ዲጂታል ኢትዮጵያ 225ትን ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት ስትራቴጂ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚህ አኳያ በዘርፉ ላይ ልዩ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ እንደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ያሉ ተቋማት የዲጂታል ክህሎት ትምህርቶችን በራስ አቅምና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር እየሰጡ ይገኛሉ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ዶክተር ዐቢይ አሕመድ “ዓለም ባልተጠበቀ ፍጥነት አራተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት እያካሄደች ትገኛለች” በማለት ማህበረሰቡ ከዚህ ክስተት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማረጋገጥ እና ወጣቶቻችን በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ውስጥ ስኬታማ እንዲሆኑ ኢትዮጵያ በንቃት መሥራት እንደሚጠበቅባት ያሳስባሉ። በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት እንደ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence)፣ የበይነ መረብ ቁሶች (Internet of things)፣ ናኖ ቴክኖሎጂ፣ እና ትልቅ ውሒብ (Big Data) ባሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚደገፉ የማምረት፣ የመገናኛ እና የአኗኗር ዘዬ ሽግግርን ለማካሄድ የኢትዮጵያ መንግስት ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ መሆኑን “በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂ ላይ ይፋ አድርገዋል። “ታዳጊዎች አዳዲስ ክሂሎት እና ዕውቀቶችን ይፈልጋሉ፤ የወደፊቱን ጊዜ በተሻለ ለመጠቀም እንዲችሉ የማድረግ ደግሞ የእኛ ኃላፊነት ነው” የሚሉት ወጣቶች የፈጠራና የቴክኖሎጂ ክህሎታቸውን የዳበር እቅድን ነድፎ እየተገበረ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
የትምህርት ተቋማት የሳይንስና ቴክኖሎጂ እውቀታቸው የላቀ ወጣቶችን በፈጠራ ሂደት ውስጥ እንዲያልፉ ከሚሰሩት ተግባር ባሻገር አዲሱ ትውልድ በግል በሚያደርገው ጥረት በርካታ ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ክህሎቶችን እያወጡ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ የፈጠራ ስራዎች በባለሃብቶችና በሚመለከተው የመንግስት አካል ድጋፍ አግኝተውና ወደ ማህበረሰቡ ደርሰው ሲያገለግሉ አይታዩም። ይሄ በሚመለከታቸው አካላት ትኩረት አግኝቶ መፍትሄ የሚሻ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ቀደም ካሉት ግዜያት በተሻለ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች ተነቃቅተው ክህሎታቸውን በመጠቀም የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎችን በየጊዜው ሲያስተዋውቁ ይስተዋላል።
በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከሰማናቸው ስኬታማ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶች ውስጥ ለምሳሌ ያክል ለማንሳት ስንሞክር፤በደብረ ብርሃን ከተማ በኤሌክትሪክ ኃይል የምትሰራ እና አራት ሰዎችን የመጫን አቅም ያላት ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) በአንድ ስራ ፈጣሪ መሰራቷ መግለፅ ይቻላል። የተሽከርካሪዋ አምራች አቶ መቅድም ኃይሉ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዋ በአብዛኛው አገር ውስጥ የሚገኙ ግብዓቶችን በመገጣጠም ነው የተሰራችው። በወርክ ሾፓቸው የተሰራችው ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዋ በማንኛውም የኤሌክትሪክ ቻርጀር ለ3 ሰዓታት ቻርጅ ተደርጋ በሰዓት 40 ኪሎ ሜትር መጓዝ የምትችል እንደሆነች ማወቅ ይቻላል። በኤሌክትሪክ ሃይል የምትሰራው ይህች ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ ሾፌሩን ጨምሮ አራት ሰዎችን የመጫን አቅም ያላትና ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያውያን የፈጠራ ባለሙያ የተሰራች ስኬታማ የቴክኖሎጂ ውጤት እንደሆነች መረዳት ይቻላል።
በተለያየ ጊዜም በወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች የሰው አልባ ድሮን፣ አውሮፕላኖችና መሰል የዲጂታል ቴክኖሎጂ መተግበሪያዎች መሰራታቸውንም መረጃዎች ያመላክታሉ። እነዚህ የፈጠራ ውጤቶች በ2025 ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራተጂ ትግበራን ለማሳካት ከሚያግዙ ክህሎቶች አንዱ እንደሚሆን መገመት ይቻላል። ለዛሬም የዝግጅት ክፍላችን በዚህ አምድ ላይ መንግስት በልዩ ትኩረት ይዞ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ የሚገኘውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ክህሎት ባለሙያዎችን የመደገፍ ስራን የሚያመላክት ጉዳይ ለማንሳት ወድደናል። በዋናነትም ሁለት ወጣትና በትምህርት ላይ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ፈጣሪ ወጣቶችን በእንግድነት በማቅረብ ክህሎታቸውን ተጠቅመው የሰሯቸውን የፈጠራ ውጤቶች እናስተዋውቃችኋለን።
ታዳጊ የፈጠራ ባለሙያ ተማሪ በፀሎት በቀለ በአቤኔዘር ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነች። ታዳጊዋ የኮንስትራክሽን ዘርፉን የሚያግዝ የመገናኛ ዘዴ (ፕላትፎርም) እንደሰራች ትናገራለች። ይህም በቀላሉ ኮንትራክተሮች እንዲሁም ኢንጂነሮች ከደንበኞቻቸው ጋር በቀላሉ መገናኘት የሚችሉበት መንገድ መሆኑን ትገልፃለች።
የቴሌግራም ማህበራዊ መተግበሪያን በመጠቀምና በውስጡ “ቦት” በሚባለው መንገድ የፈጠራ ስራዋን ደግፋ የሰራችው ታዳጊዋ በቀላሉ ግንኙነት የሚፈጠርበትን አማራጭ መስራት ችላለች። “በአገራችን የኮንስትራክሽን ዘርፍ የተማሩ ወጣቶች ተመርቀው ያለስራ ተቀምጠዋል” የምትለው የፈጠራ ባለሙያዋ በፀሎት ባለሙያዎቹ በመንግስት ፍቃድ ያላቸው ቢሆንም ከአሰሪዎች ጋር ለመገናኘት እንደሚቸግራቸው ትገልፃለች። በተጨማሪ አሰሪዎችም ቤት ከማሳደስ አንስቶ ትላልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር ሁነኛ ባለሙያ ማግኘት እንደሚቸግራቸውና የግንኙነት መንገዱ እክል ያለበት መሆኑን ትናገራለች። በዚህ ምክንያት ክፍተቱን ለመሙላት በማሰብ ፕላትፎርሙን ለመፍጠር እንዳነሳሳት ትገልፃለች።
