ዝክረ ሰሙነ ሕማማት፤
ይህ ሳምንት በክርስትና አማኒያን ዘንድ “ሰሙነ ሕማማት” [የሕማማት ሳምንት] በመባል ይታወቃል። ሳምንቱ ከሆሳዕና እስከ ትንሣኤ ያሉትን ቀናት የሚሸፍን ነው። ኢየሱስ ክርስቶስን ለመያዝ የአይሁድ አለቆችና ካህናት የመከሩበት፤ እርሱን ካልያዙ እህል አንኳን ላለመቅመስ ክፉ መሃላ የተማማሉበት፣ በአስቆሮቱ ይሁዳ ክህደት ጌታን እንደ ወንጀለኛ አስረው ወንጀለኛው በርባንን እንደ ጻድቅ ነጻ ያወጡበት ሳምንትም ነው። ፍጻሜው የተጠናቀቀው የደምና የሕይወት መስዋዕትነት በተከፈለበት የክርስቶስ የመስቀል ሥራ ሆኖ ማሳረጊያውም ትንሣኤ ነው።
ክርስቶስ የተቀበለው ስቃይና መከራ ሲተረክም ጎን ለጎን ተደጋግሞ ስማቸው ከሚነሳው መካከል የአስቆሮቱ ይሁዳ፣ የካህናት አለቆችና ፈሪሳዊያን፣ ገዢው ጲላጦስና በርባን የሚሉት ተዘውትርው ይታወሳሉ። በተለይም እስከ ሞት ድረስ አሳልፎ የሰጠው የራሱ ወዳጅና ደቀመዝሙር ይሁዳና ወንጀሉ እንደ ክብር ተቆጥሮለት ሞቱ በክርስቶስ ሞት የተለወጠለት የበርባን ታሪክም ለምድራዊው የፍትህ ርሃብና ለሰዎች ልጆች የልብ ድንዳኔ ጥሩ ማሳያ ነው።
ከላይ ተመጥኖ የታወሰውን የቅዱስ መጽሐፍ ታሪክና የክርስትና እምነት እንደ ዋና ዓምድ የቆመበትን አስተምህሮ የሚገልጹትን ዋና ዋና አናቅጽ ከአራቱ ወንጌላት (ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ) እየመዘዝን ካስታወስን በኋላ ወደ ዋናው አገራዊ ዐውዳችን ተመልስን በራሳችን ጉዳዮች ላይ ጫን ብለን እንወያያለን።
“ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ የነበረው አስቆሮቱ ይሁዳ ወደ ካህናት አለቆች ዘንድ ሄዶ ክርስቶስን አሳልፌ ብሰጣችሁ ምን ልትሰጡኝ ትችላላችሁ? አላቸው። እነርሱም ሠላሳ ብር መዘኑለት። ከዚያች ሰዓት ጀምሮም አሰልፎ ሊሰጠው ምቹ ጊዜ ይሻ ነበር።… ከእርሱም ጋር ብዙ ሕዝብ ሰይፍና ጎመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሎች ዘንድ መጡ። አሳልፎ የሚሰጠውም የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ብሎ ምልክት ሰጥቷቸው ነበር። ይሁዳም ወደ ኢየሱስ ቀረበና “መምህር ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን!” ብሎ ሳመው። ኢየሱስም መልሶ “ይሁዳ ሆይ በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው።”
“ሲነጋም የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሎች ሊገድሉት በኢየሱስ ላይ ተማከሩ። አስረውም ወሰዱት። ለገዢውም ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። … ጲላጦስም አላቸው ይህንን ሰው በፊታችሁ መርምሬ ከምትከሱበት ነገር አንድስ እንኳን በደል አላገኘሁበትም። እነሆ ለሞት የሚያደርሰው ምንም በደል አልፈጸመም” አላቸው።
