ውለታ በብዙ መንገድ ይገለጻል። በተለይ ለአገርና ወገን ሲሆን ደግሞ ትርጉሙ ለየት ይላል። ሁሉም አገር የራሱ ጀግና አለው። እኛም ለአገራችን ውለታ የዋሉ በርካታ የቁርጥ ቀን ልጆች አሉን። ኢትዮጵያ ማንን ትመስላለች ቢባል ህዝቦቿን ከህዝቦቿም ባለውለታዎቿን እላለሁ። አገር የትውልድ ቅብብሎሽ ናት። በዚህ የትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ሁልጊዜም አንድ በላጭ እውነት አለ እርሱም አገርና ህዝብ ነው።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከአገርና ህዝብ ከሉዓላዊነትም የበለጠ አንድም ግለሰባዊ ጉዳይ አልነበረም። ዛሬም በዚህ የአገርና ህዝብ እውነት ውስጥ መጓዝ ይኖርብናል። አላማችን አንድ አገር፣ አንድ ህዝብ መፍጠር ከሆነ ከግለሰብና ከቡድን እሳቤ የጸዳች ኢትዮጵያ ታስፈልገናለች።
አሁን ላይ እንወያይ፣ እንመካከር ስንል በአገር አቀፍ ደረጃ እንቅስቃሴ የተጀመረው እኮ ይሄን በብሔርና፣ በሃይማኖት፣ በጎሳና በፖለቲካ ልዩነት የተፈጠሩ ችግሮቻችንን ለማጥበብ ነው። ከእኔነት ስሜት ወጥተን የጋራ አገር ለመገንባት ነው። እኛ አልገባንም እንጂ ተነጋግሮ መግባባት የሰው ልጅ በስልጣኔው የደረሰበት የመጨረሻው የዘመናዊነት ጥግ ነው። ሀያላን አገራት እንዴት ሀያል ሆኑ፣ እንዴት ከኋላ ተነስተው ከፊት ቀደሙ ለሚል ጥያቄ አንድ መልስ ነው ያለው፤ እርሱም በልዩነታቸው ላይ ተነጋግረው ስምምነት ላይ በመድረሳቸው ነው። እኔና እናንተም ስለአገራችን ስንል በችግሮቻችን ላይ ተነጋግረን የጋራ መስማማት ላይ ካልደረስን ከዚህም በላይ ዋጋ መክፈላችን አይቀርም። እኛ ያልገባን ሀያላኖቹ የገባቸው አንድ ነገር ቢኖር የውይይት ጥበብ ነው።
የውይይት ጥበብ ከስልጣኔ ባለፈ ለአንድ አገርና ህዝብ የሰላም ዋስትና ነው። ህልማችን ሰላም ከሆነ፣ ሀሳባችን ስልጡን አገር መፍጠር ከሆነ የውይይትን ጥበብ ወደ ልባችን ማስገባት ይኖርብናል። ተነጋግሮ መግባባትን ባህል እስካላደረግን ድረስ ህልሞቻችንን ሁሉ ውሃ ነው የሚበላቸው። ከችግር ፈጣሪነት ወጥተን ወደ መፍትሄ አመንጪነት መሸጋገር አለብን። የትላንት አዳፋ ታሪኮቻችንን ዘግተን በእርቅና በመተቃቀፍ ኢትዮጵያን ለማሻገር መትጋት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል። እኛ ከትላንት እስከዛሬ ችግሮቻችን ላይ እንጂ መፍትሄ ላይ በርትተን አናውቅም። ሀሳቦቻችን ሁሉ ችግር ፈጣሪዎች ሆነው ሲጎዱን ከርመዋል። እንደ ብሔረሰብ ምድር፣ እንደ ብዙሀነታችን የተለያየ ሀሳብ ሊኖረን ይችላል። ልዩነት ለመፍጠር የምንበረታውን ያክል በውይይት አንድነት ለማምጣት ብንበረታ ኖሮ ዛሬ ላይ በዚህ ልክ በሀሳቦቻችን መከራ አናይም ነበር።
ለምሳሌ፣ ቻይናውያን ያስደንቁኛል፤ ቻይና በህዝብ ቁጥር ከዓለም አንደኛ ናት። የዓለምን አንድ ሶስተኛ የህዝብ ቁጥርም የያዘች አገር ናት። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን አንድ የማይናወጥ አቋም አላቸው፤ ቅድሚያ ለቻይና የሚል። ቻይናውያን እንደ ብዛታቸው ብዙ አይነት ሀሳብ ያላቸው ናቸው፤ በጣም የሚገርመው ደግሞ ያን ሁሉ ሀሳብ ለነውጥ ሳይሆን ለለውጥ፣ ለሽብር ሳይሆን ለብልጽግና ተጠቅመው አገራቸውን በኢኮኖሚ ከዓለም ቀዳሚ አድርገዋል። እኛም ለአንድነታችን ዋጋ ከሰጠን የህዝብ ቁጥራችንን፣ የወጣት ቁጥራችንን ለነውጥ ሳይሆን ለለውጥ መጠቀም እንችላለን።
