ስለቻይና በተነሳ ቁጥር ተደጋግሞ የሚጠቀስ የናፖሊዎን ቦናፓርት ነብያዊና አስገራሚ አባባል አለ፤ “ከእንቅልፏ ስትነቃ አለምን ስለምትገለባብጥ፤ ቻይናን ተዋት ትተኛ፤” የሚል። ቻይናም የናፖሊዎንን ትዕዛዝ የሰማች ይመስል ለ200 አመታት ሀሳቧን በኮንፊሺየስ ላይ ጥላ በሯን ዘግታና ኩራዟን አጥፍታ ለሽ አለች። ታዋቂው የቻይና ስትራቴጂካዊ አንሰላሳይ ሱን ዚ ደግሞ ሁሉም ጦርነት በድል ወይም በሽንፈት የሚጠናቀቀው ከመደረጉ በፊት ነው ይላል።
ማርሽ ቀያሪው የቻይና ፕሬዚዳንት ዴንግ ዣውፒንግ በ1970 ዓ.ም ፤ “ድመቱ አይጧን እስካደነ ድረስ ጥቁር ሆነ ነጭ ግድ አይሰጠንም፤” በማለት፤ ከእርዮተ አለም ይልቅ ኢኮኖሚን ያስቀደመ ስትራቴጂ ቀየሰ። የቻይናን ገበያ በሒደት ለአለም ክፍት አደረገ። በተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመሠረተን ዘመናዊነት አቀነቀነ። ነጮች እንደሚሉት ከዚያ በኋላ የሆነው ታሪክ ነው። ለዛውም እጅን በአፍ የሚያስጭን ታሪክ፤ ዴንግ ዣውፒንግ በድህነትና በኋላቀርነት ላይ ጦርነት ከመካሄዱ በፊት አሸነፈው።
የቻይና ኢኮኖሚ ለተከታታይ 30 አመታት በየአመቱ ዘጠኝ በመቶ ተመነደገ። ይህ በሰው ልጆች ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም አያውቅም። በእነዚህ አመታት 400 ሚሊየን ቻይናውያን ከድህነት አረንቋ ወጡ። የዜጋዋ የነፍስ ወከፍ ገቢ በሰባት እጥፍ አደገ። የ”The economisቱ” ጄፍሪ ሳችስ፤ “በአለም ታሪክ የቻይናን ያህል የተሳካ ኢኮኖሚያዊ እድገት ያስመዘገበ የለም፤” ያለው ለዚህ ነው። የቻይና የዕድገት ከአእምሮ በላይ ነው። ኢኮኖሚዋ በየስምንት አመቱ በእጥፍ አድጓል። በ1970 ዓ.ም ቻይና በአመት 200 የአየር ማቀዝቀዣዎችን ብቻ ነበር የምታመርተው። በ1997 ዓ.ም ግን ምርቷን ወደ 48 ሚሊዮን አሳደገችው። ዛሬ በአንድ ቀን ወደ ውጭ የምትልከው ምርት በ1970 ዓ.ም አመቱን በሙሉ ትልከው ከነበረው በብዙ ይበልጣል። ቻይናውያንን አጋምዶ የያዘው ይህ ኢኮኖሚያዊ ታምር ነው።
ኮንፊሽየስ፣ ርዕዮተ አለም ወይም ኮምኒዝም አይደለም። ከምንም ነገር በፊት ኢኮኖሚውን ማስቀደማቸው ከአሜሪካ ቀጥሎ 2ኛውን ግዙፍ ኢኮኖሚ እንዲገነቡ አስችሏቸዋል። ምንም እንኳ በዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ከአሜሪካ በብዙ እጥፍ ያነሰና የዕድገት ጥራት ችግር ያለበት ቢሆንም። በማኦ የባህል አብዮት የተሰበረውን ቅስማቸውን ጠግነዋል። ፈጣኑ ዕድገት ከአሁኑ ፖለቲካዊ ለውጥን መጸነሱ ስለማይቀር የቻይና ኮምኒስት ፓርቲ የሲንጋፖርን፣ የስዊድንና የጃፓንን የሊበራል መንገድ አጥንቶ፣ ቀምሮና አላምዶ ለመተግበር አበክሮ ዕንቅስቃሴ ከጀመረ ከራረመ። ከዚህ የተረዳሁት የቻይና ኢኮኖሚያዊ ተአምር ያደሩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎች ችግሮቿን በማያዳግም ሁኔታ ለመፍታት ቁልፍ መሆኑን ነው። ዛሬ አገራችን ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችና ቀውሶች የድህነታችንና የኋላቀርነታችን ውጤት ናቸው ብዬ አምናለሁ።