“…በዚያ በዓል ሕዝቡ የወደዱትን አንድ እስረኛ ሊፈታላቸው ለገዢው ልማድ ነበረው። በዚያም ወቅት በርባን የሚባል በጣም የታወቀ እስረኛ ነበራቸው። ሁላቸውም ኢየሱስን አስወግድ! በርባንንም ፍታልን! እያሉ ጮኹ። እርሱም ሁከትን በከተማ አስነስቶ ሰውን ስለ ገደለ በወህኒ ታስሮ ነበር። ጲላጦስም ኢየሱስን ሊፈታ ወዶ ዳግመኛ ጠየቃቸው። ነገር ግን እነርሱ ስቀለው! ስቀለው! እያሉ ጮኹ።”
“ለሦስተኛም ጊዜ ኢየሱስ ያደረገው ክፋት ምንድን ነው? ለሞት የሚያደርስ በደል አላገኘሁበትም ስለዚህ እፈታዋለሁ አላቸው። እነርሱ ግን በርባን እንዲፈታ ኢየሱስ ግን እንዲጠፋ ሕዝቡን አባባሉ። እንዲሰቀልም በታላቅ ድምጽ አጽንተው ለመኑት። ጩኸታቸውና የካህናት አለቆችም ቃል በረታ። ጲላጦስም ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገው አላቸው? ሁሉም በአንድ ድምጽ ‹ይሰቀል!› እያሉ ጮኹ። ያንን የለመኑትን ስለ ሁከት፣ ሰውን ስለመግደል በወህኒ ታስሮ የነበረውን በርባንን ፈታላቸው።”
“ጲላጦስም እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ እናንተ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ ሲል በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። ሕዝቡም ሁሉ መልሰው ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን አሉ። በዚያን ጊዜም በርባንን ፈታላቸው። ኢየሱስ ግን ተገርፎ ሊሰቀል አሳልፎ ሰጣቸው።”
የእኛዎቹ የአስቆሮቱ ይሁዳዎችና የበርባን ጠበቆች፤
“ግፍ የተሠራብን በእኛ፤ ካሱ ይሉናል በዳኛ” እንዲል ብሂላችን፤ ኢትዮጵያ እያለፈችበት ያለው መከራ በነበር የሚታወስ ብቻ ሳይሆን ከትውልድ ትውልድ አንገት እያስደፋ ሲዘከር የሚኖር ታሪክ ጭምር ነው። የመከራ እቶን እያጋጋሉ፣ መከረኛው ሕዝብም በረመጡ እየተንገበገበ እንዲሰቃይ አሳር ያሸከሙን አሳረኞች መልካቸውም ሆነ ብዛታቸው የትዬለሌ ነው።
የአስቆሮቱ ይሁዳን መሰል ከሃዲዎች እንደ ፍግ ላይ የጅብ ጥላ በየቦታው ፈልተው “ኢትዮጵያን ለማሰቀል” ያልሞከሩት ሙከራ፣ ያላሴሩት ሴራ አልነበረም። አንዳንዶች ይሁዳዎች በአገሪቱ የሥልጣንና የኢኮኖሚ ወጭቶች ውስጥ በቀዳሚ ተጠቃሚነት እጃቸውን ከተው እፍታውን እየፈተፈቱ ሲጎርሱ ኖረው ምሬት ባንገፈገፈው የሕዝቡ ቁጣ የ“ወጭቱ” ጥቅም ከፊታቸው ዞር ሲል ያደረሱትና እያደረሱ ያለው የግፍ ዓይነትና አበዛዝ በብዙ ማሳያዎች ሊረጋገጥ የሚችል ነው።
“ይሁዳ ክርስቶስን በመሳም አሳልፎ እንደሰጠ” ሁሉ እነዚህን መሰል የእኛ ጉዶችም ኢትዮጵያ ለክፉዎች ተላልፋ እንድትሰጥ ከአደባባይ እስከ ጓዳ፣ ከታላላቅ ጉባዔዎች እስከ የድብቅ ሸንጎዎች ያልዘረጉት መረብ፣ ያላጠመዱት አሸክላ የለም ማለት ይቻላል። ለክፉ ቀን ባህር አሻገረው “ድምጽ” እንዲሆኗው በአዘጋጇቸው የፖለቲካ ጀሌዎቻቸውና የርኩስ ሃሳብ ካህናት ልጆቻቸው አማካይነትም የኢትዮጵያን ስም ለማጠልሸት በሉዓላዊነታችን ላይ ያልለቀለቁት ጥላሸት አልነበረም። ለአይዟችሁ ባይ የዓለም ኃያላን “ፈሪሳዊያን” አሸርጋጆችም ራሳቸውንና ክብራቸውን እያነጠፉላቸው በስመ ሰብዓዊ ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም።