“ይህ ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባ ላይ ሆነን በሀዋሳ ከተማ ሳይቶችን ለመገንባት አሊያም ባለሙያዎችን ለማግኘት ብንፈልግ በቀላሉ የስራ ልምድና ሌሎች ዶክመንቶችን ማግኘት እንችላለን” የምትለው ታዳጊዋ የፈጠራ ባለሙያ እርቀት ሳይገድብ የግንኙነት አድማስን ለማስፋት በማሰብ ፕላትፎርሙን መፍጠር እንደቻለች ታስረዳለች። በተለይ ህጋዊ ውል ለመፈራረምና ምቹ የመግባቢያ መንገድ መሆኑንም ታስረዳለች።
“መተግበሪያው በርካታ ፋይዳዎች አሉት” የምትለው በፀሎት በዚህ ቴክኖሎጂ ደንበኞችና ባለሙያዎች ግንኙነት መፍጠር ከቻሉ ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር እንደሚያስችል ትናገራለች። በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብዙ ሳይቶችን ይዘው ስለሚሰሩ ወደ ክፍለ አገር ወጥተው ከደንበኞች ጋር ውል ለመፈፀም ፍላጎት ላይኖራቸው እንደሚችል በመግለፅ ይህ የግንኙነት መድረክ ግን በዚያው አካባቢ የሚገኙና የተማሩ ኢንጂነሮችን ከደንበኞች ጋር የማገናኘቱን እድል እንደሚፈጥር ትናገራለች።
ታዳጊ በፀሎት ይህን ፕላትፎርም ወደ አፕሊኬሽንና ዌብሳይት ለመቀየርና ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን እየሰራች እንደሆነ ትናገራለች። ይህ የፈጠራ ስራዋ በሁሉም ወገኖች ተደራሽ የሚሆን ከሆነ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ መፍጠር የሚችል መሆኑን ትገልፃለች። በቀጣይ የሶፍትዌር ኢንጂነር በመሆን መሰል የፈጠራ ስራዎችን ማበርከት እንደምትፈልግ ተናግራም ለዚህ ውጤታማ ስራዋ የራይድ የትራንስፖርት አገልግሎት የፈጠረችው የቴክኖሎጂ ግንኙነት ትልቅ መነቃቃት እንደፈጠረላት ገልፃለች።
“ታዳጊዎች በተለይ ሴቶች መበረታታት አለባቸው” የምትለው ተማሪና የፈጠራ ባለሙያ የሆነችው በፀሎት ማህበረሰቡ ይህን መሰል ክህሎት ያላቸውን ልጆች የሚደገፉበትን ምቹ አጋጣሚዎች ሊፈጥር እንደሚገባ ትናገራለች። በተለይ መንግስትም ሆነ የትምህርት ተቋማት የቴክኖሎጂ ምቹ መሳሪያዎችን እንዲሁም ሌሎች መሰል ድጋፎችን እንዲያደርግ ትጠይቃለች።
ሌላኛው የፈጠራ ባለሙያ ተማሪ ዘካሪያስ ወንዳፍራሽ ይባላል። የህክምና ዘርፍ ላይ በተለይ ደግሞ ለአይን ህከምና ሙያ የሚያግዝ ዲጂታል የፈጠራ ውጤትን አስተዋውቋል። በተለይ በኢትዮጵያ የህክምና ዘርፍ ላይ በአገር በቀለ የፈጠራ ውጤቶች የህክምና መሳሪያዎችን የመፍጠር ልምድ ባለመኖሩ የእርሱ የፈጠራ ውጤት በርካታ ነገሮችን እንደሚያቀል ይጠበቃል። በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገቡ መሳሪያዎችን ለማስቀረት እርሱን መሰል ባለሙያዎችን ከማበረታታት ባለፈ በባህላዊ መንገድ የሚተገበሩ ዘዴዎችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለመቀየር የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ጥርጥር አይኖረውም።
ታዳጊ የፈጠራ ባለሙያው ዘካሪያስ በዓይን ህክምና ውስጥ “ኦክታምቦሎጂ” በመባል የሚታወቀውን የዓይን እይታ መፈተሻ መንገድ ዲጂታላይዝ በማድረግና ቀደም ሲል የነበረውን ክፍተት በመሙላት፣ የስሌት ጊዜው የሚወስደውን ጊዜ እንዲቆጥብ በማድረግ በአዲስ መልክ ማስተዋወቅ ችሏል። በተለይ የዓይን እይታቸው የቀነሱ ሰዎች የሚገኙበትን ደረጃ ከማሳየቱም ባለፈ የመንጃ ፍቃድ ለማውጣት በርካታ ሰዎች የሚወስድባቸውን ጊዜ እንደሚቆጥብ ነው የሚናገረው።
