የላቀ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ክህሎት ያላቸው ወጣቶች ለአገር እድገት ጉልህ ድርሻ ያበረክታሉ። ብሩህ አእምሮውን ተጠቅሞና እይታዎቹን አስፍቶ አዲስ የቴክኖሎጂ ግኝት የሚፈጥርን ወጣት የሚያበረታታ መንግሥት ደግሞ ከሚጠበቀው ፍጥነት በተሻለ ሁኔታ የሚመራትን አገር ብልፅግና ለማረጋገጥ ዕድሉን ያገኛል።
ለዚህም ነው ዓለምን በአዲስ አቅጣጫ እየወሰዳት ያለውን የዲጂታል፣ ቴክኖሎጂና ሳይንሳዊ ውጤት በአግባቡ የሚረዱ፣ የሚግባቡና ከዚያም አለፍ ሲል የራሳቸውን ድርሻ የሚያበረክቱ ወጣቶችን ማፍራት፣ ማበረታታትና አስፈላጊውን ድጋፍ መስጠት እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት።
በኢትዮጵያ ላለፉት ዘመናት በሙሉ አቅም በሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸውን ታዳጊዎች የሚያበረታታ ሰፊ ፕሮጀክት አልታየም ነበር። ሆኖም ዓለም የሚመራበት ሥርዓት በሳይንስና ቴክኖሎጂ መቀየርን ተከትሎ አሁን አሁን መንግሥት የተለየ ትኩረት እንዲሰጥ እያደረገው ይገኛል። ቀደም ካሉት ጊዜያት በተሻለ ሁኔታም ታዳጊና ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች ዘርፉን በመቀላቀል ክህሎታቸውን ለማዳበር ሲተጉ ይስተዋላል። የትምህርት ተቋማትና መሰል ማሰልጠኛዎችም ለቴክኖሎጂና ፈጠራ ሥራዎች የሚሰጡት ትኩረት እየጨመረ መጥቷል። ይህንን ተከትሎ ታዳጊዎችና ወጣቶች ልዩ ተሰጧቸውን ተጠቅመው የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ። ለዚህ በርካታ ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል።
የዝግጅት ክፍላችንም ለዛሬ ከፈጠራ ሥራ ጋር በተያያዘ ስኬታማ ውጤቶችን እያስመዘገበ የሚገኝ ወጣት መምህር እንግዳ በማድረግ በዘርፉ ላይ እየታዩ ስላሉ ውጤቶችን ለመቃኘት ወድዷል። በተለይ የፈጠራ ባለሙያው ያስተዋወቃቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ምን ይዘት እንዳላቸው እንመለከታለን።
ወጣቱ አማኑኤል ባልቻ ይባላል። በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ላብራቶሪ መምህር ነው። በፈጠራ ሥራዎቹና በግል አዲስ ነገር ለማስተዋወቅ በሚያደርገውም ጥረት ይታወቃል። ተወልዶ ያደገው በዚያው ደንቢዶሎ ሲሆን የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለውም እዚያው ነው። የከፍተኛ ትምህርቱን ደግሞ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማጠናቀቅ ችሏል። በቢሾፍቱ የደጀን አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ለአራት ዓመታት የሠራ ሲሆን ወደ ትውልድ ቦታው ተመልሶም በዩኒቨርሲቲው በቴክኒካል ረዳት በመምህርነትና በግል የፈጠራ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ ይገኛል።