ወደ ህንድና ወደ አሜሪካ ብትሄዱም ተመሳሳይ ነገር ነው የምታገኙት። ሁሉም ስልጡን አገራት በየትኛውም ጉዳይ ላይ አገራቸውን ያስቀደሙ ሆነው ነው የምናገኛቸው። እኛ አገር ሲሆን ግን ሌላ ነው፤ አንድነታችን የሚታየው ጦርነት ላይና የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት ላይ ነው። በእርግጥ ይህ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን በውስጥ ጉዳዮቻችን አንድነት ይጎለናል። አገር ለመገንባት በምንሮጠው ሩጫ ላይ እኔ ልቅደም እኔ የምንባባል ነን። ሀሳቦቻችን እኔነትን ያረገዙ ናቸው። አምናን እያስታወስን፣ ድሮን እየፈተሽን ዛሬን የምንገፋፋ ነን። እውነት እላችኋለሁ ስልጡን ብንሆን ኖሮ ጊዜ ባለፈባቸው የመቶ አመታት ታሪክ ወደኋላ አስታውሰን አንገፋፋም ነበር። ለእኛ ኋላ ቀርነት ከዚህ የተሻለ ጥሩ ማረጋገጫ አይመጣም። በሀሳቦቻችን ኋላ ቀሮች ነን፤ እናም ዘመናዊነትን ሊያላብሰን የሚችል የሀሳብ ሞገስ ያስፈልገናል።
ሀሳብ ሞገስ ነው፤ ሀሳብ ውርደት ነው። አንዳንዶች በሀሳባቸው ሞገስን አግኝተዋል። እንደእኛ አይነቶቹ ደግሞ በሀሳባቸው ውርደትን ተከናንበዋል። ሀሳብ ድርጊት ነው፣ ድርጊት ውጤት ነው። አሁን ላይ ፍሬአቸውን እየበላን ያሉ ነገሮች ሁሉ በሀሳባችን የተጸነሱ ናቸው። በሀሳባችን ውስጥ ከእኔነት የቀደሙ፣ ከትላንት የበረቱ አገራዊ ጉዳዮች እስከሌሉን ድረስ በሀሳባችን መከራ ነው የምንፈጥረው። ማረፊያውን አገር ያደረገ ልብ ክፉ ሀሳብ አያስብም። ስፍራውን ትውልድ ያደረገ አእምሮ መጥፎ ነገር አያደርግም። ሀሳቦቻችን እና ድርጊቶቻችን ሰይጣናዊ የሆኑት በልባችን ውስጥ ከእኔነት የገዘፈ ስፍራ ለአገራችን ስለሌለን ነው።
እንደ ብዛታቸው ቢሆን ቻይናውያን ነበሩ ከየትኛውም አገርና ህዝብ ቀድመው እንደ እያሪኮ የሚፈርሱት። ግን በሀሳባቸው ውስጥ አገር የሚል ስዕል ስለሳሉ፣ በልባቸው ላይ ትውልድ የሚል ጽላት ስለቀረጹ አልፈረሱም። መፍረስ በሀሳብ አለመበርታት ነው። መለያየት ምንም ሊሆን አይችልም ተነጋግሮ አለመግባባት ነው። እንደ አገር ማድመጥን መለማመድ አለብን። እስከዛሬ አድማጭ በሌለበት ስናወራ ነበር፤ ለማድመጥ ሳይሆን ለመመለስ ተዘጋጅተን ስናደምጥ ነበር። እስኪ አሁን ደግሞ ታሪኮቻችንን ቀይረን ለመግባባት እናድምጥ፣ ለመስማማት እንናገር። እንልመድ።
ትላልቅ ተአምራቶች የሚፈጠሩት በመደማመጥ ውስጥ እንደሆነ የገባን ጥቂቶች ነን። የተናገርንውን ያክል ብናደምጥ፣ የተሰበሰብውን ያክል ወደ ተግባር ብንገባ ዛሬ ሌላ ነበርን። እመኑኝ በልባችን ውስጥ አንድነትና ወንድማማችነት ካለ ሀሳቦቻችን ጎጂዎች አይሆኑም። ለማድመጥ እንጂ ለመናገር አንበረታም። እንደ አገር እያጠቃን ያለው ነገር አለመደማመጥ ነው፤ ካለመደማመጥም አለመግባባት ነው።