ውስን የሆነው ሀብት ደግሞ በመንግስት እጅ ስለሆነ ሁሉም በስስትና በመጎምዠት አይኑን ከመጣል አልፎ ባቋራጭ ለመቆጣጠርና ለመቀራመት ፖለቲካዊ ስልጣንን መያዝን እንደ ስልት ይከተላል። ሕወሓት፣ ሸኔ፣ የጉምዝ ታጣቂ፣ የአገው ሸንጎ፣ የቅማንትና ሌሎች አገራችንና ሕዝባችንን እረፍት የነሷት እንታገልለታለን ለሚሉትና በስሙ አስር ጊዜ ለሚምሉለትና ለሚገዘቱለት ሕዝብ ጥቅም ሳይሆን ለስልጣን ነው። ስልጣንን ይዞ በአቋራጭ የአገሪቱን ሀብት ተቆጣጥሮ የግላቸውንና የቡድናቸውን ጥቅም ለማሳደድ። መሬቱም፣ ማዕድኑም፣ በጀቱም፣ ሁሉም በመንግስት መዳፍ ስር ስለሆነ፤ የፖለቲካዊ ስልጣን በመያዝ ይሄን መዳፉን ፈልቅቆ ሀብትን ለመቆጣጠር ፖለቲካዊ ስልጣን የሞት ሽረት ጉዳይ ሆኗል።
ሕወሓት በስልጣን ጥም ጢምቢራው እስኪዞር የሰከረው የትግራዋይን መብትና ጥቅም ለማስከበር ሳይሆን ለ27 አመታት ባካሄደው ዘረፋ ባለመጠርቃቱ ነው። እኩልነትንና ፍትሐዊነትን እንደወንጀል ቆጥሮ ይሄን ሁሉ ምስቅልቅል፣ እልቂትና ቀውስ ያመጣብን አልጠግብ ባይነቱ ነው። ሕገ መንግስቱና የፌደራል ስርዓቱ ሰበብና ሽፋን ነው። ሕወሓትን ጨምሮ ሌሎች የሽብር ኃይሎች ለስልጣን አራራቸው እንደሽፋን የሚጠቀሙባቸው ያሉብንን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮችን ነውና ተረባርቦ ፈትቶ ሰበብ ማሳጣትና እነዚህን ኃይሎች ከሕዝብ መነጠል ያሻል።
ሕወሓት የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ ወደፊት ያመጣው ለብሔረሰቦች መብት አሳቢና ተቆርቋሪ ሆኖ ሳይሆን፣ ከፋፍሎ ስልጣን ላይ ለመቆየት ነው። እንደ ቅኝ ገዥዎች ከፋፍሎ ለመግዛት ነው። ሕወሓትን ጥቁሩ ቅኝ ገዥ የሚያደርገው ይሄ ባህሪው ነው። አሁን ስራ ላይ ያለው ሕገ መንግስት እየተረቀቀ እያለ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፤ ረቂቁን ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሲያሳያቸው ለምን እንዲህ አደገኛና ከፋፋይ ሕገ መንግስት ማርቀቅ አስፈለገ ብለው ሲጠይቁት፤ መለስ በወቅቱ የሰጣቸው መልስ እንዲህ ካላደረግን ስልጣን ላይ መቆየት አንችልም የሚል አስደንጋጭ ምላሽ ነበር።
ሕገ መንግስቱ ከፋፋይና አገርን አደጋ ላይ እንዲጥል ሆኖ የተረቀቀው የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ ለመመለስ ሳይሆን ሕወሓት ያለተቀናቃኝና ተፎካካሪ አገዛዝ ላይ ለማስቀመጥ ነው። ለዚህ አንዱንም የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ ሳይመልስ የጨነገፈው። ጭቆናው የመደብ ነው ወይስ የብሔር የሚለው ክርክር እንዳለ ሆኖ፤ አጋርና አባል ድርጅቶች እያለ ይቆምር የነበረው ለዚህ ነው።
ይሄን ከፋፋይና እኩይ አላማውን ለማሳካት በፈጠራ ትርክት ላይ በመመስረት ጥላችን፣ ልዩነትን፣ ጥርጣሬንና በጎሪጥ መተያየትን ለ50 አመታት በጀት መድቦ መዋቅራዊና ተቋማዊ አድርጎ አራገበው። አቀነቀነው። ዛሬ እያጨድን ያለነው ይሄን ዘሩን ነው። በአገራችን አራቱ ማዕዘናት የሚያገረሹት ቀውሶች መነሻቸው ይሄ ክፉ ዘር ነው። ዛሬ በገዥው፣ በተፎካካሪና በተቃዋሚ ፖርቲዎች የምናስተውለው ውዝግብና መሳሳብ የዚህ ቅርሻ ነው።