«ከልጅነቴ ጀምሮ የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ላይ ልዩ ፍላጎት ነበረኝ» የሚለው መምህር አማኑኤል፤ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ወቅት በቤት ውስጥ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመጠቀም ልዩ ልዩ ነገሮችን ይሠራ እንደነበር ይናገራል። ወደ 10 እና 11ኛ ክፍል በሚገባበት ወቅት ደግሞ በትክክልም ጠቀሜታ የሚሰጡና የተለያዩ የቴክኖሎጂ ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደርግ ነበር። ከዚህ ውስጥ የቤት ውስጥ የማብሰያ ቁሳቁሶችን ከአየር ላይ መውረጃና መንሳፈፊያ (የፓራሹት ) እና አነስተኛ አውሮፕላኖችን ለመሥራት ጥረት ያደርግ ነበር። ሥራዎቹን ለትምህርት ቤቱ አቅርቦ በውድድሮች ላይ ለበርካታ ጊዜ አሸንፏል።
በኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ ከዋና ዋና ከተሞች ራቅ ባሉ አካባቢዎች መሰል የፈጠራ ሥራዎችን ለመሥራት ብዙ እንቅፋቶች እንዳሉ እሙን ነው። መምህር አማኑኤል የዚህ ፈተና ተጋፋጭ ነበር። ይሁን እንጂ ውስጡ የሚሻውን በቴክኖሎጂ ሥራዎች ብቁ የመሆን ህልም ለማሳካት እነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አልገደቡትም። ይልቁንም የጥንካሬው ምንጭ ሆነውታል። «በዋና ከተማዎች የፈጠራ ሥራዎችን ለማሳካት የሚያስችሉ ዕቃዎች ማግኘት በአንፃራዊነት ይቀላል» የሚለው አማኑኤል ይህ አጋጣሚ ባይፈጠርም እንኳን ጠንካራ ፍላጎት በውስጡ ስለነበር ፈተናውን ለማለፍ እንዳልገደበው ያስረዳል። የፈጠራ ባለሙያ በአካባቢ በሚገኝ ቁስ ላይ ተመስርቶ ሃሳቦችን ከግብ ማድረስ እንደሚኖርበትም ተናግሯል።
መምህር አማኑኤል በቢሾፍቱ ደጀን አቪየሽን በሚሠራበት ወቅት አውሮፕላን የመሥራት ህልሙ ከፍተኛ ነበር። በዚያ ሦስት አነስተኛ አውሮፕላኖችን በማሳያነት በመሥራት ዋናውንና ትልቁን አውሮፕላን ለመሥራት ብዙ ጥረት አድርጎ ነበር። የፕሮጀክቱ ንድፍና ፅንሰ ሃሳብም አሁን ድረስ አለው። ለሙከራ የሠራቸው ትናንሽ አውሮፕላኖች ለሦስት ደቂቃ ያህል በአየር ላይ መንሳፈፍ ችለዋል።
«አብዛኛው ተማሪ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሲገባ ወደሚፈልገው ሙያ ውስጥ አይገባም» የሚለው መምህር አማኑኤል እርሱ ግን አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሲመደብ በአጋጣሚ የሚወደውንና ፍላጎቱ የሆነውን የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት የማጥናት ዕድል እንዳጋጠው ይናገራል። ይህ አጋጣሚም የመፍጠር ፍላጎቱን ይበልጥ እንዳነሳሳውና ብዙ ፕሮጀክቶችን እንዲቀርፅ እንዳስቻለው ያስረዳል። በአርባምንጭ የአራተኛ ዓመት ተማሪ በነበረበት ወቅትም የአርቴፊሻል ኢንተለጀንት የፈጠራ ዘርፍ ላይ በአልሙኒየም ቺፍሜታ ሮቦት መሥራቱን ያስታውሳል።
መምህር አማኑኤል አሁን በደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል በላብራቶሪ ውስጥ መምህር ነው። ተማሪዎቹን በተግባር ውጤታማ የፈጠራ ሥራዎች ላይ በምን መልኩ መሳተፍ እንደሚችሉ ከራሱ ተሞክሮ ያስተምራል። በርካታ የፈጠራ ሃሳቦች ላይ አተኩሮም ችግር ፈቺ ሥራዎች ለመሥራት ፕሮጀክቶችን ይነድፋል። አሁን አንድ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራ ላይ በዋናነት እየሠራ ነው። በዚህም ሁለት ዓይነት ድሮኖችን በመሥራት እያስተዋወቀ ይገኛል። ለመሆኑ የፈጠራ ባለሙያው የድሮን ሥራ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ለምን አገልግሎትስ ይውላል? ከዚህ የሚከተለው የመምህር አማኑኤል ገለፃ ምላሽ ይሰጠናል።