ለመግባባት ማድመጥ ያስፈልጋል። ለመደማመጥ ደግሞ የጋራ ህልምና ራዕይ ግድ ይለናል። ህልምና ራዕዮቻችንን በብሔርና በጎሳ፣ በፖለቲካና በሃይማኖት ከፋፍለን የምናመጣው የጋራ ብልጽግና የለም። ከሁሉ አስቀድመን ለመስማማት መነጋገር፣ ለመነጋገር መደማመጥ ይኖርብናል። አገር ህዝብና ትውልድ ያሉበትን የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ ውስጣችን ማስረጽ ይጠበቅብናል።
ለአገር ውለታ መዋል የዜግነት ግዴታ ነው። መንግስት ብቻ አይደለም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ አይደሉም፣ ባለሀብቶችና ባለስልጣናት አይደሉም ሁላችንም ለአገር ውለታ የመዋል ግዴታ አለብን። ውለታዎቻችን ደግሞ ተነጋግሮ በመግባባት የሚጀምሩ ናቸው። ተነጋግረን ሳንግባባ ለራሳችንም ሆነ ለአገራችን ውለታ መዋል አንችልም።
ሰላም ያለው ንግግር ውስጥ ነው። እድገት ብልጽግና ያለው ውይይት ውስጥ ነው። አገርና ትውልድ የሚፈጠሩት በጋራ ሀሳብ ውስጥ ነው። እንደ አገር ይሄን ትልቅ ጸጋ ሳንጠቀምበት ከወንድሞቻችን ጋር እየተገፋፋን አይጥና ድመት ሆነን ቆይተናል። እነዚያ ጊዜያቶች ኢትዮጵያን ለመሳል፣ ትውልዱን አርነት ለማውጣት በቂዎች ነበሩ። እነዚያ ጊዜያቶች ለራሳችንም ሆነ ለአገራችን ውለታ የምንውልባቸው ነበሩ ግን ባለማወቅ ሳንጠቀምባቸው ቀርተናል።
ያለፈውን ጊዜ ማስረሻ ይሆኑን ዘንድ ዛሬን በእርቅና በንግግር መጀመር ለህዳሴአችን አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው። እየኖርን ያለነው በአባቶቻችን ውለታ ነው። የአባቶቻችን የአንድነት መንፈስ ዛሬን እንድናይ እድል ሰጥቶናል። መጪው ትውልድ በእኛ የእርቅና የድርድር ፍኖት ነገ ላይ ብርሃን እንዲያይ ለውይይት የበረታ ልብና አእምሮ ያስፈልገናል። አገር የትውልድ ቅብብሎሽ ናት ያልኳችሁ ለዚህ ነው። ከአባቶቻችን የተቀበልናትን የአንድነትና የጽናት ምድር፣ የእውነትና የፍትህ፣ የነጻነትና የእኩልነት አገር ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ የዜግነት ግዴታ አለብን።
ይሄ የአባቶቻችን አደራ በእኛ ላይ ይገለጽ ዘንድ በራስ ወዳድነት ያጠፋናቸውን ኢትዮጵያዊ ጸዳሎቻችንን መመለስ አለብን። በማን አለብኝነት ያቆሸሽናቸውን መልኮቻችንን ማደስ አለብን። በጦርና በጠመንጃ፣ በሀይልና በጉልበት የመጣንባቸውን የኋላ ቀርነት ጎዳናዎች መቀየር አለብን። ባለመደማመጥና ባለመግባባት የተጓዝንባቸውን ረጅም የብቻ ጉዞዎች መሻር አለብን። ኢትዮጵያ በነዚህ ውስጥ የለችም። የምንናፍቃትን አገር፣ የምንናፍቀውን ትውልድ ፈልገን ያጣንው በዚህ ውስጥ ስለቆምን ነው። ዛሬ ላይ ብዙ እያለምን፣ ብዙ እየተመኘን ያልተሳካልን በነዚህ አዳፋ እውነቶች ውስጥ ስለጎለመስን ነው። ዛሬ ላይ ለራሳችንም ሆነ በዙሪያችን ላሉት ውለታ መዋል ያቃተን እውቀታችን የክፋት እውቀት ስለሆነ ነው።
ወደፊት ለመራመድ ከማጡ መውጣት አለብን። ብርሃን ለማየት ጨለማዊ አስተሳሰቦቻችንን ማጽዳት ይኖርብናል። ለዘመናት በማይጠቅሙን እኩይ ነገሮች ላይ ነበርን፣ መንገዳችን ላይ እንቅፋት እያስቀመጥን ወደፊት ለመሄድ ስንጥር ነበር። ባለመስማማት ሁሉ ነገራችንን ያጣንበት ጊዜ ነበር። አሁን ግን ይበቃል፤ እነዛ ጊዜዎች ለእያንዳንዳችን የባከኑ የመክሰር ጊዜያቶች ነበሩ።