በብዙኃን መገናኛዎች የሚንበለበለው የጥላቻና የልዩነት ፍላጻ መነሻው ከሕወሓት መወጠሪያ (ደጋን) ነው። የምንገኝበት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ መነሻም ከሕወሓት የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ከስሪቱና ከውቅሩ የሚመነጭ ነው። አሁን የምንገኝበት ሁለንተናዊ ቀውስ በእዳ ከሕወሓት የተላለፈልን ነው። ብልጽግናም ሌላው ባለዕዳ ነው። አሁን እየወረደብን ያለው የቀውስ ቋጥኝና ናዳ የብልጽግና ብቻ አድርገን ካየነው ችግሩን በቅጡ አልተረዳነውም ማለት ነው። ብልጽግና ተጠያቂና ተወቃሽ የሚሆነው አቅሙ የፈቀደለትን ያህል ጥረት አድርጓል ወይስ አላደረገም የሚለው ነው።
የተንሰራፋው ስራ አጥነት፣ በዋና ዋና መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ 100 በመቶ እንዳለፈ የሚነገርለት የዋጋ ግሽበት፤ አልቀመስ ያለው የኑሮ ውድነት፤ ይሄን ተከትሎ የሚስተዋለው የሞራልና የቅስም ስብራት፤ በሰላም ወጥቶ መግባት ዋስትና ያጣው፤ በንጹሐን ላይ የሚፈጸም ጭፍጨፋና መፈናቀል፤ እየገነገነ የመጣው ሙስና፤ እንደ ሰደድ እሳት እየተስፋፋ ያለው ብልሹ አሰራር፤ አይን ያወጣው ዘረፋና ሙስና፤ እየተካረረ የመጣው ጎሰኝነት እና ሌሎች አገራዊና ሕዝባዊ ህመሞች መነሻዎች በርካታ ቢሆኑም የሕወሓት ባህሪና የተሳሳተ ርዕዮተ አለም ግን ዋነኛው ነው። ደረጃው ይለያይ እንጂ በአንድም በሌላ በኩል እኔም እናንተም ተጠያቂ ነን። አነዚህን ኅልቆ መሳፍርት የሌላቸውን ችግሮች ለመቅረፍ እንደየባህሪያቸው ፖሊሲና ስትራቴጂ ቢያስፈልጋቸውም፤ የሚሸከማቸውና ይዟቸው የሚነሳ አስማት (ማጂክ) ይፈልጋሉ። ይሄ አስማት ደግሞ ኢኮኖሚው ነው።
ኢኮኖሚው ችግሮቻችን የመፍቻ ዋና ቁልፍ (ማስተርኪይ) ነው። አሁን ከገባንበት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቅርቃር የመውጫ የማሪያም መንገዳችን ነው። አገርም ሕዝብም ሆኖ ለመዳን ፍቱን መድሀኒታችን ነው። የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ግሽበት፣ ስራ አጥነት፣ ድህነት፣ ችጋር፣ ቸነፈር፣ ጠኔ፣ ርሀብ፣ እርዛት ብሔር ወይም ሀይማኖት የላቸውም። አማራም፣ ትግራዋይም፣ ኦሮሞም፣ ሶማሌም፣ አፋርም፣ ወዘተረፈ አይደሉም። ኦርቶዶክስ፣ እስላም፣ ክርስቲያን፣ ካቶሊክ፣ ዋቄ ፈናም አይደሉም። ያለልዩነት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ችግሮች ናቸው። ቢቀረፉ ሁሉንም ያለልዩነት እልል የሚያሰኙ፤ ባይቀረፉ በአንድነት ጥያቄ የሚሆኑ ናቸው። ከብልጽግና 1ኛ መደበኛ ጉባኤ በኋላ በተዘጋጁ ሕዝባዊ መድረኮች የተረጋገጠው ይሄ ጥሬ ሀቅ ነው። በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያውያንን በአሉታም ሆነ በአንድነት የሚያቆማቸው በኢኮኖሚው ላይ በሚመዘገው ስኬት ወይም ውድቀት ነው። ሰንደቅአላማ፣ ሀገር፣ ብሔራዊ ጀግና፣ ታሪክ፣ ወዘተረፈ በ2ኛ ደረጃ የሚገኙ ናቸው። የዚህ ለውጥ አስኳል ኢኮኖሚው ነው። ሌሎች እሱን ተከትለውና በእነሱ ዙሪያ የሚመሠረቱ ናቸው። ሀቀኛና እውነተኛ ብሔራዊ መግባባትና እርቅ ላይ ለመድረስም ኢኮኖሚው ወሳኝ ሚና አለው። ቻይናን ይዞ የተነሳው፤ ሳይነጋገሩ ያግባባው፤ ሳይመካከሩ ያስታረቀው፤ ይቅር ያባባለው፤ አንድነታቸውን በጹኑ መሠረት ላይ ያቆመው፤ በኩራት ቀና ብለው እንዲራመዱ፤ ወዘተረፈ ያደረገው ኢኮኖሚው ነው። ብልጽግናም ሆነ መደመር ኢኮኖሚውን አስኳል ያደረገው፤ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የቀረጸው ለዚህ ነው። ሆኖም በሙላት፣ በወጥነት፣ በእልህና በቁጭት መገለጥ ላይ ብዙ ስራ ይጠብቀዋል። የዚህ መጣጥፍ ማጠንጠኛ ችግሮቻችንን ሊወክላቸው በሚችል ሌላ አንድ ትልቅ ችግር ለመፍታት መሞከር ነው።