ይሁዳ ከሩቅ አይመጣም። አብሮ ኖሮ እስከ ሞት ላለመለያየት በመሃል ጭምር ኪዳን ቢገባም እንኳን፤ “ጥቅም” ከተመዘነለት ግን ከራሱ ውጭ ማንንም ቢሆን አሳልፎ ለመስጠት ሙት ኅሊናው አይወቅሰውም፤ አይገስጸውም። አስቆሮታዊ ይሁዲነት መልኩ ብዙ፣ ቀለማቱም አያሌ ናቸው። ከሀዲስ አንዴ በክህደቱ ጸንቶ ያሻውን ለመፈጸም ሊታወር ይችላል። አስቸጋሪዎች አስቆሮታዊያን በጋራ ማዕድ ላይ እንደ ብርቱ ወዳጅ እየተጎራረሱ “በሞቴ” “በሞቴ”ን እያስቀደሙ ሞትን ደጋሾች ናቸው። ኢትዮጵያም በእነዚህ ጭምር በጽኑ እየተፈተነች ነው። ሁለት ባላ ተክለው አንዱ ሲነቀል በአንዱ ለመንጠልጠል ዝግጁ የሆኑ በርካቶች በመንግሥታዊ ሥርዓት ውስጥ ተሰግስገው የጭቃ ውስጥ እሾነት ሚናቸውን እየተወጡ እንዳሉ ከራሳቸው ከቁንጮ መሪዎች አንደበት ደጋግመን አድምጠናል።
የአንዳንዶች ጨኸትና የዘመቻ ሩጫ ወንጀለኛውን በርባንን ለማጽደቅ እንደሆነም እያስተዋልን ነው። በወንጀላቸው፣ በግፋቸውና በክህደታቸው ምድራዊ ብቻ ሳይሆን ሰማያዊ ቅጣት እንኳን የሚያንሳቸው የዘመናችን ከሃዲያን እንደ “ጻድቃንና ሰማዕታት” እየተቆጠሩ በሽብሸባ እንዲወደሱ፣ በአድናቆት እንዲሞካሹ የሚደረገው ሩጫና “የሆሳዕና” አድናቆትም በእኛም ዘመን የተለመደ ከሆነ ውሎ አድሯል።
ኢትዮጵያ በአስቆሮቱ ይሁዳ አማካይነት “ለሞት ተላልፋ እንድትሰጥ”፣ የወንጀለኞቹ የእነበርባን ጠበቆችም መላው የዓለም ሕዝብ በአንገታቸው ላይ ኒሻን እንዲያጠልቅ፣ በደረታቸው ላይም ሜዳሊያ እንዲያንጠለጥል” ቀን ከሌት እንቅልፍ አጥተው እየተቅበዘበዙ እንደሆነ እያስተዋልንና እየሰማን ነው።
ከመንፈሳዊ አንድምታ ጋር እያቆራኘን የቆዘመንበትን እውነታ በግልጽ ቋንቋና በተራ የመግባቢያ ወጋችን ትንሽ እናፍታታው። ያለ ምንም የግነት ገለጻ ያለፉት ጥቂት ዓመታት ለኢትዮጵያ ሰሙነ ሕማማት እንደነበሩ ማንም ሊክደው የማይችለው ሐቅ ነው። የሕመሟ ጥዝጣዜም ቀላል የሚባል አልነበረም። በተለይም ከሥልጣን ተገፍትሮ ወደ ተፈጠረበት በረሃ ዳግም የሸፈተው ቡድን የፈጸማቸው የክህደት ተግባራት በቀላሉ ተዘርዝርው የሚያበቁ አይደሉም።
መከላከያን የሚያህል የአገር ኩራት ተክዶ የተወጋውና በታሪክ ይቅር የማይባል በደል የደረሰበት በውስጡ በነበሩት በከሃዲያኑ የአስቆሮቱ ይሁዳ ወላጆች ነበር። በውስጥም የአገሪቱ የፖለቲካ መልካ/ጅረት እንዲናጋ፣ የኢኮኖሚው መሠረት እንዲርድ፣ የማሕበራዊ ትስስሩ ገመድ እንዲላላ፣ የኅብረተሰቡ በጎ እሴቶች እንዲናዱ፣ የሃይማኖት ውቅሩ ስንጥቅ እንዲገጥመው የተቀናበረውና እንዲተገበር የተደረገው እነዚሁ የጥፋት መልእክተኞች “በተጠበቡበት” ሴራ እንደሆነ መካድ አይቻልም።
በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የመሸጉና የተሸሸጉ “የፖለቲካው ካባ ለባሾም” እንዲሁ በሥልጣናቸው ሼል ውስጥ ተደብቀው ሕዝብ እያማረሩ ይሁዳዊ ድርጊታቸውን እየተወጡ እንዳለ በምናያቸው ብዙ ድርጊቶች እያረጋግጥን ብቻም ሳይሆን እውነት መሆኑንም መሪዎቻችን በይፋ እየገለጡልን ነው።
ኢትዮጵያ “የመስዋት በግ” (Scapegoat) ሆና የአገር ከዳተኞችና ወንጀለኞች ጀግና ሆነው እንዲከበሩና የዓለምን ቀልብ እንዲገዙ የሚደረገው ርብርብም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። “ታላቅነታቸውን” በታናናሽ ድርጊታቸው እየገለጹ ያሉ መንግሥታትም በነጋ በጠባ ጉባዔያቸው ላይ እየተሰየሙ መንጫጫታቸውና በማዕቀብ ዱላ ማስፈራራታቸው መዘግየት ካልሆነ በስተቀር ቆሟል ብሎ ለመናገር አይቻልም።
“የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪነታቸውን” መታወቂያ እያውለበለቡ በፍርደ ገምድልነት ኢትዮጵያን ለማሳጣትና የግፈኞቹ ድርጊት እንደ “ጽድቅ” እንዲቆጠር የበርባን ጠበቃ የመሆናቸው ድርጊትም ከበስተጀርባው በማን እንደሚዘወርና እንደሚነዱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠፋዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።
የሁለት ሺህ ዓመቱ የአስቆሮቱ ይሁዳ ድርጊት ዛሬም “ፍሬሽ” ነው። ለበርባን ጥብቅና ካልቆምን ባይ የጯሂዎች ኡኡታም የአጯጯሁ ስልት ካልሆነ በስተቀር ድምጸቱ ልዩነት የሌለው አንድ ዓይነት ነው። ጲላጦሶችም በየአገራቱ የሥልጣን ወንበሮች ላይ ዛሬም እንደተሰየሙ አሉ። ሕማማት የአንድ ሣምንት ጉዳይ ነው። ትንሣኤ ግን ዘላቂና ቀጣይ ነው።
የኢትዮጵያ ሕማማት የሚጠናቀቀው በትንሣኤ ብርሃን ፈክቶ ስለመሆኑ ይሁዳዎቹም ሆኑ የበርባን ጠበቆች በሚገባ አሜን ብለው እውነታውን በመቀበል ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ በሕዝብ ድምጽ እንመክራቸዋለን። እያስተዳደሩን ካሉት መካከልም “ይሁዳዎች” ፍጻሜያቸው ስለማያምር በንስሃ ቢመለሱ ይበጃቸዋል። ከሕዝብ ጉሮሮና ሀብት ላይ እየቆነጠሩ የሚሰበስቡትና የሚዘርፉት ሀብት “ሳይበሉት” እንደሚያልፉ ቢረዱት አይከፋም። ይሁዳ ክርስቶስን በሸጠበት ሠላሳ ዲናር የተገዛው የደም መሬት ነው። በመንግሥት ሥልጣን የተሸሸጉ ኅሊና ቢሶችም ከአገር መቀነት የሚፈቱት “ሀብት” ቤታቸውን የደም ቤት እንዳያደርግ ራሳቸውን ቢያጸዱ ይበጃቸዋል።
ይሁዳ ሆይ ክህደትህ አያዋጣም። በአካላዊ አንደበት በርባን እንዲፈታ መጮኽ ቢቻልም ከውስጥ ኅሊና ኡኡታ ግን ማምለጥ እንደማይቻል የሚመለከታቸው ሁሉ ይወቁት። የሕማማት ሣምንቱ የሚያበቃው ነገ ነው። ነገ ትንሣኤ ይበሰራል። የኢትዮጵያ ሕማማትም እንዲሁ ማለቂያው ቅርብ ነው። አገራዊ ትንሣኤያችንም ሩቅ አይደለም። ሰላም ይሁን! መልካም በዓል።
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 /2014