አሁን በመነጋገርና በጋራ ሀሳብ የባከንበትን ጊዜ የምንክስበት የእርቅ ጊዜ ይሁን። የመደማመጥ፣ የምክክር ጊዜ ይሁን። አገራችን ምን እንደምትፈልግ እንጂ እኛ ምን እንደምንፈልግ የምንጠይቅበት ጊዜ የሚያበቃበት ትክክለኛ ጊዜ አሁን ይመስለኛል። ለአገራችን ውለታ ለመዋል ዛሬ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ተመራጭ ነው። እንደ አገር መንግስት ለዘላቂ ሰላም ሲል ችግሮቻችንን በውይይት የምንፈታበትን አገራዊ ምክክር ይፋ አድርጓል። በዚህ እድል በመጠቀም የማያግባቡንን ነገሮች በመለየትና መፍትሄ በመስጠት ወዳላደረስንበት የከፍታ ጉዞ መሄድ ቀጣይ አላማችን መሆን አለበት። ካለንበት ሳንቀሳቀስ እዛው እየረገጥን የምናመጣው አገራዊ በረከት የለም። ከአምና ዘንድሮ መማር አለብን፣ ጥፋቶቻችን አስተማሪዎቻችን ሆነው ለተሻለ ድል ሊያበቁን ይገባል።
እኛ የቆምንው ሳይነጋገሩ በተግባቡ አባቶቻችን ሀቅ ላይ ነው። እኛ የቆምንው ኢትዮጵያን ብለው ስለ ስሟ በተንገላቱ ባለውለታዎቻችን ላይ ነው። ታዲያ እንዴት እኛ ተነጋግሮ መግባባት አቃተን? እንዴት ስለአገራችን አንድ አይነት ሀሳብ፣ አንድ አይነት ምኞት አጣን? ለአገራችን የእኛ ውለታ ምንድነው? እንደ ዜጋ፣ እንደ መንግስት፣ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ምን እያደረግን ነው ያለነው? እኚህ ጥያቄዎች መልስ ያሻቸዋል። ለአገራችን ውለታ የምንውለው የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ስናውቅ ብቻ ነው።
የዛሬዋን ኢትዮጵያ በክብርና በነጻነት ያቆሙ አባቶቻችን በኢትዮጵያዊነት ብቻ የተግባቡ ነበሩ። በሰውነት ዋጋ ያወጡ ነበሩ። ወደእኛ ሲመጣ ይሄ እውነት የከሰረ ሆኖ እናገኘዋለን። ኢትዮጵያዊነት እያግባባን አይደለም። ሰውነት ዋጋ አጥቶ ብዙ ቦታ ላይ አይተናል። የአባቶቻችን አይነት ኢትዮጵያዊ እውነት፤ የአባቶቻችንን አይነት የሰውነት መንፈስ ያስፈልገናል።
የአገር ክብር በብሔርና በፖለቲካ አይመዘንም። የአገር ክብር በግለሰብና በቡድን እኔነት አይለካም። የአገር ክብር መመዘኛው ህዝብ ነው፤ ትውልድ ነው። የአገር ክብር መለኪያው የአንድነትና የጋራ መንፈስ ነው።
የራቁ ታሪኮቻችንን እያስታወስን በትውልዱ ላይ እሳት ማንደድ ተገቢ አይደሉም። ዳግም ወደማንመለስበት ተነጋግሮ የመግባባት፣ ተግባብቶ የመስማማት ከፍታ ላይ መውጣት አለብን። ዳግም ወደማንመለስበት የአንድነት ስልጣኔ መሸጋገር አለብን። ያለ ምንም ቅደመ ሁኔታ ሰላም ያስፈልገናል፣ እርቅ ግድ ይለናል።
አገራችን ከሰላም ሌላ ሁሉንም አይታለች፤ የሰላም ርሀብ ለትውልዱ የህልውና ድርቀት ነው። የሰላም እጦት ለህዝቦች የስጋት ምንጭ ነው። እንደ አገር ደግሞ ሁሉንም አይነት ዋጋ የሚያስከፍል ሁሉንም አይነት ክስረት ነው። ይሄን ድርቀት፣ ይሄን ስጋት፣ ይሄን ክስረት በንግግር መመለስ አለብን። ያኔ ለውዷ አገራችን ውለታ እንውላለን። ለዛሬው አበቃሁ፤ ሰላም!
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11 /2014