እንደ ማንኛውም ሜጋ ፕሮጀክት የ“ረጲ ከደረቅ ቆሻሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ጣቢያ”ም ሲፀነስ የራሱን አላማ ይዞ ነው። ይህ በካምብሪጅ ኢንዱስትሪያል ሊሚትድ ስራ ተቋራጭና በቻይናው ኢኢፒ የተገነባውና፣ በ65 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ፣ 120 ሚሊዮን ዶላር (ከ2ነጥብ6 ቢሊየን ብር በላይ) የፈሰሰበትና ዘርፈ-ብዙ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ያስገኛቸዋል የተባሉ ፋይዳዎች አንድ፣ ሁለት ተብለው ተቀምጠው ነበር።
በተለይ በቀን 50 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ሀይል ይሰጣል የመባሉ ጉዳይና ቆየት ብሎ “ወደ 25 ሜጋ ዋት ወርዷል” መባሉ ሲያነጋግር ቆይቷል። አሁንም እያነጋገረ ነው። የረጲ ከደረቅ ቆሻሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ታደሰን ጠይቀን እንደተረዳነው የረጲ ከደረቅ ቆሻሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ መብራት ሀይል ከካምብሪጅ ኢንዱስትሪያል ሊሚትድ ጋር የተፈራረመው እአእ ጃንዋሪ 2013 ነው። ወደ ስራ የተገባው ግን ዘግይቶ ሴፕቴምቤር 2014 ነው።
ይህም የሆነበት ምክንያት በኮንትራት ስምምነቱ ላይ የተቀመጡና ቅድመ-ክፍያን የመሳሰሉ ጉዳዮች ባለመሟላታቸው ነው። ተቋራጩን በተመለከተ የሚነሱ የተለያዩ አስተያየቶች መኖራቸውን ጠቅሰን ትክክለኛውን እንዲያስረዱ የጠየቅናቸው ኃላፊው መብራት ሀይል ግንባታውን የሰጠው ለካምብሪጅ ኢንዱስትሪያል ሊሚትድ ነው ይላሉ። ነገር ግን ካምብሪጅ ከቻይናው ሲኤንኢሲ ጋር ውል ተፈራረሙና መጡ፤ የኢትዮጵያ መብራት ሀይልም አፀደቀላቸው። ወደስራም ገቡ። አሁን በእኛ በኩል የሚታወቀው ፕሮጀክቱ በሁለቱ ተቋራጮች በጋራ መሰራቱን ነው።” በማለት መልሰውልናል።
በጣቢያው ተገኝተን ያነጋገርናቸው የፕሮጀክቱ ቁጥጥርና ጥገና ስራ አስኪያጅ ሚስተር ሴም ንይም የሚያረጋግጡት ይሄንኑ በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ነው። ይህ ነሀሴ 13/2010 ዓ.ም የተመረቀ ፕሮጀክት ወደ ስራ ለመግባት አልዘገየም ወይ? ላልናቸውም “በርግጥ ከአራት አመት በላይ ዘግይቷል። ለምን ዘገየ፣ እንዴት ዘገየ? የሚለው ወደፊት በልዩ ሁኔታ የሚታይ ነው። አሁን ግን ስራው ከ96 በመቶ በላይ ተጠናቋል። ተቋራጩ በተሰጠው አስተያየት መሰረት ሁሉንም ነገር አሟልቶ ሲገኝ እንረከበዋለን።” ያሉ ሲሆን ማመንጫ ጣቢያው ከሶስት ወር በኋላ ወደኦፕሬሽን ስራ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።
ሚስተር ሴም ንይ ግን ስራውን ሙሉ ለሙሉ ማጠናቀቃቸውንና ለማስረከብ ዝግጁ መሆናቸውን ነው የሚያስረዱት። እጅግ ቢበዛ ምን ያህል ጊዜ ይቆያል? ላልናቸውም “እኛ 100 በመቶ አጠናቀናል፤ ከዚህ በኋላ እጅግ ቢቆይ ምናልባት በሁለት ወር የሚረከቡን ይመስለኛል” ነበር ምላሻቸው። ከዚህ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ሲያወዛግብ የቆየው የፕሮጀክቱ ኃይል የማመንጨት አቅም ጉዳይ ነው። ሲጀመር በአመት 50 ሜጋ ዋት ሀይል ያመነጫል ተብሎ የነበረው እያደር ሟሸሸና “አይ አቅሙ 25 ሜጋ ዋት ነው” ወደሚል አሽቆለቆለ። አቶ ሰለሞንም ከዚሁ ጋር በተያያዘ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
