በሃገር ውስጥ ሊጎች ብቻ ለሚጫወቱ ተጫዋቾች ዕድል ለመስጠት በሚል የተጀመረው የቻን ዋንጫ፤ በየሁለት ዓመቱ እየተካሄደ አሁን ስድስተኛው ላይ ደርሷል። ኢትዮጵያ ደግሞ የስድስተኛው የቻን ዋንጫ አዘጋጅ እንድትሆን ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፈቃድ ከተሰጣት ከዓመት በላይ ሆኗታል፡፡
የቀራት የመሰናዶ ጊዜም በወራቶች የሚቆጠር ዕድሜ ብቻ ነው ያለው። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን እንዲሁም ከሌሎች መንግስታዊ አካላት ጋር የሚያከናውነው ስራ ጊዜውን ከግምት ያስገባ አይመስልም። አዲስ ዘመን ጋዜጣ በተለያዩ ጊዜያት በጉዳዩ ላይ በሰራው ዘገባ ፌዴሬሽኑ የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ነው የገለጸው። ውድድሩን የማዘጋጀት ፍላጎትና ዝግጁነት መኖሩንም እንዲሁ፤ ነገር ግን ስራው በግልጽ የሚታይ አልሆነም።
በቻን የሚሳተፉት ሃገራት 16 ሲሆኑ፤ በአራት አራት ቡድኖች ተከፍለውም በአንድ ስታዲየም ውድድራቸውን ያደርጋሉ። በዚህም መሰረት አራት ስታዲየሞች ለውድድሩ አስፈላጊ በመሆናቸው፤ በአዲስ አበባ ከተማ በመገንባት ላይ የሚገኘው ብሄራዊ ስታዲየም፣ የባህርዳር፣ የመቐሌ እና የሃዋሳ ስታዲየሞች ተመርጠዋል። ዝግጅቱን አስመልክቶ የካፍ የባለሙያ ቡድኖች በየወቅቱ ቅኝት የሚያደርጉ ሲሆን፤ ባሳለፍነው ሳምንትም በኢትዮጵያ በነበረውን ጉብኝት አጠናቆ መመለሱን ሶከር ኢትዮጵያ አስነብቧል። ለአምስት ቀናት በነበረው ጉብኝት ልኡኩ በስታዲየሞቹ ተዘዋውሮ የዝግጅቱን ግምገማ በማጠናቀቅ ተመልሷል።
በቅኝቱ መሰረትም የቻን 2020 የኢትዮጵያ መሰናዶ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል የሚለውን ግብረ መልስ በተያዘው ሳምንት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ለሀገሪቱ መንግስት እንደሚልክም ታውቋል። ባለፈው ሐሙስ አዲስ አበባ የገቡት የቡድኑ አባላት፤ አርብ ዕለት በሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ጉብኝታቸውን በማድረግ ነው ግምገማቸውን የጀመሩት። ጉብኝቱን በመቀጠልም በመቐለ የትግራይ ዓለም አቀፍ ስታዲየምን ተመልክተዋል።
በቅኝታቸውም የመጫወቻ ሜዳውን፣ በስታዲየሙ ቅጥር ግቢ የተሰራውን የመለማመጃ ሜዳ እንዲሁም የመቐለ ዩኒቨርሲቲን ስታድየም ጎብኝተዋል። በስታድየሙ ውስጣዊ እና ውጫዊ ምልከታ ካደረጉ በኋላም በሀዋሳ ስታዲየም የተገጠመው መብራት በመቐለ አለመከናወኑን እንደ ጉድለት ማንሳታቸውን ዘገባው ጠቁሟል። ሶስተኛ መዳረሻቸውን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም በማድረግም፤ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ (ፔዳ ጊቢ) የአፄ ቴዎድሮስ ስታድየም የመለማመጃ ሜዳውን ተመልክተዋል። ከትናንት በስቲያም የመጀመሪያ ዙር ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን ብሄራዊ ስታዲየም ጎብኝተዋል።
በዚህም ስታዲየሙ የሚጠናቀቅበትን ጊዜ አስመልክቶ ጥያቄ ማቅረባቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አስታውሷል። ውድድሩ ከሚካሄድባቸው ስታዲየሞች ባሻገር ለልምምድ የሚያገለግሉትን በወጣቶች አካዳሚ ያሉ ሁለት ሜዳዎችን እንዲሁም አንጋፋውን የአዲስ አበባ ስታዲየም ተመልክተዋል። በሰጡት ግብረመልስ መሰረትም አንድ ተጨማሪ የመለማመጃ ሜዳ በቶሎ መሰራት እንዳለበት ለፌዴሬሽኑ አሳስበዋል። በቅኝት ቡድኑ የተካተቱት፤ የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የሆኑት ሊሆድጋር ቴንጋ እና ሞሰስ ማጎጎ፣ የካፍ የክለቦች ፍቃድ ሰጪ ኃላፊ አህመድ ሀራዝ እንዲሁም ሁለት የሚዲያ ባለሙያዎች ናቸው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 9/2011
በብርሃን ፈይሳ