እአአ በ2020 በጃፓን ቶኪዮ ለሚካሄደው ኦሊምፒክ በእግር ኳስ ለመሳተፍ ብሄራዊ ቡድኖች የማጣሪያ ጨዋታቸውን በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድንም በመጪው ሐሙስ ይጫወታል። በዝግጅት ላይ የሚገኘው ቡድኑ በዕቅዱ መሰረት ባለፈው ሳምንት ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን አካሂዷል።
የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ያለፉትን ወራት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር እና ባልደረቦቻቸውንም ወደ ስታድየሞች በማሰማራት ከፕሪምየር ሊጉ እና ሌሎች ሊጎች ለኦሊምፒክ ቡድኑ የሚሆኑ ተጫዋቾችን ሲመለከቱ ቆይተዋል። በዚህም በሀገሪቱ ሁለተኛ ሊግ ከሆነው ከፍተኛ ሊግ ስምንት ተጫቾችን ማካተት ተችሏል። አሰልጣኙ ለወጣት ተጫዋቾች ምርጫ ወደ ከፍተኛ ሊግ ቢያመሩም የተመለከቱት ግን በአንፃራዊነት ለረጅም ጊዜ የተጫወቱ እና በእግር ኳስ ጊዜያቸው በማብቃት ላይ የሚገኙት በርካታ ተጫዋቾች እንደሆኑ መታዘባቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ጠቁመዋል።
በምልመላቸውም ለቡድኑ አንድ የውጭ ተጫዋችን ጨምሮ ለ34 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገዋል። በጥሪው መሰረትም ቡድኑ ማረፊያውን በዋቢ ሸበሌ ሆቴል በማድረግ ልምምዱን የጀመረው ባለፈው ሳምንት ሲሆን፤ ከሲሺየልስ ብሄራዊ ቡድን ጋር ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችንም አከናውኗል። የአቋም መለኪያ ጨዋታዎቹን ተከት ሎም ለቡድኑ ብቁ የሆኑ ተጫዋቾችን በመለየት ከቡድኑ ጋር አብረው የሚቀጥሉ ይሆናል። በዚህም በቅድሚ 26 ተጫዋቾችን በመምረጥ ስምንቱ የተቀነሱ ሲሆን፤ በቀጣይም ሦስት ተጫዋቾችን ወደ ክለባቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል። ሐሙስ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከማሊ ጋር ለሚደረገው ጨዋታም ቡድኑ ዝግጅቱን ቀጥሏል።
የመልሱን ጨዋታም በ19 ባማኮ ላይ የሚያደርግ ይሆናል። በዚህ ውድድር ህግ መሰረት የወንዶች ቡድን ተጫዋቾች ከ23 ዓመት በታች ሲሆኑ፤ በሴቶች በኩል ግን የዕድሜ ገደብ አልተደረገባቸውም። የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድንም በማጣሪያው የሚሳተፍ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ጨዋታውንም በቀጣዩ ወር ማገባደጃ ላይ ያደርጋል። ቡድኑ አሰልጣኝ ሳይኖረው የቆየ በመሆኑ አዲስ አሰልጣኝ መቅጠር አስ ፈላጊ በመሆኑ ፌዴሬሽኑ አሰልጣኞችን አወዳድሯል።
በዚህም በሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ብሄራዊ ቡድኑን ስትመራ የቆየችው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ አሰልጣኟ ሰላም ዘርዓይ ማለፏ ታውቋል። በመሆኑም ቡድኑ በቅርቡ ጥሪ ተደርጎለት ወደ ልምምድ እንደሚገባ ይጠበቃል። በውድድሩ ላይ የሚሳተፉት 15የወንድ ቡድኖች ሲሆኑ፤ ከስድስት ኮንፌዴሬሽኖች የተወጣጡ ሃገራትም ይሆናሉ። ጃፓን ለእግር ኳስ ጨዋታዎቹ አምስት ስታ ዲየሞችን አዘጋጅታለች። ብራዚል እና ጀርመን በሪዮው ኦሊምፒክ በወንድና በሴት ሻምፒዮን የሆኑ ቡድኖችም ናቸው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 9/2011
በብርሃን ፈይሳ