ወደ ለውጥ ኃይሉ ስንመጣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ከፍ ሲልም የፀጥታና የሕግ የበላይነት ችግሮችን በአንድ ላይ ለመፍታት መንቀሳቀሱ ትኩረቱን በታትኖታል። ጊዜውን፣ ጉልበቱን፣ ሀብቱን አባክኖታል። ስለሆነም በኢኮኖሚው (በጆከሩ) ላይ ማተኮር፣ መረባረብ አልቻለም። ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ማለትም የኑሮ ውድነቱ፣ ስራ አጥነቱ፣ ግሽበቱ፣ ከትልቅ መንግስትነት ወደ ትንሽ መንግስትነት ማለትም መንግስት በሒደት ኢኮኖሚውን ለገበያውና ለዜጋው ትቶ እሱ ድንበር፣ የሕግ የበላይነት፣ መልካም አስተዳደር፣ ወዘተ . ሲያተኩር ዜጋው መሰረታዊ ፍላጎቱን አሟልቶ በሂደት ጥሪት፣ ሀብት ሲያፈራ፣ ተስፋ ሲሰንቅ ወዘተ . በሂደት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ ቀውሶችን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ያቀለዋል።
ተስፋ ከሰነቀ፣ ስራ ካለው፣ በኑሮ ውድነትና በዋጋ ግሽበት ካልተማረረ፣ በየሰዓቱ በሚያሻቅብ የሸቀጥ ዋጋ ካልተራቆተ፣ የትርፍ ህዳግ ከተቀመጠለት እንደ አሽዋ ከበዛ ቀማኛ ደላላ ከተላቀቀ፣ ስለሚበላውም ሆነ ለልጆቹ ምሳ ስለመቋጠር ወዘተ . ሀሳብ ጭንቀት ከሌለበት እንዲሁም ከ5/11 ስሌት የተላቀቀ ሲቪል ሰርቫንት መፍጠር ከተቻለ ቁጭ ብሎ በተረጋጋ ሁኔታ ስለሰላም፣ ስለፍቅር፣ ስለእርቅ፣ ስለይቅርታ፣ ስለዴሞክራሲ፣ ስለፖለቲካ ፣ ወዘተ . ቢወራ መደማመጥ መቀባበል ይቻላል። ከዚህ በላይ ኢኮኖሚው በማንነት፣ በዘውግ ፖለቲካ፣ በሴራ ተረክ ተከፋፍሎ የሚገኘውን ዜጋ ድልድይ ሆኖ የማቀራረብ፣ የመገናኘት አቅም አለው።
ኢኮኖሚው ብሔር፣ ማንነት፣ ዘውግ የለውም። የኦሮሞውም፣ የአማራውም፣ የወላይታውም፣ ወዘተ . የጋራ ወኪል፣ የጋራ አካፋይ ነው። የጋራ ችግር ነው። ኢኮኖሚው እንደ ጆከር ዘር፣ ማንነት ሳይለይ ሁሉንም ወክሎ ሊያጫውት ይችላል። የአንድነት ሆነ የንኡስ ብሔር ኃይላትን ሊወክል ይችላል። የሊበራል ዲሞክራቱንም ሆነ ሶሻል ዲሞክራቱን አልያም “አብዮታዊ ዲሞክራቱን” ያለ ልዩነት ይወክላል። ብልጽግናን፣ ኢዜማን፣ አብንን፣ የእነ ኦቦ ቀጀላን ኦነግ፣ እናትን፣ ወዘተ. ከፍ ሲልም አገርን ሕዝብን ያለ ልዩነት ይወክላል። አዎ! በዚህ ወሳኝ ሰዓት የአገራችንን ዜጎች ለአንድነት፣ ለእርቅ፣ ለመነጋገር፣ ለመቀባበል፣ ለሰላም የሚያቀራርብ ለጊዜው (ታክቲካዊ) እና እጃችን ላይ የቀረን ካርድ ኢኮኖሚውና አኮኖሚው ብቻ ነው። ምንከተለው ፖለቲካዊ ስርዓት በማንነት ላይ የተመሰረተው ፌደራሊዝም ይሁን በግለሰብ መብትና ነፃነት የተዋቀረው ሊበራል ዴሞክራሲ ወይስ ራሱን ሶስተኛ አማራጭ ብሎ የሚጠራ ይሁን ኢኮኖሚው ሁሉን ወክሎ ማጫወት፣ መጫወት ይችላል።
በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራው የለውጥ ኃይል ወደስልጣን ከመምጣቱ ኢኮኖሚውን ወደለየለት ቀውስ ከመግባት የታደገ የማሻሻያ እርምጃዎችን ወስዷል። ከመድሀኒት እና ሌሎች መሰረታዊ ሸቀጦች ግዥ ውጭ ከሶስት ወር በላይ የማይዘለውን የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ በማሳደግ ኢኮኖሚውን ከኮማ ተላቆ ነፍስ እንዲዘራ ተደርጓል። እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ችግር በጥናት በመለየትም ከውድቀት መታደግ ተችሏል። በማስከተልም በርካታ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው። በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ግብረ ኃይልም ቀጣይ ስራዎችን እያጠና ይገኛል። ይሁንና የኢኮኖሚው ችግር ትላንት የተፈጠረ ሳይሆን የበርካታ አመታት የተዛባ የአመራርና የፖሊሲ ችግሮች ድምር ውጤት ስለሆነ ከተዘፈቀበት መዋቅራዊና ተቋማዊ አረንቋ በቀላሉ ይወጣል ተብሎ አይታሰብም። ስለሆነም አገሪቱ በታሪኳ አይታው የማታውቅ ኢኮኖሚያዊ ችግር ላይ ወድቃለች።
ይሄው መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ችግር በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ከመጣው የሕዝብ ብዛት ዕድገት፤ ከአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን፤ ከምርታማነት ባለበት መርገጥ፤ ከንግድ ስርዓቱ መረን የለሽነት፤ ከገበያ ስርዓቱ የተራዘመ ሰንሰለት፤ ከሕገ ወጥ ድለላ ወዘተ. ጋር አብሮ፣ አድሞ ኢኮኖሚውን ፅኑ ታማሚ አድርጎታል። በዚህ የተነሳ የኑሮ ውድነቱ በሰዓታት፣ በቀናት ልዩነት ጣራ እየነካ ነው። የብር የመግዛት አቅም በብርሀን ፍጥነት በሚባል ደረጃ እያሽቆለቆለ ነው። የስራ አጡ ቁጥር እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ ይገኛል። የእነዚህ ሁሉ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሁሉ ድምር ቅርሻት የሆነ ፖለቲካዊ ቀውስ እንደ ሰኔ ዝናብ መጣሁ መጣሁ እያለ ሰማዩም እያጉረመረመ ነው። እስካሁን እዚህም እዚያም ያስተዋልናቸው ግጭቶች ለአመታት ሲቀነቀን ከኖረው የልዩነት ተረክ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ቀውሱን ተከትለው የተከሰቱ ማህበራዊ ቀውሶች ለመሆናቸው ሞራ ገላጭ መሆን አይጠይቅም።
የተሳሳተው ፖለቲካዊ አመራር ለኢኮኖሚያዊ ቀውስ ዳርጎናል። ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ ማህበራዊ መፍረክረክን አሰከትሏል። መላ ካልተበጀለት በዚህ ይቆማል ተብሎ አይጠበቅም። ወደለየለት የፀጥታ፣ የደህንነት ስጋት ሊሸጋገር ይችላል። ይህ ከመሆኑ በፊት ከገጠመን ምስቅልቅል በጊዜ ለመውጣት መስራት አለብን። ከዚህ ለመውጣት ደግሞ ዜጋው፣ መንግስት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማህበራት ከፖለቲካው ይልቅ ኢኮኖሚው ላይ በአንድነት ሊረባረቡ ይገባል።
ሁሉም ነገር ወደ ኢኮኖሚው ግንባር!
መልካም ትንሳኤ!
ረመዳን ከሪም!
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 /2014