በዓለም ከቀዳሚ ተወዳጅ ሊጎች መካከል ይጠቀሳል፤ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ። ነገር ግን በአንድ ነገር ይታማል፤ ክለቦቹ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በሚያሳዩት ደካማ ብቃት። ለዚህም በማሳያነት የሚነሳው የሊጉ ተሳታፊ ክለብ(ቼልሲ) ለመጨረሻ ጊዜ ባለ ጆሮ ረጅሙን ዋንጫ ያነሳው እአአ በ2012 መሆኑ ነው። ከዚህም ባሻገር በዚህ የውድድር መድረክ የተሻለ ታሪክ መጻፍ የቻለው ክለብ ሊቨርፑል ብቻ ነው። በዘንድሮው ሻምፒዮንስ ሊግ ግን፤ ከተለመደው ውጪ አራት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ለሩብ ፍጻሜው ደርሰዋል።
ዋንጫውን ለተከታታይ ዓመት ለማንሳት በግስጋሴ ላይ የሚገኘው የፔፕ ጋርዲዮላው ማንቺስተር ሲቲ፣ የሊጉን ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የክለባቸው ለማድረግ እየተጉ ያሉት ቀያዮቹ ሊቨርፑሎች፣ በአዲሱ አሰልጣኛቸው ከነበሩበት ቀውስ ወጥተው አስደማሚ የውድድር ዓመት በማሳለፍ ላይ የሚገኙት ቀያዮቹ ሰይጣኖቹ ማንችስተር ዩናይትዶች እንዲሁም በውድድር ዓመቱ የዋንጫ ተፋላሚ ከሆኑት መካከል አንዱ ቶትንሃም ሆትስፐር ናቸው።
እአአ ከ1999 ጀምሮ ባሉት የውድድር ዓመታት የእንግሊዝ ክለቦች የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳዩት በ2007/2008 እና 2008/2009 ነው። በወቅቱ አራት አራት ክለቦቻቸው ስምንት ውስጥ የገቡ ሲሆን፤ ከዚያን በፊትም ይሁን በኋላ ግን ዕድሉን አላገኙም። ከአራቱ ክለቦች የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ ያነሱት ሁለቱ ክለቦች ብቻ ሲሆኑ፤ ማንቸስተር ሲቲ እና ቶተንሃም ግን በመድረኩ የተመዘገበ የአሸናፊነት ታሪክ የላቸውም። በአንጻሩ የላሊጋው ክለቦች በመድረኩ ጫና የፈጠሩ ሲሆን፤ ያለፉትን አምስት ዋንጫዎችም የስፔን ክለቦች ነበሩ የወሰዷቸው።
በተለይ በዚህ ውድድር ስኬታማ የሆነው ሪያል ማድሪድ፤ አንድ ጊዜ በተቀናቃኙ ባርሴሎና የበላይነቱን አሻግሮ ከመስጠት ባለፈ ለአራት ተከታታይ ዓመታት ዋንጫውን በማንሳት አቻ ያልተገኘለት ክለብ ነው። ነጫጮቹ ዋንጫውን ለ13ጊዜያት በማንሳትም ማንም የማይደርስበትን ክብረወሰን አርቀው ሰቅለዋል። ለክለቦች በየሃገራቱ ከሚካሄዱት የሊግ ጨዋታዎች ባሻገር በዚህ ውድድር ውጤት ማስመዝገብ በእግር ኳስ ታላቅ ክብርን የሚያቀዳጅ ነው። ከዚህም ባሻገር ከአውሮፓ ምርጥ ክለቦች ተወዳድሮ አሸናፊ የሚሆነው ክለብ ምርጥ የመባል እንዲሁም በባሎን ድ ኦርም ተጫዋቾችን የማስመረጥ ሰፊ ዕድል ይፈጥርለታል። የፕሪምየር ሊጉ ግለቦችም ይህንን ለማሳካት እንደሚፋለሙም ይጠበቃል።