“የእይታ መለኪያ ማሽኑ በቀላል ወጪ የተሰራና ከውጭ የሚመጡ ማሽኖችን የሚያስቀር ነው” የሚለው ታዳጊው የፈጠራ ባለሙያ፤ አጠቃላይ ወጪው 2ሺ800 ብር እንደሆነ ገልጾ ከውጭ የሚገባው ግን እስከ 14ሺ ብር እንደሚፈጅ ነው የሚናገረው። ከዚህ አንፃር ታዳጊው የሰራው ይህ የዓይን እይታን መለኪያ ዲጂታላይዝድ ማሽን ወደ ትግበራ የሚገባ ከሆነ በርካታ ነገሮችን እንደሚያቀል መገንዘብ ይቻላል።
የዲጂታል የዓይን እይታ ደረጃ መለኪያው በቀላሉ በታካሚው በራሱ ቁጥጥር የሚተገበር ሲሆን ውጤቱ ግን ሚስጢራዊ በሆነ መንገድ ወደ አካሚው (ነርስ ወይም ዶክተር) በመግባት ቀልጣፋና ተዓማኒ ውጤትን የሚያስተላልፍ ነው።
የታዳጊ ዘካሪያስ የፈጠራ ስራ የሆነው የአይን ህክምና መሳሪያ ለማምረትና በሁሉም የህክምና ጣቢያዎች ለማደረስ ቀላል እንደሆነ ይናገራል። በተለይ በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ ጤና ጣቢያዎች፣ ጤና ኬላዎች እንዲሁም የመንግስትም ሆነ የግል የጤና ተቋማት ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ወጥቶበት ከሚመጣው መሳሪያ ይልቅ የእርሱን የፈጠራ ውጤት በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንደሚችሉ ያስረዳል።
“ወደፊት በህክምና ዙሪያ ላይ ያሉ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎችን መስራት እፈልጋለሁ” የሚለው ታዳጊው የፈጠራ ባለሙያ ዘካሪያስ በተለይ በህክምና የክፍያ ስርዓትና አላስፈላጊ ብክነት ላይ አንድ የፈጠራ ውጤት ለማበርከት ፍላጎት እንዳለው ይናገራል። ይህ ብቻ ሳይሆን በህክምና ሂደት ላይ ያሉ ማንኛውንም አሰራሮች ዲጂታላይዝድ ለማድረግና የአሰራር ስርዓቶቹን ለማዘመን እንደሚተጋ ይናገራል። ይህን መሰል ህልም ያላቸው ታዳጊዎች ስኬታማ እንዲሆኑ መንግስትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ይገልጻል። አሁን ላይ ግን ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ የፈጠራ ባለሙያዎችን የሚያበረታቱ ጅምር ሙከራዎችን እንዳሉም ተናግሯል።
እንደ መውጫ
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የትግበራ ሂደት የሚሳካው መሰል ታዳጊ ፈጣሪ ባለሙያዎችን ማበረታታት ሲቻል እንደሆነ የዝግጅት ክፍላችን ያምናል። በአገሪቱ ባሉ በሁሉም የትምህርት ተቋማት ውስጥ ብሩህ አእምሮ ያላቸው ታዳጊ ተማሪዎች እንዳሉም እንዲሁ። ለእነዚህ ተማሪዎች ምቹ ሁኔታን መፍጠር ለተያዘው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሽግግር መሳካት የራሱን ድርሻ እንደሚጫወት መገመትም የሚከብድ አይደለም።
በተጨማሪ በዲጂታል ስትራቴጂው የአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳው ግብርናን፣ ማኑፋክቸሪንግን፣ ማዕድንን፣ ቱሪዝም ፣ አይሲቲ እና የፈጠራ ኢንዱስትሪው የቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ የመረጣቸው ዘርፎች ሲሆኑ፤ እነዚህ ዘርፎች የስራ እድል እንዲፈጥሩ፣ የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኙ እና አካታች እድገትን ዕውን እንዲያደርጉ ይጠበቃል። ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ መሰል የፈጠራ ውጤቶችን ማበረታታት እንዲሁም በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ በርካታ ወጣቶችና ታዳጊዎች ብቁ ክህሎት እንዲኖራቸው ለማስቻል መስራት አስፈላጊ ነው እንላለን።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11 /2014