የድሮን የፈጠራ ሥራ
ዓለማችን የረቀቁ ቴክኖሎጂ ውጤት ባለቤት እየሆነች ነው። ከዚህ ውስጥ በርካታ አገራት የሚፎካከሩበት ረቂቅ ሳይንሳዊ ፈጠራ ውስጥ ደግሞ ሰው አልባ በራሪ ድሮን ይገኝበታል። ይህ ቴክኖሎጂ መተዋወቅ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አያሌ ለውጦችን ምድራችን አስተናግዳለች። የግብርና፣ ማዕድን፣ የንግድ፣ የፊልም ኢንዱስትሪ እንዲሁም ወታደራዊ ሳይንስ ፈጣን ለውጦችን ማስመዝገብ ችለዋል። የእርስ በእርስ ፉክክሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ለዚህ እንደ ማሳያ የሚሆነው በቱርክ ለወታደራዊ ተልዕኮ የሚመረቱት ድሮኖችን ማንሳት ይቻላል። እነዚህ ድሮኖች በጦርሜዳ ተልዕኮ ውጤት ቀያሪ እየተባሉ ይጠቀሳሉ።
መምህር አማኑኤል ከበርካታ የፈጠራ ሙከራና ተግባሮች በኋላም የፈጠራ ክህሎቱን በልዩ ሁኔታ ሰው አልባ ድሮን መሥራት ላይ እንዲያደርግ በዓለማችን ላይ እየታየ የመጣው ፈጣን የቴክኖሎጂ ለውጥ መነሻ ሆኖታል። በዚህም የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ሁለት ዓይነት ድሮኖችን መሥራት ችሏል። የመጀመሪያው የድሮን ፈጠራ ሥራው «መልቲኮፕተር» የሚባል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ መሬት ላይ ተንደርድሮ የሚነሳ «ፊክስድ ዊንግ ድሮን» የሚባለው ዓይነት ነው። ሁለቱም «አርዶ ኮፍተርና» «ኬኬ ቦርድ» በሚባሉ የበረራ መቆጣጠሪያ የሚሠሩ ናቸው።
መምህር አማኑኤል በመጀመሪያ ድሮን ለመሥራት ሲነሳ አገልግሎቱ እንዲሆን የፈለገው በሚያስተምርበት ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ለሚገኝ ሰፊ እርሻ ለዘር፣ ፀረ ተባይና መሰል የቅኝት አገልግሎት እንዲጠቅም በማሰብ ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ሃሳቡን መሬት ላይ ለማውረድ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ የሠራቸው ድሮኖች ለተለያየ አላማ እንዲውሉ በማድረግ እንዲተገበሩ አድርጓቸዋል። ለምሳሌ በእርሱ የፈጠራ ውጤት የተሠሩት ድሮኖች ዕቃ ለማድረስ፣ ቅኝት ለማድረግና ሌሎች ተግባሮችንም ለማከናወን እንዲችሉ አድርጎ በማንኛውም ጊዜ ማቀናጀት እንደሚቻል ነግሮናል።
መምህር አማኑኤል በማሳያነት የፈጠራቸውን ሁለት ድሮኖች ወደ ተግባራዊ ሥራ ለማስገባትና በስፋት እንዲመረቱ ለማድረግ ጥረት እያደረገ እንደሆነ ይገልፃል። በተለይ የእርሱን ሃሳብ የሚደግፉ አካላት ድሮኖቹን ለማምረት የሚያስችል ወርክ ሾፕ ለመሥራት በሂደት ላይ እንዳሉ ይናገራል። በመጪው ሁለት ወራት ውስጥም ለግብርና ምርት መቀላጠፍ የሚረዱ ድሮኖችን ለመሥራት እያሰበ መሆኑን ይገልፃል። ሁለተኛው እቅዱ ደግሞ በአደጋ ጊዜ እሳት ለማጥፋት የሚያስችሉ ድሮኖችን በተመሳሳይ ማምረት ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን ረጃጅም የኤሌክትሪክ ምሰሶና ገመዶች ላይ የሚቀመጡ አላስፈላጊ ቁሶችን በእሳት አቅልጦ ማውረድ የሚያስችሉና የኤሌክትሪክ ስርጭት እንዳይስተጓጎል የሚረዱ ተመሳሳይ የድሮን ምርቶችን የማስተዋወቅ እቅድ ነድፎ እየሠራ ነው።
መምህርነትና የተግባር ምሳሌ