በአራቱ ዓመታት ተሳትፏቸው ለሶስት ጊዜያት ስምንት ውስጥ መግባት የቻሉት ውሃ ሰማያዊዎቹ ዋንጫውን ማንሳት የዚህ ዓመት ስኬታቸው ነው። አሰልጣኙ ፔፕ ጋርዲዮላ ፕሪምየር ሊጉን ከመቀላቀላቸው አስቀድሞ ከባርሴሎና ጋር ሁለቴ ዋንጫውን ያነሱ ሲሆን፤ ክለባቸው በሻምፒዮንስ ሊጉ የነበረው እንቅስቃሴ ለአሸናፊነት ሊያበቃቸው እንደሚችልም ይገመታል። ለዚህም ከሻካታር ዶንቴስክ እና ከሻልክ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ያስመዘገቡት ውጤትም ማሳያ ነው። የክለቡ አጥቂ ሰርጂዮ አጉዌሮ አሁንም ግብ በማምረት ላይ ሲሆን፤ በየ70 ደቂቃው አንድ ግብ እያስቆጠረ እንደሚገኝም የሻምፒዮንስ ሊጉ መረጃ ያሳያል። እአአ በ2017 የውድድር ዓመት 16 ውስጥ መግባት የቻለው ቶትንሃምም በተመሳሳይ ከስምንቱ ክለቦች መካከል አንዱ ሆኗል።
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ ድልድል መሰረትም ሁለቱ ክለቦች ከሊጋቸውም አልፈው አቅማቸውን የሚለኩበት መድረክ ፈጥሮላቸዋል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ይፋ በተደረገው በዚህ የጨዋታ መርሃግብር መሰረትም አንድ የእንግሊዝ ቡድን ግማሽ ፍጻሜውን መቀላቀል እንደሚችል ማረጋገጥ ይቻላል። በአንድ ጎል ብልጫ የተለያየ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የሁለቱ ክለቦች የግብ አምራቾች አጉዌሮ እና ሃሪ ኬይንም ለክለባቸው ግቦችን በማስቆጠር ይፎካከራሉ። ያለፈው የውድድር ዓመት ለፍጻሜ ደርሰው በሪያል ማድሪድ የተሸነፉት ቀያዮቹ፤ በመድረኩ የተሻለ ተሳትፎ አላቸው።
የአምስት ጊዜ የዋንጫ ባለቤት የሆኑት ሊቨርፑሎች በምድብ ጨዋታዎች የነበራቸው እንቅስቃሴ ጥሩ የሚባል ሲሆን፤ በሩብ ፍጻሜው ከፖርቶ ጋር የሚገናኙ ይሆናል። ያለፈው ዓመት 16 ውስጥ የተገናኙት ሁለቱ ክለቦች በሊቨርፑል ሰፊ የጎል ብልጫ መጠናቀቁም የሚታወስ ነው። በቀድሞው የክለቡ ተጫዋችና በአሁኑ አሰልጣኛቸው ሶሻየር ከነበሩበት ያገገሙት ማንችስተር ዩናይትዶች፤ ጉዳት እየፈተናቸውም የፈረንሳዩን ክለብ ፒኤስጂን ያሸነፉበት ውጤት አስደናቂ የሚባል ነበር።
ቀያዮቹ ሰይጣኖች ሶስት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ከእንግሊዝ ክለቦች ሁለተኛውን ስፍራ ይይዛሉ። በሩብ ፍጻሜ ድልድሉ የሚገናኙት ከስፔኑ ኃያል ክለብ ባርሴሎና ጋር ሲሆን፤ ይህም ጨዋታ ሳይፈትናቸው እንደማይቀር ይጠበቃል። ሁለቱ ክለቦች እአአ 2009 እና 2011 የፍጻሜ ጨዋታ ቢገናኙም ድሉ የካታሎኑ ክለብ ነበር። ስምንቱን ከተቀላቀሉት ክለቦች መካከል ከእንግሊዝ ክለቦች ውጪ የተገናኙት ደግሞ አያክስ እና ጁቬንቱስ ናቸው።
አያክስ ከሊቨርፑል ቀጥሎ አራት ዋንጫዎችን በማንሳት የሚቀመጥ ክለብ ሲሆን፤ በኮከቡ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሃትሪክ ሳይታሰብ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለው የጣሊያኑ ክለብ ሁለቴ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል። በግማሽ ፍጻሜውም የማንቺስተር ሲቲ እና የቶትንሃም አሸናፊ ከጁቬንቱስና አያክስ አሸናፊ ጋር የሚገናኝ ይሆናል። የማንችስተር ዩናይትድና ባርሴሎና አሸናፊ ደግሞ ከሊቨርፑል እና ፖርቶ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 9/2011
በብርሃን ፈይሳ