በዘንባባ ያሸበረቀው የውቧ ባህርዳር ጎዳናዎች ባላለፉት ቀናት ከመኪና ይልቅ ብስክሌቶች ነበሩ የሚታዩባት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብስክሌት መጠቀም እየቀነሰ የመጣባት ባህርዳርም በርካታ አፍሪካዊያን የብስክሌት ጋላቢዎችን ስታስተናግድ ቆይታ ለማጠናቀቅ አንድ ቀን ብቻ ቀርቷታል። ኢትዮጵያ ያላት የመልከዓምድር አቀማመጥ እንዲሁም ከአየሩ ጋር በተያያዘ ለብስክሌት ስፖርት ምቹ መሆኗ ይነገራል።
በተለይ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች ደግሞ ተዘውታሪነቱ የላቀ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ኢትዮጵያን ወክለው እስከ ኦሊምፒክ መሳተፍ የቻሉ ጋላቢዎች ከትግራይ ክልል የተገኙ ናቸው። ክልሉ በርካታ ክለቦችን በመያዝ ወጣቶችን የሚያሰለጥን ሲሆን፤ ያፈራቸው ስፖርተኞችም በውጭ ሃገራት ክለቦች እስከ መጫወት ደርሰዋል። በአማራ ክልልም በተመሳሳይ በርካታ የብስክሌት ስፖርተኞች የሚወጡ ሲሆን፤ ጥረት ኮርፖሬሽንን እና አምባሰልን የመሳሰሉ ክለቦችን ማንሳት ይቻላል። በአፍሪካ አህጉር ትልቅ የሆነውን ብስክሌት ሻምፒዮናም ክልሉ (ባህርዳር ከተማ) በማካሄድ ላይ ትገኛለች።
በአፍሪካ ብስክሌት ኮንፌዴሬሽን የሚመራው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና በየዓመቱ የሚካሄድ ውድድር ሲሆን፤ የዘንድሮው ለ14ኛ ጊዜ ነው። ያለፈው ዓመት መጨረሻ የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመወያየትም ከመግባባት ደርሰዋል። በዚህም መሰርት ለአዘጋጅነቱ ፍላጎት ካሳዩት ከተሞች መካከል ባህርዳር የፌዴሬሽኑን መስፈርት በማሟላት ተመራጭ ሆናለች። በዚህም መሰረት ላለፉት ስድስት ወራት ዝግጅት ሲካሄድ ቆይቶ፤ ውድድሩ በደማቅ ሁኔታ በመካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ነገ ይጠናቀቃል።
ይህንን ውድድሩን ከሌላው ጊዜ ለየት የሚያደርገው የ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ማጣሪያ በመሆኑ ነው፤ በመሆኑም በርካታ ሃገራት ተሳታፊ እንደሚሆኑ ይጠበቅ ነበር። ይሁን እንጂ ከ46ቱ የኮንፌዴሬሽኑ አባል ሃገራት የተመዘገቡት 17 ሲሆኑ፤ በውድድሩ ላይ እየተካፈሉ ያሉት ግን 13 ቡድኖች፤ 180 ልዑካን ናቸው። በውድድሩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙትም አዘጋጇን ኢትዮጵያ ጨምሮ፤ ቡርኪናፋሶ፣ ሩዋንዳ፣ ኤርትራ፣ ቤኒን፣ ኮትዲቯር፣ ግብፅ፣ ናሚቢያ፣ ሞሪሽየስ፣ ሲሼልስ፣ አልጄሪያ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ እና ደቡብ አፍሪካ ናቸው።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተካሄደው የመክፈቻ መርሐ ግብር ላይም፤ የክልሉ ፕሬዚዳንት ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳውና ሚኒስትር ዴኤታው ሀብታሙ ሲሳይ፣ የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ርስቱ ይርዳ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ፣ የአፍሪካ ብስክሌት ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር መሃመድ ወጋይ፣ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ወርቁ ገዳ እንዲሁም የክልል እና የሃገራት ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ አባላት ተገኝተዋል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተጀመረው በዚህ ሻምፒዮና በመጀመሪያው ዕለት ኢትዮጵያ ሦስት ወርቅ እና አንድ ነሐስ በማስመዝገብ ነበር መምራት የጀመረችው። በወጣት ሴቶች 15 ኪሎ ሜትር የቡድን ክሮኖ ኢትዮጵያዊያኑ ብስክሌተኞች ተፎካካሪያቸውን ኤርትራዊያንን በመብለጥ የወርቅ ሜዳሊያውን ወስደዋል። በአዋቂ ሴቶች 30 ኪሎ ሜትር የቡድን ክሮኖም በተመሳሳይ የወርቅ ሜዳሊያውን ወስደዋል። በወጣት ወንዶች የ30 ኪሎ ሜትር የቡድን ክሮኖም የበላይነቱ በኢትዮጵያዊያን ሲያዝ በአዋቂ ወንዶች 46 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያውን ወስደዋል።
ኢትዮጵያ ከአዘጋጅነቷ ባሻገር በውድድሩ ተሳታፊ እንደመሆኗ ዝግጅቷን ቀድማ ነው የጀመረችው። ባለፈው ታኅሣሥ ወር የብሄራዊ ቡድን ምልመላ የተካሄደ ሲሆን፤ በተደረገው ማጣራት 35 የብስክሌት ጋላቢዎችን በብሄራዊ ቡድኑ በማካተት አንድ ወር ያህል ልምምድ ሲደረግ ቆይቷል። ኢትዮጵያ በዚህ ሻምፒዮና እንደ ኤርትራ እና ደቡብ አፍሪካ የተሻለ ስም ያላት ሃገር ስትሆን፤ ከረጅም ዓመታተ በኋላ በሪዮ ኦሊምፒክ በስፖርቱ መሳተፏም ይታወሳል። በአምናው ሻምፒዮና ቡድኑ ሁለተኛ በመውጣት አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል።
አሁን ደግሞ በራሳቸው አየር ላይ በሚያደርጉት ውድድር የተሻለ ውጤት እንደሚመዘገብ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በዚህም በቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ የምትወከልበት አንድ ስፖርት ይሆናል። ውድድሩ አራት ተግባራትን የሚያጠቃልል ሲሆን፤ እነርሱም በቡድን የሰዓት ሙከራ፣ በግል የሰዓት ሙከራ፣ የጎዳና ውድድር እንዲሁም ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው የቅልቅል ውድድር ናቸው። ይህ ውድድር 50 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን፤ ሦስት ሴት እና ሦስት ወንዶች ርቀቱን እኩል ተካፍለው በቅብብል ይወዳደራሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 9/2011
በብርሃን ፈይሳ