ወጣት አማኑኤል በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ላብራቶሪ አስተማሪ እንደመሆኑ መጠን ለተማሪዎቹ በሚሠራቸው የፈጠራ ሥራዎች አማካኝነት መነቃቃትን እየፈጠረ ይገኛል። ከዩኒቨርሲቲው ውጪ ባሉ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ታዳጊ ተማሪዎችም በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚዘጋጁ ስልጠናዎች ላይ እየተገኘ ተሞክሮውን ያጋራቸዋል። የፈጠራ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩና «እኔም እችላለሁ» የሚለው መልካም መነቃቃት እንዲሰርፅባቸው የቻለውን ሁሉ ጥረት ያደርጋል።
የመምህሩ ራእይ
መምህር አማኑኤል በሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራ ላይ እሩቁ የመጓዝና ስኬታማ ሥራዎችን ለአገሩ ለማበርከት ህልም አለው። በተለይ በአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ላይ የመሳተፍ ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ተመርቶ አገልግሎት መስጠት የሚችል የአውሮፕላን አምራች ካምፓኒ የመመስረትና የመፍጠር ራእይ ይዞ በረጅም ጊዜ እቅድ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
የፈጠራ ባለሙያና መምህሩ ሌሎች በርካታ ችሎታዎች አሉት። በአንድ የሙያ ዘርፍ ላይ ብቻ መገደብን አይሻም። ከዩኒቨርሲቲ ውጪ በቤቱ ውስጥ በፈጠራ ላይ የተመረኮዙ የእንጨትና ብረታ ብረት ሥራዎችን ያከናውናል። በተለይ ለግንባታ ግብአት የሚውል ብሎኬትን በቀላሉና ወጪን በሚቆጥብ መንገድ የሚያመርት ማሽን የመሥራት ግብ ሰንቆ ለተግባራዊነቱ እየሠራ ይገኛል። በእንጨት ሥራ ጣውላ መሰንጠቂያና በግብርናው ዘርፍ ደግሞ የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን የመሥራት እቅዶችም አሉት።
መምህሩና የፈጠራ ባለሙያው ከላይ ያነሳቸውን ሃሳቦች እውን ለማድረግ የሚመለከተው የግልም ሆነ የመንግሥት ተቋማት እገዛና ማበረታታትን እንደሚፈልግ በማጠቃለያ ሃሳቡ ላይ ያነሳል። በተለይ ወጣትና ታዳጊ የፈጠራ ባለሙያዎች ወደ ህልማቸው መቅረብ እንዲችሉ አቅም ባላቸው አካላት ሊበረታቱ እንደሚገባም ይገልፃል። እርሱ አሁን ላለበት ደረጃ እንዲደርስ በርካታ አካላት እንደደገፉት ሳይሸሽግ በተለይ አሁን የሚያስተምርበትን የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲና በዚያ የሚሠሩ ባልደረቦቹንና የደገፉትን ግለሰቦች ያመሰግናል።
በማጠቃለያ መልዕክቱም «ወጣትና ታዳጊ የፈጠራ ባለሙያዎች ህልማቸውን ከግብ ለማድረስ ትግል ማድረግ ይኖርባቸዋል» በማለት በተለይ በውስጣቸው የተጠነሰሰው ፕሮጀክት መሬት ነክቶ የማህበረሰባቸውን ችግር መቅረፍ እስከሚችል ድረስ ጥረታቸውን ማቆም እንደማይኖርባቸው ይመክራል። እራሱን እንደ ምሳሌ በማንሳትም ለሚሠራቸው የፈጠራ ሥራዎች ተስፋ እያየ የመጣው ከፍተኛ ትግልና ጥረት በማድረጉ መሆኑን አንስቶ በተመሳሳይ ታዳጊና ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችም ህልማቸው ጋር ለመድረስ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንደሚኖርባቸው በመምከር ሃሳቡን ይቋጫል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18 /2014