳንድ ሰዎች አሉ፤ ከቤት ይወጡና ወዴት እንደሚሄዱ የማያውቁ:: የት ነው የምትሄዱት ተብለው ሲጠየቁ ወዴት እንደምሄድ አላውቀውም ዝም ብዬ ነው የምራመደው የሚሉ::
ካለማሰብ፣ ገበያ ስለሆነ ብቻ ገበያ የምንሄድ እኮ አለን:: ካለማስተዋል፣ በለው ሲባል ሰምተን በለው እያልን የምንጮኽ ሞልተናል:: ካለመረዳት ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያየነውን ውሸት እውነት ነው ብለን ለሌሎች አጋርተን እናውቃለን:: የጋራ ተስፋ አጥተን በልዩነቶቻችን ላይ ጊዜ የምናጠፋ አለን:: ይሄ ሁሉ መቀየር አለበት:: በትልቅ ተስፋ ትልቅ አገርና ሕዝብ መገንባት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል::
ሕይወት ማሰብ ናት፤ ካለማሰብ የምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ጉዳት ነው ይዘውብን የሚመጡት:: ላለመግባባት ብንወያይ፣ ላለመስማማት ስብሰባ ብንቀመጥ የምናተርፈው ትርፍ የለም:: ተነጋግረን መግባባት ካልቻልን፣ በአንድ የሚያቆመን የጋራ ተስፋ ከሌለን ለራሳችንም ሆነ ለአገራችን ውለታ መዋል አንችልም:: ይሄ ሆነ ማለት ደግሞ ትልቁ ተስፋ ከእኛ ጋር አይደለም ማለት ነው፤ ወይም ደግሞ በሕይወት ውስጥ የምንለፋለት፣ ማለዳ..በየቀኑ አብዝተን የምናስበው የስኬት ጫፍ የለንም ማለት ነው:: ትልቅ ተስፋ ውስጣቸው ያለ ሰዎች ከአገር የሚበልጥባቸው ምንም ነገር የለም:: ለውይይት፣ ለእርቅ የሚሆን ብዙ አቅም፣ ብዙ ችሎታ አላቸው::
ውሳኔያችንን ለእግሮቻችን ሳይሆን ለአእምሯችን እንተውለት፡ ዓይኖቻችን መልካም እንዲያዩ፣ ጆሮዎቻችን መልካም እንዲሰሙ ራሳችንን በመልካምና በሚገባ ቦታ ላይ እናቁመው:: ምርጥ ነገሮች ሁሉ በምርጥ ተስፋዎች ውስጥ የተቀመጡ ናቸው:: አሁን ላይ በእውቀታቸው፣ በጉልበታቸው በገንዘብና በጊዜአቸው አገርና ሕዝብ እያገለገሉ ያሉ እነሱ በምርጥ ተስፋ ውስጥ የሚኖሩ የምርጥ ተስፋ ውጤቶች ናቸው:: ትልቅነታችን ያለው በዚህ ትልቅ ተስፋ ውስጥ ነው:: ተስፋ የሌለው ትውልድ ተስፋ የሌለው አገርና ሕዝብ የመፍጠር ኃይል አለው:: ተስፋችን ለእኛ ብቻ ሳይሆን ከእኛ ቀጥሎ ለሚመጣው አዲሱ ትውልድም የላቀ ዋጋ አለውና አገርና ሕዝብን ወደ ፊት ሊያራምድ የሚችልን ትልቅ በጣም ትልቅ ተስፋን የእኛ ማድረግ ይኖርብናል:: በሕይወት ውስጥ የብዙ ነገር መጨረሻዎች ከተስፋ ብዛትና ከተስፋ ማጣት የሚመጡ ናቸው::
እንዳልኳችሁ ትላልቅ ተስፋዎች ትላልቅ ሰዎችን የመፍጠር ኃይል አላቸው:: በትላልቅ ተስፋ የተፈጠሩ ትላልቅ ሰዎች ደግሞ በአካል፣ በአእምሮ፣ በሥነ ልቦናና በኢኮኖሚ አቅማቸው የተገነቡ ናቸው:: እኚህ ግለሰቦች ለአገር የሚሆን ብዙ ነገር ይኖራቸዋል:: እኚህ ግለሰቦች ችግር ፈጣሪ ሳይሆኑ ችግር ፈቺ ናቸው:: በነዚህ ግለሰቦች የተፈጠረች አገር ደግሞ ከፍ ያለ ገጽታ ይኖራታል:: በትልቅ ተስፋ ውስጥ መኖር ራስን በትልቅ አገራዊ እውነት ውስጥ ማስቀመጥ ነው:: አሁን ላይ አገራችን ላለችበት ማህበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ቀውሶች ችግር ፈጣሪዎች ሳይሆኑ በእውቀትና በተስፋ የተካኑ ችግር ፈቺ ዜጎች ያስፈልጋሉ:: በእውቀት በሥልጣኔ የሚበልጡን ሰዎች በዙሪያችን መኖራቸው የላቀ ዋጋ አለው:: ከሚበልጡን ጋ ስንሆን እነሱን ለመሆን፣ የደረሱበት ለመድረስ እንበረታለን:: ትንሹን ተስፋችንን ገድለን ትልቁን ተስፋ ውስጣችን እንገነባለን:: በዚህም ብርቱና ታታሪ በመሆን አገር አሻጋሪ ከሆኑት ውስጥ እንመደባለን ማለት ነው::
በእወቀትም ሆነ ተስፋ በማድረግ ከእኛ ካነሱት ጋር ስንሆን ግን ራሳችንን ከማሻሻልና ከማበርታት ይልቅ በነበርንበት እንድንቆይ እንገደዳለን:: ስለዚህም በዙሪያችን በተስፋ የተለቁ በእውቀትና በጥበብ የተሻሉ ሰዎች ስለመኖራቸው እርግጠኛ መሆን ይጠበቅብናል:: ከሚበልጡን ሰዎች ጋር ወዳጅነትን ስንፈጥር ከነበርንበት አስተሳሰብ፣ ከነበርንበት ኋላ ቀር ሕይወት የመውጣት ዕድሎች ይኖሩናል::
ሁሌም ቢሆን ትንሹን ተስፋችንን ገድለን ወደ ትልቁ ለመሄድ ጉልበትና ኃይልን የሚፈጥሩልን ሰዎች ያስፈልጉናል:: ከተኛንበት የሚያነቃን ውስጣችን ትልቅ ተስፋ የለም ማለት ራሳችንን እያጣነው ነው ማለት ነው:: ተነጋግረን መግባባት ካልቻልን አገራችንን እያጣናት ነው ማለት ነው:: ይሄ እንዳይሆን አገር የሚገነባ፣ አገር የሚያቆም የጋራ ተስፋ ያስፈልገናል:: እንደ አገርም ሆነ እንደማኅበረሰብ አሁን ካለንበት የሕይወት ምስቅልቅል የምንወጣው በትልቅ ተስፋ ትልቅ ነገር ስንጀምር ነው::
ከምኞት ወጥተን ወደ ተጨበጠ ገሀዳዊ እውነት ለመሸጋገር ልዕለ ኃያል ተስፋ ያስፈልገናል:: ልዕለ ኃያል ተስፋ የሚገነባው በጠንካራ የሥራ ልምድ፣ ምንም ነገር እንደምንችልና እንደምናሳካ ማመን ስንጀምር ነው:: ከሁሉም በፊት ግን ከገደለንና ብዙ ነገር ካሳጣን፣ እያሳጣንም ካለው ብሔር ተኮር እሳቤ መውጣት ግድ ይለናል::
ብሩህ ነጋችን ያለው በትልቁ ተስፋችን ውስጥ ነው:: አሁኑኑ ራሳችንን ከነሙሉ ቀልባችን ልናገኘው ይገባል:: ከነሙሉ ቀልብ መገኘት ራስን በትክክለኛ ቦታ ላይ ትክክል ሆኖ ማግኘት ማለት ነው:: ከነሙሉ ቀልባችን ስንገኝ ትናንሽና ውዳቂ ሀሳቦች አይፈነጩብንም:: ኧረ እንዲያውም አጠገባችንም አይደርሱም:: ትልቁ ተስፋችን በሕይወት ውስጥ የማይጠቅሙንን ሞታዊ መከራችንን የሚዋጋልን ጋሻና ጦራችን ነው:: ከነሙሉ ቀልብ መገኘታችን ይሄን ትልቅ ተስፋችንን ወደ ውጤት ለመቀየር በምናደርገው ትግል ውስጥ ቀዳሚው መስፈርት ነው:: ትልቁን ተስፋ የእኛ ስናደርግ በሕይወታችን ውስጥ፣ በአገራችን ውስጥ የተበላሹ ብዙ ነገሮች መስተካከል ይጀምራሉ:: በተስፋ ወደ ፊት…፤ ለዛሬው አበቃው፤ ሰላም!
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18 /2014