50 ሜጋ ዋት፣ 25 ሜጋ ዋት የሚለው ነገር ላይ ምክንያቱ ያልታወቀ ብዥታ ያለበት ጉዳይ ነው ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ በጉዳዩ ላይ እስካሁንም ድረስ ብዥታው እንዳልጠራ ይናገራሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከኮንትራክተሩ ጋርም ክርክር ላይ ነን። ነገር ግን ከሁለቱ አንዱን ይዘን መሄድ ይሻላል በሚል፤ በተለይም የአዲስ አበባ ቆሻሻን ከማፅዳትና ሀይል ማመንጫውን ወደ ስራ ከማስገባት አኳያ ለጊዜው 25 ሜጋ ዋት በሚለው ተስማምተን እየሄድን ነው፤ ይህም የሆነው ከፍተኛ አመራሩ በሚያውቀው ደረጃ ነው በማለት አስረድተዋል። የኮንትራት ስምምነቱ ላይ ያለውንና “በአመት 185 ጊዋሰ/ጊጋ ዋት ሰዓት/ ሀይል ይሰጣል” የሚለውን ያሟላል የሚሉት ኃላፊው አሁን ስምምነት ላይ ያልተደረሰው 50 ወይም 25 ሜጋ ዋት የሚለው ላይ መሆኑንም አስረድተዋል። “እኛ 50 ሜጋ ዋት ነው እያልን ነው ያለነው።
ኮንትራክተሩ ደግሞ 25 ሜጋ ዋት ነው የሚለው። ወደ ክርክር እንግባ ከተባለ ጉዳዩ ሌላ መልክ ነው የሚይዘው። ስለዚህ አሁን የተደረሰበት ውሳኔ በቅድሚያ ጣቢያው ወደ ስራ ይግባ የሚለው ነው። በተለይ የአዲስ አበባን ቆሻሻ ከማስወገድ አኳያ ስራውን ይጀምር፤ ከዛ በኋላ 50 እና 25 ሜጋ ዋት የሚለውን ወይ በውይይት ወይ በክስ የምንሄድበትና ህግ የሚፈታው ይሆናል። በሙከራው እንደተረጋገጠው ግን 25 ሜጋ ዋት ማመንጨት እንደሚችል ነው። 50 ሜጋ ዋት የሚለው ግን ካሁን በኋላ አይገኝም።
የፕሮጀክቱ ፕላንም ሆነ ዲዛይኑ ለ25 ሜጋ ዋት እንጂ ለ50 ሜጋ ዋት አይመጥንም።” ሲሉም እቅጩን ተናግረዋል። 50 እና 20 ሜጋ ዋት በሚለው ብዙም ያልተመሰጡት ሚስተር ሴም ፕሮጀክቱ በቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክቡር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ መመረቁን ወደሚያሳየውና በህንፃው መግቢያ በረንዳ ላይ የተሰቀለውን ፅሁፍ፣ ከፅሁፉም ውስጥ 185 ጊ.ዋ.ስ የሚለውን በማመልከት እሱን ማምረት እንደሚችልና እየሰሩ ያሉትም ከዚሁ አንፃር መሆኑን ገልፀውልናል።
ሀይል ማመንጫ ጣቢያው ለአገሪቱ ምን ያህል ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አለው? የሚለውን ለማወቅ ባደረግነው ጥረት ለጊዜው ካነጋገርናቸው አካላት ያገኘነው መልስ “በአመት የሚገኘውን 185 ጊ.ዋ.ስ ግን በገንዘብ ማባዛትና የሚገኘውን ገንዘብ ማወቅ ይቻላል” ከሚል በስተቀር በአሀዝ የሚያስቀምጥልን ከሁለቱም ወገን አላገኘንም። አቶ ሰለሞንን አሰራሩ ለምን ተወሳሰበ፤ ከሙስና የፀዳ ነው ብለው ያምናሉ? ብለን ጠይቀናቸውም ነበር። “እኔ ከመጣሁ ገና ስድስት ወሬ ነው።
አሰራሩን ሳየው ግን ትክክለኛ አካሄድን የተከተለ ነው። ለማንኛውም እሱ በኋላ የሚጣራ ነው። አሁን ዋናው ጉዳይ ጣቢያውን ወደስራ ማስገባት ነው የሚፈለገው። ሌላው በኋላ ገሀድ የሚወጣ ጉዳይ ነው።” ብለውናል። ከዚሁ ጋር በተያያዘና በስምምነት ከመፍታት ይልቅ ለምን በህግ እንዲታይ አልተደረገም በሚል ለቀድሞዋ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አዜብ ጥያቄ ቀርቦላቸው ጉዳዩ በህግ እንዲታይ ቢደረግም ከተቋራጩ ጋር የተገባው ኮንትራት ግልፅ አልነበረም ሲሉ መመለሳቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 9/2011
በግርማ መንግሥቴ